Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹ኢትዮሮፒያንስ ማን ናቸው?››

‹‹ኢትዮሮፒያንስ ማን ናቸው?››

ቀን:

‹‹የጋራ ግንዛቤ በሌለበት ሀገር ወይም አህጉር ውስጥ እውነተኛ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ነፃነት መጎናጸፍ ዘበት ነው። ብሔራዊ መግባባት ላይ መድረስ የሚቻለው የጋራ ግንዛቤ ሲኖር ብቻ ነው። ሌላው ቀርቶ፣ ባለመስማማት መስማማት (agreeing to disagree) የሚቻለው አሁንም የጋራ ግንዛቤ ሲኖር ብቻ ነው። በዘመናዊነት ስም የተዘረጋው አውሮፓዊነት ግን፣ በአፍሮፒያንስ ወይም በኢትዮሮፒያንስ ማኅበረሰብና ልሂቃን ዘንድ የጋራ ግንዛቤ እንዳይኖር ትልቅ እንቅፋት ሆነዋል።››

ይህን ኃይለ ቃል የሚያስተጋቡት የአፍሪካ ፍልስፍና መምህር ዮሴፍ ሙሉጌታ ባባ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ በቅርቡ ‹‹የኢትዮሮፒያንስ ‘ፍልስፍና’›› የተሰኘና ተሻሽሎ የቀረበ መጽሐፍ ለንባብ አብቅተዋል፡፡

በተወለዱበት ምሥራቅ ወለጋ ነቀምት/ኰንቺ ልዩ ስፍራ በመነሳትም በመጽሐፉ ንዑስ ርዕስነት ‹‹የኰንቺ ሰው-ፍልስፍናዊ ዘዴ›› የሚልም ተጠቅመዋል፡፡

በመቅድማቸው እንደገለጹት የአፍሪካ ወይም የኢትዮጵያ ፍልስፍና፣ በፍልስፍና ስም እየተቀነባበሩ የሚጻፉ የምዕራቡን ‹‹ዓለም›› የፈጠራ ጽሑፎችን በጥልቀት ፈትሾ ምንም ፍልስፍናዊ መሠረት የሌላቸውን ጽንሰ ሐሳቦችን እየፈለፈለ የማውጣትና የመናድ ተልዕኮ አለው፡፡

በመጽሐፉ የቀረቡ ጽሑፎች የአፍሪካ ፍልስፍናን በአጠቃላይ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ፍልስፍና በተለይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው፡፡ የአፍሪካ ፍልስፍና ‹‹ጥበብን ለጥበብ›› የተሰኘውን የኢትዮሮፒያንስ አርቲ-ቡርቲ ፍልስፍናዊ ክርክር አይቀበልም፡፡ በተቃራኒው ‹‹ዕውቀትን ለዕውቀት›› የተሰኘውን ጉንጭ አልፋ ክርክር ወደ ጎን በመተው፣ በሁለት አንኳር አንኳር ነጥቦች ላይ ያተኩራል፡- የመጀመርያው፣ ዲበ-ፍልስፍናዊ ጥያቄ (The Question of Metaphilosophy) ሲሆን፣ ሁለተኛውና በጣም አንገብጋቢው ጉዳይ ደግሞ የምዕራባውያንን የተሳሳተ የኑባሬ ግንዛቤ በማጋለጥ ያልተዋረደውን አፍሪካዊ (የራስ) ማንነትን ፈልጎ ማግኘት ናቸው፡፡

አንድን ‹‹ነገር›› በመገንዘብ ሒደት ውስጥ የአተያይ እንቆቅልሽ (puzzles of perception) ወይም የአመለካከት ልዩነት መኖሩ የማይካድ ቢሆንም ቅሉ፣ የአውሮፓዊነት መንፈስና ዘረኛ አስተሳሰብ ሥር በሰደደበት ኢትዮጵያና ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ግን፣ የጋራ ግንዛቤ የመፍጠርን የመሰለ አስቸጋሪ የለም። ከሁሉ በላይ፣ በአገራችን ኢትዮጵያ የጋራ ግንዛቤን ለመፍጠርና ብሔራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ እንቅፋት የሚሆነው የኢትዮሮፒያንስ የለየለት ጽንፈኛ አስተሳሰብ ነው።

ኢትዮሮፒያንስ

ኢትዮሮፒያንስ ማን ናቸው?

እንደ ዶ/ር ዮሴፍ አገላለጽ፣ ኢትዮሮፒያንስ በኩረጃ ፍልስፍና የተካኑና የምዕራባውያንን የአስተሳሰብ ዘይቤ ተከትለው ማንነታቸውን የሰለቡ ግለሰቦች ናቸው። በተለይ ምዕራቡ ዓለም ባስታጠቃቸው ርዕዮተ ዓለም ወይም ፍልስፍናዊ ጽንሰ ሐሳብ ላይ ተመሥርተው፣ በፍፁም የበታችነት ስሜት የራሳቸውን ማንነት (ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ፣ ፍልስፍና) አብዝቶ የሚጸየፉ ሲሆን፣ በተቃራኒው የነጮችን ባህልና ማንነት በለየለት ሁኔታ ያመልካሉ። ኢትዮሮፒያንስ ዘመናዊነትን እንደ ወረደ በመቅዳት፣ ተጨባጩን የአገሪቱን ሁኔታ ያላገናዘበና የምዕራቡን ዓለም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ብቻ የሚያስጠብቅ ፖሊሲዎችን በመተግበር፣ ሀገራችንን ለእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ዳርጓታል።

‹‹ኢትዮሮፒያንስ ከአውሮፓውያን ጠበብት በኮረጁት የታሪክ አጻጻፍ ስልት፣ የአንድን ሕዝብ ታሪክ ሙሉ በሙሉ አዋርደው፣ ውሸትን አውነት በማስመሰል ጽፈው ያስተምራሉ። ይህ ከቅኝ ገዢዎች የተቀዳ የታሪክ ትንተናና አረዳድ እኛእነሱ የሚል የሁለታዊነት (dualism) ጽንሰ ሐሳብ (ሰሜንደቡብ፣ ክርስቲያንአረመኔ፣ ባንዳኢትዮጵያዊ፣ እስላምክርስቲያን፣ ሴማዊሻንቅላ ወዘተ) በመፍጠሩ ምክንያት እስከ ዛሬ ድረስ በአንድነት ኃይሎች (ultra-right) እና በብሔርተኞች (ultra-left) መካከል ያላባራ ጦርነት አስከትለዋል።

‹‹በአብዮቱ ጊዜ በብዙሂቃን ዘንድ የነበረው አንዱ ችግር ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ›› የሚተረጉሙበት መንገድ ነበር። በቅርጽና ይዘት የተለያየ ቢሆንም፣ ይህ የታሪክ አረዳድና ልዩነት የመደብና የብሔር ጥያቄን ይዞ ብቅ ብለዋል። የማንነት ጥያቄን ያመነጨው ኢሕአዴግ እንደሆነ የሚሞግቱ ብዙ ሰዎች አሉ። ይህ ትክክል አይደለም። ኢሕአዴግ መተቸት ያለበት የማንነት ጥያቄን ከመጠን በላይ እንዲለጠጥ በማድረጉ ላይ ነው። ተወደደም ተጠላ፣ የመደብም ሆነ የብሔር ጥያቄ በነበረበት ኢትዮጵያ ‹‹ሁለቱም አልነበሩም›› ወይም ‹‹አንዱ ብቻ ነበር›› ብሎ መፈላሰፍ በተዘዋዋሪ ‹‹በግድ እኛን ሁኑ›› የሚል አንደምታ አለው። ‹‹በግድ እኛን ሁኑ›› የሚለውና ከምዕራቡ ‹‹ዓለም›› የተቀዳ ፍልስፍናዊ አስተሳሰብ በኢትዮጵያ ምድርም እንደማይሠራ ነው።

‹‹የኢትዮሮፒያንስ (Westernized Ethiopians) ዋነኛ ችግር፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት፣ የምዕራቡን ዓለም የዕድገት ሞደል የመከተላቸው ጉዳይ ነው፤›› የሚሉት ዶ/ር ዮሴፍ በምሳሌነት የሚከተለውን ያስቀምጣሉ፡– ‹‹የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ኢሕአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲ መከተሉ በአንፃራዊነት ስንመለከተው ትክክል ነበር። ይሁን እንጂ፣ ኢሕአዴግ ከሕገ መንግሥቱ ይልቅ ኢትዮሮፒያንስን አብዝቶ ስለሚሰማ፣ በአፈጻጸም ላይ ከፍተኛ ችግር እየገጠመው ነው። ለምሳሌ፡ሙስና ለሚሉት ካንሰር መፍትሔው ምን እንደሆነ ወይም ያለብንን የውጭ ዕዳ መቼ ከፍለን እንደምንጨርስ የሚያውቁት ዋቃዮና ኢሕአዴግ ብቻ ናቸው!››

መጽሐፉ በፊት ሽፋኑ ግርጌ ‹‹አበበ በሶ በላ›› Vs ‹‹ጫላ ጩቤ ጨበጠ›› የሚል ሰምና ወርቃዊ ንዑስ ርዕስም ይታያል፡፡ ይህ ንዑስ ርዕስ በ17ኛው [ምዕራፍ] የዶ/ር መረራና በዕውቀቱ መንገድ! ሥር ተፍታቶ የቀረበ ነው፡፡ ‹‹የሱጌቦ፣ የጫላ፣ የሐጎስ፣ የአበበ፣ የኦባንግ… ወዘተ የማንነት ጥያቄ አንፃራዊ ምላሽ ባገኘ ከ28 ዓመታት በኋላ፣ ዛሬም የአበበ በሶ በላ እና ጫላ ጩቤ ጨበጠ ፖለማኖታዊ [ፖለቲካና ሃይማኖት] አስተሳሰብ ጨርሶ መርገብ እንዳልቻለ ከዚህ በፊት በግልጽና በድፍረት ሞግቼ ነበር፡፡›› በሚል መንደርደርያዊ ዐረፍተ ነገር፡፡

የኢትዮሮፒያንስ ‹‹ፍልስፍና›› መጽሐፍ በሦስት ክፍሎች የተደራጀ ሲሆን ቀዳማዊ ክፍል የምዕራባውያን ሥነ ዕውቀታዊ ጥቃት እና የአፍሪካ ፍልስፍና ግብረ መልስ! የሚል ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ፍልስፍና ጋር ወደፊት! የሚለው መፈክር ሁለተኛው ክፍል ሲሆን፣ የመጨረሻው ክፍል ከኰንቺ ሰው ፍልስፍናዊ ዘዴ ጋር ወደፊት ይሰኛል፡፡ ባጠቃላይ 56 ምዕራፎችን ይዟል፡፡ መጽሐፉ በ102 ብር ለሸመታ ቀርቧል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...