Monday, March 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የፍጥነት መንገዱ ገቢ በእጥፍ መጨመሩ ተገለጸ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገሪቱ የመጀመርያው የፍጥነት መንገድ በመሆን ከአራት ዓመት በፊት ሥራ የጀመረው የአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ ዕለታዊ የተሽከርካሪዎች ፍሰት እያደገ በመሄዱ ገቢው እየጨመረ መምጣቱ ተመለከተ፡፡ አማካይ ዕለታዊ ገቢው በእጥፍ መጨመሩም ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ አኃዛዊ መረጃና ሰሞኑን ይፋ ያደረገው የ2011 ግማሽ በጀት ዓመት አፈጻጸሙ እንደሚያሳየው፣ ከአራት ዓመት በፊት የነበረውን ዕለታዊ ገቢ በ2011 በጀት ዓመት አጋማሽ ላይ በእጥፍ ማሳደግ መቻሉን ነው፡፡

ድርጅቱ የ2011 ግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን የተመለከተው አኃዛዊ መረጃ እንደሚያሳየው፣ በስድስት ወራት ውስጥ ያገኘው ገቢ ከ131.2 ሚሊዮን ብር በላይ ሆኗል፡፡ ይህ ገቢ ከቀደመው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ20 በመቶ በላይ ዕድገት የታየበት ነው፡፡

እንደ ድርጅቱ መረጃ በ2007 በጀት ዓመት ሥራ ሲጀመር የተሽከርካሪዎች ፍሰቱ በቀን 12 ሺሕ የተሽከርካሪዎች ምልልስ የነበረ ሲሆን፣ አማካይ የቀን ገቢው 331,494 ብር እንደነበር ያሳያል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ይህ አማካይ የቀን ገቢው በእጥፍ አድጎ 677,057 ብር ሊደርስ መቻሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የተገልጋዮቹ ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ በ2009 ዓ.ም. የቀን ገቢው ወደ 554,891 ብር ሲያድግ፣ አሁን በ2011 ሒሳብ ዓመት የመጀመርያ ስድስት ወራት በቀን የተገኘው አማካይ ገቢ ወደ 677,057 ብር ደርሷል፡፡

የስድስት ወሩ የድርጅቱ አፈጻጸም እንደሚያመለክተው፣ በግማሽ በጀት ዓመቱ ከተገኘው ጠቅላላ ገቢ ውስጥ 124.8 ሚሊዮን ብር የተገኘው 4.23 ሚሊዮን የትራፊክ ፍሰት በማስተናገድ ነው፡፡ በቀጥታ ከተሽከርካሪ በማስተናገድ ካገኘው ገቢ ሌላ ከማስታወቂያና ከተለያዩ ገቢዎች ተጨማሪ 6.7 ሚሊዮን ብር ያገኘ ሲሆን፣ በአጠቃላይ የአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ በግማሽ በጀት ዓመቱ በጥቅል ያገኘው ገቢ 131.2 መሆኑም ታውቋል፡፡

በአጠቃላይ ከ2007 ዓ.ም. እስከ 2009 ዓ.ም. የድርጅቱ ገቢ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ ችሎ የነበረ ሲሆን፣ በ2010 በጀት ዓመት ደግሞ 231 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘት ችሏል፡፡ ሰሞኑን ባወጣው መረጃ በግማሽ ዓመት ውስጥ ያገኘው 131.2 ሚሊዮን ብር ሲጠጋ፣ ድርጅቱ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ አጠቃይ ያገኘው ገቢ ከ850 ሚሊዮን ብር በላይ መድረሱን ያሳያል፡፡

በአሁኑ ወቅት ግን በቀን በአማካይ ከ22 ሺሕ በላይ ተሽከርካሪዎችን እያስተናገደ ይገኛል፡፡ በጥር ወር 2011 ዓ.ም. በአንድ ቀን 26,901 ተሽከርካሪዎችን በማስተናገድ፣ 820,230 ብር የተገኘበት አጋጣሚ እንደነበርም ከድርጀቱ የመረጃ ቋት ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

የድርጅቱ ቀደም ያሉ መረጃዎች እንደሚጠቁሙትም በ2010 በጀት ዓመት 7,810,351 የትራፊክ ፍሰት በማስተናገድ 231 ሚሊዮን ብር ገቢ ሲያገኝ፣ ከተለያዩ ገቢዎች ደግሞ 13.8 ሚሊዮን ብር በማሰባሰቡም የበጀት ዓመቱ ጥቅል ገቢ 244.8 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ድርጅቱ በ2011 በጀት የያዘው ዕቅድ 8.8 ሚሊዮን የተሽከርካሪዎችን ምልልስ በማስተናገድ፣ 265.7 ሚሊዮን ብር ለማግኘት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሁለተኛውን የአገሪቱ የፍጥነት መንገድ አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ የሚጠበቀው የድሬዳዋ ደወሌ የፍጥነት መንገድን በቅርቡ ለማስጀመር መታቀዱ ታውቋል፡፡ የድሬዳዋ ደወሌ መንገድ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ይጠበቅ የነበረው ከሁለት ወራት በፊት ቢሆንም፣ ሥራው ሳይጀመር ሊዘገይ የቻለበት ምክንያት ተገምግሞ በቶሎ ሥራ ለማስጀመር ዝግጀቶች እየተደረጉ ነው፡፡ እነዚህም ዝግጅቶች የክፍያ ትርፍ ዝግጅት፣ የቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት መዋቅር፣ የሥራ ማስጀመርያ ቅጽ፣ የባለሙያዎች ምደባና የቴክኖሎጂ ዝርጋታ ላይ ሙያዊ ክትትል፣ ድጋፍና ምክረ ሐሳብ የመስጠት ሥራን ያካተቱ ናቸው ተብሏል፡፡ ከባለድርሻ አካላት ጋርም ውይይት ተደርጓል፡፡

በተለይም የድሬዳዋ ደወሌን የፍጥነት መንገድ በክፍያ አገልግሎት ለማስጀመር የታሪፍ ዝግጅት ተዘጋጅቶ ለትራንስፖርት ሚኒስቴር እንዲፀድቅ መላኩም ታውቋል፡፡ ከድርጅቱ ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተውም የተዘጋጀውን ታሪፍ በተለያዩ አማራጮች የተቀረፀ ሲሆን ሲፀድቅ ይፋ ይደረጋል፡፡

አሁን በአገልግሎት ላይ ያለውን የአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ ጨምሮ ከዚህ በኋላ በተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ መንገዶች የሚተዳደሩት በክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ ነው፡፡

ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በክፍያ አገልግሎት ይሰጣሉ ተብለው ከሚታሰቡ መንገዶች ውስጥ አዳማ-አዋሽ-ሜኤሶ-ድሬዳዋ መንገድ ይገኝበታል፡፡ ይህ መንገድ ሲገነባ በክፍያ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የድሬዳዋ ደወሌ መንገድ ግን በአሁኑ ወቅት ግንባታው የተጠናቀቀና የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ እንደተረከበው የባለሥልጣኑ መረጃ ያስረዳል፡፡

የአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ሲሆን፣ ለግንባታ የወጣውም ወጪ በቻይና ወጪና ገቢ ንግድ ባንክ (ኤግዚም ባንክ) እና በኢትዮጵያ መንግሥት ነው፡፡

ከጠቅላላው ወጪ 57 በመቶውን የሸፈነው ከቻይና ወጪና ገቢ ንግድ ባንክ የተገኘ ብድር ነው፡፡ ይህ ብድር በ20 ዓመታት ውስጥ የሚመለስ ስለመሆኑ መገለጹ አይዘነጋም፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች