የየካቲት 1966 ዓ.ም. አብዮት ፍንዳታ ተከትሎ የተቋቋመው የጦር ኃይሎች፣ የፖሊስ ሠራዊትና የብሔራዊ ጦር አስተባባሪ ኮሚቴ ‹‹120›› መሥራች አባላት መካከል አንዱ ነበሩ፡፡ በኋላም የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ሥልጣን ከተቆናጠጠ በኋላ በሒደት የደርጉ ቋሚ ኮሚቴ ውስጥ በአመራርነት የተቀመጡት ሊቀመንበሩን ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ጨምሮ ከሰባቱ ከፍተኛ ሹማምንት አንዱ ሻምበል ለገሠ አስፋው ነበሩ፡፡
የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲን (ኢሠፓ) እንዲያዋልድ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሠርቶ አደሮች ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን (ኢሠፓአኮ) የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል፣ ኢሠፓ ከተመሠረተ በኋላ የፖሊት ቢሮ አባልና የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ የነበሩት ሻምበል ለገሠ፣ በትግራይ ራስ ገዝ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በ1980 ዓ.ም. ሲታወጅ የበላይ ወታደራዊ አስተዳዳሪ በመሆን አካባቢውን ሕወሓት እስከሚቆጣጠረው ድረስ ሠርተዋል፡፡ በዘመናቸው በሐውዜን ገበያ ላይ በደረሰ በአየር በተፈጸመ ድብደባ ላለቁት ሰዎች ተጠያቂ ተደርገውም ነበር፡፡
የደርግ (ኢሕዲሪ) መንግሥት በ1983 ዓ.ም. መወገድ ተከትሎ በሰው ዘር ማጥፋት ወንጀል ተጠርጥረው ከታሠሩትና በሞት እንዲቀጡ ከተወሰነባቸው ከፍተኛ ባለሥልጣናት መካከልም አንዱ የነበሩ ሲሆን፣ 20 ዓመት በእስር ካሳለፉ በኋላ የሞት ቅጣቱ በይቅርታ ወደ ዕድሜ ልክ ተለውጦ በአመክሮ መፈታታቸው ይታወቃል፡፡ ሻምበል ለገሠ ከእስር ከተፈቱ በኋላ በግል ሥራ ተሰማርተው እንደ ነበር ይወሳል፡፡
በቀድሞ ሸዋ ጠቅላይ ግዛት በመናገሻ አውራጃ መስከረም 21 ቀን 1935 ዓ.ም. የተወለዱት ሻምበል ለገሠ፣ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት ጥር 17 ቀን 2011 ዓ.ም. አርፈው ሥርዓተ ቀብራቸው ጥር 19 ቀን በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ሌተና ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታና ጠቅላይ ሚኒስትር ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ በተገኙበት ተፈጽሟል፡፡
ሻምበል ለገሠ ባለ ትዳርና የአምስት ልጆች አባት የነበሩ ሲሆን አራት የልጅ ልጆችም አይተዋል፡፡