እ.ኤ.አ. በ1990ዎቹ ከ11 ልጆች መካከል አንዱ የአምስት ዓመት ልደቱን ሳያከብር ይሞት ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2017 አምስት ዓመት ልደታቸውን ሳያከብሩ የሚሞቱ ልጆች ቁጥር ከፊተኛው ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ ቀንሷል፡፡ በሌላ አገላለጽ በዘጠናዎቹ ከተወለዱ ሕፃናት ይልቅ በዚህ ዘመን የሚወለዱ የመኖር ዕድላቸው ሰፊ ሆኗል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2017 አምስተኛ ዓመት ልደታቸውን ሳያከብሩ የሞቱ ሕፃናት ከ26 ሕፃናት አንዱ ብቻ ነበር፡፡
የእነዚህን ሕፃናት ሕይወት መታደግ የሁሉንም ርብርብ የሚሻና አንገብጋቢ የዓለም አጀንዳ ነው፡፡ ወዲያ ደግሞ በየደቂቃው የሚወለዱ 250 ሕፃናትን ውልደት መቀነስ ከዚያ ባልተናነሰ መጠን ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ አገሮች የድህነት ምንጭ የሆነውን ከአገሮች ሀብት ጋር ያልተመጣጠነ የሕዝብ ቁጥር በልክ ማድረግ አቅምን የሚፈታተን ጉዳይ ሆኖ እስካሁን ዘልቋል፡፡
የሚላስና የሚቀመስ ሳይኖራቸው የተራቡ ሕፃናትን የሚጎትቱ ብዙ ናቸው፡፡ አንገታቸውን የሚያስገቡበት ጎጆ የሌላቸው፣ የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ሰርክ የሰው ፊት መቆም ግድ የሚላቸው፣ የጎዳና ተዳዳሪዎች ሳይቀሩ መውለድ የተፈጥሮ ፀጋ ነውና ደጋግመው ሲወልዱ ይታያሉ፡፡ ወልዶ መሳም ለወግ ማዕረግ የመድረስ ቀመር እስኪመስል የብዙዎች ሕይወት ዑደት ሥራ መያዝ፣ ማግባትና ከዚያ መውለድ ነው፡፡ አለመውለድ ለበርካቶች ምርጫ አይደለም፡፡ ወልዶ መሳም ለአንዳንዶች ምትክ ከማስቀረት ዓይንን በዓይን ከማየት በላይ ነው፡፡
ደጋግሞ መውለድ የሰውነት ወግ ተደርጎ በሚቆጠርበት ማኅበረሰብ ውስጥ የልጆቼን ቁጥር በገቢዬ ልክ ላድርግ ብሎ መወሰንም ከባድ ነው፡፡ የደግማችሁ ውለዱ ውትወታ የሚጀመረው ከዘመድና ጎረቤት ነው፡፡ አለመውለድ ግን ሌላ ጉዳይ ነው፡፡ አለመውለድ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን መውለድ ያለመቻል፣ የመጉደል ወይም መጥፎ የሕይወት አጋጣሚ ተደርጎ በብዙዎች ይታሰባል፡፡
ወልዶ የመሳምን ፀጋ የሚነፍገውን መሀንነትን በርካቶች ለመቀበል ይቸገራሉ፡፡ ቅጽል የሚያሰጠው መሀንነት ከእርግማን ይቆጠር የነበረበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡ መውለድ ስላልቻሉ ብቻ የስንቶች ትዳር ፈርሷል፡፡ ጥንዶች ያለውን እውነታ ተቀብለው ለመኖር ቢስማሙም፣ ቤተሰብ ጣልቃ ገብቶ የሚቻለውን ከማድረግ ወደ ኋላ አይልም፡፡ ስንቶችስ ደስታ አልባ ሕይወት ይመራሉ? ልጅ ባገኝ ብለው በየፀበሉ የሚንከራተቱ፣ የሚሳሉ፣ አድባሩን የሚለማመኑ ጥቂት አይደሉም፡፡ እንዲህ የሰዎችን ሕይወት የሚያመሳቅለው መሀንነት እርግማን ሳይሆን ሳይንሳዊ ማብራሪያ ያለው የጤና እክል መሆኑን ለማወቅ ጊዜ ፈጅቷል፡፡
መሀንነት በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚፈጠር የጤና ጉዳይ መሆኑ በሳይንስ ተረጋግጧል፡፡ ጥንዶች ያለምንም የእርግዝና መከላከያ በሳምንት ሁለቴና ከዚያ በላይ ጾታዊ ግንኙነት እየፈጸሙ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እርግዝና ካልተፈጠረ ከሁለት አንዳቸው መሀን ናቸው ማለት ነው፡፡ በሴቷ በኩል የእንቁላል አለመመረት፣ የቱቦ መዘጋት ወይም የሆርሞን አለመመጣጠን የመሳሰሉት መፀነስ እንዳትችል ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በወንዱ በኩል ደግሞ በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚፈጠር የዘረመል አለመመረትና ሌሎችም አጋጣሚዎች ማስረገዝ እንዳይችል ያደርገዋል፡፡
መሀንነት ሴቶችንም ሆነ ወንዶችን በእኩል መጠን የሚያጠቃ ችግር ነው፡፡ ችግሩ ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ወይም በአካባቢያዊ ተፅዕኖ እንደሚከሰት የሚናገሩት፣ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የማህፀንና ጽንስ ስፔሻሊስቱ ዶ/ር ቶማስ መኩሪያ፣ አብዛኛው የመሀንነት ችግር የሚከሰተው በአካባቢ ተፅዕኖ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ከፍተኛ የአባላዘር በሽታዎች ሥርጭት ባለባቸው አገሮች ከሌሎቹ አገሮች በተለየ የመካንነት ችግር በስፋት ይከሰታል፡፡
ባደጉት አገሮች መሀንነት የሚያጋጥማቸው አምስት በመቶ በሚሆኑት ዜጎች ላይ ነው፡፡ መሀን የመሆን ዕድልን በሚያሰፋው የአባላዘር በሽታዎች ሥርጭት ከፍተኛ በሆነባቸው ታዳጊ አገሮች በተለይም በኢትዮጵያ ከ15 እስከ 20 በመቶ በሚሆኑ ሰዎች ላይ መሀንነት ይታያል፡፡ ከጊዜ በኋላ በአጋጣሚዎች የሚፈጠረውን መሀንነት አስቀድሞ መከላከል ይቻላል፡፡ ከተያዙም በኋላ በአካል ላይ ተጨማሪ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ፈጥኖ መታከም መሀንነት የሚከሰትበትን ዕድል እንደሚቀንስ ያብራራሉ፡፡
እንደ እርግማን ይቆጠር የነበረው መሀንነት የሴቶች ብቻ ችግር ተደርጎ ይታሰብ ነበር፡፡ እንዲያውም በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ለፈጸሙት ኃጥያት ከፈጣሪ የተጣለባቸው ቁጣ ተደርጎም ይታሰብ ነበር፡፡ በሴቶችም ሆነ በወንዶች ላይ እኩል የመከሰት ዕድል እንዳለው እስኪታወቅ ሴቶች ብዙ ደርሶባቸዋል፡፡ በሕክምና መዳን እንደሚችል እስኪታወቅም ሚሊዮኖች ወልዶ የመሳምን ፀጋ ተነፍገው ኖረዋል፡፡
የመሀንነት ሕክምና የረዥም ጊዜ ታሪክ አለው፡፡ ተመራማሪዎች ጉዳዩን በሳይንስ መነጽር ማየት ሲጀምሩ መሀንነት እርግማን ሳይሆን በሕክምና ሊስተካከል የሚችል አጋጣሚ ሆነ፡፡ ምዕራባውያን ተመራማሪዎች ከ18ኛው ምዕት ዓመት መጨረሻ ጀምሮ ነበር ለጉዳዩ ትኩረት የሰጡት፡፡ በመጀመርያ የሴቶችን የመራቢያ አካል ክፍል አጠኑ፡፡ ቀጥሎ እርግዝና እንዲፈጠርና እንዳይፈጠር የሚያደርጉ አጋጣሚዎችን ለዩ፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ደግሞ እርግዝና የሚከሰተው በወንዴ ዘር ፈሳሽ አማካይነት መሆኑን አረጋገጡ፡፡ ይህንን መሠረታዊ መልስ ይዘው እርግዝና እንዳይከሰት የሚያደርጉ አጋጣሚዎችን መለየትና ለእነሱም መፍትሔ ወደ መስጠት ተሸጋገሩ፡፡
የመጀመርያው ተስፋ ሰጪ ሕክምናም በሰው ሠራሽ መንገድ (አርቴፊሻል ኢንሲሚኔሽን) ጽንስ እንዲፈጠር ማድረግ ነበር፡፡ ዶ/ር ማርቲን ሲምስ የተባለ ተመራማሪ በአርቴፊሻል ኢንሲሚኔሽን ጽንስ እንዲፈጠር ያደረገው ሙከራ አድካሚ ነበር፡፡ በስድስት ሴቶች ላይ 55 ጊዜያት ያህል ተደጋጋሚ ሙከራ አድርጓል፡፡ ሴቶቹ በአርቴፊሻል ኢንሲሚኔሽን እንዲያረግዙ በሚያደርግበት ወቅት የወር አበባ ዑደትን በተመለከተ ዕውቀት አልነበረምና ያደርግ የነበረው ሙከራ የሴቶቹን የመፀነሻ ጊዜ ያላገናዘበ ነበር፡፡ ከስድስቱ መካከል መፀነስ የቻለችው አንደኛዋ ሴት ብቻ ነበረች፡፡
መሀንነት ሴቶችን ብቻ ሳይሆን ወንዶችንም የሚያጠቃ የጤና እክል መሆኑንም በውል አያውቁትም ነበርና ከወንዶቹ የሚወስዱት ዘረመል የመሀንነት ምርመራ ሳይደረግለት ነበር፡፡
እንዲህ ያሉ ጅማሮዎች ይብዛም ይነስም የመሀንነት ሕክምና ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ መሠረት ሆነዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የመሀንነት ሕክምና ረቂቅ ሆኗል፡፡ ዘርን የማስቀጠል ሁለተኛ ዕድል ለሚሊዮኖች ሰጥቷል፡፡ ዛሬ ላይ የተለያዩ የመሀንነት የሕክምና ዓይነቶች በዓለም ላይ ተግባራዊ ይደረጋሉ፡፡
እንደ ዶ/ር ቶማስ ገለጻ፣ ሰዎች ወልደው መሳም እንዲችሉ የሚያደርጉ ቀላልና ውስብስብ የሕክምና ዓይነቶች አሉ፡፡ ለትዳር መፍረስ ምክንያት የነበረው መሀንነት በቀላሉ በሚዋጥ መድኃኒት ሊታከም ይችላል፡፡ ሕክምናው መሀንነት እንደተከሰተበት ምክንያት የተለያየ ነው፡፡ ለምሳሌ መሀንነቱ የተከሰተው በእንቁላል ያለመመረት ችግር ከሆነ እንቁላሎች እንዲመረቱ የሚያደርጉ መድኃኒቶች በመስጠት ችግሩን መቅረፍ ይቻላል፡፡ ከዚህም ባሻገር አንዳንድ መሀንነት የሚያስከትሉ እክሎች እጅግ ቀላል በሆነ ቀዶ ሕክምና መፍትሔ ያገኛሉ፡፡ በቀዶ ሕክምናም ሆነ በመድኃኒት መስተካከል የማይችሉ ደግሞ አማራጭ ሕክምና አላቸው፡፡ መሀንነቱ የተከሰተው በሁለቱም በኩል በሚከሰት የቱቦ መዘጋት ከሆነ በመድኃኒትም በቀዶ ሕክምናም የመስተካከል ዕድሉ በጣም አናሳ ነው፡፡ እንዲህ ላለው ውስብስብ ችግር መፍትሔው ኢፕቪትሮ ፈርትላይዜሽን ነው፡፡ ኢንቪተሮ ፈርትላይዜሸን እንቁላል ከሴቷ፣ የወንዴ ዘር ፈሳሽን ከወንዱ በመውሰድ ጽንስ ውጭ ላይ እንዲፈጠር ማድረግና ወደ እናትየው ማህፀን መልሶ የመክተት ቴክኒክ ነው፡፡
ከዓለም ጤና ድርጅት የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው፣ ከ15 እስከ 20 በመቶ የሚሆኑ የዓለም ሕዝቦች መካንነት ያጠቃቸዋል፡፡ አብዛኛው የመሀንነት አጋጣሚ የሚፈጠረው ከአካባቢ ተፅዕኖ ጋር በተያያዘ ከመሆኑ አንፃር ችግሩ በስፋት የሚታየው በታዳጊ አገሮች ነው፡፡
በኢትዮጵያ አገራዊ ጥናት ባይደረግም በተለያዩ ጊዜያት የተሠሩትን ጥናቶች ዋቢ አድርገው የሚናገሩት ዶ/ር ቶማስ፣ በጎንደር 21 በመቶ በቡታጅራ አካባቢ ደግሞ ከ16 እስከ 20 በመቶ የሚሆኑ ጥንዶች የመሀንነት ችግር ያጋጥማቸዋል ብለዋል፡፡ ለመውለድ ያደረጉት ሙከራ በተደጋጋሚ ጊዜ ያልሠራላቸው ጥንዶች ሥጋታቸውን ለማረጋገጥ በየጤና ተቋማቱ ይንከራተታሉ፡፡
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ብቻ የመሀንነት ችግር ያጋጠማቸው 1,720 ጥንዶች ታይተዋል፡፡ ‹‹ብዙ ጊዜ እኛ አገልግሎቱን ስለማንሰጥ ወደ እኛ አይመጡም እንጂ ችግሩ ያለባቸው ከዚህ በጣም ብዙ ናቸው፤›› የሚሉት ዶክተር ቶማስ፣ አቅሙ ያላቸው ውጭ ሄደው እንዲታከሙ እንደሚመክሯቸው ይገልጻሉ፡፡
ዘርን የማስቀጠል አቅም ያለው ይህንን ሕክምና ለማግኘት ሚሊዮኖች ባህር እንደሚያቋርጡ በቅዱስ ጳውሎስ ሜዲካል ኮሌጅ የሕክምና አገልግሎት ምክትል ፕሮቮስት ዶ/ር ሊዲያ ተፈራ ይናገራሉ፡፡
በኢትዮጵያ በየዓመቱ እስከ አምስት ሚሊዮን የሚሆኑ ጥንዶች ችግሩ የሚያጋጥማቸው ሲሆን፣ 1,000 የሚሆኑት በየዓመቱ ለሕክምና ወደ ውጭ ይወጣሉ፡፡ ለአንድ ጊዜ የሕክምና ቆይታም ቢያንስ 12,000 ዶላር ወይም ከ340 ሺሕ ብር በላይ እንደሚያወጡ ይነገራል፡፡ በአጠቃላይ በመሀንነት ሕክምና ሳቢያ አገሪቱ በየዓመቱ 20 ሚሊዮን ዶላር ታጣለች፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከሚላኩ የውጭ አገሮች የሕክምና አገልግሎቶችን ዝርዝር የያዙ በራሪ ጽሑፎችም የመሀንነት ሕክምናን እንደ መሳቢያነት ሲጠቀሙ ይታያል፡፡
ወልዶ ለመሳም ያልታደሉ የመውለድን ፀጋ ለማግኘት የማይከፍሉት የለም፡፡ ጥሪታቸውን አሟጠው ሕክምናውን ከማግኘት የሚያግዳቸው አይኖርም፡፡ ዕድሜ ለዘረመልና ለእንቁላል ለጋሾች ባደጉት አገሮች መሀንነት ብዙም የማያስጨንቅ የሕይወት አጋጣሚ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ግን ማህፀን ማከራየትም ሆነ አርቴፊሻል ኢንሲሚኔሽን በሕግ የተከለከለ ስለሆነ መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ሕክምናውም አገር ውስጥ የማይሰጥ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወጪው አቅሙ ላላቸው እንጂ ለሌላው የማይደፈር ነው፡፡
ከሰሞኑ ግን ለሚሊዮኖች ተስፋ የሚሰጥ ዜና ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በኩል ተሰምቷል፡፡ ሆስፒታሉ በአገሪቱ ካለው የችግሩ ስፋት አንፃር በአገር ውስጥ የመሀንነት ሕክምና መስጠት የሚያስችለውን ዝግጅት አጠናቋል፡፡ በአንዳንድ አጋጣሚዎች ዘገየ እንጂ እንደ አጀማመሩ ከሆነ አገልግሎቱን ከዚህ ቀደም ብሎም መስጠት ይችል ነበር ተብሏል፡፡
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የተጀመረው የመሀንነት ሕክምና ጽንስ ውጭ ላይ የሚፈጠርበት የኢንቪትሮ ፈርትላይዜሸን ቴክኒክን ያካተተ ነው፡፡ ‹‹በእኛ አገር ያልተለመደ ቢሆንም በቀሪው ዓለም በስፋት የሚሠራበት ነው፡፡ ይኼ ቴክኒክ በሥራ ላይ መዋል የጀመረውም በ1970ዎቹ ነው፤›› የሚሉት ዶ/ር ቶማስ፣ ከጥንዶቹ እንቁላልና ዘረመል በመውሰድ ጽንስ እንዲፈጠር የማድረግ ሕክምና ላይ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሠራ ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡ ወደፊት ግን ከማኅበረሰቡ ጋር በመወያየት አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ እንቁላል ማምረት የማትችል ሴት፣ መሀን የሆነ ወንድ ከሌሎች ሰዎች እንቁላል ወይም ዘረመል ተውሰው መውለድ የሚችሉበትን ሕክምና ሊሰጥ ይችላል ብለዋል፡፡
የሕክምና ማዕከል ከኢንቪትሮ ፈርትላይዜሸን ውጪ ያሉን ሕክምናዎች አስቀድሞ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ በቀዶ ሕክምና፣ በሚዋጥ መድኃኒት የሚሰጡትን የመሀንነት ሕክምና አገልግሎቶች በመቶዎች ለሚቆጠሩ ጥንዶች ተሰጥቷል፡፡ የኢንቪትሮ ሕክምና ከማዕከሉ ምርቃት በኋላ የሚጀመር እንደሆነ የሚናገሩት ዶ/ር ቶማስ፣ ሕክምናውን ለመስጠት የሚያስፈልጉ መሣሪያዎችም ሆነ የሰው ኃይል ዝግጁ መሆኑን ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡ ምዝገባ ጨርሰው የሕክምናውን መጀመር በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ 450 የሚሆኑ ጥንዶች አሉም ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ይህንን ሕክምና የሚሰጡ ሁለት የግል ተቋማት አሉ፡፡ በመንግሥት ደረጃ ሕክምናው ሲሰጥ ግን ይህ የመጀመርያው ነው፡፡ በመጀመርያው ዓመት 500 የሚሆኑ ጥንዶችን ለማከም ዕቅድ መያዙን፣ ቀጥሎ ግን በየዓመቱ 2,000 እና ከዚያ በላይ የሚሆኑ ጥንዶችን እንደሚያክም ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡
የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሥነ ተዋልዶ ሕክምና ማዕከል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሰናይት በየነ፣ ማዕከሉ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትና ደኅንነቱ የተጠበቀ ጽንስ የማቋረጥ አገልግሎትም ይሰጣል ብለዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ የሥልጠና ማዕከልም እንዲሆን ታስቦ የተሠራ ነው፡፡ መንግሥት የውልደት መጠንን መቆጣጠር ላይ ትኩረት አድርጎ በመሥራቱ የመሀንነት ሕክምና ወደ ጎን ተብሎ መቆየቱን የሚናገሩት ሥራ አስፈጻሚዋ፣ እንዲህ ያለ ሕክምና የሚሰጡ ማዕከላትን ማደራጀትም አቅም የሚጠይቅና አገልግሎቱን በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርብበት ሁኔታን በተመለከተም እየተመከረበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህንን ያሉት ሆስፒታሉ በእናቶች የጤና አገልግሎት ላይ የሚያከናውኗቸውን ተግባራት አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ነበር፡፡ በሆስፒታሉ በዓመት እስከ 30 ሺሕ እናቶች የቅድመ ወሊድ ምርመራ እንደሚያደርጉ፣ በአንድ ወር ውስጥም እስከ 1,000 እናቶችን የማዋለድ ሥራ እንደሚሠራ አስታውቋል፡፡ ዶ/ር ሊዲያ እንደገለጹት፣ ሆስፒታሉ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተንቀሳቅሶ ለተለያዩ ጤና ተቋማት ዕገዛ ያደርጋል፡፡ የእናቶችና ሕፃናት ጤና አገልግሎት የሚውል 400 አልጋዎችን የሚይዝ ማዕከልም በሚቀጥሉት ወራት ሥራ ይጀመራል፡፡