Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሪል ስቴት ዘርፍ በተካሄደ ዳሰሳ ጥናት በወረቀትና በተግባር ባለው እውነታ ከፍተኛ ልዩነት መኖሩ ይፋ ሆነ

ተዛማጅ ፅሁፎች

 የአዲስ አበባ አስተዳደር በአግባቡ ለሚገነቡ አጋር እሆናለሁ ብሏል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) በሪል ስቴት ዘርፍ የተንሰራፉ ችግሮችን እንዲፈታ ከሁለት ሳምንት በፊት ያቋቋሙት ግብረ ኃይል ባካሄደው መጠነኛ ዳሰሳ፣ በማኅደር በሠፈረውና ተግባራዊ በሆነው ግንባታ መካከል ከፍተኛ ልዩነት እንዳለ አመለከተ፡፡

ምክትል ከንቲባው በቀጥታ የሚቆጣጠሩትና በመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የሚመራው ግብረ ኃይል በ15 ቀናት ውስጥ ያካሄደውን የመጀመርያ ዙር ጥናት፣ ጥር 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ዋነኛ የሪል ስቴት ዘርፍ ተዋናዮች በተገኙበት አቅርቧል፡፡

የዳሰሳ ጥናቱ በማዕከል ደረጃ የሚገኙ 87 የሪል ስቴት ልማት ፕሮጀክት ፋይሎችን፣ በሳይት ደግሞ 51 ፕሮጀክቶችን መመልከቱን ገልጿል፡፡ የቀድሞው የኮንስትራክሽን ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አሁን ደግሞ የግብረ ኃይሉ ተጠሪ የሆኑት አቶ መለስ አለቃ ባቀረቡት ዳሰሳ ጥናት፣ የተወሰኑ ኩባንያዎች በድርድር በሊዝ መነሻ ሒሳብ የወሰዱትን ቦታ ግንባታ ሳያካሂዱበት ለሦስተኛ ወገን አስተላልፈዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በቀድሞው ሊዝ ቦርድ ከተፈቀደው ውጪ ግንባታዎችን መቀያየር፣ የአፓርታማ ቤቶችን ቁጥር በመቀነስ የቪላ ቤቶችን ቁጥር መጨመር፣ የአገልግሎት ለውጥ ማድረግ፣ ቪላ ገንብቶ አፓርታማ አለመገንባት፣ ግንባታ ጀምሮ ማቆም፣ ከተፈቀደው መሬት ውጪ ቦታ አስፋፍቶ መያዝና በአረንጓዴ ቦታዎች ላይ ግንባታ ማካሄድ ተጠቃሽ ልዩነቶች መሆናቸው በአቶ መለስ የቀረበው የዳሰሳ ጥናት ያመለክታል፡፡

በጥናቱ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሠራት ሲገባቸው ያልተሠሩና በሪል ስቴት ልማት ከፍተኛ ችግር ፈጥረዋል የተባሉ ጉዳዮችም በዝርዝር ቀርበዋል፡፡ ከእነዚህ ችግሮች መካከል የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች በተለይም የውኃ፣ የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ያለመኖር፣ የመንገድ ጥናት መቀያየር፣ በተገነቡ ቤቶች ላይ የሚያልፍ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር መኖር፣ በአቪዬሽን ምክንያት የሕንፃ ከፍታ መቀያየር፣ የኦፕቲካል መስመር በሳይት ላይ መኖር፣ የወሰን ችግሮች፣ የሊዝ ውል ማሻሻያ ጊዜ አጭር መሆን፣ በግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ ላይ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መኖር ተጠቃሽ መሰናክሎች ሆነው ቀርበዋል፡፡

በዕለቱ የተገኙ የአስተዳደሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና የሪል ስቴት ኩባንያዎች ባለቤቶች ችግሮቻቸውን በመቀበል መተማመን ላይ ደርሰዋል፡፡ በውይይቱ ወቅት የሪል ስቴት ኩባንያዎች የቀረበው ጥናት ጥልቀት የሚጎለው መሆኑን በመጥቀስ፣ ምክትል ከንቲባውን ጨምሮ ግብረ ኃይሉ በተናጠል እንዲያነጋግሯቸው ጠይቀዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ቤቶች ተገንብተው ሲያልቁ የተናጠል ካርታ በፍጥነት እንዲሰጥ የሊዝ ውል ማሻሻያ ላይ ያለው አሠራር እንዲስተካከል የሪል ስቴት ኩባንያዎች ጠይቀዋል፡፡ በተጨማሪ በከተማው ሪል ስቴት ቤቶችን የሚገነቡ ኩባንያዎችን አስተዳደሩ በአጋርነት እንዲመለከት ተጠይቋል፡፡

ከሪል ስቴት ኩባንያዎች ለቀረቡ ጥያቄዎች የአዲስ አበባ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሽመልስ እሸቱ (ኢንጂነር) እና ምክትላቸው አቶ ሚሊዮን ግርማ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የቢሮ ኃላፊው እንዳሉት፣ አንድ የሪል ስቴት አልሚ ለተጠቃሚው ስም ሲያዞር መሟላት ያለባቸው መሥፈርቶች አሉ፡፡

‹‹የተናጠል ካርታ ለመስጠት በምንዘጋጅበት ወቅት ጠያቂው በውሉ መሠረት በአግባቡ ገንብቷል ወይ? የሚጠበቅበትን ክፍያዎች ፈጽሟል ወይ? ተብሎ ሲታይ ብዙ ጊዜ ይህ አይሆንም፡፡ በአግባቡ ያልተካሄደን ግንባታ ለማስተናገድ ደግሞ እንቸገራለን፤›› ሲሉ አቶ ሽመልስ ገልጸው፣ ‹‹በአካባቢ ልማት ጥናት አረንጓዴ የተባሉ ቦታዎች ላይ ግንባታ አካሂዶ፣ ሊዝ ቦርድ የወሰነውና መሬት ላይ ያለው ሀቅ የተለያየ ሆኖ እያለ የተናጠል ካርታ ጥያቄ ሲቀርብ ጥያቄውን ለማስተናገድ እንቸገራለን፤›› በማለት አስተዳደሩ የገጠመውን ተግዳሮት  አብራርተዋል፡፡

ግብረ ኃይሉ በዋናነት የተቋቋመው የሪል ስቴት ልማት በከተማው የተፈጠረውን የመኖርያ ቤት ችግር የሚፈታ ስለሆነ ተገልጾ፣ ዘርፉም ለአስተዳደሩ አጋር ነው ተብሏል፡፡ ‹‹በአግባቡ የሠራውን እንደግፋለን፣ ጫፍ ያወጣውን ደግሞ እናስተካክላለን፤›› ሲሉ አቶ ሽመልስ አስረድተዋል፡፡

ምክትል ከንቲባ ታከለ ውይይቱን ሲያሳርጉ እንደተናገሩት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሪል ስቴት ልማትን ስትራቴጂካዊ የቤት ልማት ፕሮግራም አድርጎ ይመለከተዋል፡፡

‹‹ከክፍላተ ከተሞች አንስቶ እስከ ማዕከል ድረስ የሚመለከተው የአስተዳደሩ ክፍል የሪል ስቴት አልሚዎችን በተናጠል ያስተናግዳል፤›› በማለት የገለጹት ምክትል ከንቲባው፣ ‹‹በከተማው የሚካሄደውን የሪል ስቴት ግንባታ አስተዳደሩ የራሴ ነው ብሎ ይመለከተዋል፤›› በማለት አጋር መሆኑን አሳውቀዋል፡፡

ምክትል ከንቲባው ጨምረው እንደገለጹት፣ አስተዳደሩ የሚከታተለው በምደባ ወይም በሊዝ ጨረታ መሬት ወስደው የሚያለሙትን ብቻ አይደለም፡፡ ይልቁኑም ከግለሰቦች ቦታ አግኝተው የሚያለሙትን ጭምር ስለሆነ እነዚህ አልሚዎች መረጃቸውን ለክፍላተ ከተሞች እንዲያቀርቡና መረጃው እንዲደራጅ እንዲተባባሩ ጠይቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች