Sunday, February 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርለውጭ ግንኙነት የተሰጠውን ትኩረት ያህል ለውስጥ ግንኙነትም ይሰጥ

ለውጭ ግንኙነት የተሰጠውን ትኩረት ያህል ለውስጥ ግንኙነትም ይሰጥ

ቀን:

በምግባሩ ታየ

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የአገሪቱ መንግሥታት አስተዳደሮች የውጭ ግንኙነት ዘርፍ መልካም የሚባል እንደነበረ ነው፡፡ የውስጥ ጉዳያችን ግን መሠረት እንዳልበረው ለማሳየት አንዳንድ ጸሐፍት በመረጃ አስደግፈው ኢትዮጵያ እስካሁን ብቁ የውስጥ አስተዳደር አላገኘችም እስከ ማለት ደርሰዋል፡፡

የቅርቡን የአፄ ኃይለ ሥላሴ የመንግሥት አስተዳደር እንኳን ብንመለከት ከውጭ መንግሥታት የነበራቸው ግንኙነት በተለያዩ መንገዶች የሚገለጽና ውጤታማ የነበረ ነው፡፡ ገና አፍሪካ ከቅኝ ግዛት ተጠቃላ ባልወጣችበት አስቸጋሪ ጊዜ ለአፍሪካውያን በዓለም መድረክ በመከታነት ኢትዮጵያ የተጫወተችው ሚና፣ እንዲሁም በሰላም ማስከበር እንደ ሌሎች የሠለጠኑ አገሮች እኩል እምነት ተጥሎባት በዓለም አቀፍ የወዳጅነት እሳቤ ወታደሮቿን በመላክ አኩሪ ተግባር በመፈጸሟ እስካሁን ድረስ የሚዘከርላት የታሪክ ምዕራፍ ነው፡፡ የአፍሪካ ወንድማማቾችን ለማቀራረብና የጋራ ጉዳያቸውን በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተወያይተው እንዲፈቱ የተጫወተችው ሚና አሁንም የጎላ ቦታ አለው፡፡ ይህም ከሌላ የመጣ ሳይሆን መልካም የውጭ ግንኙነት የፈጠረው ውጤት መሆኑ ነው፡፡

እነዚህ በፖለቲካው መስክ የነበሩ ጎላ ጎላ ያሉ ሲሆኑ መልካም የውጭ ግንኙነት በመኖሩ ከተለያዩ አገሮች በተገኘ ትብብር የአገሪቱ ኢኮኖሚ፣ ትምህርትና ሥልጠና፣ በጤና፣ በእርሻና በሌሎች ዘርፎች ለማሻሻል ጥረት መደረጉን የሚያመለክቱ ቋሚ ሆነው የሚታዩ ምልክቶች አሉ፡፡ ይህም ሆኖ በአፄው ጊዜ የነበረው የውስጥ የፖለቲካው ሁኔታ ብዙ ትንታኔ የሚፈልግ ቢሆንም፣ በጥቅሉ በ1966 ዓ.ም. የሕዝብ አመፅ በወለደው አብዮት የአፄው መንግሥት አስተዳደር ተንኮታኩቶ መውደቁ በዋነኛነት በአገር ውስጥ በነበረው ያልተገባ የውስጥ ፖለቲካ አያያዝ እንደነበር፣ ለብዙዎች የሚያከራክር እንደማይሆን ይሰማኛል፡፡

የደርግ አስተዳደርም በተመሳሳይ በውጭ ግንኙነት በኩል የነበረው ሪከርድ መልካም የሚባል ነበር፡፡ በተለይ የተወሰኑ አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት ለመውጣት ሲያደርጉት ለነበረው ትግል አጋርነት በማሳየትና በመርዳት ይተጋ እንደነበር ሀቅ ነው፡፡ ለዚህም የኢሕአዴግ የበላይ አመራሮች ዘንድ ሳይቀር ምስክርነት የተሰጠበት ነው፡፡ ይሁን እንጂ በደርግ አስተዳደር ከአፄው ባልተለየ እንዲያውም በከፋ ሁኔታ ሕዝባዊነት ያልነበረውን፣ ከሥልጣን አያያዙ ጀምሮ በሕዝብም ዘንድ ቅቡልነት ያልነበረውን የአገር ውስጥ የፖለቲካ ጉዳይ አያያዝ ሽኩቻ የተሞላበት፣ ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎችን በኃይል በመጨፍለቅና ለሕዝባዊ አመፅ ያመቻቸ፣ ከዚህም አልፎ የተከፉ ኃይሎችን ትጥቅ አንግበው እንዲፋለሙት ያደረገና በመጨረሻ ተሸንፎ እስከ ወዲያኛው የከሰመ የመንግሥት አስተዳደር ብለን ልንወስደው እንችላለን፡፡ ይህ የሆነው የአገር ውስጥ ግንኙነት አያያዙና ሕዝባዊነቱ ወርዶ ወርዶ ወደ ዜሮ በመጠጋቱ ለውድቀት ዳርጎታል በማለት በአጭሩ መግለጽ ይቻላል፡፡

የኢሕአዴግ የመንግሥት አስተዳደር በውጭ ጉዳይ ግንኙነት በኩል ተመሳሳይ አካሄድ እንደሚከተል ከማሳያዎቹ መካከል በአፍሪካ ጉዳይ ላይ የተጫወተው ሚና፣ በገለልተኝነት በአገሮች ፖለቲካ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ ያለመግባት፣ ከምዕራቡም ከምሥራቁም ሚዛናዊ ግንኙነት መፍጠርን፣ የፀጥታ መደፍረስ በተከሰተባቸው አገሮች በሰላም ማስከበር ላይ በጉልህ የመሳተፍ፣ ስደተኞችን በወንድማዊ አቀባበልና አያያዝ የነበረው መልካም ስም በዓለም ማኅበረሰብ ዘንድ ተገቢ ቦታ እንዳለው የተመሰከረ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እንዳለፉት መንግሥታት ሁሉ የአገር ውስጥ አያያዝ ጉድለት ስለነበረበት፣ የተፈጠረው የሕዝብ አመፅ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በጥልቅ ተሃድሶ ነጥሮ የወጣው በዶ/ር ዓብይ የሚመራው የኢሕአዴግ ቡድን የውጭ ፖሊሲ፣ ያለፉት መንግሥታት አስተዳደሮች ሲያራምዱት የነበረ አካሄድ እየተከተለ እንደሆነ አመላካች ነገሮች አሉ፡፡ በምሳሌነት ለመጥቀስ ያህል በምሥራቅ አፍሪካ መንግሥታት መካከል የነበረውን መልካም ያልሆነ ግንኙነት ለማሻሻል እየተጫወተው ያለው የማቀራረብ ሚና፣ እንዲሁም በአገሮቹ መካከል ውህደት ለመፍጠር እየተጣለ ያለው መሠረት በእጅጉ የአገሪቱን ገጽታ የሚቀይርና ወሳኝ ዕርምጃ ነው ተብሎ የሚወሰድ ነው፡፡ በተለይ በኢትዮጵያና በኤርትራ ሕዝቦች መካከል ተፈጥሮ የነበረው ሰው ሠራሽ ግንብ በማፍረስ በደም፣ በባህል፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በሥነ ልቦና አንድ የሆኑ ሕዝቦች በዓይነ ሥጋ እንዲገናኙ የተጫወተው ሚና በታሪክ የማይዘነጋ፣ ለሁለቱም ሕዝቦች የአሁንና መፃዒ ትውልዶች ትልቅ ትምህርት ትቶ ያለፈ ወሳኝ የውጭ ፖሊሲ ዕርምጃ ነው፡፡

ይሁን እንጂ አሁንም እንደ ቀደምት የአገሪቱ የመንግሥት አስተዳደሮች በውስጥ ጉዳይ ፖሊሲ አያያዙ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ መሆኑ፣ ከተለያዩ ወገኖችና አስተያየት ሰጪዎች የተለያዩ ምክር አዘል ትችቶች የሚቀርብበት ነው፡፡ ይኸውም በውስጥ ፖሊሲና ግንኙነት ቀረፃ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል በሚልና በዋና ዋና ሐሳቦች ለማጠቃለል ተሞክሯል፡፡

በአገሪቱ ያለውን የፀጥታና የሕግ የማስከበር ሁኔታ ስንመለከት፣ በአሁኑ ጊዜ በእጅጉ አሳሳቢ ደረጃ መድረሱና በአንፃሩ መንግሥት ለዚህ እየሰጠ ያለው ምላሽ አጥጋቢ አለመሆኑ ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ አገሪቱ ከአሁን ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሕዝብ ከቀየው የተፈናቀለበት፣ ከምንጊዜውም በላይ በመላው አገሪቱ ተንቀሳቅሶ ሠርቶ ለመኖር አይደለም፡፡ ለሐዘንም ሆነ ለደስታ ከአንድ ቦታ ወይም ክልል ወደ ሌላ ቦታ ወይም ክልል ደርሶ ለመመለስ እንኳን አዳጋች የሆነበት ጊዜ በመሆኑ፣ ከዛሬ ነገ ትፈርስ ይሆን በሚል ሥጋት መረጋጋት የታጣበት ሁኔታ መፈጠሩን ስንመለከት በሥልጣን ላይ ያለው የመንግሥት አስተዳደር (በተለይ የፌደራል መንግሥት) ይኼንን ለመቀልበስና አገሪቱ እንደ አገር እንድትቀጥል ለማድረግ በእጅጉ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ምልከታ ከአገር አልፎ በውጭ ጸሐፍትም አትኩሮት የተሰጠው ስለመሆኑ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ካላቸው የውጭ ፖሊሲ ዕይታ አንፃርና ከቅን ልቦና በመነጨ ይመስለኛል፡፡ በቅርብ ጊዜ በየመንና በሶሪያ ያለውን የወንድማማቾች ዕልቂት እንዲቆም ለሚያሳስብ ጥሪያቸው ምላሽ  በአንድ ጽሑፍ የተሰነዘረው አስተያየት ቃል በቃል ባይሆንም፣ ‘ጠቅላይ ሚኒስትር በቅድሚያ በአገራቸው ውስጥ ያለውን መፈናቀልና መገዳደል ሊያስቆሙ በተገባ’ በማለት ስላቅ በሚመስል አገላለጽ ተጽፏል፡፡ ይህ መልዕክት በቀጥታ የውስጥ ፖሊሲ ግድፈትን የሚያመለክት በሌላ አካል የተሰነዘረ ቁም ነገር ያለው መልዕክት ነው፡፡

የመገናኛ ብዙኃንና የሚዲያ ነፃነት በተመለከተ ከነበረው ሥርዓት በተለየ ሚዲያ  የመንግሥት አገልጋይ ሳይሆን፣ ሕዝብና መንግሥት ጤናማ ግንኙነት እንዲኖረው የሕዝብ ዓይንና ጆሮ በመሆን የመንግሥት አገልግሎት በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ መንገድ ለሕዝብ ግልጽ የሚያደርግና ማን ምን ደስ ይለዋል ሳይሆን፣ እንደ ስያሜው ብዙኃንን የሚያገለግል ተቋም መሆን ይገባዋል፡፡ በመንግሥት በጀት የሚተዳደሩም ሆነ የሚደጎሙ ወይም በሌላ አካል የሚተዳደሩ ሚዲያዎች የሚያዘጋጁዋቸው ፕሮግራሞች ሕዝብን የሚያቀራርቡ፣ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያጎሉ፣ በአንድነት ውስጥ ልዩነት ዕውቅና የሚሰጥበት፣ ልዩነቶች የሚደመሩበት፣ የአገሪቱ ህልውና በሁሉም ሕዝቦቿ እኩል ድርሻ እንደሚፀና፣ ወዘተ. ገንቢ ሐሳቦች ዕለት በዕለት መዘመር አለባቸው እንጂ፣ ከዚህ በማፈንገጥ ጥላቻን በሚሰብኩ፣ አንዱን ሕዝብ የበላይ ሌላውን የበታች፣ አንዱ ለአገሪቱ ህልውና ያለው ድርሻ ከፍ ያለ ሌላው ዝቅ ያለ፣ በአንድነት መፃዒ ጊዜን የመኖር ተስፋ በማጨለም የሚንቀሳቀሱ ከሆነ በእርግጠኝነት ለአገሪቱ መፈራረስ ሁኔታዎች እያመቻቹ መሆናቸውን መገንዘብ አለባቸው፡፡ ሚዲያዎችም በትክክለኛ አቅጣጫ ለአገሪቱ በሚበጅ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ በመንግሥት በኩል የተለያዩ የሕግና የፖሊሲ ማዕቀፎች ተዘጋጅተው፣ ሁሉም አካላት ሕጉን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ ይዋል ይደር የማይባል የመንግሥት ተግባር መሆን እንዳለበት ይታመናል፡፡

በገዥው ፓርቲ ያለው የውስጥ ጥንካሬና መተማመን ምን ደረጃ ላይ ይገኛል? አገሪቱ በአሁኑ ጊዜ አገሪቱ በአራት እህት ድርጅቶች በተዋቀረው ኢሕአዴግ እንደምትመራ በመርህ ደረጃ የሚታወቅ ሆኖ እያለ፣ በተግባር ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ መንገድ እየተመለከተው እንዳልሆነ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ አንድ ያልሆነ ፓርቲ የሕዝብ አንድነት ሊፈጥር የሚችልበት ዕድል እስከምን ድረስ ነው? ጎልተው በወጡ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ቢሆን ከላይ የተገለጸው የፓርቲ አንድነት አለመኖሩን በሚያሳብቅ ሁኔታ፣ ይኸው የሕዝብ ስሜትን የሚያጠናክሩ የተለያዩ አገላለጾች በየአጋጣሚው ሲሰነዘሩ ይደመጣሉ፡፡ የአንድን አገር ሕዝብ የማስተዳደር ኃላፊነት ወስዶ ሲያበቃ እኛና እነሱ በሚል የውስጠ ፓርቲ አሠራር ፀሐይ እንዲሞቀው በማድረግ፣ እስከምን ድረስ የሕዝብ አመኔታ አግኝቶ የአገርን አንድነትና ሉዓላዊነት አስጠብቆ ማስቀጠል ይቻላል?

የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ግንኙነት ሲታይ በዕውን የፌደራል መንግሥት በክልል መንግሥታት ቅቡልነት አለው? የፌዴራል መንግሥትስ በሥልጣን ገደቡ ልክ እየተጠቀመ ነው? የፌዴራል መንግሥት የሚያወጣቸው ሕጎች በሕዝብ ተሳትፎ የታገዙ ናቸውን? የፌዴራል መንግሥት ከሌሎች አገሮች ጋር የሚፈጽማቸው ስምምነቶች ግልጽነት እስከምን ድረስ ነው? የክልል መንግሥታት በዚህ በኩል ያላቸው ተሳትፎ እንዴት ይገለጻል? እነዚህና ሌሎች መሰል ተያያዥ ጥያቄዎች ተደጋግመው ከመነሳታቸው አኳያ፣ የመንግሥት የውስጥ ፖሊሲ ትኩረት የሚሹ ናቸው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡

በአጠቃላይ የአንድ አገር የውጭ ፖሊሲ የውስጥንም እንዲያንፀባርቅ መቀረፅና መከለስ አለበት፡፡ ማለትም የውጭ ፖሊሲ መሠረቱ የውስጥ ፖሊሲ መሆን አለበት፡፡ ምን ያህል ጠንካራ ቢሆንና በሌሎች አገሮች ያለው ተቀባይነት ጣራ ቢደርስም፣ የውስጥ ሁኔታን ማስተካከል ካልተቻል የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር እንደ ከዚህ በፊቱ መንግሥት አስተዳደሩ መንገዳገዱ እንደማይቀር፣ በቅርቡ ያለፍንባቸውን ሒደቶች በመማሪያነት መጠቀም ብልህነት ነው እላለሁ፡፡  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]  ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በጦርነቱ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ የመገንባቱ ውጥን

በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል በሦስት ዙር ተካሄዶ በነበረው ጦርነት ምክንያት...

በርካታ ሰዎችን እያጠቁ የሚገኙት የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች

ትኩረት የሚሹ የትሮፒካል /ሐሩራማ በሽታዎች በአብዛኛው ተላላፊ ሲሆኑ፣ በዓይን...

ስለአገር ኢኮኖሚ ማሰብ የነበረባቸው ጭንቅላቶች በማያባሩ ግጭቶች ተነጥቀዋል!

አገራችን ኢትዮጵያ ውጪያዊና ውስጣዊ ፈተናዎቿ መብዛት ብዙ ዋጋ እያስከፈላት...