Friday, September 22, 2023

የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አዋጅ ከፀደቀ በኋላ የቀጠለው ፖለቲካዊ ውዝግብ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ሕገ መንግሥቱን ይጣረሳል የሚል ተቃውሞ የቀረበበት የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአብላጫ ድምፅ ቢፀድቅም፣ በሕገ መንግሥታዊነቱ ላይ የቀጠለው ክርክር ሌላ የሕገ መንግሥታዊነት ጥያቄና ክርክር ጭሮ ወቅታዊውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ አየር ተቀላቅሏል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ የቀረበለትን የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ፣ በታኅሳስ 2011 ዓ.ም. በ33 ተቃውሞና በአራት ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ ማፅደቁ ይታወሳል።

በወቅቱ የትግራይ ክልል ተወካይ የሆኑ የሕወሓት አባላት ረቂቅ አዋጁ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጋጭ በመሆኑ፣ መፅደቅ የለበትም በማለት ከፍተኛ ክርክር በምክር ቤቱ ውስጥ አድርገው ነበር። የሙግታቸው ማጠንጠኛ ሆኖ የቀረበው የወሰንና የማንነት ጉዳይ ኮሚሽን አዋጅ በሕገ መንግሥቱ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የተሰጠ በመሆኑ፣ ተመሳሳይ ኃላፊነት ለኮሚሽኑ ሊሰጥ አይገባም ነው።

አዋጁን በማፅደቅ ኮሚሽኑ እንዲቋቋም ማድረግ ሕገ መንግሥቱን በሁለት መንገድ እንደሚጣረስ፣ አንድም የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን በመንጠቅ በሌላ በኩል ደግሞ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ያልተከተለ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ማድረግ እንደሆነ በመጥቀስ ተከራክረዋል።

ኮሚሽኑን ለማቋቋም የቀረበው አዋጅን እንደሚደግፉት በመግለጽ የተከራከሩት አብላጫዎቹ የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው፣ ኮሚሽኑ ቢቋቋም በአገሪቱ ለግጭት እየዳረጉ የሚገኙ የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮችን በአጠቃላይ በማጥናት መንስዔያቸውንና መፍትሔ ሊሆኑ ይችላሉ የሚላቸውን በተመለከተ ምክረ ሐሳብ ማቅረብ ብቻ እንጂ፣ ኮሚሽኑ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነት ተክቶ ውሳኔ እንደማይወስንና ፈጽሞ ከሕገ መንግሥቱ የሚጣረስ እንዳልሆነ ሞግተዋል።

የሕወሓት ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ አጽብሃ አረጋዊ አዋጁ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጣረስ መሆኑን በመጥቀስ ከተከራከሩ በኋላ፣ ‹‹በቀላሉ እንደሚፀድቅ እርግጠኛ ነኝ፣ ነገር ግን የሚያመጣውን ጣጣ ቆም ብለን ብናይ?›› ሲሉ በወቅቱ ምክር ቤቱን አሳስበው ነበር።

አቶ አጽብሃ ይኼንን መናገራቸው በአንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ላይ ቁጣ ፈጥሮ ነበር። ከእነዚህም መካከል የአዴፓ አባል የሆኑት አቶ አጥናፍ ጌጡ የተባሉ የምክር ቤቱ አባል፣ ‹‹ጣጣ ያመጣል፣ አደጋ አለው የሚሉ ኃይለ ቃላትና ማስፈራሪያዎችን መናገር ለዚህ ምክር ቤት አይመጥንም፤›› ሲሉ የግሳፄ አስተያየታቸውን በወቅቱ ሰጥተዋል።

ሌሎች የምክር ቤት አባላት በሰጡት አስተያየት ደግሞ የዜጎች ሰብዓዊ መብታቸው ሲጣስና ሲኮላሹ የሕገ መንግሥት ጥሰት ጥያቄ ሳይነሳ፣ ለሰላም ፋይዳ ያለው ኮሚሽን እንዳይቋቋም የሕገ መንግሥት መጣረስን እንደ ምክንያት ማቅረብ እንደማይገባ በመግለጽ ተከራክረው ነበር።

የሁለቱ ጎራ የክርክር መጨረሻም በድምፅ ተወስኖ ኮሚሽኑን የሚያቋቁመው አዋጅ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል። የአዋጁ መፅደቅ ግን የክርክሩ መቋጫ መሆን አልቻለም።

የትግራይ ክልል ምክር ቤት ዓርብ ጥር 17 ቀን 2011 ዓ.ም. ስብሰባው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያፀደቀውን የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ሕገ መንግሥቱን የሚጣረስ ስለሆነ፣ እንደሚቃወመውና እንዲታረም በመጠየቅ ውሳኔ አሳልፏል።

የትግራይ ክልል ውሳኔ የወለደው ሌላ የሕጋዊነት ክርክር

የትግራይ ክልል ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባካሄደው ስብሰባው ከተመለከታቸው ጉዳዮች መካከል፣ የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ዋነኛ አጀንዳ ነበር ማለት ይቻላል።

የክልሉ ምክር ቤት የኮሚሽኑን ማቋቋሚያ አዋጁን ኢሕገ መንግሥታዊ ነው በማለት ባሳለፈው ውሳኔ ፈርጆታል። የክልሉ ምክር ቤት በዚሁ ባፀደቀው ውሳኔ ላይ የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ውድቅ ሊሆን እንደሚገባ ወስኗል።

 በተጨማሪም የፌዴራል ፓርላማ ኮሚሽኑን ለማቋቋም አዋጅ ማፅደቁ ከሕገ መንግሥቱ የሚጣረስ የሕግ ስህተት በመሆኑ፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት ስለተፈጸመው የሕገ መንግሥት ጥሰት ትርጉም ሊሰጥ ይገባል ሲል የክልሉ ምክር ቤት ውሳኔ አሳልፏል፡፡ በማከልም የትግራይ ክልል መንግሥት ሥራ አስፈጻሚ ጉዳዩን በዝርዝር ዓይቶ፣ የትርጉም ጥያቄ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲያቀርብ ኃላፊነት መስጠቱን ባፀደቀው ውሳኔ አመልክቷል።

የትግራይ ክልል ምክር ቤት የቀረበለትን የወሰንና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ውድቅ እንዲሆን የሚጠይቀውን የውሳኔ ሐሳብ በሙሉ ድምፅ ነው ያፀደቀው።

የፀደቀውን ውሳኔ በተመለከተ አስተያየታቸውን ለሚዲያዎች የሰጡት የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አቶ አማኑኤል አሰፋ፣ ‹‹የክልሉ ምክር ቤት አሁን ካፀደቀው ውሳኔ በላይ በመሄድ የውሳኔ ሐሳብ ማቅረብ ይችላል፤›› ብለዋል፡፡

ነገር ግን ዛሬ ክልሉ ሕጋዊ ሥነ ሥርዓቱን ተከትሎ የወሰንና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ውድቅ እንዲሆን ግልጽ ጥያቄ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ለማቅረብ መምረጡን፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ጉዳዩን ተመልክቶና አዋጁን አግዶ ይመረምረዋል ብለው እንደሚጠብቁ ገልጸዋል፡፡

በክልሉ ውሳኔ የቀሰቀሰው ሕጋዊነት ጥያቄ

የክልሉ ምክር ቤት በፌዴራል ፓርላማ የፀደቀው የስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አዋጅ ከሕገ መንግሥቱ እንደሚጣረስና ውድቅ እንዲደረግ ያፀደቀው ውሳኔ ደግሞ፣ ሌላ የሕገ መንግሥት ጥሰት ጥያቄ ተነስቶበታል።

በርካታ የፖለቲካ ልሂቃን የክልሉ ምክር ቤት ውሳኔውን ያስተላለፈበት መንፈስ የፌዴራሉ ፓርላማ ያፀደቀው ኮሚሽኑን የሚያቋቋም አዋጅ በትግራይ ክልል ተግባራዊ አይደረግም ወደ ማለት የተቃረበ እንደሆነ በመቁጠር፣ ክልሉ ሕገ መንግሥቱን ለመጣረስ ሞክሯል ብለዋል።

በሌላ በኩል ክልሉ ያሳለፈው ውሳኔ አዋጁን በመቃወም አቋሙን እንደገለጸ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትም በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ኮሚሽኑ ሕገ መንግሥቱን የሚጣረስ መሆኑን ተመልክቶ ውድቅ እንዲያደርገው ጥያቄ እንዲቀርብ እንጂ የፈጸመው ጥሰት የለም የሚሉ አሉ።

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ለሪፖርተር የሰጡት የሕግ ባለሙያና የፖለቲካ ተንታኝ አቶ አብዱ ዓሊ ሒጅራ፣ ‹‹የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅም ሆነ የክልሉ ምክር ቤት ያፀደቀው ውሳኔ ትክክል ነው አይደለም ከማለት ይልቅ፣ ሁለቱም ወገኖች በጨዋታው ሕግ ላይ መስማማት አለመቻላቸው አሳሳቢ ነው፤›› ይላሉ።

የብዙኃን ውሳኔ ገዥ በሚሆንበት የዴሞክራሲ ሥርዓት ውስጥ የሐሳብ ፍጭት ከተደረገ በኋላ የብዙኃን ውሳኔ ተፈጻሚ እንደሚሆን፣ በዚህ ሥርዓት ውስጥ እውነት ሌላ ቦታ ሆና አብዛኞች የተስማሙበት ጉዳይ ስህተት እንኳ ቢሆን ጉዳዩ እዚያ ላይ እንደሚያልቅ ያስረዳሉ።

‹‹ኳስ አበደች ተብሎ አብሮ አይታበድም፣ ብሔር ብሔረሰቦች ተነሱ አይባልም፣ የተቃውሞ አቋምን ለመግለጽም የጨዋነት ሕግን መከተል ያስፈልጋል፤›› ሲሉ ይገልጻሉ።

በአገሪቱ የተዘረጋውን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በአግባቡ ዜጎች ሳይለማመዱት በመቆየታቸው ትንሽ ተስፋ ሰጪ ጅማሮን ማጨለም እንደማይገባ፣ ሥርዓቱ ስህተቶችን የሚያርምበት አሠራር እስካለው ድረስ አለ የሚባልን ስህተት በጨዋነት ማረም ይገባል ብለዋል።

የትግራይ ክልል ባፀደቀው ውሳኔ የኮሚሽኑ መቋቋም ሕግን የጣሰ እንደሆነ በመግለጽ በፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲታረም መጠየቁ የጨዋታው ሕግ አለማለቁንና የጨዋታውን ሕግ መከተሉን ያሳያል የሚል ክርክር የሚያቀርቡ ስለመሆናቸው የተጠየቁት አቶ አብዱ፣ ‹‹እሱም ቢሆን መፈጸም ያለበት በጨዋነት እንጂ ሌሎችን ተነሱ ተቃወሙ በማለት አይደለም፤›› ብለዋል።

ጉዳዩን በምሳሌ ሲያስረዱም በራሱ በሕወሓት ውስጥ በ1990ዎቹ ተፈጥሮ የነበረን አለመግባባት ያስታውሳሉ።

 ‹‹በወቅቱ ኤርትራ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ሕወሓት ለሁለት ተከፍሎ ከኤርትራ ጋር ጦርነት ውስጥ መግባት አያስፈልግም የሚል አቋም በያዙት የወቅቱ የድርጅቱ ሊቀመንበር የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ፊታውራሪነት የሚመራ ቡድንና ጦርነት መታወጅ አለበት በሚለው አብዛኛው የሕወሓት አመራሮች መካከል ተፈጥሮ የነበረው ፍጭት፣ አብዛኞቹ በያዙት አቋም አሸናፊነት መጠናቀቁንና የተሸነፉት አቶ መለስ ዜናዊም ሽንፈታቸውን ውጠው እንደ አገሪቱ ጠቅላይ የጦር አዛዥነታቸው ያላመኑበትን ጦርነት መርተዋል። ዴሞክራሲ ደግሞ ይህ ነው፤›› ይላሉ››።

የትግራይ ክልል ያሳለፈውን ውሳኔ በተመለከተ አስተያየታቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት እንግሊዝ አገር በሚገኘው የኬል ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር የሆኑት ዓወል ቃሲም አሎ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የክልሉ ምክር ቤት ውሳኔ ከሕገ መንግሥቱ ጋር እንደሚጣረስ ገልጸዋል።

አንድ አዋጅ ወይም የመንግሥት ውሳኔና ድርጊት ሕገ መንግሥቱን የጣሰ ነው በማለት ሐሳብን መግለጽ የሚቻል ቢሆንም፣ ሕገ መንግሥቱን ጥሷል ስለተባለው ሕግ ወይም የመንግሥት ውሳኔ አልያም ድርጊት በሕግ ሥልጣን የተሰጠው አካል ውድቅ እስካላደረገው ድረስ ተፈጻሚ መሆኑን እንደሚቀጥል፣ በዚህ ጉዳይ ላይም ሐሳብን ከመግለጽ ባለፈ በሕግ ኃላፊነት የተሰጠውን ሌላ አካል ተክቶ ሕገ መንግሥቱን የጣሰ ነው የሚል ውሳኔ ማስተላለፍ በራሱ ሕገ መንግሥቱን እንደሚጣረስ ያስረዳሉ።

 የትግራይ ክልል ሰሞኑን ያሳለፈው ውሳኔም የሕግ ጥሰት እንደሆነ አመላክተዋል። የፌዴራል ፓርላማ የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽንን ለማቋቋም ያፀደቀው አዋጅ ከሕገ መንግሥቱ የሚጣረስ ነው ተብሎ ከታመነ፣ ትክክለኛው መንገድ የተባለው የሕግ ጥሰት እንዲታይ ይኼንን ማድረግ ኃላፊነት ለተሰጠው የሕገ መንግሥት ትርጉም አጣሪ ጉባዔ ማቅረብ እንደሆነ አመልክተዋል።

በዚህ ጉባዔ ገለልተኝነት ወይም አቅም ላይ ጥርጣሬ እንኳን ቢኖር ያለው አማራጭ፣ በዚህ መንገድ ተጉዞ ውሳኔውን መቀበል ብቻ እንደሆነ ይገልጻሉ።

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፌዴራሊዝም ጉዳዮች ባለሙያ ግን በኮሚሽኑ መቋቋም ላይ የተነሳው የሕገ መንግሥት ጥያቄም ሆነ ከዚሁ ጋር በተገናኘ የትግራይ ክልል ያሳለፈው ውሳኔ፣ አንድም የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ እንዲጠናከር ዓይነተኛ ሚና ሊኖረው እንደሚችል በሌላ በኩል ግን በፖለቲካዊ ብሽሽቅና መሸናነፍ የታጀበ በመሆኑ ወዳልተፈለገ ሁኔታ አገሪቱን ሊከት እንደሚችል ሥጋታቸውን ይገልጻሉ።

ፌዴራላዊ የመንግሥት አወቃቀርን በሚከተሉ አገሮች መካከል በማዕከላዊ መንግሥትና በክልል መንግሥታት መካከል አለመግባባት፣ በተለይም የፌዴራል መንግሥት ውሳኔን የክልል መንግሥታት ላለመቀበል መገዳደርና መናቆራቸው የተለመደ መሆኑን ያስረዳሉ። ነገሩ አሁን ለኢትዮጵያውያን ሥጋት ሆኖ የታየው የፌዴራሊዝም ሥርዓትን የዛሬ 24 ዓመት ቢያፀድቁትም፣ መኖርና መለማመድ የጀመሩት ገና አሁን ከመሆኑ ጋር እንደሚገናኝ ጠቁመዋል።

በአሜሪካ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ውስጥ ስቴቶች (የክልል መንግሥታት) በማዕከላዊ መንግሥት የሚፀድቁ ሕጎችን በክልላቸው (States) ተግባራዊ እንዳይደረግ በመወሰን ክልከላ ማድረግ የተለመደ መሆኑን፣ ለዚህም የኦባማ ሄልዝኬር ኢንሼቲቭና መሰል ሕጎች ገጥሟቸው የነበረውን ፈተና ያስታውሳሉ።

በናይጄሪያም ተመሳሳይ ክስተቶች እንደሚፈጠሩና በለተይም የነዳጅ ሀብት ገቢን ላለማጋራት ክልሎች እንደሚወስኑ የጠቆሙት እኚሁ ባለሙያ፣ በኢትዮጵያ የፌዴራል መንግሥት ለክልሎች እየወሰነ ሲኖር በመቆየቱ ክስተቱ አዲስ ቢሆንም፣ ወደዚህ የፌዴራሊዝም ሥርዓት መገለጫ ባህርይ ኢትዮጵያ ደጋግማ መግባቷ እንደማይቀር ገልጸዋል።

በእርግጥ አንድ ክልል አንድን አዋጅ በመቃወም በክልሉ ተግባራዊ እንዳይደረግ ሲወስንና አዋጁ ደግሞ ከአንድ ክልል በላይ በጋራ የሚመለከት በሚሆንበት ጊዜ፣ የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ ማንነት ላይ የተመሠረተ ከሆነ ጉዳዩን በጥንቃቄ መያዝ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -