በብሔራዊ፣ በስታዲየም፣ በፒያሳ፣ በኢትዮጵያ ሆቴል፣ በለገሃርና በተለይ የትራፊክ መብራቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ታዳጊ ሕፃናትና ወጣቶች አንዳንዴ ልጅ ያዘሉም ጭምር በአውራ ጎዳናው የሚያልፈውን መኪና እየተከተሉ የሚበላ አሊያም፣ የውኃ፣ ፕላስቲክ ስጡን የሚሉ ጎዳና ተዳዳሪዎች የአዲስ አበባ መገለጫ ከሆኑ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
ሲያሻቸው የመኪና ሰውነት እየወለወሉ አልያም እንዲሁ መኪናውን እየተከታተሉ ሳንቲም መጠየቁም የተለመደ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ሙሉውን ቀን እምብዛም የማይታዩትና አመሻሽ ላይ ብቅ የሚሉት ጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ዛሬ ላይ ሙሉውን ቀን ከዚህ እዚያ እየተሯሯጡ መለመኑን፣ ሲያሻቸው ፀያፍ መናገሩን ተክነውበታል፡፡ እንደቀድሞው ፖሊስ ሲያዩ ለመደበቅ የሚያደርጉትን ጥረት በመተው ሮጥ ብለው ለጊዜው በማምለጥ ዞር ብለው እዛው አስፋልት መሐል ገብተው መታየቱም የተለመደ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም ጎዳና ተዳዳሪዎች ማታ ማስቲሽ ስበውበት ቀን የሚደብቁትን የፕላስቲክ ውኃ መያዣ በየመንገዱ አካፋይ ማንም ሊያየው ይችላል፡፡ በየሚቀመጡባቸው አካባቢዎች መሬት ያስቀምጡት አልያም በእጃቸው ይይዙት እንደሆነ እንጂ፣ እንደቀድሞው በእጅጌያቸው ሸጉጠው መያዝን ረስተውታል፡፡ የደረሰባቸው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ብሎም ሥነልቦናዊ ጉዳት ክፍና ደጉን አስረስቶ ፈር ወደ ለቀቀው የጎዳናው ዓለም ከቷቸዋል፡፡
የአዲስ አበባን ዋና ዋና መንገዶች ከወዲህ ወዲያ እየተሯሯጡ የሚገልጿት ጎዳና ተዳዳሪዎች፣ አብዛኞቹ ለዚህ ሕይወት ያበቃቸው የቤተሰብ መለያየት እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡ ከሁሉም አካባቢ በተለይ ከደቡብ እንደሚመጡም ይናገራሉ፡፡ ብዙዎችም ትምህርትን ከጅምሩ አሊያም መሃል ደርሰው ያቋረጡ ናቸው፡፡
ቤተሰብ፣ ምግብ፣ ትምህርት ማደሪያና ሁሉንም ያጡ ጎዳና ተዳዳሪዎች፣ የሙጥኝ ብለው የያዙት በሱስ ውስጥ መጠመድን ነው፡፡ ሁሉን ለመርሳት በሱስ መጠመድን ይመርጣሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ያነጋገርነውና በቦሌ አካባቢ ያገኘነው ጎዳና ተዳዳሪም ‹‹እኔም ማስቲሽ በሳቡኩና ሁሉን በረሳሁኝ›› ሲል፣ የጎዳና ሕይወት አስመራሪ ግን ብዙዎች ምርጫ በማጣት የሚገቡበት እንደሆነ ነግሮናል፡፡
በአዲስ አበባም ሆነ በየክልሉ ከተሞች የሚገኙ ጎዳና ተዳዳሪዎችም ለተለያዩ ሱስ የተጋለጡ ናቸው፡፡
ከኢትዮጵያ የምግብ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ያገኘነው መረጃም፣ የጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናትና ወጣቶች ማስቲሽ ቤንዚን፣ የመኪና ጭስ፣ ቀለምና ሌሎችንም ያሸታሉ፣ ይስባሉ፡፡ የለገሃር አካባቢ ፖሊስን ባነጋገርንበት ወቅት ደግሞ አንዳንዶቹም ኪስ እንደሚገቡ ገለጻ ነበር፡፡
የጎዳና ልጆች ሕይወታቸው ውስብስብ ያለ ከመሆኑም አንፃር፣ ከዚህ ቀደም በመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እነሱን ለማንሳትና የተሻለ ሕይወት እንዲኖሩ ለማድረግ የተሠራው ሥራ እምብዛም ለውጥ አላሳየም፡፡ ዘላቂነትም አልነበረውም፡፡
በመሆኑም በተለይ አዲስ አበባ የጎዳና ተዳዳሪዎችም መናኸሪያ ሆናለች፡፡ ይህ ግን እንዲህ ሆኖ የሚቀጠል አይደለም፡፡ ለከተማዋ ገጽታም ብቻ ሳይሆን የሕፃናቱንና የታዳጊ ሕፃናቱን ሕይወት ከጎዳና ለመታደግና ልመናን ለማስቀረት ሲባል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ የሚገኙ የጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናትና ወጣቶችን ከልመናና ከጎዳና ሕይወት፣ ብሎም ከገቡበት የተመሰቃቀለ የአኗኗር ዘይቤ ለማውጣትና ብቁ ዜጋ ለማድረግ የትግበራ ዕቅድ አውጥቷል፡፡
የትግበራ ዕቅዱን ለመተግበር ማን ምን መሥራት እንዳለበት ከባለድርሻ አባላት ጋር ውይይትም ተደርጓል፡፡ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ከጎዳና የማንሳትና ሕይወት የመቀየሩ ሥራም ከዚህ ቀደም እንደነበረው ያዝ ለቀቅ ሳይሆን በዘላቂነት ችግሩን ለመቅረፍና ያለመ ነው፡፡
የትግበራ ዕቅዱ መንገድ ላይ የወደቁ አረጋውያንን፣ የአዕምሮ ሕሙማንን፣ ለማኞችን የሚያነሳ ፕሮጀክት ሲሆን፣ የማንሳት ሥራውም ከ12 እስከ 14 ወራት ይጠናቀቃል፡፡
ይኼንን ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሚመድበው በተጨማሪ ከኅብረተሰቡ ተጨማሪ ድጋፍ ለማግኘት የማኅበራዊ ትረስት ፈንድ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ይፋ ሆኗል፡፡
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የበላይ ጠባቂ የሆኑበት ማኅበራዊ ትረስት ፈንድ፣ በጎዳና ላይ የሚኖሩ ደጋፊ ያጡ አረጋውያንን፣ የአዕምሮ ሕሙማንን፣ አካል ጉዳተኞችንና ለማኅበራዊ ችግር የተጋለጡትን በዘለቄታዊነት ለመርዳት ያስችላል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ የከፈተው የአዲስ አበባ ማኅበራዊ ትረስት ፈንድ የባንክ ቁጥር 1000272444726 ወይም በ6400 ላይ A ብሎ በመላክ የከተማው ሕዝብ፣ የእምነት ተቋማት፣ የልማት ድርጅቶችና የሚዲያ ባለሙያዎች እንዲደግፉም የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አሳውቀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የውስጥ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን፣ ለፈንዱ ማስጀመሪያም 100 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡
በአዲስ አበባ የሚገኙ 50 ሺሕ የጎዳና ተዳዳሪዎችን የማንሳቱ ሥራ የሚጀመር ሲሆን ሥራውም ስድስት በሚሆኑ ማዕከላት የጎዳና ተዳዳሪዎችን በማንሳት ይጀመራል፡፡ ሥራውን የተሳካ ለማድረግም ከተማው በሚያደርገው ጎን ለጎን የሃይማኖት አባቶች፣ ሚዲያ፣ አርቲስቶችና የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ከክልል ጋር የሚሠራውን ሥራ ጭምር በየሙያቸውም እንዲያግዙ ኢንጂነር ታከለ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ሥራውን በአግባቡ ለመሥራት ቦርድ መቋቋሙን፣ አማካሪ ምክር ቤቱም ሥራ መጀመሩን በመግለጽም፣ ትውልድን የማዳኑን ሥራ በበጎ ፈቃድ የሚያግዙ በሺዎች የሚቆጠሩ የከተማዋ ወጣቶች መዘጋጀታቸውን አክለዋል፡፡
በአገሪቱ የሚወደዱ የሚዚቃ ባለሙያዎችና በተለይ አርቲስት ቴዲ አፍሮና አጫሉ እሙዴሳና ኮንሰርት ሠርተው የሚገኘውን ገቢ ሙሉ ለሙሉ ወደ ትረስት ፈንዱ አካውንት ለማስገባት ቃል ገብተዋል ብለዋል፡፡
ጎዳና ተዳዳሪነትን ከምንጩ ለማድረቅ ከክልሎች ጋር እየተሠራ መሆኑን፣ ወጣቶች በያሉበት በየክልሉ ሥራ የሚያገኙበትና የሚታገዙበት ሁኔታ እንደሚኖር ገልጸዋል፡፡
ጎዳና ተዳዳሪዎች ማዕከል ገብተው ካገገሙ በኋላ ወደ ቤተሰብ የሚመለሱበት፣ ከሚሰበሰበውም ገንዘብ በዓይነትም ሆነ በሌላ ክልሎች የሚረዱበት፣ ሥራ እየተከናወነ መሆንና በአብያተ ክርስቲያናትና በመስኪድ አካባቢ ለለማኝ የሚደረግ ምፅዋት በትረስት ፈንዱ በኩል እንዲሆን ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት ከማስተማር ባሻገር ከጎዳና የተነሱትን በየሃይማኖታቸው በማስተማር ደግሞ ወደ ጎዳና ሕይወት እንዲያገቡ ይረዳሉ ተብሎ ታስቧል፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ ጎዳና ተዳዳሪ የማይሆንበትን ሥርዓት መዘርጋት፣ ከተማ ውስጥ ያለውን ነዋሪ መመዝገብ፣ ሕጋዊ ሥርዓት እንዲኖር በመሥራት ችግሩ ይቀረፋል ተብሏል፡፡