Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በወሊድና በቅድመ ወሊድ የሚያጋጥም የደም መፍሰስ በሁለት ሰዓት ውስጥ ይገድላል››

ዶ/ር ተመስገን አበጀ፣ በብሔራዊ የደም ባንክ አገልግሎት የደም ለጋሾች ዘርፍ አገልግሎት ዳይሬክተር

በኢትዮጵያ የደም ማስተላለፍ ሕክምና የተጀመረው በ1962 ዓ.ም. ለሚሽነሪ ሥራ ወደ ኢትዮጵያ በመጡ እሥራኤላዊ የቀዶ ሕክምና ባለሙያ ነው፡፡ በቀድሞ ቤተሳይዳ በአሁኑ የካቲት 12 ሆስፒታል ነው አገልግሎቱ መሰጠት የተጀመረው፡፡ በወቅቱ ሥራውን እንዲያሳልጡ በአዲስ አበባና  በጂማ፣ በሐረር፣ በጎንደር፣ በአዳማና በመሳሰሉት ከተሞች 12 ትልልቅ የደም ባንኮች ተቋቋሙ፡፡ የደም ማሰባሰብ ተግባሩን እንዲያከናውን ኃላፊነቱ ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ተሰጥቶ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ተጠሪነቱን ለጤና ሚኒስቴር እንዲሆን በማድረግ ከቀይ መስቀል ማኅበር ሥር እንዲወጣ ከተደረገ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የባንኩን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በተመለከተ ሻሂዳ ሁሴን የደም ለጋሾች ዘርፍ አገልግሎት ዳይሬክተሩን ዶክተር ተመስገን አበጀን አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡– በኢትዮጵያ የደም ልገሳ ታሪክ ውስጥ የቤተሰብ ምትክ የተለመደ አሠራር ነበር፡፡ የቤተሰብ ምትክ ምን ዓይነት ችግሮች ነበሩበት?

ዶ/ር ተመስገን፡– እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ የደም ማስተላለፍ ሕክምና ትኩረቱን አድርጎ ይሠራ የነበረው ከቤተሰብ ምትክ ነበር፡፡ የደም ማስተላለፍ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ከቤተሰብ ምትክ ደም ተወስዶ ነው ይሰጣቸው የነበረው፡፡ ይህም ማለት አንድ ሰው ቢታመምና ለሚሰጠው ሕክምና ደም ቢያስፈልግ ደም የሚሰጠው ዘመድ ያስፈልገዋል ማለት ነው፡፡ ቤተሰብ ከሌለው ደግሞ ገንዘብ ይከፍልና ሌላ ሰው እንዲሰጠው ይደረጋል፡፡ የደም ማስተላለፍ ሕክምና ለረዥም ዓመታት በዚህ መልኩ ሲፈጸም የተለያዩ ችግሮች ነበሩበት፡፡ አንደኛ የተደራሽነት ችግር ነው፡፡ ሁሉም የጤና ተቋማት የሚፈልጉትን ያህል ደም ለማግኘት ይቸገሩ ነበር፡፡ ከነበሩት አጠቃላይ የጤና ተቋማት መካከል የደም ማስተላለፍ ሕክምና ይሰጡ የነበሩት 54 በመቶ እንኳን አይሞሉም ነበር፡፡ በቤተሰብ ምትክ ስለነበር አቅርቦቱ ውስን ነው በቂና ደህንነቱ የተጠበቀ ደምም አይገኝም፡፡ ቤተሰብ ወይም ገንዘብ ያለው ካልሆነ ደም አያገኙም ነበር፡፡ አራት ዓይነት የደም ዓይነቶች አሉ፡፡ አራቱ ደግሞ ፖዘቲቭና ኔጌቲቭ አላቸው፡፡ የሚፈለገውን የደም ዓይነት ከማግኘት አኳያ ችግር አለ፡፡ ታካሚዎች የሚሰጣቸው ደም ጤንነቱ የተጠበቀ መሆን አለበት፡፡ ከቤተሰብ ምትክ ወይም በግዢ የሚገኘው ደም ብዙ ጊዜ ጤንነቱ የተጠበቀ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሰዎች ወደው ሳይሆን በግዳጅ ነው የሚሰጡት፡፡ በሰዓቱ የሚታየው የቤተሰብ ጭንቀትና ደሙ መገኘቱ ላይ ነው እንጂ ጤነኛ ነው አይደለም የሚለው አይደለም፡፡ በዚህ አንደኛ ሰውየው ይጎዳል ሁለተኛ ደግሞ የሚሰጠው ደም በደም ሊተላለፉ ከሚችሉ በሽታዎች ንፁህ ላይሆን ስለሚችል በሽታን የማስተላለፍ ዕድል አለው፡፡

ሪፖርተር፡ደሙ ሳይመረመር ለበሽተኛው ይሰጥ ነበር እያሉ ነው?

ዶ/ር ተመስገን፡–  አስፈላጊው ምርመራ ይደረጋል፡፡ ሲመረመር በሽታ ያለበት ሆኖ ሲገኝ ይወገዳል፡፡ ያንን ሁሉ መንገድ መጥቶ፣ ሰውየውም ደሙን ሰጥቶ ጥቅም ላይ አይውልም፡፡ ከዚህ ባሻገር በስህተትም ይሁን ባልታሰበ አጋጣሚ ደሙ አልፎ ለታካሚዎች ሊደርስ ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡ብሔራዊ የደም ባንክ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ሥር እንዲወጣ የተደረገበት ምክንያት ምንድነው?

ዶ/ር ተመስገን፡– የእናቶችና ሕፃናትን ሞት መቀነስ ከምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች መካከል ነው፡፡ ለእናቶች ሞት ትልቁ ምክንያት ደም መፍሰስ ነው፡፡ ስለዚህ እናቶችን ለመታደግ ደም ያስፈልጋል፡፡ የደም ማስተላለፍ ሕክምናን ከጤናው ዘርፍ እንዲሆን በአንድ ለማቀናጀት፣ በቂና ጤንነቱ የተጠበቀ ደምም ለማግኘት ሲባል የደም ባንክን ከቀይ መስቀል ማኅበር ወደ ጤና ሚኒስቴር በ2004 ዓ.ም. እንዲዛወር ተደረገ፡፡ ለሦስት ዓመታት ያህል በጤና ሚኒስቴር እንደ አንድ መምሪያ ሆኖ ሲሠራ ቆየ፡፡ በ2007 ዓ.ም. በሚኒስትሮች ምክር ቤት በአዋጅ ፀድቆ ራሱን የቻለ ኤጀንሲ ሆኖ ተጠሪነቱም ለጤና ሚኒስቴር እንዲሆን ተደረገ፡፡ አገልግሎቱ ወደ ጤና ሚኒስቴር እንዲገባ ከተደረገበት ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ ብዙ ለውጦች ታይተዋል፡፡ ለምሳሌ 12 የነበሩት ደም ባንኮች ቁጥር ወደ 25 እንዲያድጉ ተደርጓል፡፡ ደም ባንኩም በእስትራቴጂ መሥራት የጀመረው ከዚያ ወዲህ ነው፡፡ ጤና ተቋማት በዙሪያቸው ቢያንስ ከ100 እስከ 150 ኪሎ ሜትር ራዲየስ ውስጥ ደም ባንክ እንዲኖርና ደም ማግኘት አለባቸው የሚል ስትራቴጂ ተቀመጠ፡፡ በአሁኑ ወቅት 92 በመቶ የሚሆኑት የጤና ተቋማት ደም ያገኛሉ፡፡

ሪፖርተር፡ቀሪው ስምንት በመቶ ተደራሽ ያልሆኑበት ምክንያት ምንድነው?

ዶ/ር ተመስገን፡– ይኼንን በትክክል እንዲህ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ ምናልባት እነዚህ ተቋማት ባሉበት ሁኔታ የደም ማስተላለፍ ሕክምና መስጠት የማይችሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ሪፖርተር፡መስጠት የማይችሉ በየትኛው ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው?

ዶ/ር ተመስገን፡– የደም ማስተላለፍ ሕክምና ለመስጠት መሟላት ያለባቸው ነገሮች አሉ፡፡ በመጀመሪያ ደም የማስተላለፍ ሕክምና የሚያዝ ሐኪም ሊኖር ይገባል፡፡ ሐኪም በሌለበት የደም ማስተላለፍ ሕክምና አይሰጥም፡፡ አንዳንዴ የግል የሕክምና ተቋማትም ጋር የደም ማስተላለፍ ሕክምና የሚሰጡ ሐኪሞች ላይኖሩ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ ተቋማት የደም ማስተላለፍ ሕክምና መስጠት አይችሉም፡፡ ከዚህ ባሻገርም የደም ማስተላለፍ ሕክምና ለመስጠት ራሱን የቻለ ክፍል፣ ፍሪጅና የተለያዩ መሣሪያዎች ያስፈልጋሉ፡፡ እነዚህን የማያሟሉ አገልግሎቱን መስጠት አይችሉም፡፡

ሪፖርተር፡ጤና ጣቢያዎችና ከጤና ጣቢያ በታች የሚገኙ የጤና ተቋማት ይኼንን አገልግሎት መስጠት ይችላሉ?

ዶ/ር ተመስገን፡– የደም ማስተላለፍ ሕክምና የሚሰጡ ከ400 በላይ የጤና ተቋማት በአገር አቀፍ ደረጃ አሉ፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ ከ90 በላይ ተቋማት አሉ፡፡ ይኼንን አገልግሎት የሚሰጡት የመንግሥት የጤና ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ የግል ተቋማት ናቸው፡፡ ሁሉም ትንሹን መስፈርት ማሟላት እስከቻሉ ድረስ ሕክምናውን መስጠት ይችላሉ፡፡ ለጤና ጣቢያም ቢሆን እንሰጣለን፡፡ ለምሳሌ ጤና ጣቢያዎች አብዛኛውን የማዋለድ አገለግሎት ይሰጣሉ፡፡ ነገር ግን ከፍተኛ የደም መፍሰስ አጋጣሚ ከተፈጠረ ወደ ሆስፒታል ነበር ሪፈር የሚያደርጉት፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ሳይቀር በጤና ጣቢያ ደረጃ እየተሠራ ነው፡፡ ሐኪሞችም ወደ ጤና ጣቢያ እየሄዱ አገልግሎት እየሰጡን ነው፡፡ አሁን ባለን መረጃ የመንግሥት ጤና ተቋም ሆኖ ከእኛ ጋር ደም የማይወስድ የለም፡፡ በዚህ ረገድ ትልቅ ለውጥ አምጥተናል፡፡

ሪፖርተር፡በደም ፍላጎትና አቅርቦት ላይ የታየ ለውጥ አለ?

ዶ/ር ተመስገን፡– የደም ፍላጎትና አቅርቦት ላይ ትልቅ ለውጥ መጥቷል፡፡ በ2004 ዓ.ም. የተሰበሰበው የደም መጠን 54,000 ከረጢት ነበር፡፡ በ2010 ዓ.ም. ግን 184,000 ከረጢት ደም በአገር አቀፍ ደረጃ ተሰብስቧል፡፡ ይኼ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ ከቤተሰብ ምትክና ከበጎ ፈቃደኞች የተሰበሰበውን ብንመልከት፣ በ2004 ደም ከበጎ ፈቃደኞች የተሰበሰበው ደም ከጠቅላላው አሥር በመቶ ብቻ ነበር፡፡ አምና ግን ወደ 98 በመቶ የሚሆነውን ከበጎ ፈቃደኞች የተገኘ ነው፡፡ ከቤተሰብ ምትክ ደም ያመጡ ሁለት ወይም ሦስት የሚሆኑ የደም ባንኮች ናቸው፡፡ እነሱም በሐረርና በጅግጅጋ የሚገኙ ደም ባንኮች ናቸው፡፡ ሌሎቹ ደም ባንኮች ደምን ከበጎ ፈቃደኞች ብቻ እየሰበሰቡ ለታካሚዎች አድርሰዋል፡፡  

ሪፖርተር፡ጤንነቱ የተጠበቀ ደም ከመሰብሰብ አኳያስ ምን የታዩ ለውጦች አሉ?

ዶ/ር ተመስገን፡– ጤንነቱ የተጠበቀ ደም ከማግኘት አኳያ ብዙ ለውጦች ታይተዋል፡፡ ቁጥሩን በትክክል መግለጽ ባልችልም በየጊዜው የነበረውን በማነፃፀር ማሳየት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በ2004 ዓ.ም. ደም ለጋሹን በደም ሊተላለፉ ከሚችሉ በሽታዎች ነፃ መሆኑን ስንመረምር 3.5 በመቶ የሚሆኑት ኤችአይቪ ታይቶባቸዋል፡፡ አሁን ግን የኤችአይቪ ሥርጭት በለጋሾች ዘንድ እስከ 0.5 በመቶ ወርዷል፡፡ ሄፒታይተስ ቢ በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው ሥርጭት ከፍተኛ ስለሆነ በለጋሾችም ዘንድ ይኸው እውነታ ይንፀባረቃል፡፡ ለጋሾች በደም ሊተላለፍ ከሚችሉ በሽታዎች ሥጋት ነፃ ስለመሆናቸው ጠንከር ያሉ ጥያቄዎች ይጠየቃሉ፡፡ በመጠይቁ ላይ የቀረቡ ጥያቄዎች ለጋሹ ከሥጋት ነፃ ስለሆኑ በተለያዩ መንገዶች የሚያረጋግጡ ተደርገው የተዘጋጁ ናቸው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ምላጭ ቢቆርጠው ደም መለገስ አይችልም፡፡ ምክንያቱም በአባላዘር በሽታዎች የመያዘ ዕድል አለው፡፡ የተነቀሱ ሰዎችን ደግሞ ለአንድ ዓመት እንከለክላለን፡፡ 

ሪፖርተር፡ታሪክ ሆነው ቀርተዋል የሚባሉ እንደ ቂጥኝ ያሉ የአባለዘር በሽታዎች ሁሉ በማኅበረሰቡ ላይ እንደሚታዩ ይነገራል በዚህ ረገድ ያጋጣማችሁ ነገር ካለ ቢያብራሩልን?

ዶ/ር ተመስገን፡– የቂጥኝ ሥርጭቱ ይጠፋል ብለን አንጠብቅም፡፡ ትልቁ ነገር ቁጥሩ እየቀነሰ ነው ወይ? የሚለው ነገር ነው፡፡ ላጥፋው ቢባል ከዜሮ በታች አይሆንም፡፡ እኛ ኤች አይቪ፣ ሄፒታይተስ ቢ፣ ሲ እና ቂጥኝ እንመረምራለን፡፡ ሥርጭቱን ከባለፉት ዓመታት አንፃር ስንመለከት በከፍተኛ ሁኔታ ሦስቱ ቀንሰዋል፡፡ ኤችአይቪ፣ ሄፒታይተስ ሲ እና ቂጥኝ ሥርጭት በጣም ቀንሷል፡፡ ምክንያቱም ደሙ የሚሰበሰበው ከበጎ ፈቃደኞች ነው፡፡ የሚሰጣቸው ሁለት ገጽ መጠይቅ በሽታ አለብኝ ብለህ ምታስብ ከሆነ አትስጥ ይላል፡፡ በጓደኛ ግፊት መጥቶ ደም ቢለግስ እንኳ ስልክ ደውሎ ጤነኛ አይመስለኝም አታስገቡት ሊል ይችላል፡፡ እንዲህ ያለ ጠበቅ ያለ መጠይቅ ስለሚሞሉ የሚጠራጠሩት ነገር ሲኖር ራሳቸውን ቀድመው ያገላሉ፡፡ ስለዚህ ነው በለጋሾቻችን ዘንድ ያለው የእነዚህ በሽታዎች ሥርጭት አንሶ የሚታየው፡፡ የሂፒታይተስ ደግሞ በፊት ከነበረበት አምስት በመቶ ወደ 2.8 በመቶ ወርዷል፡፡

ሪፖርተር፡ደሙ የሚመረመረው ከመውሰዳችሁ በፊት ነው? በኋላ?

ዶ/ር ተመስገን፡– ከተወሰደ በኋላ ነው የሚመረመረው፡፡ ደሙን የሚመረምረው ባለሙያ የማንን ደም እንደሚመረምር እንኳ አያውቅም፡፡ ኮድ ተለጥፎበት ነው የሚገባው፡፡ ደም ከመውሰዳችን በፊት ግን የለጋሹን የሂሞግሎቢን መጠን ለማወቅ ምርመራ እናደርጋለን፡፡ የሂሞግሎቢን ምርመራ አንድ ሰው ደም ማነስ አለበት የለበትም የሚለውን ለማወቅ የሚደረግ ምርመራ ነው፡፡ የልብ አመታት፣ የደም ግፊቱና በሰውነቱ ውስጥ ያለውን የብረት መጠንም አስቀድመን እንመረምራለን፡፡ በደም ሊተላለፉ የሚችሉ በሽታዎች የሚመረመሩት ግን በኋላ ላይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡– ደም ለማስተላለፍ ሕክምና የሚታዘዘው መቼ ነው?

ዶ/ር ተመስገን፡የዓለም የጤና ድርጅት ባወጣው እስታንዳርድ መሠረት ነው የምንሠራው፡፡ ደም ማስተላለፍ ሕክምና በኢትዮጵያ ገና እንጭጭ ነን፡፡ ጤንነቱ የተጠበቀ ደም ለሰዎች ለማድረስ የመጀመሪያው ነገር ደምን ከበጎ ፈቃደኛ መሰብሰብ ነው፡፡ ይህም የሚሆነው ከበጎ ፈቃደኛ የሚሰበሰብ ደም በተሻለ ጤናማ ነው ተብሎ ስለሚታሰብ ነው፡፡ ሁለተኛ ለአራቱ በደም ለሚተላለፍ በሽታዎች ምርመራ መደረግ አለበት፡፡ ሦስተኛ አግባብነት ያለው የደም ማስተላለፍ ሕክምና በጤና ተቋማት መሰጠት አለበት፡፡ በመርህ ደረጃ ደም መሰጠት ያለበት የመጨረሻ አማራጭ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ደም ማስተላለፍ በራሱ ጉዳት ሊኖረው ስለሚችል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ደም ለሚያስፈልጋቸው ብቻ ነው መሰጠት ያለበት፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ወድቆ ቢጎዳ ቅድሚያ የሚሰጠው ግሉኮስ ምናምን ነው እንጂ ደም አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡ከጥቅም ውጪ የሆኑ ወይም በሽታ የተገኘባቸውን የደም ከረጢቶች የምታስወግዱት በምን ዓይነት ሥርዓት ነው?

ዶ/ር ተመስገን፡– እኛ ዘመናዊ ጢስ አልባ ማስወገጃ አለን፡፡ ጊዜ ያለፈባቸውን ደሞችና በሽታ ያለባቸውን የምናስወግደው በዚሁ ዘመናዊ ማስወገጃ ነው፡፡

ሪፖርተር፡በዓመት ከሚሰበሰበው ደም መካከል ምን ያህሉ ጊዜ ያልፍበታል?

ዶ/ር ተመስገን፡– እኛ ጋር ጊዜ አያልፍበትም፡፡ አንድ ነገር ልንገርሽ እኛ ቀይ የደም ሴል፣ ፍሬሽ ፍሮዝን ፕላዝማ፣ ፕላትሌት የተባሉ የደም ተዋፅኦዎች እናመርታለን፡፡ ቀይ የደም ሴል የቆይታ ጊዜው 72 ቀን ነው፡፡ ፕላትሌት የሚባለው ደግሞ አምስት ቀን ድረስ ይቆያል፡፡ ፍሬሽ ፍሮዝን ፕላዝማ ግን የቆይታ ጊዜው አንድ ዓመት ነው፡፡ ማቀዝቀዣ ውስጥ ገብቶ ለአንድ ዓመት ይቆያል፡፡ ቀይ የደም ሴልና ፕላትሌት ካለው ፍላጎት አንፃር በማንኛውም መንገድ ጊዜ አያልፍባቸውም፡፡ ፍሬሽ ፍሮዝን ፕላዝማ ብዙ ጊዜ አይፈልግም፡፡ ብዙ ተጠቃሚም የለውም፡፡ በሳምንት 10 ወይም 20 ጊዜ ብንጠየቅ አንዳንድ ደሞች በተፈጥሮ አይፈለጉም፡፡ ለምሳሌ ኤቢን ማንሳት እንችላለን፡፡ የእኛ ማኅበረሰብ አብዛኛው የደሙ ዓይነት ‹‹ኦ›› ነው፡፡ ኢቢ ደግሞ ከስንት አንድ ነው፡፡ ኢቢ ለራሱ አንጂ ለሌላ የደም ዓይነት መሆን አይችልም፡፡ ኤቢ ደም ይሰበሰብና ለረዥም ጊዜ ይቆያል፡፡ ነገር ግን ሆስፒታሎች የቆይታ ጊዜው ከማብቃቱ አምስት ቀናት አስቀድመው ወደኛ ያመጡታል፡፡ እኛ የሚፈልጉ ካሉ ለሌሎች በፍጥነት እንዲሰራጭ እናደርጋለን፡፡ ፍላጎት ከሌለ ግን እንዲወገድ ይደረጋል፡፡

ሪፖርተር፡ኢትዮጵያ በዓመት ምን ያህል ከረጢት ደም ያስፈልጋታል?

ዶ/ር ተመስገን፡– ብዙ ዓይነት የደም መጠን መለኪያዎች አሉ፡፡ የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው ግን በታዳጊ አገሮች ቢያንስ አንድ በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ደም መለገስ አለባቸው፡፡ ባደጉት አገሮች ደግሞ ሦስት በመቶ የሚሆኑ ደም መስጠት እንዳለባቸው ይገልጻል፡፡ ከዚህ አንፃር የኛን አገር ብንመለከት ለ100 ሚሊዮን ሕዝብ በዓመት አንድ ሚሊዮን ከረጢት ደም ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ይኼ ትክክለኛ ቁጥር ነው የሚለውን አሁን ካለው የደም ፍላጎትና አጠቃቀም አንፃር ስንመለከት ትክክል አይመስልም፡፡ የጤና ተቋማት መስፋፋት፣ የደም ማስተላለፍ ሕክምና፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የመጠቀም ነገር የሚታየው ከተማ ላይ ነው፡፡ በገጠር አካባቢ ብዙም አይደለም፡፡ ስለዚህ ካለው ፍላጎት አንፃር በዓመት አንድ ሚሊዮን ከረጢት ደም መሰብሰብ አያስፈልግም፡፡ ነገር ግን እኛ በስትራቴጂክ ዕቅዳችን የያዝነው አለ፡፡ እኛ ካለው ፍላጎት አንፃር እ.ኤ.አ. በ2020 500 ሺሕ ከረጢት ደም ለመሰብሰብ ዕቅድ ነድፈናል፡፡  

ሪፖርተር፡በዚህ ዓመት ምን ያህል ከረጢት ደም ለመሰብሰብ አቅዳችኋል?

ዶ/ር ተመስገን፡– 280 ሺሕ ከረጢት ደም ለመሰብሰብ አቅደናል፡፡ በስድስተኛ ወራችን ላይ 106 ከረጢት ደም ሰብስበናል፡፡ ከአምናው ጥሩ ለውጥ ያለ ይመስላል፡፡ በዓመቱ በሁለተኛ አጋማሽ ላይ ሁሌ ቁጥሩ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ምክንያቱም ክረምት ላይ የደም ልገሳ እንዲሁ ይቀንሳል የትምህርት ተቋማት ይዘጋሉ፣ የአየር ጠባዩም አይመችም፡፡ ስለዚህ የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት አስቸጋሪ ናቸው፡፡ ሐምሌ፣ ነሐሴ፣ መስከረም ከባድ ጊዜያት ናቸው፡፡ መሰብሰብ የሚጀመረው ከዚያ በኋላ ነው፡፡ በሁለተኛው ግማሽ ዓመት ግን ምንም ችግር ሳያጋጥመው የማሰባሰብ ሒደቱ ተጠናክሮ ይጥላል፡፡

ሪፖርተር፡– ግጭትና ግርግር በደም ማሰባሰብ ሒደቱ ላይ ምን ያህል ተፅዕኖ እያሳረፉ ይገኛሉ?

ዶ/ር ተመስገን፡– በጣም ተፅዕኖ ያሳድራሉ፡፡ በዚህ ዓመት በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዱ የደም ባንኮች አሉን፡፡ ለምሳሌ ነቀምት አካባቢ የሚገኘው የደም ባንካችን ከባለፈው ዓመት ያነሰ አፈጻጸም ነው ያሳየው፡፡ ከባለፈው ዓመት አንፃር 46 በመቶ ብቻ ነው መሰብሰብ የተቻለው፡፡ ረብሻና ግጭት በነበረባቸው ወቅቶት በጅግጅጋ፣ በአሶሳ ደም መሰብሰብ አልተቻለም፡፡ ረብሻና ግጭት ሲኖር ደም የማሰባሰብ ሒደቱ ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ ከዚህ ባለፈው ‹‹ረብሻና ግጭት ባላቸው ወቅቶች የደም ፍላጎት ይጨምራል፡፡››

ሪፖርተር፡– አሁንም ድረስ እናቶች በደም መፍሰስ እየሞቱ ነው፡፡ እነሱን መታደግ ለምን አልተቻለም?

ዶ/ር ተመስገን፡– ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚከሰተው የእናቶች ሞት 60 በመቶ የሚሆነው በደም መፍሰስ የሚከሰት ነው፡፡ ‹‹በወሊድና በቅድመ ወሊድ የሚያጋጥም የደም መፍሰስ በሁለት ሰዓት ውስጥ ይገድላል›› ስለዚህ እነሱን ለመታደግ ሁሌም ዝግጁ ሆኖ መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ በነገራችን ላይ አገሪቷ የእናቶችን ሞት በመቀነስ ረገድ ከአፈሪካ ቀዳሚ ነች፡፡ ለዚህም የደም አቅርቦቱ ተደራሽ መሆኑ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ ነገር ግን ከዚህም በላይ የደም አቅርቦቱ መሻሻል አለበት፡፡ ለሚታየው የእናቶች ሞት ደም ማጣት አንዱ ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡ ትክክለኛውን ጉዳይ ለማወቅ ግን ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አብዛኛው በገጠር አካባቢ የሚከሰተው የእናቶች ሞት የጤና ተቋማት ለመድረስ በሚወስደው ረዘም ያለ ጊዜ የሚከሰት ነው፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

አደራውን ለመጠበቅ ዕድል ያላገኘው ቅርስ ባለአደራ

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር ከተመሠረተ ሦስት አሥርት አስቆጥሯል፡፡ ማኅበሩ በእንጦጦ ተራራማ ቦታዎች በአደራ በመንግሥት በተረከበው 1,300 ሔክታር መሬት ላይ የተለያዩ አገር በቀል ዛፎችን በመትከል...

ብዝኃ ትምህርቱን ‹ስቴም› ለማስረፅ

ስሜነው ቀስቅስ (ዶ/ር) የስቴም (Stem) ፓውር ግብረ ሰናይ ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተርና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቴክኖሎጂ አማካሪ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የማስተርስና የፒኤችዲ...

‹‹እውነታውን ያማከለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ግንዛቤን ማጠናከር ያስፈልጋል›› ደመቀ ደስታ (ዶ/ር)፣ በአይፓስ የኢትዮጵያ ተወካይ

በሥነ ተዋልዶ ጤና ጉዳዮች ላይ በመሥራት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሰው አይፓስ፣ የኢትዮጵያን ሕግ መሠረት አድርጎ በሴቶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ከጤና ሚኒስቴርና ከክልል ጤና ቢሮዎች...