Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየባንክ ኢንዱስትሪው ከድጋፍ በተጨማሪ ቁንጥጫም ያስፈልገዋል

የባንክ ኢንዱስትሪው ከድጋፍ በተጨማሪ ቁንጥጫም ያስፈልገዋል

ቀን:

በመርዕድ አባተ

የኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ አፍሪካ ውስጥ ካሉ በርካታ ባንኮች ጋር ሲወዳደር በዕድሜው አንጋፋ ቢሆንም በአገልግሎት አሰጣጡ፣ በአደረጃጀቱ፣ በዘመናዊነቱም ሆነ በካፒታል አቅሙ ሁለንተናዊ ድክመት ይታይበታል፡፡ ለዚህም በርካታ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ተጠቃሽ ምክንያት ሆነው ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ ባንኮች ከሕዝብ በአደራ የተቀበሉትን ገንዘብና የውጭ ምንዛሪ እንዲያስተዳድሩ በሕግ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡ ባንኮች በሚያንቀሳቀሱት ዕምቅ ሀብት ምክንያት ኢኮኖሚው ላይ ያላቸው ተፅዕኖም ከፍተኛ ስለሆነ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል አለባቸው፡፡

የውጭ ባንኮች አገር ውስጥ መሥራት ሲፈቀድላቸው የሚፈጠረውን የሰላ ውድድር ለመቋቋም እንዲችሉ የገበያ ጥበቃ የሚደረግላቸው ቢሆንም፣ በኮርፖሬት ገቨርናንስ እንዲመሩ በብሔራዊ ባንክ በኩል የሚከናወኑ አስገዳጅ ሙያዊ ቁጥጥሮች አሉባቸው፡፡ እነዚህ ተግባራት ዕውን የተደረጉት ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች ውድድር ክፍት በሚሆንበት ጊዜ አገር በቀል ባንኮቹ በቴክኖሎጂ፣ በሙያዊ ብቃትና በካፒታል አቅም ራሳቸውን አብቅተው እንዲገኙና ውድድሩን ለመቋቋም እንዲችሉ በማሰብ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ባንኮቹ ለአገሪቱ ልማታዊ እንቅስቃሴዎች የሚያግዝ ዘመናዊ አገልግሎት እንዲያገኙ፣ ዜጎችም ከባንኮቹ ሙያዊ ዕገዛ በማግኘት የዕድገት ጎዳናችንን በስኬት ለመወጣት እንዲችሉ ለማድረግ ነው፡፡

ከላይ ባነሳሁት መሠረታዊና አገራዊ ዕቅድና ራዕይ ምክንያት ከገበያ ጥበቃ በተጨማሪ፣ መንግሥት በከፍተኛ ድካም የሚያገኘው የውጭ ምንዛሪ ላይ ባንኮች በብቸኝነት የመወሰንና የማትረፍ መብት ሰጥቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አገሪቱ ከምታስመዘግበው ዓመታዊ ግሽበት አኳያ ሲመዘን እዚህ ግባ በማይባል ደረጃ እጅግ በጣም ዝቅተኛ በሆነ ምጣኔ ወለድ ለቆጣቢዎች እየከፈሉ፣ ሁለት እጥፍ ሊባል በሚችል የወለድ ምጣኔ እንዲያበድሩ ዕድሉ ተመቻችቶላቸዋል፡፡ ይኼንን ልዩ አጋጣሚ ባንኮቹ እንዴት እየተጠቀሙበት ነው ስንል ግን፣ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በሚመጥን ደረጃ ሆኖ አናገኘውም፡፡ እነዚህ ሁሉ ልዩ ጥቅሞችን ተንተርሰው ዕውን ማድረግ የሚገባቸውን እሴት የሚፈጥር፣ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ የሚያሻሽል፣ በዚያው ልክ ደግሞ ተገቢውን ትርፍ በሚያስገኝ ተግባር ላይ ከማተኮር ይልቅ፣ ቀዳሚና ዋና አጀንዳቸው አድርገው የሚንቀሳቀሱት ትርፍ ማዕከል በማድረግ ብቻ ሆኗል፡፡ 

በትርፍ ላይ የተመሠረተው ውድድር በሚፈጥረው የሞት የሽረት፣ ትግል ምክንያት በሒደት ቀሪዎቹ ባንኮቹ በአንድ በኩል እጅግ የሠላና ፍፁም በቅራኔ የተሞላ ሕገወጥ ድርጊት ውስጥ የተጠመዱ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለትርፍ ሲባል ፍፁም አገራዊ ራዕይና ሕዝባዊ ምልከታ ያጡበትና ራስን ብቻ የማበልፀግ ተግባር ውስጥ ተዘፍቀዋል፡፡ ይህ ፍትጊያ የበዛበት፣ አንዳችም ሙያዊ ዕገዛ የሌለው፣ ክህሎት የጎደለውና አብሮ በማደግ ላይ ያልተመሠረተ አካሄድ ደግሞ የውድቀት ሀ፣ ሁ . . .  መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ 

ባንኮቹ የብድርም ሆነ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦታቸውን ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ በአብዛኛው በአንድ ኢኮኖሚያዊ መደብ (Economic Class) ውስጥ ለሚካተት ከፍተኛ ባለሀብት ብቻ እያበደሩ ይገኛሉ፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንዶች ባንኮች ጥቂት ባለሀብቶች ገበያውን እንዲቆጣጠሩና ብቸኛ የገበያ ዋጋ ወሳኝ እንዲሆኑ ዕድሉን እያመቻቹ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በሚቋቋሙበት ጊዜ ከፍተኛውን ድርሻ ለወሰዱ ባለቤቶቻቸውና አጃቢዎቻቸው አገልጋይ ስለሆኑ፣ የውጭ ምንዛሪና ብድር ላይ አርቴፊሻል እጥረት በመፍጠር አብዛኛውን ማኅበረሰብ ከባንኮቹ ተጠቃሚነት እንዲገለል አድርገዋል፡፡

የባንክ ኢንዱስትሪው ሠራተኛ ከመቅጠር ጀምሮ ዕድገትና ዝውውር፣ እንዲሁም የብድርና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ማዕከል ያደረገው በአብዛኛው በጥቅም ትስስርና በብሔር ተወላጅነት ላይ የተመሠረተ ስለሆነ፣ አዳዲስ ባንኮች ኢንዱስትሪውን ሲቀላቀሉ ገና ከምሥረታቸው ጀምሮ ብሔር ተኮር ወይም ሃይማኖትን ማዕከል እንዲያደርጉ አስገድደዋቸዋል፡፡ ይህ ጉዳይ በባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ ጊዜያዊ ጥቅም የሚያስገኝ ስትራቴጂ ቢመስልም፣ ለዘለቄታው ግን ከፍተኛ ሥጋት የሚደቅን መሆኑ መራራ እውነታ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

ይህ አስተሳሰብ ገለልተኛ የሆነው ማኅበረሰብና በተለይ ደግሞ የአገሪቱን አጠቃላይ ቁጠባ በማሳደግም ሆነ ከአፈር ጋር ታግሎ የውጭ ምንዛሪ ከሥር ከመሠረቱ ለማመንጨት ምክንያት በመሆን ከፍተኛ ተሳትፎ የሚያደርገው ሰፊው ማኅበረሰብ፣ ከብድር ሥርዓቱም ሆነ ከውጭ ምንዛሪ አቅርቦቱ ፍፁም የሚያገል ነው፡፡ በዚህም ምክንያቱም በሀብትና በድህነት መካከል እየተፈጠረ ላለው ክፍተት መንስዔ ከመሆናቸውም በላይ፣ የገንዘብ ዝውውርን በማጥበብ ባንኮች ምን ያህል መሰናክል እየፈጠሩ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡

ከዚህም በላይ ባንኮቹ በተመጣጣኝ የወለድ ምጣኔ መካከለኛና ዝቅተኛውን ነጋዴ ወይም ቀሪውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ አንዳችም ሥርዓት ያልዘረጉ ከመሆናቸውም በላይ፣ እጅግ የሚያሳስበው ጉዳይ ደግሞ በርካሽ አግኝተው ከፍተኛ ትርፍ የሚያጋብሱበትን ቁጠባም ሆነ የውጭ ምንዛሪ የሚለግሳቸውን ሕዝብ በድህነቱ ምክንያት በቂ የትርፍ ማጋበሻ መሆን፣ ስለማይችል ከጨዋታ ውጪ በማድረግ ራሳቸውንና ተከታዮቻቸውን ብቻ የብድርና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ተጠቃሚ በማድረግ፣ በከፍተኛ ሀብት የማግበስበስ ሥራ የተጠመዱ መሆናቸውን መመልከት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የባንኮቹ የቦርድ አባላትም ሆኑ ከፍተኛ አመራሮቻቸው ምን ያህል ለሕዝባዊ አደራ የማይበቁ መሆናቸውን ያሳያል፡፡

ከዚህ መረዳት የሚቻለው የባንኮቹ ተጠሪዎችም ሆኑ አመራሮቹ ትርፍ ለማጋበስ መንስዔ ሊሆናቸው ካልቻለ በስተቀር ባንኮቹ ማኅበራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ለማድረግ አንዳችም የኃላፊነት ስሜት የሌላቸው ከመሆኑም በላይ፣ በአጠቃላይ ማኅበረሰቡን ለግሽበት በሚዳርግና አገራዊ ተቀማጭን በጣት ለሚቆጠሩና እሴት ለማይፈጥሩ ባለሀብቶች በማከፋፈል፣ ወይም ባንኮቹን በባለቤትነት ተቆጣጥረው በሰየሟቸው የቦርድ አመራሮች አማካይነት ብድርና የውጭ ምንዛሪውን ‹‹ለባለቤቶች›› ማከፋፈልና ቀሪውን ደግሞ በድርሻ መልክ በመከፋፈል የአገሪቱን ሀብት በሞኖፖሊ እየተቆጣጠሩት መሆኑን ነው፡፡

ከላይ ለማንሳት እንደሞከርኩት ባንኮቹ ከትርፍ ባሻገር ማኅበረሰባዊ  ግዴታቸውን የመወጣት ሞራላዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው ፈጽመው መዘንጋታቸውን ነው፡፡ ማኅበረሰባዊ ግዴታ ማለት ደግሞ፣ ዓመቱ መጨረሻ ላይ ከተንበሸበሹበት ትርፍ ላይ ትንሽ ቆንጥረው በምፅዋት መልክ ለመረጡት በጎ አድራጎት ድርጅት ድጎማ መስጠት ብቻ የሚመስላቸውም ባንኮች አሉ፡፡ ዋናው ቁም ነገር ያለው የትርፍ መነሻቸው የሆነው ከሕዝብ በቁጠባ መልክ በአደራ የሚሰበስቡት ገንዘብና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት የአገሪቱን ዕድገት በማቀላጠፍ ገንቢ ሚና ለሚኖራቸውና እሴት ለሚፈጥሩ ልማታዊ ሥራዎች ተጨባጭ ድጋፍ በማድረግ ድርሻቸውን መወጣት ስላለባቸው፣ ትኩረት መስጠት አስፈላጊ መሆኑን መረዳት አለመፈለግ ላይ ነው፡፡ ዜጎች በቀጥተኛም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ከዚህ ዕምቅ ሀብት የሚጠቀሙበትን መንገድ መቀየስ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ የባንክ ኢንዱስትሪው አጠቃላይ ውጫዊ ገጽታ ነው፡፡ ፈረንጆቹ እንደ ሚሉት ሰይጣኑ የሚገኘው በዝርዝሩ ውስጥ ስለሆነ (The Devil is in the Detail) እስቲ ወደ ባንኮቹ ጓዳ ጎራ ብለን ውስጣዊ ገመናቸውን በደምሳሳው እንፈትሸው፡፡

‹‹የዓሳ . . . ከአናቱ ነው›› እንዲሉ የብዙዎቹ ባንኮች ችግር የሚጀምረው ከቦርድ ነው፡፡ የአብዛኛዎቹ ባንኮች የቦርድ አባላት ከሚያገኙት የትርፍ ህዳግ መጠን ውጪ፣ በሌላው ጉዳይ ላይ አዕምሯቸው መሥራት ያቆመ እስኪመስል ድረስ በሕጋዊነትና በሕገወጥነት መካካል እየተገላበጡ በእሳት የሚጫወቱ ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ በምሳሌነት የሚቀርበው የአንዳንድ ባንክ ቦርድ አመራሮች በመርህ ደረጃ ‹‹በልቶ የሚያስበላ ሠራተኛን እንደ ችግር አናየውም፤›› እስከ ማለት መድረሳቸው ነው፡፡ የቦርድ አመራሮቹ ብድርና የውጭ ምንዛሪ በማቅረብ ሒደትና ብድር በመስጠት ዙርያ ሥርዓት አልበኝነትንና ሕገወጥነትን ያለ ኃፍረት የሚያበረታቱ፣ ሙስናና እጅ መንሻ መቀበል እጅግ አስነዋሪና በማኅበራዊ ጠንቅነቱ የተወገዘ መሆኑን እያወቁ የሚያወድሱና የሚያበረታቱ ናቸው፡፡

‹‹በዳፍንት ላይ . . . ተጨምሮበት›› እንዲሉ አብዛኛዎቹ የቦርድ አመራር አባላት በባንክ ሙያም ሆነ በባንክ አስተዳደር ዘርፍ ግንዛቤ የሌላቸው፣ ራሳቸውንም በዘርፉ ሙያ ለማሳደግ እንዳይችሉ የድሜ ገደብ የተጫጫናቸው ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት በባንኮቹ የውስጥ አሠራር ውስጥ ጣልቃ የሚገቡበት የተጋፊነት ደረጃ በሙያ ያልታገዘ፣ ገደብ የሌለውና በተለይ ደግሞ ከግል ጥቅማቸውና ዕውቀት ማነስ ከሚፈጠረው የበታችነት ስሜት የሚመነጭ ነው፡፡

በተለይ የቦርዶቹ ሥር የሰደደ ጣልቃ ገብነት የግል ጥቅማቸውን ለማስከበር ከሚነሳ ስግብግብነት የሚመነጭ መሆኑን ግልጽ የሚያደርገው፣ ብድርና የውጭ ምንዛሪ የሚያመቻችላቸውን ጥገኛ ከመሾምና ከመቅጠር የማይቦዝኑ መሆናቸው በተደጋጋሚ በባንኮቹ ሠራተኞች እሮሮ የሚሰማበት ጉዳይ መሆኑ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ባንኮቹ በሙያ ይመሩ በሚሉትና ግለኝነት በተጠናወታቸው መካከል በሚደረገው ግብግብ፣ ከአንድም ሁለት ባንኮች የመፍረስ አደጋ ተጋርጦባቸው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

ሌሎቹ ዓይነቶች የቦርድ አባላት ደግሞ የእኔ ክልልና የብሔሬ ሰዎች አልተሾሙም በማለት ንግድና ብሔረተኝነትን የሚያደበላልቁና ዘረኝነት የሚያሠራጩ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ የባንክ ቦርድ አባላት ደግሞ የትልቅ አክሲዮን ባለቤት ውክልና ስላላቸው  ብቻ ባንኩን እንደ ጓዳቸው፣ ሠራተኞቹን እንደ አሽከራቸው የሚቆጥሩ ናቸው፡፡ ለሁሉም ዓይነት የቦርድ አባላት ያልተገለጸላቸው ጉዳይ ግን ተቀማጩ ገንዘብም ሆነ የውጭ ምንዛሪው፣ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ልፋትና የአገሪቱ አንጡራ ሀብት መሆኑን  ነው፡፡ 

ሁሉም የቦርድ አባላት ሊባል በሚችል ደረጃ በገቡበት ቅጥ ያጣ የትርፍ ውድድር ውስጥ ተዘፍቀው በመርህ ደረጃ ሠራተኛውን በሙስና እንዲዘፈቅና በሕዝብ ሀብት ኪሱን አደልቦ የእነሱን ጥቅም እንዲያስከብር የሚበረታቱ ከሆነ፣ የሌላቸውን ተቀማጭ የሚያበድሩና ያላፈሩትን የውጭ ምንዛሪ ለአየር በአየር ንግድ የሚያከፋፍሉ ከሆነ፣ ወይም ባለቤትና የቦርድ አባላት እየተፈራረቁ ዕምቅ ሀብቱን የሚከፋፈሉት ከሆነ፣ ባንኮቹ እንዴት በቴክኖሎጂና በዘመናዊ አሠራር እየተደራጁ እንደ ተቋም በእግራቸው ሊቆሙ ይችላሉ? ባንኮቹስ ከትርፍ ውጪ ራቅ አድርገው በማሰብና በመሥራት አገራዊ ግዴታቸውን እንዴት ሊወጡ ይችላሉ?    

በባንኮች የውስጥ አሠራር ላይ ከፍተኛ ሚና ያለቸው ወሳኝ አካላት ደግሞ የባንኮቹ የማኔጅመት ወይም ከፍተኛ አመራር አካላት ናቸው፡፡ ከፍተኛ የባንኩ አመራሮች በአገሪቱ ውድና ዕምቅ አንጡራ ሀብት ላይ የሚወስኑ ተቋማትን የሚመሩ እንደ መሆናቸው መጠን፣  የኃላፊነት ደረጃቸውም በዚያው ልክ ከፍተኛ ነው፡፡ በግለሰብ ከሚመሩና በዕምቅ ሀብት ላይ ከማይወስኑ ሌሎች ተቋማት እኩል ሊታዩ አይገባም፡፡ ከፍተኛ ኃላፊዎች በየተቋማቸው ውስጥ የሚገኘውን ወሳኝ የሆኑ አገራዊ ሀብት፣ ማለትም በውጭ ምንዛሪና በብድር ላይ የሚወስኑ ኃላፊዎችን ሲሾሙና ሲመርጡ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

በእነዚህ አንጡራ ሀብቶች ላይ የሚወስኑ ባለሙያዎች ከዚህ ቀደም በተግባርም ሆነ በዝንባሌ ደረጃ በሙስና ተሳትፎ ያልነበራቸውና አስተሳሰባቸውም ያልተበከለ መሆኑን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በሥራቸው የሚሰማሩት ሠራተኞችም ሰብዕናቸው የሙስና ዝንባሌ የሌለው (Incorruptible) መሆኑን፣ ሚዛናዊናት ያልጎደላቸው፣ ለግለሰባዊ ጥቅም፣ ለዝምድና ወይም ለወዳጅነት ሲባል ውድ ሀብትን አሳልፈው የማይሰጡ መሆናቸውንና በሚመደቡበት ቦታ ላይ ከተለመደው በላይ ሙያዊ ብቃት ያላቸው መሆናቸውን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ በተለይ ደግሞ የሚወስኑበትን ዕምቅ ሀብት በአግባቡና እጅግ ውጤታማ በሆነ መንገድ በበቂ መተማመኛ ተደግፎ እንዲሰጥ በማድረግና በተገቢው ሁኔታ ለተገቢው ጥቅም መዋሉን ማረጋገጥ የሚችሉ፣ ለዚህም ድፍረቱና ተነሳሽነቱ አልፎ ተርፎም ግልጽነቱ ያላቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡

መሠረታዊ በሆኑ ኢኮኖሚያዊ ግብዓቶች ላይ ተቀምጠው የውጭ ምንዛሪና ብድር አሰጣጥ ላይ ውሳኔ የሚሰጡ ኃላፊዎች መመርያዎችንና ደንቦችን ተከትለው በመሥራት፣ አገሪቱ በከፍተኛ ጥረት ያፈራችውን ወሳኝ የሆነ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ከትርፍ ባሻገር አርቆ በማቀድ የተፈጠረውን እጥረት ለማካካስ አገራዊ ጥቅምን በሚያረጋግጥ መንገድ እንዲከፋፈል አሠራሮችን ማመቻቸት የሚችሉ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ አመራሮቹ ትርፍ ከማጋበስ ውጪ አገሪቱ በውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ቅድሚያ የምትሰጣቸው ዘርፎች ቅድሚያ የሚገኙበትን ሁኔታ የማረጋገጥ፣ ሕጋዊ ግዴታቸውን የመወጣትና አገራዊ ወገንተኛነታቸውን ማረጋገጥ የሚችሉ መሆን አለባቸው፡፡

ብድር  በቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ዘርፎችም በአግባቡ ተለይተው ዘርፎቹ በአገሪቱ ልማትና ዕድገት ላይ ባላቸው ተፅዕኖ ልክ ትኩረት መስጠት እንጂ፣ የቦርድ አባል በመሆናቸው ወይም እጅ መንሻና ጉቦ በማቀባበላቸው መሆን አይገባውም፡፡ ለዚህ ደግሞ የባንክ አመራሮች ምርጫ መካሄድ ያለበት እንደዚህ ዓይነቱን ኃላፊነት ለመውሰድ ባላቸው ተነሳሽነት ተመዝኖ መሆን አለበት፡፡ የባንኮቹ ከፍተኛ አመራሮችም የብድር አሰጣጡን ማማከል ያለባቸው ውጤታማ የሆኑ፣ ግን ሥር የሰደደ እጥረት ያለባቸው ዘርፎች ላይ የተሰማሩ አምራቾች ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑን፣ በተለይ ደግሞ ያለ መጉላላትና ያለ እጅ መንሻ ተጠቃሚ መሆን የሚችሉበትን ሥርዓት መዘርጋቱን ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ በአንፃራዊነትም ቢሆን በኑሮ ያልተደላደለው ማኅበረሰብ በባንኮች ዙርያ ከተፈጠረው ዕምቅ አቅም ተጠቃሚ የሚሆንበት፣ በተመጣጣኝ ወለድ ቤት የሚሠራበት፣ ከፍተኛ ትምህርት የሚማርበት፣ ልጆቹን የሚያስተምርበትና ንብረት የሚያፈራበት መንገድ ማመቻቸት አለባቸው፡፡ 

በአንድ ወቅት የሁለት ባንኮች ኃላፊዎች በሕገወጥ መንገድ የሚፈልጉትን ብቻ ለመጥቀም ሲሉ የውጭ ምንዛሪ በመፍቀዳቸውና በሒሳባቸው ውስጥ በቂ ተቀማጭ የውጭ ምንዛሪ ሳይኖር ኤልሲ በመክፍት፣ ላኪዎች በተገቢው ጊዜ ለላኩት ቁሳቁስ ክፍያ እንዳያገኙ በማድረግና የተዛባ የግብይት ሥርዓት በመዘርጋት የአገሪቱን የውጭ ንግድ ግብይት አደጋ ላይ ጥለው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት የውጭ ምንዛሪ አቅራቢዎችንና ተጠቃሚዎችን በማመሳጠር በአየር በአየርና በደላላ አማካይነት ሕገወጥ የውጭ ምንዛሪ ዝውውርና ትስስር በመፍጠራቸው፣ ከፍተኛ የሥራ አመራሮቻቸውና የቦርድ አባላቶቻቸውን ጨምሮ ሌሎችም ሠራተኞች በብሔራዊ ባንክ ትዕዛዝ ከሥራ እንዲሰናበቱ መደረጉን በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን መስማታችንን አስታውሳለሁ፡፡

ብሔራዊ ባንክ ከወገንተኝነት በፀዳ መንገድ በዚህ ዓይነቱ ራስንና ውስጥን የመፈተሽ አልፎ ተርፎም ቤትን የማፅዳት አሠራር ሊቀጥል ይገባዋል፡፡ ይህም ሆኖ ለሕዝብም ሆነ ለባለሀብቶቹ አደራ የማይበቃ አሠራር ውስጥ የተዘፈቁት ባንኮች ከላይ  የተጠቀሱት ብቻ ናቸው ወይ የሚል ስሞታ አለ (ይህ የመንግሥት ባንኮችንም ይጨምራል፣ የመንግሥት ባንኮችን አስመልክቶ ወደፊት የምመለስበት ጉዳይ ይኖረኛል)፡፡ ይህንን ጥያቄ መመለስ የሚገባው ብሔራዊ ባንክ ቢሆንም፣ በግንዛቤ ደረጃ ግን አገር ያወቀውና ፀሐይ የሞቀው ችግር እንዳሆነ ልብ ሊባል ይገባዋል፡፡ 

ዛሬ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ተራ መጠበቅም ሆነ ቅድሚያ በሚሰጠው የአምራችነት ዘርፍ መሰማራት ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ለደላላውና ለውጭ ምንዛሪ ኃላፊው ከእጅ ገፋ ማድረግ፣ ለባንኩ ደግሞ በሕገወጥ መንገድ ያገኘው የውጭ ምንዛሪ ላይ ተመርኩዞ እስከ አንድ መቶ ፐርሰንትና ከዚያም በላይ ተቀማጭ ማስገባት ግዴታ ነው፡፡ ይህ ድርጊት በተለይ የትርፍ ህዳጋቸውና ተቀማጫቸው አለቅጥ ያበጡ ባንኮችን በቀጥታ የሚመለከት መሆኑ፣ ከብሔራዊ ባንክም ሆነ ከዜጎች ዓይን የተሰወረ አይደለም፡፡  

ወደ ትልልቆቹ ባንኮች ስናመራ ባንኮቹ በኢንዱስትሪው ውስጥ በነበራቸው አንጋፋነትና በቴክኖሎጂ የታገዘ፣ ዘመናዊ አሠራርና እንደ ኤሌክትሮኒክስ ያሉ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማምጣት በጎ ገጽታ ነበራቸው፡፡ አሁን ግን ከተቋምነት ወርደው በግለሰብ ብቻ የመመራትና በቦርድ ገደብ የለሽ ጣልቃ ገብነት፣ አልፎ ተርፎም የማኔጅመንት ቅርብ ክትትል በጎደለው የላላ አሠራር ተጠምደው ማየት አሳዛኝ ነው፡፡

በቀዳሚነት፣ ቅርንጫፍ በማስፋፋትና ገጠሪቱን ኢትዮጵያ ተደራሽ በማድረግ ግንባር ቀደም ቢሆኑም ዛሬ የተጠመዱበት እጅግ የተጋነነ ትርፍ የመሻት ግብግብ፣ ውሎ አድሮ ባንኮቹን ከተቋምነት ወደ ግለሰብ ኢምፓየርነት እየለወጣቸው ይገኛል፡፡ በባንኮቹ ውስጥ የግለሰብ ፈላጭ ቆራጭነት መንሠራፋት እውነትም በጤናማ መንገድ ውስጥ እየተራመዱ መሆኑን ለመገምገም እንኳን ዕድል የነሳ ወጥመድ መሆኑን፣ ከከፍተኛ አመራሮች በተደጋጋሚ የሚነሳ እሮሮ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ሕገወጥ ብድር በመውሰድ የጋዜጦች መነጋገርያ የነበሩ ይታወሳሉ፡፡ ግለሰባዊ ተክለ ሰውነትን ለማጎልበት ሲባል ትርፍ የማጋነንና የተቀማጭ መጠንን የማዛባት በሽታ ባንኮች ውስጥ ተወልዶ እንደ ወረርሽኝ እየተዛመተ፣ የሁሉንም ባንኮች  የሞራል መሠረት በመናድ በሕገወጥ ውድድር ውስጥ እንዲጠመዱ እያደረገ ይገኛል፡፡

በአንድ ወቅት ቴክኖሎጂን፣ ዘመናዊ የባንክ አሠራርን፣ ኤሌክትሮኒክ ባንኪንግን፣ ጠንካራና በዲስፕሊን የሚመራ የብድርና የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም አሠራርን በመተግበር ይታወቁ የነበሩ ባንኮች፣ ዛሬ ፈራቸውን ስተው ሌሎችንም እያበላሹ ነው፡፡ የአገሪቱ የባንኪንግ ኢንዱስትሪ ወሳኝ ምዕራፎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተሻግረው ለውጤት ይበቃሉ የሚል ተስፋ የሰነቁ ነበሩ፡፡ በተለይ ወደፊት የውጭ ባንኮች ገበያው ሲከፈትላቸው እንደ አገር ሊገጥመን የሚችሉ ተፅኖዎችን በውቀት፣ በክህሎትና በዘመናዊ አሠራር አልፎ ተርፎም ባዳበሩት አቅም መሠረት ተወዳዳሪ ሆነው ችግሮችን በመቋቋም አገራዊ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይችላሉ ተብለው የሚጠበቁ ባንኮች ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ሆኖም ዛሬ ገበያው በፈጠረው የተጋነነ ትርፍ ውድድር ውስጥ ተጠምደውና በአንዳንድ የቦርድ አባላት የማያቋርጥ ጣልቃ ገብነትና ጥቅም ፍለጋ የሚደረግ ሩጫ ተወጥረው፣ አልፎ ተርፎም አዲስ የዘረጉት አሠራር በራሳቸው ቁመናና ልክ ያልተቃኘ በመሆኑ በተፈጠረባቸው ምስቅልቅል ተጠምደው፣ በጥቂት ነገር ግን ከፍተኛ የውሳኔ አቅም በተሰጣቸው ከፍተኛ አመራሮች የጥቅመኝነትና የቡድነኝነት አሠራር፣ እንዲሁም በአንዳንዶቹ አቅም ማነስና ቸልተኝነት ተደናቅፎ የዕውቀትና የክህሎት ጎዳናቸው ፈተና ውስጥ ገብቷል፡፡ 

ትርፍ ማጋበስ ብቻ ማዕከል በሆነበትና ጠዋትና ማታ ትርፍ እንዴት ማጋበስ እንደሚቻል በሚቃዥበት የኢትዮጵያ ባንኮች አዕምሮ ውስጥ ሆኖ ዕውቀትና ክህሎት፣ እንዲሁም ድርጅታዊ ብቃት ሊሰናሰልና ዘለቄታ ያለው ከዕለት ተዕለት ፍጆታ ያለፈ ሥራ መሥራት  ወደማይቻልበት የውድቀት ጎዳና ጥድፊያ ውስጥ እየተገባ ነው፡፡ ቀስ በቀስም ቀሪዎቹ ባንኮችም በዚህ ዓይነት በሽታ መለከፋቸው የማይቀር ነው፡፡

ይህ የተጋነነ ትርፍን ብቻ ማዕከል ያደረገ አሠራር ከወዲሁ ልማታዊና እሴት ፈጣሪ ወደሆነ አሠራር ካላደገ፣ ጉዳቱ ከባንኮቹ ባለቤቶች አልፎ ወደ አገራዊ ኢኮኖሚያዊ ችግር መሸጋገሩ አይቀሬ ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክ ከተቋቋመበት ዋነኛ ዓላማዎች መካከል የተረጋጋ የኢኮኖሚ ሥርዓትና የተፋጠነ ልማት ማምጣት በመሆኑ ከላይ በዝርዝር ያነሳናቸው የባንኮቹ ድክመት እንዲታረም፣ በተቃራኒው ደግሞ የባንኮቹን አቅም በማሳደግና አቅጣጫ በማስያዝ በቂ ሚና አለመጫወቱ ከፍተኛ ሥጋት ነው፡፡ ያለ ባንክ ስለዕድገትም ሆነ ስለልማት ማሰብ ያለመቻሉን ያህል፣ በሥርዓት ስለሚመሩ ባንኮች ማቀድና ችግር ሲኖር የእርምት ዕርምጃ መውስድ ከግዴታም በላይ አገራዊ ግዴታ ነው፡፡.

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ