የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር ከግብፅ አቻቸው አብዱል ፈታህ አልሲሲ ጋር ለመምከር እሑድ ጥር 19 ቀን 2011 ዓ.ም. ወደ ግብፅ አምርተዋል፡፡
ሱዳናውያን የዳቦ ዋጋ በሦስት እጥፍ መጨመርንና የኑሮ መወደድን ተቃውመው ሠልፍ መውጣት ከጀመሩ ወር ያለፋቸው ሲሆን፣ ፕሬዚዳንቱ በሽር ተቃውሞው ከተጀመረ ወዲህ የውጭ ጉዞ ሲያደርጉ ይህ ሁለተኛቸው መሆኑን ዘ ኢስት አፍሪካን ዘግቧል፡፡
የሱዳን ባለሙያዎች ማኅበር ለ30 ዓመታት የዘለቀውን የፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር መንግሥት በመቃወም፣ የተቃውሞ ዘመቻ መጥራቱን ፕሬዚዳንቱ ቢኮንኑም፣ ማኅበሩ እሑድ ጥር 19 በካርቱም፣ በኦምዱራህማንና ናይልን ተከትለው በሚገኙ ከተሞች ሁሉ ነዋሪው ከቤቱ ባለመውጣት ተቃውሞውን እንዲገልጽ አድርጓል፡፡
ማኅበሩ ‹‹በቤት ውስጥ ቁጭ በሉ ተቃውሞ›› ከመጥራቱ በተጨማሪ እስከዛሬ የሚዘልቅ ተከታታይ ተቃውሞ እንዲካሄድም ጥሪውን አቅርቧል፡፡
የዶክተሮች፣ የመምህራንና የኢንጂነሮች ማኅበራትን ያቀፈው የሱዳኑ የሙያተኞች ማኅበር፣ ባለፈው ቅዳሜ የምሽት ተቃውሞ ጠርቶ የነበረ ቢሆንም፣ እማኞች በዕለቱ ብዙዎች ለተቃውሞ እንዳልወጡ ለዘ ኢስት አፍሪካን ተናግረዋል፡፡
ሱዳን ካለፈው ታኅሣሥ ወዲህ በተቃውሞ እየተፈተነች ነው፡፡ በዳቦ ዋጋ መጨመር የተቀሰቀሰው ተቃውሞም ወር አልፎት ዓይነቱን ቀይሯል፡፡
ተቃዋሚዎች ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመጋጨታቸው 30 ሰዎች መሞታቸውን ባለሥልጣናት ሲገልጹ፣ የመብት ተሟጋቾች ደግሞ ቁጥሩን ከ40 በላይ ያደርሱታል፡፡ ሕፃናትና የሕክምና ባለሙያዎችም ከሞቱት ይጠቀሳሉ፡፡
የግብፅ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሸኩሪ ባለፈው ወር ሱዳንን ሲጎበኙ፣ ውጥረት ውስጥ የሚገኘውን የሱዳን መንግሥት ግብፅ እንደምትደግፍ ተናግረው ነበር፡፡
‹‹ሱዳን ያለችበትን ያልተረጋጋ ሁኔታ እንደምትወጣው ግብፅ ታምናለች፤›› ሲሉም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
ግብፅ ሁሌም ከሱዳን ጎን እንደሆነች በተደጋጋሚ የተገለጸ ሲሆን፣ የአል በሽር የግብፅ ጉብኝትም በአገራቸው የተፈጠረውን ተቃውሞ ለማረጋጋት ከግብፅ ጋር ለመምከር ነው፡፡
የሱዳን አንድነትና መረጋጋት ሁሌም እንደምትደግፍ የምትገልጸውን ኳታር ለመጎብኘት ባለፈው ሳምንት ኳታር የነበሩት አል በሽር፣ ከኳታሩ አሚር ሼክ ታሚም ቢን ሐሚድ አል ታኒ ጋር ተወያይተዋል፡፡
አልባዋብ በድረ ገጹ እንዳሰፈረው፣ የግብፅ መንግሥት ውይይታቸውን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፣ በሱዳን አንድ ወር ያስቆጠረውን ተቃውሞ አልጠቀሰም፡፡ ሆኖም ሱዳን እንድትረጋጋ እንደግፋለን ብሏል፡፡
ፕሬዚዳንት አል በሽር፣ ሱዳን አለመረጋጋት ውስጥ መግባቷን በመግለጽ፣ ለዚህም ‹‹ጎጂ ድርጅቶች›› ብለው የገለጿቸውን ማኅበራት ኮንነዋል፡፡ የመገናኛ ብዙኃንም የተቃውሞውን መጠን አጋንነው መዘገባቸውንም ወቅሰዋል፡፡
‹‹በሱዳን ችግር አለ፡፡ ችግር የለም አላልንም፡፡ ሆኖም አንዳንድ መገናኛ ብዙኃን አጋንነው በሚዘግቡት ልክ አይደለም፤›› ሲሉም ከፕሬዚዳንት አልሲሲ ጋር የነበራቸውን ውይይት አጠናቀው በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡
በሱዳን ያለውን ተቃውሞ በዓረብ አገሮች እ.ኤ.አ. ከ2010 እስከ 2011 ተከስቶ እንደነበረው ዓረብ ስፕሪንድ ለማስመሰል ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውም፣ ለዚህ በሱዳን ያለውና በዓረብ ስፕሪንግ የነበረው ተቃውሞን የሚያመሳስሉ መፈክሮችና የማኅበራዊ ድረ ገጽ መልዕክቶች እንዳሉም ገልጸዋል፡፡
በሱዳን ላለው የኢኮኖሚ አለመረጋጋት በአሜሪካ አነሳሽነት በሱዳን ላይ ለ20 ዓመታት የተጣለውንና ሃቻምና የተነሳው የንግድ ማዕቀብ ዋና አስተዋጽኦ እንደነበረው ተናግረዋል፡፡
የሱዳን ሙያተኞች ማኅበር ማን ነው?
የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር፣ ተቃዋሚዎች በሱዳን የፖለቲካ ጥያቄ ቢያነሱም ለአሠርታት ያህል ድምፃቸውን እምብዛም አሰምተው አያውቁም፡፡ ሆኖም እየተባባሰ የመጣውን የኢኮኖሚ ቀውስና የኑሮ ውድነት በመቃወም፣ ሕዝቡ ተቃውሞ ከወጣ ካለፈው ወር ወዲህ ግንባር ቀደም በመሆን ለፖለቲከኞችም ዕድል የከፈተው ይህ ‹‹የሱዳን ሙያተኞች ማኅበር›› ነው፡፡
ማኅበሩ በብዙዎች ባይታወቅም ለተቃውሞ ጥሪ ሲያስተላልፍ ግን በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች በየከተማው ይወጣሉ፡፡
የሱዳን ሙያተኞች ማኅበር ተቋማዊ ሥርዓት የሌለውና ምን ያህል አባላት እንዳሉት እንኳን እንደማያውቅ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ አስፍሯል፡፡ ሆኖም ማኅበሩ ካለፈው ወር ወዲህ የፖለቲከኞችን ሚና ይዞ እያበጠ የመጣውን ተቃውሞ ይጠራል፣ ተቃዋሚዎችን ያበረታታል፣ የተቃውሞ ቀናትንና ዓይነትን ያሳውቃል፡፡
የሕክምና ባለሙያዎች፣ ኢንጂነሮችና የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች አንድ ላይ በመሆን የመሠረቱት ማኅበር፣ ፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር ከሥልጣን እንዲወርዱም ጠይቋል፡፡
የማኅበሩ ቃል አቀባይ መሐመድ ዩሱፍ ሙስጠፋ፣ ‹‹ሱዳን የፖለቲካና የኢኮኖሚ፣ የደኅንነትና የማኅበራዊ መሪ የላትም፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ሱዳን 100 ያህል የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢኖራትም፣ አሁን ያለውን ተቃውሞ እየመሩ አይደለም፡፡ በመሆኑም ማኅበሩ ተቃውሞውን እየመራ ይገኛል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2012 በሱዳን የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚገድብ ሕግ መውጣቱን በመቃወም በካርቱም ዩኒቨርሲቲ በሚገኙ 200 ፕሮፌሰሮች የተቋቋመው ማኅበሩ፣ ሌሎች የሙያ ማኅበራት እንዲደራጁም ሲወተውት ከርሟል፡፡
በመሆኑም የእንስሳት ሐኪሞች፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ የፋርማሲ ባለሙያዎች፣ የመምህራንና የሕግ ባለሙያዎችን ጨምሮ ስምንት ዋና ማኅበራት እ.ኤ.አ. በ2016 ተቋቁመዋል፡፡
እነዚህ ባለሙያዎችም በየከተማው በሚኖሩ ተቃውሞዎች ግንባር ቀደም ሆነው ይወጣሉ፡፡
ማኅበሩ በመንግሥት ዕውቅና ባይሰጠውም የተቋቋመው ሕግ በሚፈቅደው ‹‹በሰላማዊ መንገድ የመደራጀት መብት›› የሚለውን በመጠቀም ነው፡፡ ማኅበሩ ሙያተኞች የሚገጥማቸውን ችግር በመፍታት ላለፉት አራት ዓመታት ቢዘልቅም አሁን ላይ ደግሞ የፖለቲካ ካባ ተላብሶ አመፅ ጠሪ ሆኗል፡፡ ከዚህም አልፎ የሽግግር መንግሥት ለማቋቋም ዕቅድ እስከማውጣት ደርሷል፡፡ ሆኖም ማኅበሩ ወደ ፖለቲካ ፓርቲ እንደማይቀየር ቃል አቀባዩ ሙስጠፋ ተናግረዋል፡፡
ማኅበሩ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር እንደሚሆንና ለዚህም ለስላሳ የመግባቢያ ቃላትን እየተጠቀመ ይገኛል፡፡ የፕሬዚዳንቱ ኦማር አል በሽር የግብፅ ጉብኝትም ከቀን ቀን ዓይነቱን እየቀየረ የመጣውን ተቃውሞ ለማርገብ የሚያስችልን መላ ከግብፅ ለማግኘት ነው ተብሏል፡፡
(ጥንቅር በምሕረት ሞገስ)