Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እንኳን ተቀምጠን ቆመንም አልቻልንም!

ሰላም! ሰላም! “ውኃ ወርዶ ወርዶ ሽቅብ ያማትራል፣ አትበሳጭ ልቤ የባሰ ይገኛል፤” አለ የወንዙን ልጅ ትቶ የሰው አገር ሲያድን የመነመነው። ምን በምግብ ዋስትና ራስን ብንችል መመንመን አይተወንማ። እናም ውዷ ማንጠግቦሽ ራሷን አልችል ብላው፣ ደረቴ ላይ ጣል አድርጋው ሳለ ቅዥት ነው መሰል ብንን አልኩ። መባነን ደግሞ በቀን ትቶ ሌት ሌት ይቀናናል። ውዴን ስባንን ቀሰቀስኳት። እየተገላበጠች፣ “ስንት ሰዓት ነው?” ብላ ጠየቀችኝ። አይገርምም? እስኪ አሁን በጨለማ ተቆጠረ አልተቆጠረ ምን ይፈይዳል? ‘ከሌሊቱ ስንት ሰዓት ነው?’ ይሉናል ደርሰው። እንጃ የእናንተን። ብቻ እኔ ሳልደርስባቸው የሚደርሱብኝ እያደር ጨምረዋል። ምናልባት እኔ ሳባርራቸው ወደ እናንተ ከመጡ መልሱ ‘አልነጋም ገና ነው!’ ነው። አደራ ከእኔ አልሰማችሁትም እሺ። ደግሞ ያስኮርጃል ተብዬ በኋላ ጣጣ እንዳይመጣብኝ። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ “ማንም አይነካህም አይዞህ። መጀመርያ በኩረጃ እያለፉ ያስመረቁዋቸውን ይከልሱ፤” ሲለኝ ነበር። ማን ተመራቂ ማን አስመራቂ እንደሆነ እሱ ሲያወራ ግራ ገባኝ።

ግን እንዲያው አደራችሁን ሌት ከሆነ ሰዓት ማስላት ምን ይጠቅማል? ሰቅዞ ይዞኝ እኮ የምደጋግምባችሁ። የቀኑን ብርሃን ሳይቀር ይህንን የዘመን ጨለማ ከል እያለበሰው፣ የመንገድ መብራት 24 ሰዓት ይብራልን ሳንል አንቀርም ትላላችሁ ትንሽ ቆይተን? “አይ አንበርብር! ‘ዩ አር ቱ ፋር ፍሮም ዘ ሪያሊቲ፤” ይለኛል ምሁሩ ወዳጄ። “አብራራ” ስለው “አንተም ቤት ለቤት በቅጡ ያልተዳረሰና የሚቆራረጥ ኃይል እንዴት ሆኖ ለመንገድ 24 ሰዓት ሊበራ እንደምታስብ አብራራ፤” ብሎ ይስቅብኛል። ኧረ እኔስ አልስቅም። ቀኑ በጨለማ ኃይል የተያዘበት ምስኪን ይኼን ሁሉ ዕልቂት፣ ይህን ሁሉ ፍጅት፣ ይኼን ሁሉ የፖለቲካ የበላይነትን ለማስጠበቅ የሚደረግ የአውሬዎች ሴራ እያየ እንዴት ይስቃል? ማን ነበር ‘የሳቅ መቆራረጥ ያስቸገረን በዓለም መንግሥታት የአስተዳደር ብልሹነት ነው’ ብሎ ሲደመድም የሰማሁት?

እና እላችኋለሁ ‹እሳት ከነደደ አመድ መቼ ይገዳል፣ እንዲህ ነው ሰው ሁሉ አጥፊውን ይወዳል› ይባል ነበር አሉ ድሮ በአገራችን። አሁንማ ከቅኔና ከሰዋሰው ወደ ወንዜና ጎጤ ሠፈር ጥበብ ሳትቀር ፊቷን አዙራ በየት ብለን ቁምነገር እንሰማለን? ለነገሩ የሥራው ፀባይ ነው። “እንዴት?” አላችሁ። ጎሽ! ምነው ሁሉም እንደናንተ ሐሳብ ሳያስጨርስ ገና ለገና ለኮሜንት የተሰጠኝ ቦታ እያለ በፍረጃና በስድብ ጀምሮ ባይቋጭ። እውነቴን እኮ ነው! “ካልተደራጁ ወይ ካልተዛመዱ ወይም ካላደገደጉ ገና ለገና በዜግነት ብቻ ባዶ ቦታ በቀላሉ አይሰጥምና ወገኔ ቁጭቱን በፌስቡክ ርስቱ ላይ መወጣት ተያይዞታል’ ነው የሚባለው፤” ብዬ አንድ ወዳጄን ባወራው (ሲባል ነዋ የምሰማው) “ፌስቡክ አትጠቀምም እንዴ?” ብሎ ዞረብኝ። ወይ ጉድ ይህች መጠቀም የምትባል አባባል የማትገባበት ቦታ የለም በቃ። የምር! ለነገሩ ያለ መጠቃቀም ዘንድሮ ምንም ዓይነት ቦታ ላይ መቀመጥ፣ መቆም፣ ወይም መወሸቅ አዳጋች ሆኗል።

ታዲያ ይኼ ወዳጄ ‘ፌስቡክ’ የማልጠቀመው እንዳሻኝ እንድቆርሰውና እንድቆፍረው ያላግባብ የተሰጠኝ ቦታ ቢኖር ነው ብሎ ጠረጠረ። ‘በምን አወቅክ መጠርጠሩን?’ ብትሉኝ ሄዶ ‘ፌስቡኩ’ ላይ “በአገሩ ሙሉ መሬቱን የተቆጣጠረው ያውም ደላላ መሆኑን ‘ፌስቡክ’ ላይ በማየው ግፊያ አስተዋልኩ፤” ብሎ መለጠፉን መጥተው ነገሩኝ። አቤት የጠብ አጫሪው ብዛት። እውነቴን ነው የምላችሁ ዘንድሮ እኮ እንደ ጠብ አጫሪው ብዛት ቢሆን ውሎ ገባችን አጥፍቶ ማጥፋት መሆን ነበረበት። ግን ‘እሱም አውቆ ሰማይን አርቆ’ ሆኖ ነገሩ ንቆ ማለፍን ከየነፍሳችን ጋር ሰፋት። ይኼን ጊዜ የዘመኑ ቁምን ነገር ይከሰታል። ‘መተላለፍ ብሎ ነገር የለም’ ብለው በነፍስ የሚፈልጉን በዙ። ወሬው፣ ሐሜቱ፣ ትችቱና በአጠቃላይ ሁለ ነገራችን ስለታጣቂዎችና አስታጣቂዎቻቸው፣ ስለማክረርና መበጠስ ሆነና አረፈው። ታሪክ ከአሸናፊው በተጨማሪ በአወናባጁ እጅ ሲጻፍ ይኼው ዓለም እንደ ገልቱ ማኅበረሰብ እርፍና ማጭዱን ጥሎ፣ አፉን ደም ደም እስኪለው ስለጥፋት እያሰበ እያወራ ውሎ ማደር ጀመረ። እህ የት ይኬዳል?

“የጀርባዬ ሸክም ያለቅጥ ቢከብደኝ . . .፤” አለ አሉ አዝማሪው “. . . የጀርባዬ ሸክም ያለቅጥ ቢከብደኝ፣ ከድካሜ በቀር የለም ያዋረደኝ፤” በአገር ቅኝት እንፍሰስ ብዬ እኮ ነው ጣል ጣል የማደርግባችሁ። ጣል የሚያደርግብን ሲገኝማ ለቀም ነው ጎበዝ። ጥሎ ለረጋጭ የሚሰጥ እንጂ ባለን ላይ የሚጨምር የት ይገኛል በዚህ ጊዜ? ዋሸሁ? ቆይ ግን ደላላና ፖለቲከኛ ውሸታም ነው ብሎ የነዛው ማን ነው? በእርግጥ ፖለቲከኛ ሆኖ አልዋሽም ባይ ካለ የልጅ ልጅ አይታ ድንግል ነኝ የምትል አለች ማለት ነው። ባሻዬ መቼ ዕለት በዚሁ ዙሪያ አደባባይ ስንዞር ምን አሉን መሰላችሁ? “ሕዝብ እኮ ከፖለቲከኞች ጋር በውሸት ተጣልቶ አያውቅም፤” ብለው ዝም አሉ። “እንዴት ነው ነገሩ? ስንት አላየንም እንዴ ከጫካ እስከ ከተማ፣ ከከተማ እስከ መንደር?” ስላቸው፣ “ነገርኩህ! በመወሻሸት ሒደት ቴክኒክና ታክቲኩ ላይ፣ ወይም አነጣጡ አጠቋቆሩ ላይ ካልሆነ የትኛውም ሕዝብ ዋሻችሁ ብሎ ፖለቲከኞቹን አኩርፎ አያውቅም። የዓለምን ታሪክ በጥንቃቄ ደግመህ አንብብ፤” አይሉኝ መሰላችሁ? ለራሴ የግራ እጄ መዳፍ ሰበዛ ሰበዙ አሁን ዓይቼው አሁን እየተዘበራረቀ አስቸግሮኛል፣ ባሻዬ ዓለምን ጨብጣት እያሉ ያሳቅቁኛል። ለራሴ “እኔማ ዘንድሮ ሆኛለሁ ጀርጀርቱ፣ ቢጠሩኝ አልሰማ ጨርቄን ካልጎተቱ፤” እያልኩ ሲሸጡ ስሸጥ፣ ሲያከራዩ ሳከራይ፣ ሲለውጡ ሳለዋውጥ እውላለሁ፣ ባሻዬ ጭራሽ ‘ከጋርዮሽ ሥርዓት ምሥረታ አንስተህ ሽብርተኛው  . . . ይቅርታ  . . . ስምንተኛው ሺሕ ድረስ ተቀምጠህ አንብብ’ ይሉኛል። እንኳን ተቀምጠን ቆመንስ ቻልነው እንዴ? ምኑን? . . . እንጃላችሁ!

ጨዋታ ላይ ነን መሰለኝ። ነው ወይስ ፍርኃት ላይ ነን? ስደት ላይ ነን? ወይስ ሽብር ላይ ነን? ይጠፋኝ ጀመር ዕርምጃዬ ሁሉ። ታዲያ ለዚህ መድኃኒቱ (ዕድሜ ማራዘሚያው ብል ሳይሻል አይቀርም መሰል፣ እንጋታለን ይኼው መቼ ሻረልን?) በደፈናው መጫወት፣ በደፈናው ማውጋት ነው። ‘ሲከፍቱት ተልባ ሲወቅጡት እንቦጭ’ እንደሆነ በቃህ ካልተባለ አልሆነም። እናም በዚህ መሀል ደህና ሽቀላ ለማግኘት፣ ሁለት አይሱዙ አሻሽጬ ደግሞ የሚከራይ እንድፈልግ ወደ ታዘዝኩት ባለ ሦስት መኝታ ኮንዶሚኒየም ቤት ልጓዝ ነው፣ ባሻዬ “አድሮ ጥጃ” ብለው የሚተርቱበት ዓይነት ሰው ነኝ። አደራችሁን ባሻዬ ትልቅ ሰው ናቸው። ስድብ መስሏችሁ ግምታችሁ እንዳያንስብኝ። እንጂ ቋንቋውንማ ትተነው ይኼው ስድቡና ፈሊጡ ተምታቶብን ሲያተጋትገን ነው የሚውል። አሁን ወደ ሌላ ሳልሄድ ያ ያልኳችሁ ወዳጄ ክውክው እያለ መጥቶ “አዋጣ” አለኝ። በእጄ ጣሳ የለ፣ ሲኒ የለ፣ ኩባያ የለ። “ምኑን ነው የማዋጣው?” አልኩት። የሕዝብ ሀብትና ንብረት ያለተቆርቋሪና ተቆጣጣሪ በሞኖፖል እየተያዘ ኩባያና ሲኒ አዋጡ ስለሚሉን ብዬ ነበር እኔማ። ምነው?

“በሴረኛ ፖለቲከኞች ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን እንድረስላቸው። ያለ እኛ ማን አላቸው?” አለኝ። ብልጭ አለብኝ። ብልጭ ያለብኝ ‘ትራንስፎርመር’ ፈንድቶ አይደለም። እንዲያው ለአዝማሪ እበትነዋለሁ ብዬ የመደብኩት ገንዘብ ኖሮኝ ‘ለምን ተፈናቀሉ?’ ብዬም አይደለም። ጓዴን ስለማውቀው ብቻ ብልጭ አለብኝ። ገንዘቡን እየጠጣበት አሁን አብራው ያለችውን ሦስተኛ ሚስቱን እንዴት በችጋር እንደሚቀጣት አውቃለሁ። የቀደሙትን ሁለቱን ሚስቶቹን ሲፈታ አምስት ሳንቲም እንዳይካፈሉት እንዴት ንብረቱን እንዳሸሸ (አታምኑኝም እንጂ ከሚበሉት ብሎ የሸጠውን ቤቱን ያሻሻጥኩለት እኔ ነኝ) ታዝቤያለሁ። ልጆቹን ዞር ብሎ ዓይቶ ምን በሉ ምን ጠጡ እንደማይል አውቃለሁ። የማውቀውን ስለማውቅ ብቻ ነው ብልጭ ያለብኝ። በተገበዘ ፍቅር ተጠፍንጎ ሰው መሳይ በሸንጎው መድረሻ አሳጣን አቦ!

ታዲያ እኔ የምንተስኖት ልጅ (አባቴ በልጅነቴ ሞቶ በደንብ ባላውቀውም የዘር ዘመን ነውና ሲያንዘረዝረኝ እንዳትገላግሉኝ) ልክ ልኩን ነገርኩታ። ፍጥጥ ብዬ “አላዋጣም!” ስለው ተንጣጣ። “እንዴት አታዋጣም? ወገን አይደል እንዴ? እኛ ያለ እኛ . . .፤” ቅብጥርሶ ዘበዘበ። “ዕድሜ ለመንግሥታችን ሁሉም በቁጥጥሩ ሥር ነው፤” አልኩት። ስሜታዊ እየሆንኩ ሄድኩ። “እንዴት ሁሉም?” ሲለኝ ሁለቴ አላሰብኩም። “በቃ! መንግሥታችን በመቆጣጠር አይታማም። ከዚህ ቀደም ፓርላማውን ብትል መቶ በመቶ። ልማት ብትል ያውም በአፍርሶ መገንባት። በትምህርት ብትመጣ ከተማሪም ብሶ ያውም አብዮታዊ ዴሞክራሲ ከፊልዱ ቀድሞ የገባው…” ምን ያላልኩት አለ። “እናስ?” ሲለኝ፣ “ከቁጥጥሬ ውጪ ነው ሲለን እናዋጣለን። እስከዚያው ግን እኛም በቁጥጥሩ ሥር ነን፡፡ ዞር በልልኝ!” ብዬ አባረርኩት። ከበረረ በኋላ ግን ያልኩትን መልሼ ሳስበው ብዙ ዓመታት በአንድ እግሬ ቆሜ ሳልፀልይ ክንፍ የሚያስተክል ምትሃት በኖረ ነው ያልኩት። ቀላል ደነበርኩ? በዚያ የማይረባ ወስላታ ንዴት የወገኖቼን ጉዳይ የዘነጋሁ መስሎኝ ኅሊናዬ እየጮኸብኝ እስከ ዛሬ ራሴን መቆጣጠር አቅቶኛል። እናም አደራችሁ ለልጆቻችሁ ብላችሁ ሌላው ቢቀር ምላሳችሁን ተቆጣጠሩ። መቼም ምላስን ለመቆጣጠር ብሶት እስኪወልደን መጠበቅ አይጠበቅንም። አይደል እንዴ?

እንሰነባበት። ያን ያልኳችሁን ባለሦስት መኝታ ኮንዶሚኒዬም ቤት አከራይቼ ኮሚሽኔን ተቀብዬ የወጉን ለማድረስ ግሮሰሪ ገባሁ። አገሩ እንደሆነ በቢራ ማስታወቂያ ቁጥጥር ሥር ወድቋል። ቴሌቪዥኑ ቢራ ነው። ሬዲዮኑ ቢራ ነው። “እኔ እኮ አንዳንዴ መንገዳገድ ቢጤ ሸርተት የማለት አባዜ ሲበዛብኝ፣ ድሮስ ሰው በመጠጥ ተከቦ የሚናገረውን ምኑን ያውቀዋል እላለሁ፤” ይሉኛል ባሻዬ ስለሬዲዮና ቴሌቪዥን ተናጋሪዎች የአፍ ወለምታ እያነሳን ስንጫወት። እኛስ ወለም ቢለን ምን ይለናል ታዲያ? ግሮሰሪ ስገባ የባሻዬ ልጅ ጥጉን ይዞ ጠቀሰኝ። ገና ሳልቀመጥ አጠገቡ የተቀመጡ የዘወትር ደንበኞች የጀመሩትን ጨዋታ ቀጥለዋል። “. . . የአውሬው መምጫ ደርሷል፤” ይላል አንዱ። የባሻዬን ልጅ ቀና ብዬ አየሁት። ‘የምን አውሬ?’ ስል፣ ‘ዝም ብለህ ስማ’ ብሎ ጎሸም ያደርገኛል። “ከዚህ ወዲያ በቃ ሰላም የለም፣ ነውጥ በነውጥ ላይ፣ ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ ሃይማኖት በሃይማኖት ላይ መነሳቱ ግድ ነው . . .” ብሎ ሰውዬው ሲጎነጭ ሁሉም በመስማማት ራሳቸውን ያወዛውዛሉ። መፍትሔ የሌላቸው የመሰሉን የወቅቱ አንገብጋቢ የዘር፣ የሃይማኖት፣ የልዩነቶችና አስተዳደራዊ ችግሮች እየተነሱ ሳይንሳዊ ትንታኔ ይሰጥባቸውና በጨለማ ነቢያት የማይያዝና የማይጨበጥ ድምዳሜ ሲዘጉ የታዳሚዎች ‘አሜን’ ባይነት ገረመኝ። ይኼን ጊዜ ታዲያ ገና ሳልጎነጭ መስከር እጀምራለሁ። ማንን እንመን? ትናንትን? ዛሬን? ወይስ በጨለማ ነቢያት የሚጠቆመውን ነገን? ‘ከሌሊቱ ስንት ሰዓት ነው?’ ማለት ታዲያ ይኼኔ አልነበር? የዘንድሮ ዝባዝንኬ ተንባዮችንና ተመፃዳቂ ነቢያትን እንኳን ተቀምጠን ቆመንም አልቻልናቸውም እኮ? መልካም ሰንበት!    

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት