Thursday, July 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሪል ስቴት ኩባንያዎች ያለባቸውን ውዝፍ ዕዳ እንዲከፍሉ ተጠየቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቅርቡ በከተማ ደረጃ የታክስ ንቅናቄ የጀመረው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የሪል ስቴት ኩባንያዎች ያለባቸውን ውዝፍ ዕዳ እንዲከፍሉ ጠየቀ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 130 የሪል ስቴት ኩባንያዎች የሚገኙ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ ባካሄደው ጥናት ስድስት ሪል ስቴት ኩባንያዎች ብቻ በአግባቡ የቤት ግብር መክፈላቸውን ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡

ቀሪዎቹ 21 የሪል ስቴት ኩባንያዎች ግብር መክፈል ጀምረው ያቋረጡ መሆናቸውን፣ 103 ሪል ስቴት ኩባንያዎች ደግሞ እስካሁን ምንም ዓይነት ክፍያ መክፈል አለመጀመራቸው ተገልጿል፡፡

የቤትና የቦታ ግብር አንዱ የንብረት ግብር ዓይነት ሲሆን፣ የግብር አሰባሰብን አስመልክቶ በደንብ ቁጥር 36/1968 መሠረት በቤቱ ዓመታዊ የኪራይ ግምት ላይ በመመሥረት እስከ 600 ብር ዓመታዊ ኪራይ ያላቸው አንድ በመቶ፣ ከዚህ በላይ ዓመታዊ ኪራይ ያላቸው ደግሞ 4.5 በመቶ መክፈል ይኖርባቸዋል፡፡

የሪል ስቴት ኩባንያዎች የከተማውን የቤት ፍላጎት ለማሟላት ለመኖሪያና ለንግድ ቤት የሚሆኑ ሕንፃዎችን በመገንባት በሽያጭ እያስተላለፉ መሆኑ ይታወቃል፡፡

የገቢዎች ቢሮ እንዳለው፣ እነዚህ የተገነቡ ቤቶች በሽያጭ ከመተላለፋቸው በፊት የሪል ስቴት ባለቤቶች በአዋጅ ቁጥር 80/1968 አንቀጽ 8 መሠረት የቤት ግብር፣ በየዓመቱ እስከ የካቲት 30 ቀን ድረስ ባለው ጊዜ መክፈል አለባቸው፡፡

ቢሮው ጨምሮ እንዳስገነዘበው የቤት ግብር የተረጋጋና አስተማማኝ የገቢ ምንጭ በመሆኑ፣ ከሌሎች የታክስ ዓይነቶች በተለየ የማይለወጥና የማይሰወር፣ ለቁጥጥር አመቺና ከታክስ ለመሸሽ የማይመች ነው፡፡

‹‹ሆኖም የተጠናቀቀው መረጃ እንደሚያሳየው ከ4.4 ሚሊዮን ካሬ ሜትር ቦታ ላይ መሰብሰብ የሚገባው የቤት ግብር እየተሰበሰበ አይደለም፤›› በማለት የገቢዎች ቢሮ አስታውቋል፡፡

ያለባቸውን ውዝፍ ዕዳ የተጠየቁ የሪል ስቴት ኩባንያዎች ግን ይህ ጥያቄ ግርምት ፈጥሮባቸዋል፡፡ የሪል ስቴት ኩባንያዎች እንዳሉት፣ እነሱ መክፈል የሚጠበቅባቸው የሊዝ ክፍያ ብቻ ነው፡፡ ከሪል ስቴት ኩባንያ ቤት የሚገዙ ግለሰቦች ደግሞ ካርታውን ካገኙ በኋላ፣ የቤትና የአፈር ግብር የመሳሰሉትን መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ የሪል ስቴት ኩባንያዎች የቤት ግብር እንዲከፍሉ የሚጠየቁበት በምን አግባብ እንደሆነ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሽሰማ ገብረ ሥላሴ እንደተናገሩት፣ የቤትና የቦታ ግብር ቀላሉ የግብር ዓይነት ነው፡፡

‹‹ማንኛውም ቤትና ቦታ የያዘ አካል አንድ በመቶ፣ ወይም 4.5 በመቶ መክፈል ይኖርበታል፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ሽሰማ እንዳሉት፣ የሪል ስቴት ኩባንያዎች የገነቡትን ቤት ለተጠቃሚዎች ካዞሩና ካስታወቁ፣ ግብሩን የሚከፍሉት ተጠቃሚዎቹ ናቸው፡፡

‹‹እኛ የምናውቀው በሪል ስቴት ኩባንያዎች የተገነቡ ቤቶች የሚገኙት በኩባንያዎቹ እጅ ነው፡፡ ስለዚህ የእኛ መረጃ የሚያሳየው ቤቶቹ ግብር እንዳልተከፈለባቸው ነው፤›› በማለት አቶ ሽሰማ የሪል ስቴት ኩባንያዎች ያለባቸውን ግብር እንዲከፍሉ ጠይቀዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች