Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናከሱዳን በብዛት የሚገቡ የጦር መሣሪያዎች የሁለቱን አገሮች ግንኙነት እንዳያበላሹ የመፍትሔ ምክክር መደረጉ...

ከሱዳን በብዛት የሚገቡ የጦር መሣሪያዎች የሁለቱን አገሮች ግንኙነት እንዳያበላሹ የመፍትሔ ምክክር መደረጉ ተገለጸ

ቀን:

 በኢትዮጵያና በኤርትራ የገንዘብ አጠቃቀምና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ስምምነቶች ሊፈረሙ ነው

በከፍተኛ መጠን ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው የቀጠለው ሕገወጥ የጦር መሣሪያዎች የኢትዮጵያንና የሱዳን ግንኙነት እንዳያበላሹ፣ የሱዳን መንግሥት ጥንቃቄና ቁጥጥር እንዲያደርግ ውይይት መደረጉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አስታወቁ።

ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማክሰኞ ጥር 21 ቀን 2011 ዓ.ም. ሲያቀርቡ፣ የምክር ቤቱ አባላት ከጎረቤት አገሮች ወደ ኢትዮጵያ በተለያዩ ድንበሮች በኩል የጦር መሣሪያዎች በከፍተኛ መጠን መግባታቸውን ለመግታት ሚኒስቴሩ ምን እያደረገ መሆኑን ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር።

ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ ወደ ኢትዮጵያ በገፍ እየገቡ የሚገኙ የጦር መሣሪያዎች ለአገሪቱ ደኅንነት ሥጋት መሆናቸው በመግለጽ፣ የጦር መሣሪያዎችን ከሚያመርቱ አገሮች ጋር በመወያየትና ግንኙነት በማጠናከር ለማስቆም ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

በተለይ ሱዳን ውስጥ ሆነው የሚያዘዋውሩትን በቁጥጥር ሥር ለማዋል እየተሠራ እንደሆነ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አል በሽር በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በነበረበት ወቅት በዚህ ጉዳይ ላይ በከፍተኛ ደረጃ ምክክር መደረጉን፣ በሱዳን በኩል ተጠናክረው መግባት የቀጠሉት የጦር መሣሪያዎች ጉዳይ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ሊያበላሹ የሚችሉበት ሁኔታ ሊፈጥሩ እንደሚችሉ በመግለጽ፣ የሱዳን መንግሥት አስፈላጊውን የጥንቃቄና የቁጥጥር ሥራ ማከናወን እንደሚገባው ምክክር መደረጉን ገልጸዋል።

በሌሎች አካባቢዎች ወደ ኢትዮጵያ ይገቡ የነበሩ የጦር መሣሪያዎች በተመሳሳይ ዲፕሎማሳዊ ጥረት መቆማቸውን ነገር ግን በሱዳን በኩል መጠናቸው ቢቀንስም አሁንም የጦር መሣሪያዎች በመግባት ላይ ስለሆኑ በልዩ ትኩረት ጉዳዩን መከታተል እንደሚቀጥሉ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

የአገሪቱን ድንበር በተመለከተ ከኬንያ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከርና አልፎ አልፎ የሚነሱ ግጭቶችን ለመቅረፍ የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት ተጠናቆ ቀጣይ ወደ ሥራ የሚገባ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ በኢትዮጵያና በሱዳን ድንበር የይገባኛል ጥያቄ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም እንዲያስከብር ለመፍታት በሁለቱ አገሮች ስምምነት ልዩ የድንበር ኮሚቴ እንደ አዲስ መደራጀቱን ገልጸዋል።

 በሱዳን በኩል ላለው የድንበር ውዝግብ ልዩ ትኩረት መሰጠት ሚኒስትሩ ገልጸው ምክንያቱን ሲያስረዱ፣ ‹‹የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ሳይፈታ የሚቆይ ከሆነ ባልታወቀ ሰዓት የሚፈነዳ ቦምብ ነው፤›› ብለዋል። በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካዊ ሁኔታን የቀየረ እንደሆነም ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም የተፈጠረው ስህተት እንዳይደገም ሲባል በኢትዮጵያና በኤርትራ በኩል የተጀመረውን ወዳጃዊ ግንኙነት ተቋማዊ ለማድረግ ሕጋዊ የግንኙነት ማዕቀፎች ላይ ረጅም ሒደት የፈጀ ድርድር በመደረግ ላይ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በኢትዮጵያ በኩል በሁለቱ አገሮች መካከል ቀድሞ ስለነበሩ ስምምነቶችና ችግሮቻቸው ጥናት ላይ የተመሠረተ ዕውቀት፣ እንዲሁም በወቅቱ ከነበሩ ባለሙያዎች ልምድ በመውሰድ ድርድሩ እየተካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ድርድሩ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑንና ቢበዛ በቀጣዮቹ ሦስት ሳምንታት ውስጥ እንደሚፈረም አስታውቀዋል።

ስምምነቶቹ በሁለቱ አገሮች መካከል የሚኖረውን የገንዘብ ግብይት አጠቃቀም፣ የጉምሩክ፣ የድንበር ንግድና በመንግሥታት መካከል የሚደረግ ንግድን፣ እንዲሁም የኢሚግሬሽን ጉዳዮችና የወደብ አጠቃቀምን የሚመለከቱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

አስተማማኝና ደኅንነቱ የተጠበቀ የወደብ አገልግሎት ኢትዮጵያ ማግኘት እንድትችልም ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች መደረጋቸውን አስረድተዋል።

 ከእነዚህም መካከል በጂቡቲ ወደብ ኮሪደር ላይ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት መደረጉን፣ የኤርትራን ወደቦች አጠቃቀም በተመለከተም ረቂቅ የስምምነት ሰነድ ተዘጋጅቶ ለኤርትራ ወገን ለአስተያየት መቅረቡን፣ እንዲሁም የሶማሊያ ወደቦችን ለመጠቀም በሁለቱ አገሮች መሪዎች መካከል ውይይት መደረጉን ገልጸዋል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...