የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የበርካታ ድንቅ አትሌቶች መገኛ በሆነችው አሰላ አረንጓዴው ስታዲየም ያዘጋጀው ዕድሜያቸው ከሃያ ዓመት በታች ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ባለፈው እሑድ ጥር 19 ቀን 2011 ዓ.ም. መጠናቀቁ ይታወቃል፡፡ በታዳጊ ስም ወላጆች የደመቁበት ብቻ ሳይሆን ፍፁም ስያሜውን የማይመጥንም ተብሏል፡፡
በሥፍራው በመገኘት የታዳጊዎች ተብየውን ሻምፒዮና ከተከታተሉት መካከል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንና የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ክለብ ዋና አሠልጣኝ ሱፐር ኢንቴንደንት ሁሴን ሽቦ ይጠቀሳሉ፡፡ እንደ ዋና አሠልጣኙ ከሆነ፣ ‹‹ሻምፒዮናው የታዳጊዎችን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ የሚያጨልም ፍፁም ወንጀል ነው፡፡ በሁለቱም ጾታ ለውድድር የቀረቡት ወላጆች ናቸው፣ ለዚህ ተጠያቂዎቹ ሁላችንም ስንሆን በዋናነት ብሔራዊ ፌዴሬሽኑን ጨምሮ አትሌቶቹን በበላይነት እየመሩ ወደ አሰላ የተጓዙት የቡድን አመራሮችና ኃላፊዎች ናቸው፤›› በማለት ትዝብታቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
የውድድሩ ባለቤት ብሔራዊ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ስለጉዳዩ ያለው ነገር ባይኖርም የተገቢነት ጉዳይ እያሳሰበው መሆኑን በወቅቱ በነበረው የየዕለቱ የውድድር ሪፖርት ላይ ከቡድን መሪዎች ጋር ሲነጋገር የነበረ መሆኑ ተወስቷል፡፡
በውድድሩ ሲሳተፉ የነበሩት ብዙዎቹ ቢያንስ ከ30 በላይ መሆናቸውን ያከሉት አሠልጣኝ ሁሴን፣ ‹‹የአሰላው የታዳጊዎች ውድድር ተደርጓል ለማለት ካልሆነ የሚያዋጣ አይደለም፡፡ አሳዛኙና አስገራሚው ግን ችግሩ እልባት ሳያገኝ በዚሁ ከቀጠለ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ታዳጊና ተተኪ የምንለው ነገር የማይታሰብ መሆኑ ዕውን ይሆናል፤›› ይላሉ፡፡ ዋና አሠልጣኙ በአሰላው ወድድር ላይ የተመለከቷቸው ብዙዎቹ አትሌቶች ክለብ ውስጥ ገብተው አልሳካ ብሏቸው ወደ የክልሎቻቸው በመሄድ በወጣት ስም በአዲስ ስያሜና ዕድሜ የተመለሱ ናቸው፡፡
የብሔራዊ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ ዱቤ ጅሎ በበኩላቸው፣ ‹‹የዕድሜ ችግር ሙሉ በሙሉ ተቀርፏል ባይባልም ካለፉት ዓመታት አንፃር ሲታይ ዘንድሮ የተሻለ ነው፤›› ብለው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በዚህ ጉዳይ ላይ ጠንክሮ እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡