የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚታየውን ሐሰተኛ ማስረጃና ማጭበርበር ለመግታት፣ የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ሰርተፍኬት፣ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ፣ የልደትና ሞት ሰርተፍኬት እንዲሁም የጋብቻና ፍቺ ሰርተፍኬቶችን በዲጂታል ሊቀይር መሆኑን አስታውቋል፡፡
አስተዳደሩ በማኅበራዊ ድረ ገጹ እንዳስታወቀው ከመታወቂያ ሥራው በተጨማሪ ‹‹ትሮይ ሴክዩሪቲ ሶሉውሽንስ ግሩፕ›› ከተባለ የአሜሪካ ኩባንያ ጋር ሰርተፍኬቶቹን ወደ ዘመናዊ ዲጂታል ሰርተፍኬት ለመቀየር ተስማምቷል፡፡
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ከድርጅቶቹ ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት፣ መረጃዎቹን በዲጂታል ሰርተፍኬት መለወጥ የሕገወጥ ማስረጃ አገልግሎትን ከማስቀረቱ በተጨማሪ በከተማዋ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ምቹና ዘመናዊ ያደርጋል ብለዋል፡፡