Sunday, March 26, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የሥልጡን ፖለቲካ የጨዋታ ሕግ እፍርታም አይፈልግም!

ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናት ሲባል ለስታትስቲክስ ቀመር ማሟያ ብቻ አይደለም፡፡ ነገር ግን ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ በተዘረጋው ሰፊ ምድሯ ውስጥ የተለያዩ ማንነቶችን፣ ቋንቋዎችን፣ ባህሎችን፣ እምነቶችንና የአኗኗር ዘይቤዎችን ይዘው ኅብረ ብሔራዊነትን ጌጥ አድርገው የሚኖሩ 108 ሚሊዮን ያህል ዜጎች አገር ናት፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከ108 ሚሊዮን ያህል የኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ 60 በመቶ ያህሉ ከ25 ዓመት በታች ሲሆን፣ በዚህ ሥሌት መሠረት አብዛኛው ሕዝብ ባለፉት 30 ዓመታት የተወለደ ነው፡፡ ከዚህ አዲስ ትውልድ ውስጥ 30 ሚሊዮን ያህሉ በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛል፡፡ አዲሱ ትውልድም ሆነ ነባሩ በአገሩ ውስጥ ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ፍትሕና እኩልነት ሰፍነው መኖር እንደሚፈልግ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ አብዛኛው ሕዝባችን ለዓመታት ሲመኘው የኖረው የትኛውም ዓይነት የብሶትና የፖለቲካ ጥያቄ በውይይት፣ በክርክር፣ በድርድርና በሌሎችም ሰላማዊ መንገዶች እንጂ፣ በጉልበት ወይም በጭፍለቃ እንዲፈታ አይደለም፡፡ በአገሩ ሥልጡን ፖለቲካ አብቦና ጎምርቶ በነፃነት የሚኖርበት ሥርዓት እንዲገነባ የሚፈልግ ትጉህና አስተዋይ ሕዝብ ባለበት አገር፣ እፍርታም ፖለቲከኞች ሲያስቸግሩ ማየት ያሳዝናል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብ በአመዛኙ እየጠየቀ ያለው የፖለቲካ ልዩነቶችና አለመግባባቶች፣ ንትርኮች፣ ቅሬታዎችና የመሳሰሉት ወደ ጠመንጃ የሚሄዱበት ዕድል እየጠበበና እየተዘጋ ሄደ ወይ? ሰላማዊ፣ ሕጋዊና ዴሞክራሲያዊ መስተንግዶና መሰባሰብ እየሰፋ ሄደ ወይ? በማለት ነው፡፡ ሕዝብን እንወክላለን በማለት ለፍላጎታቸውና ለዓላማቸው ዓርማና ምልክት በማበጀትና የፖለቲካ ቀለም በመቀባት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ወይም ስብሰቦች ዛሬም በአዲሱ ዕድል ውስጥ ሰላማዊውንና ዴሞክራሲያዊውን የፖለቲካ የጨዋታ ሕግ ያወቁበት አይመስልም፡፡ ኢሕአዴግ በ1983 ዓ.ም. አዲስ አበባ በድል አድራጊነት ሲገባና የሽግግር መንግሥት ሲያቋቁም፣ ያከተመው የመሣሪያ ትግሉ እንጂ ሰላማዊ ትግሉ ይቀጥላል ብሎ ነበር፡፡ በወቅቱ ሰላማዊና ሕጋዊ ትግሉ ቢታወጅም፣ ኢሕአዴግ ራሱ እንደ ፓርቲ ወይም ድርጅት ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ተፎካካሪነት መለወጥ አልቻለም ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ሰላማዊ የፖለቲካ ተፎካከሪነት ከሚጠይቀው አስተሳሰብና ምግባር በመጣላቱ፣ ሰላማዊ ተቃውሞን የጫካ መንገድ እያሳየ ከአገር አባረረ፡፡ የአገር የውስጥ ተቃውሞ ታፈነ፡፡ ራሱ ኢሕአዴግ ያባረረው ተቃውሞ ከውጭ ባላጋራነት ጋር ተሸራረበ፡፡ በአገር ውስጥም መመለሻና መተንፈሻ ያጣው በፕሮፓጋንዳና በፀጥታ ኃይል ታምቆ የኖረው ብሶት ፈነዳ፡፡ በሕዝብ በተለይም በወጣቶች ትግልና በገዥው መንግሥት የድቆሳ መስተጋብር፣ የመንግሥት ግርሰሳ ያልታየበት አስገራሚ ለውጥ ውስጥ ተገባ፡፡ ይህ ሒደት ግን የሺዎችን ሕይወት የቀጠፈ፣ በርካቶችን ለአካላዊና ለሥነ ልቦናዊ ጉዳት የዳረገና ከፍተኛ የአገር ሀብት ያወደመ ነበር፡፡

ለውጡ የሕዝብ ተቀባይነትን አግኝቶ በቅጡ መሠረት ሳይዝ ሽብርተኛ ተብለው የተፈረጁ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ አገር ቤት ተመልሰው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንዲያካሂዱ ጥሪ ቀረበ፡፡ ለውጡ ከአገር ውስጥ ተቃውሞና ከአካባቢያዊ የአሸባሪነት ሥጋት ጋር የተሳሰረውን የጎረቤት ጠላትነት አረከሰ፡፡ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች ተፈቱ፡፡ በውጭ የመከራ ገፈት ቀማሽ የነበሩ ስደተኞች ጭምር ተመለሱ፡፡ በተጨማሪም ነበረ የተባለውን ስቃይና ሰቆቃ እስረኞችና እስር ቤቶች ተናገሩ፡፡ ይፈለጉ የነበሩና ያልተጠበቁ የለውጥ ዕርምጃዎችና እየተከታተሉና እየተግተለተሉ ሲመጡ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩ ከሚችለው በላይ ጭንቅ ውስጥ ገባ፡፡ ሰላማዊ ጥሪውን ተቀብለው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለማድረግ ከመጡት መሀል፣ በየራሳቸው መንገድ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ተፎካካሪነት መለወጥ ሲቸግራቸውና ይህም የሚጠይቀውን አስተሳሰብና ጨዋነት መያዝ ሲሳናቸው ታዩ፡፡ ደም መቃባት በሌለበት መንገድ ለቅሬታ ምንጭ የሆኑ ችግሮችን ለማስወገድና መፍትሔ ለመስጠት ሲቸገሩና አገር ሲያስቸግሩ በስፋት ታዩ፡፡ ሥልጡን የሆነው የጨዋታው ሕግ ላይ አልተስማሙም፡፡ ከዚህ ይልቅ ጠመንጃ ነካሽነትን መረጡ፡፡ ለገላጋይ እስኪያስቸግሩ ድረስ አገርንና ሕዝብን መከራ አሳዩ፡፡ አሁንም ከመጠማመድ ወደ መደማመጥ መሸጋገር አልቻሉም፡፡ ችግሩ ያለው መንግሥትን በሚመሩትና ከመንግሥት ውጪ ባሉት ቡድኖች መሀል ብቻ አይደለም፡፡ በኢሕአዴግ ውስጥ ሳይቀር መገለባበጥ በመብዛቱ፣ ሰሚና መላሽ አጥተው የቆዩና ያደሩ ጥያቄዎችና ውዝግቦች እየተንተከተኩ ነው፡፡

ኧረ ለመሆኑ የጨዋታው ሕግ ምን ይላል? ልዩነትን በውይይት የመፍታት ዴሞክራሲና ጨዋነት መላበስ፣ ልዩነት አብሮ ለመሥራት አያመችም ከሚል ቅዥት መውጣት፣ ያልተገደበ የሕዝብ ውይይትና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ክርክር ማድረግ፣ ዝምታን የሚጭን፣ አሉባልታንና ሹክሹክታን የሚያባዛ የተወጠረ አየርን ማስተንፈስ፣  ዴሞክራሲያዊነት ማለት በመብቶችና በመቻቻል ውስጥ ለመኖር መቻል ማለት መሆኑን፣ ይኼንን መሠረት ለማስያዝ በመረባረብ ችግሮች ወይም አለመግባባቶች ሲከሰቱ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገዶች መፍታትና ውጤቱንም መቀበል መቻል የጨዋታው ሕግ አካል ናቸው፡፡ ጥያቄዎች ወይም ልዩነቶች የአመፅ መንገድ ውስጥ ሳይገቡ የሚስተናገዱበት፣ ጥፋቶች ወይም ሕገወጥነቶች የትግል ወይም የመብት ሽፋን ሳያገኙ የሚጋለጡበት፣ በዚህ ወይም በዚያ ፓርቲ መስመር በትክክል የመመራት ጉዳይ፣ ወይም የዚህ ወይም የዚያ ወገን አቋም የመከበር፣ ከሐሳቦች ጋር ውድድር ገጥሞ ሐሳብን በሐሳብ የመርታትና ሰፊ ተቀባይነት የማግኘት፣ ይኼንንም በሕዝብ ወይም በወኪሎቹ ነፃ ድምፅ ማረጋገጥ የጨዋታው ሕግ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ዘንዳ በጨዋታው ሕግ ማፈር ተገቢ አይሆንም ማለት ነው፡፡

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከሚሳተፉ ኃይሎች የብዙዎቹ ችግር የጨዋታውን ሕግ አለማወቅ ወይም ሆን ብሎ ማበላሸት ነው፡፡ ከሕዝብ በፊት ሥልጣን ስለሚቀድም በሥልጡን መንገድ ለመጓዝ ብዙዎቹ ወገቤን ይላሉ፡፡ አባላትንና ደጋፊዎችን ንቃተ ህሊናቸውን አጎልብቶ የጠራ መንገድ ከማስያዝ ይልቅ፣ ሰላማዊውን ድባብ በማደፍረስ ሁከትና ግጭት መቀስቀስ ይቀላቸዋል፡፡ ከፖለቲከኞቹ ባልተናነሰ የተለያዩ ፍላጎቶችን አንግበው የሚንቀሳቀሱ አክቲቪስቶችም የዚህ በሽታ ሰለባ ሆነዋል፡፡ ትናንት ጉልበተኞች የፈጸሙት ሸፍጥና ጥፋት ቁስሉ ሳይደርቅ፣ ዛሬም ጉልበት ለማሳየት ጡንቻቸውን የሚወጣጥሩ አክቲቪስቶች በተለያዩ ገጽታዎች እየታዩ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ለሐሳብ የበላይነት፣ ለነፃነትና ለመብቶች ተቆርቋሪ መሆናቸውን ሲደሰኩሩ ከነበሩት ውስጥ፣ የጉልበት ፖለቲካ ለማንገሥ የሚሯሯጡ በስፋት እየተስተዋሉ ነው፡፡ ስም በማጥፋትና በማሸማቀቅ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ የፖለቲካ ምኅዳር እንዳይፈጠር ተግተው እየሠሩ ሲሆን፣ ከግለሰብ እስከ ቡድን እንዲንበረከኩላቸው በተለያዩ መንገዶች ያስገድዳሉ፡፡ ታዋቂነትንና ዝነኝነትን ተገን በማድረግ አገር ለማጥፋት እንቅልፍ ማጣት የዘመኑ ፋሽን ሆኗል፡፡ እነዚህ ሁሉ የሚርመሰመሱበት የአገሪቱ ፖለቲካ የእፍርታሞች መድረክ ሆኗል፡፡ የሥልጡን ፖለቲካ የጨዋታ ሕግ ግን ይኼንን እፍርታምነት በፍፁም አይፈልግም!

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

ጥቁር የመልበስ ውዝግብና የእምነት ነፃነት በኢትዮጵያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኅዳር ወር ላይ በፓርላማ...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...

ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ የአዲስ አበባን ንግድና ዘርፍ ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት በተደረገው ምርጫ አሸነፉ

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት፣...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...

ብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ይፋ ሊያደርግ ነው

የፋይናንስ ዘርፉን ለማረጋጋት የሚረዳ ሪፎርም ማጠናቀቁን የገለጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሠራር ለአገር አይበጅም!

ሰሞኑን የአሜሪካና የኢትዮጵያ መንግሥታት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የጦር ወንጀሎች መግለጫ ላይ አልተግባቡም፡፡ አለመግባባታቸው የሚጠበቅ በመሆኑ ሊደንቅ አይገባም፡፡ ነገር ግን...

የምግብ ችግር ድህነቱን ይበልጥ እያባባሰው ነው!

በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣...

መብትና ነፃነትን የሚጋፉ ድርጊቶች ይወገዱ!

ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የመዘዋወር፣ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት ሕጋዊ መብት አላቸው፡፡ ይህ መብት በግልጽ የተደነገገው በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ሲሆን፣ አሁንም ሕገ...