Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበአዲስ አበባ ዘላቂ ሥራ እየፈጠሩ የመሄድ ችግር መኖሩ ተገለጸ

በአዲስ አበባ ዘላቂ ሥራ እየፈጠሩ የመሄድ ችግር መኖሩ ተገለጸ

ቀን:

– የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ትኩረት አልተሰጠውም

በአዲስ አበባ ያለውን የዜጎች ድህነትና ሥራ አጥነት ለመቅረፍ በየደረጃው የሚፈጠሩ የልማት ሥራዎች፣ ዘላቂ የሥራ ዕድል እየፈጠሩ የመሄድ ችግር እንዳለባቸው የከተማዋ የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

ቢሮው የስድስት ወር የተግባር አፈጻጸም ሪፖርት ጥር 23 ቀን 2011 ዓ.ም. ባቀረበበት ወቅት እንደተገለጸው፣ ዘላቂ ሥራ መፍጠሩ ችግር የተጋረጠበት ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በቂ ትኩረት ባለመሰጠቱ ነው፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሚኪያስ መሉጌታ ሪፖርቱን ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራው ከማኑፋክቸሪንግ ይልቅ አገልግሎትና ንግድ ላይ አተኩሯል፡፡

ለሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት፣ ሁሉም ተቋም ለሥራ ዕድል ፈጠራ ራሱን የቻለ ዕቅድ እንዲያዘጋጅ፣ አፈጻጸሙን እንዲገመግም፣ ጥራቱን የጠበቀ የመረጃ ቅብብሎሽ እንዲኖር የሚያስችልና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን የ2011 በጀት ዓመት ዕቅድ በጋራ መዘጋጀቱን ያወሱት አቶ ሚኪያስ፣ ባለፉት ስድስት ወራት በነበረው ክንውን በከተማዋ የሥራ ፈላጊን በመመዝገብ ቦሌና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች ዝቅተኛ አፈጻጸም አሳይተዋል ብለዋል፡፡

አቃቂ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶና ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተሞች ከሥራ ፈላጊ ምዝገባ አንፃር የተሻለ አፈጻጸም ነበራቸው፡፡

ፀጋን ወይም አማራጭ የሥራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ፣ የሥራ ዕድል ልየታ በራሱ ግብ ባይሆንም፣ ቦሌ 183 የሥራ ዕድል ብቻ በመፍጠርና ከዕድሎቹም 3.22 በመቶውን በመፈጸም ከአሥሩም ክፍለ ከተሞች በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ የተሻለ የሥራ ዕድል ልየታ ያስመዘገቡት አቃቂ፣ አዲስ ከተማ፣ ልደታና ቂርቆስ ክፍለ ከተሞችም ቢሆኑ፣ የፈጠሩትን የሥራ ዕድል በመፈጸምና ወደ ተግባር በመቀየሩ ረገድ ያስመዘገቡት እመርታ በቂ አይደለም፡፡ አቃቂ ከፈጠረው 1,400 የሥራ ዕድል ልየታ 17.7 በመቶውን፣ አዲስ ከተማ ከ1390 የሥራ ዕድል 17.9 በመቶ፣ ቂርቆስ ከ1047 የሥራ ዕድል 9.66 በመቶ ልደታ ከ1872 የሥራ ዕድል 23.6 በመቶውን ብቻ ፈጽመዋል፡፡

በከተማዋ የሥራ ዕድል ከመፍጠር አንፃር በተያዘው በጀት ዓመት በስድስት ወር ውስጥ ለ72 ሺሕ 489 ሥራ ፈላጊዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ፣ የሥራ ዕድል የተፈጠረው ለ39 ሺሕ 688 በመሆኑ ሥራው በሚፈልገው ደረጃ አለመሄዱን የቢሮው ዋና ኃላፊ አቶ ጀማሉ ጀምበር ተናግረዋል፡፡

የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆንና ንግድና አገልግሎት ዘርፎች መብዛታቸውን በተመለከተም፣ ሥራ ፈላጊዎች እንደ እንጨት፣ ብረታ ብረትና ሌሎች የማኑፋክቸሪግ ዘርፎች ላይ ከመሰማራት ይልቅ፣ ፈጥኖ ገቢ የሚገኝበት ላይ የመሰማራት ፍላጎት ማሳየታቸውና በዘላቂ ሕይወታቸውን ሊቀይር በሚችለው ዘርፍ አለመሰማራት፣ ዘርፉ የራሱ የሆነ የመሥሪያ ቦታ የሚፈልግ ቢሆንም የመሥሪያ ቦታ አቅርቦት በሚፈለገው መልኩ አለመቅረብና የመሠረ ልማት አቅርቦት ከፍተቶች እንደ ችግር ተነስተዋል፡፡

ከመሥሪያ ቦታ ጋር ተያይዞ የተለያዩ ችግሮች እንደሚነሱ፣ ለዚህም ዝርዝር ጥናት መካሄዱን ኃላፊው ጠቁመው፣ ከግንባታ አንፃር በስድስት ወር ውስጥ 32 ሼዶችን ለመገንባት ታቅዶ፣ ቅድሚያ አስፈላጊ ግብዓቶችን በማዘጋጀት ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡ ለዚህም 23 ሄክታር መሬት የሚያስፈልግ መሆኑ ተለይቶና ለመሬት ልማት ቀርቦ 14.8 ሄክታር ቦታ በመረከብ ሦስት ሼዶች ተገንብተዋል፡፡ የ691 ሼዶችን መሠረተ ልማት ማሟላት ታቅዶም፣ ለ414 ሼዶች ተሟልቷል፡፡ በ2010 ዓ.ም. ግንባታቸው ተጀምሮ ካልተጠናቀቁ 270 ሼዶች ውስጥ 212ቱን ማጠናቀቅ ተችሏል፡፡

ከሼዶች ግንባታ በተጨማሪ በሕገወጥ የተያዙትንና አምስት ዓመት የሞላቸውን 2366 ሼዶች የማጥራት ሥራ ተሠርቷል፡፡ ለተጠቃሚዎች ከማዘጋጀት አንፃርም በግማሽ ዓመቱ 224 ሼዶችና 1,062 ካሬ ሜትር ከሕገወጥ ተጠቃሚ ለማስለቀቅ ታቅዶ 191 ሼዶችንና 459.5 ካሬ ሜትር ማስለቀቅ ተችሏል፡፡

 የመሥሪያ ቦታዎችን ለተጠቃሚዎች ከማስተላለፍ አኳያ፣ በአጠቃላይ ለ1 ሺሕ 240 ኢንተርፕራይዞች 1,240 ሼዶችን ለማስተላለፍ ታቅዶ ለ770 ኢንተርፕራይዞች 770 የመሥሪያ ቦታዎች ተላልፈዋል፡፡

ለሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚዎች የሥራ ቦታ ሰጥተናል ለማለት ያህል በከተማ መሐልና የከተማ ገጽታ በሚያበላሹ ሥፍራዎች የመስጠት ሁኔታ መኖሩን በተመለከተም፣ እንደ ከተማ በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ለሚሰማሩ መሥሪያ ቦታዎች ልማት የሚውል በጀት መመደቡን፣ የከተማ አስተዳደሩ የመሬት ልማት ማኔጅመንትም ከማስተር ፕላኑ ጋር በተነጻጸረ መልኩ መሬት እንደሚሰጥና ዘንድሮም 23 ሺሕ ካሬ ሜትር መሬት ለማልማት ዕቅድ ተይዞ ማልማት መጀመሩን አቶ ጀማሉ ተናግረዋል፡፡

ለልማት ሳይውሉ ታጥረው የተቀመጡና ቆሻሻ መጣያ የሆኑ አካባቢዎችን ለወጣቶችና ሴቶች የሥራ ዕድል መፍጠሪያ እንዲሆኑ አቅጣጫ መቀመጡን፣ ሆኖም በሥፍራው ሥራ ሲሠራ ምንም ዓይነት ግንባታ ሳይካሄድና ለተወሰነ ጥሪት ማፍሪያና ለሌላ ሥራ መነሻ ለማግኘት እንዲችሉና ቆጥበው ወደ ሌላ ሥራ እንዲሸጋገሩ ለማድረግ ታስቦ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ቦታዎቹ ለሌላ ልማት ሲፈለጉ ወጣቶቹ ቦታውን እንደሚለቁ፣ በክፍለ ከተሞችና በወረዳዎች የሚሠሩ ሥራዎች መኖራቸውን፣ ከአቅጣጫ ውጭ የተሠሩ ሥራዎች መታረም እንዳለባቸው አስተዳደሩ አቅጣጫ ማስቀመጡንና የማስተካከል ሥራ መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡

የቢሮው የሥራ ዕድል ፈጠራና የቴክኖሎጂ ሽግግር ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ዘርፍ የስድስት ወር የአፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ የሥራ ዕድል አማራጭ መስኮች የባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራውን በየጊዜው ለመከታተልና ለመደገፍ ጥረት መደረጉና በሥራ ዕድል ፈጠራ የወጣቶች ተጠቃሚነት ከ75 በመቶ በላይ እንዲሆን ትኩረት መሰጠቱ እንደ ጥንካሬ ተነስቷል፡፡

የዘርፉ ድክመት የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ ተቋማት በዕቅዳቸው መሠረት የሥራ ዕድል እየፈጠሩ አለመሆኑ፣ ሥራ ዕድል ፈጠራው በአገልግሎትና በንግድ ዘርፍ ላይ ያተኮረና ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ትኩረት አለመስጠቱ፣ በክፍለ ከተማዎች መካከል ያለውን የአፈጻጸም ልዩነት ተገቢውን ድጋፍ አድርጎ አለማመጣጠን፣ በተለያየ ጊዜ ሠልጥነውና ተደራጅተው የተቀመጡ ሥራ ፈላጊዎችን ችግር ፈቶ ወደ ሥራ አለማስገባት፣ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸውን አካላት ቀጣይነት ያለው ድጋፍ በማድረግ ያሉበትን ደረጃ በየጊዜው አለመከታተል፣ ማደራጀትን ወይም ሥራ ማስቀጠርን እንደ መጨረሻ ግብ የማየት፣ የተደራጀ መረጃ በተገቢው መንገድና ጥራት አለማስተላለፍ፣ የሥራ ዕድል መፍጠሪያ የተለዩ አማራጮችን ወደ ተጨባጭ ተግባር አለመለወጥ የተለመዱ ምክንያቶችን ማቅረብ፣ የሴቶች ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት አድርጎ አለመሥራት ተቀምጠዋል፡፡

ኢንተርፕራይዞች የግብዓትና ትስስር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማመቻቸትን በተመለከተ፣ የጥቃቅን ማኑፋክቸሪግ ኢንተርፕራይዞችን መረጃ ማጥራት፣ ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ መቻሉና የኢንተርፕይዞችን የድጋፍ ፍላጎት መለየቱ መልካም ቢሆንም፣ በተለየው ድጋፍ መሠረት ችግር ፈቺ ድጋፍና ክትትል አለመደረዱ እንደ ድክመት ተነስቷል፡፡

ለአዲስ አበባ ወጣቶችና ሴቶች ሥራ ለመፍጠርና ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ አልሞ በታቀደው የሥራ ዕድል ፈጠራ ከአስተዳደሩ ጀምሮ እስከ ወረዳ ያሉ የመራር አካላት ወሳኝና ተጠያቂነት ያለባቸው ቢሆንም፣ ዘርፉ ያሉትን መልካም አጋጣሚዎች ከመጠቀም አንፃር አመርቂ ውጤት አልተገኘበትም፡፡

በሥራ የታቀፉ፣ ለመታቀፍ የሚፈልጉ የከተማዋ ነዋሪዎችም በተደጋጋሚ ጊዜ አድልኦ፣ የሥራ መጓተት፣ ብድር የማግኘትና ብሎም የመደራጀት ችግር መኖሩን በተደጋጋሚ ሲያነሱ ተደምጠዋል፡፡ በተለይ ታች በወረዳና ክፍለ ከተማ ደረጃ ችግሩ እንደሚጎላም ሲናገሩ ቆይተዋል፡፡

ቢሮው የስድስት ወር አፈጻጸም ሪፖርቱን ሲያቀርብ፣ ከአሥሩም ክፍለ ከተሞች የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተው በተሠሩ ሥራዎችና ባጋጠሙ ችግሮች እንዲሁም ችግሮችን ለመፍታት በሚያስችሉ መፍትሄ አቅጣጫዎች ለመወያየት ታስቦ የነበረ ቢሆንም፣ አንዳንድ ኃላፊዎች ሳይገኙ ቀርተዋል፡፡

የቢሮው ኃላፊ አቶ ጀማሉ ዘርፉ በከተማ ደረጃ ትልቅ ቦታ ተሰጥቶታል፣ ከአገራዊ ለውጡ ጋር ተያይዞ ለወጣቶችና ለሴቶች የሥራ ዕድል መፍጠርም ዋና ዓላማው ነው፣ በስብሰባው ካልተገኙ የዘረፉ አመራሮች አንዳንዱ ሰንካላ ምክንያት እየደረደረ ላለመገኘት የሚሸሽ በመሆኑ ማጣራት ይደረጋል፣ በመድረኩ ላይ አለመገኘትም የአመራሩን ውድቀት ያሳያል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ