Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ዘመቻዎች የሚጀመሩብኝ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን የሚያስደስቱ ትልልቅ ተግባራት በምንፈጽምበት ወቅት ነው››

ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)

በሰኔ ወር 2010 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ሆነው የተሾሙት አቶ ታከለ ኡማ በንቲ (ኢንጂነር) ኃላፊነቱን ተቀብለው ከተማዋን ማስተዳደር ከጀመሩ ሰባተኛ ወራቸውን ይዘዋል፡፡ ኃላፊነቱን ተቀብለው መሥራት በጀመሩባቸው ሁለት መቶ ቀናት ውስጥ ያከናወኗቸው ተግባራት በብዙዎች ዘንድ ዘንድ ዕውቅናና ከበሬታን እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡ ከቢሮ ውጥተው የሚመሩት ማኅበረሰብን በመቅረብና ችግሮችን በአካል ተገኝተው ከማኅበረሰቡ በቀጥታ በመስማት የአመራር ሥልታቸው የሚታወቁት ምክትል ከንቲባ ታከለ፣ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ አንስቶ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ትችት የሚሰነዘርባቸው መሪም ናቸው፡፡ በዚህ አጭር የኃላፊነት ቆይታቸው ያከናወኑዋቸውን ተግባራትና በዚህ ኃላፊነት ቆይታቸው ሊያሳኩትና በማኅበረሰቡ ቢታወሱበት ስለሚመርጡት ጉዳይ፣ እንዲሁም በሌሎች ፖለቲካዊ ይዘት ባላቸው ጉዳዮች ላይ ከዮሐንስ አንበርብር ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አዲስ አበባን በማስተዳደር ረገድ በዕድሜ የመጀመርያው ወጣት ከንቲባ (የሕግ ሥነ ሥርዓትን ለማሟላት ሲባል ማዕረጉ ምክትል ከንቲባ ቢሆንም) ነዎት፡፡ ይህ ደግሞ ወደ ፖለቲካ ሕይወት በስንት ዓመታቸው ቢገቡ ነው የሚል ጥያቄ ያጭራልና እስኪ ወደ ፖለቲካ ሕይወት እንዴት እንደገቡ መቼ የሚለውን በአጭሩ ያካፍሉን፡፡

ምክትል ከንቲባ ታከለ፡የፖለቲካ ሕይወትን እንድመርጥ ተፅዕኖ ያደረገብኝ ተወልጄ ያደግኩበት አካባቢ ይመስለኛል፡፡ ተወልጄ ያደግኩት አምቦ አካባቢ ነው፡፡ እንደሚታወቀው አምቦና የአካባቢው ማኅበረሰብ ለመብቱ የሚቆረቆር ነው፡፡ ለራሱ መብት ብቻ ሳይሆን፣ ለአገር የሚቆረቆር ጠያቂ ሕዝብ ነው፡፡ ሁለተኛ የቤተሰብ ተፅዕኖ ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ ከቤተሰባችን መካከል ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅንን መጥቀስ እችላለሁ፡፡ ከሎሬት ፀጋዬ ጋር ሦስተኛ ትውልድ ላይ ነው የምንገናኘው፡፡ አባቴ ታከለ ብሎ ጠርቶኝ አያውቅም፣ የሚጠራኝ አሁንም ድረስ በረዋቅ ብሎ ነው፡፡ በረዋቅ የአባቴ ቅድመ አያት መጠሪያ ስም ሲሆን፣ በነበረበት ዘመንና በሚኖርበት ከአምቦ ወጣ ብላ በምትገኝ ቦዲቲ በምትባል አካባቢ በጀብደኝነት የሚታወቅ ቤተሰብ ነው፡፡ በረዋቅ በእናቱ ላይ ተፈጽሞ የነበረ በደልን በአፍላነት ዕድሜው የካሰ በመሆኑ ቤተሰባችን በበረዋቅ ስያሜ በአካባቢው ይታወቃል፡፡

አባቴ ከልጅነቴ ጀምሮ ነው በረዋቅ እያለ የሚጠራኝ፡፡ እንዲሁም ስለበረዋቅ ታሪክ ሲያጫውተኝ የኖረው ለተልዕኮ እያዘጋጀ ይሁን አይሁን እሱ ነው የሚያውቀው፡፡ ይህ ታሪክ ግን በእኔ ሕይወት ውስጥ ተፅዕኖ ነበረው፡፡ በተለይ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለሁ የባሌ ደን ተቃጠለ በተባለበት ወቅት ፖለቲካዊ ይዘት አለው ብለን በማመናችን፣ ተማሪዎችን አስተባብረን እሳት ለማጥፋት ዘመቻ አድርጌያለሁ፡፡ በአምቦ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለን በፖሊስ መደብደብ የተለመደ ነበር፡፡ በወቅቱ ከኦሕዴድ ውጪ ለኦሮሞ ሕዝብ የሚታገል ድርጅት አልነበረም፡፡ እኛ ደግሞ ኦሕዴድ ይኼንን ትግል መምራት አይችልም ብለን እናምን ስለነበር፣ በወቅቱ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የነበርን ወጣቶች ከባድ የሆነ እንቅስቃሴ እንፈጥር ነበር፡፡ እየበሰልን ስንመጣ ደግሞ የዶ/ር መረራ ፓርቲ በአምቦ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ስለነበረው፣ ዶ/ር መረራ በወቅቱ ያደርጉት የነበረውን የፖለቲካ ክርክርና እንቅስቃሴ እንከታተል ነበር፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ጨርሰን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ1993 ዓ.ም. አራት ኪሎ ግቢ ከገባን በኋላም ከፍተኛ የፖለቲካ እንቅስቃሴ አደርግ ነበር፡፡ መቼም በ1993 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የነበረው የተማሪዎች አመፅ ይታወሳል፡፡ ፖሊሶች ከግቢ ይውጡ፣ ምግብ ይስተካከል የሚል አመፅ ነበር፡፡ የጀርባ ፖለቲካዊ ምክንያቱ ግን ሌላ ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ እኛ የኦሮሞ ተማሪዎችን ብሔራዊ ቴአትር ሰብስበው ለመብታችን እንድንታገል ያደፋፍሩን የነበሩ አሁን ስማቸውን መጥቀስ የማልፈልጋቸው ሰዎችም ነበሩ፡፡ ሄዶ ሄዶ ዩኒቨርሲቲው በተማሪዎች አመፅ ተዘጋ፡፡ ተማሪዎች ወደየቤታቸው እንዲመለሱ ተደረገ፡፡

እኔም ወደ አምቦ ተመልሼ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን ማስተማር ጀመርኩኝ፡፡ ነገር ግን ማስተማር ብቻ አልነበረም፡፡ ዩኒቨርሲቲው ለትምህርት እንደገና ሲከፈት ወደ አደስ አበባ በተመለስኩት ወቅትን ግን በሕይወቴ ያዘንኩበት ነገር ተፈጠረ፡፡ በ1993 የነበረውን አመፅ ያስተባበራችሁትና የመራችሁት እናንተ ናችሁ ተብለን 14 የኦሮሞ ተወላጅ ተማሪዎች በየትኛውም የአገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች እንዳንማር ተወስኖ ተባረርን፡፡ ትምህርቴን የምወድና ጎበዝ ተማሪ ስለነበረኩ አዘንኩ፣ በጣም ተስፋ ቆረጥኩ፡፡ የተባረርንበት ምክንያት ኦነግ ናቸው የሚል በመሆኑ፣ ኦነግ ይንቀሳቀስበታል ወደሚባሉ ቦታዎች እንሂድ ተባብለን ሦስት አራት ተማሪዎች ሆነን ወደ ሞያሌ ብንሄድም ከኦነግ ጋር መገናኝት አልቻልንም፡፡ ስለዚህ በቀጥታ ወደ ኬንያ በመዝለቅ የስደተኛ ካምፕ ተቀላቀልን፡፡

በዚህ የኬንያ ካምፕ ውስጥ የሰብዓዊ መብት ስደተኞች ሆነን ቁጥር ተቀብለን ወደ ካናዳ ለመሄድ ዕድሉን አገኘን፡፡ ነገር ግን ወደ ካናዳ ለመሄድ ሁለት ወራት ሲቀረን እኔ አዕምሮዬ ሊቀበለው አልቻለም፡፡ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ነበር የምፈልገው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ደግሞ በእግር ስለመጣንና ሌላ ነገር እንዳይጠመጠምብን የፖለቲካ ፓርቲ አባልነት መታወቂያ መያዝ መረጥን፡፡ የዶ/ር መረራ ፓርቲ የሆነውን የኦሮሞ ኮንግረስ ፓርቲ ይዘን ከሁለት ልጆች ጋር ወደ ኢትዮጵያ ተመለስን፡፡ በተመለስንበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የዩኒቨርሲቲ መምህራንን ያወያዩበት ጊዜ ነበር፡፡ ከውይይቱ በኋላም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራንን አነሱ፡፡ እኛን ያባረሩን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት የነበሩት እሸቱ ወንጨቆ ከአመራርነት ተነስተው ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ ተሾሙ፡፡ እውነቱን ለመናገር ሰዎች ገብቷቸውም ይሁን ሳይገባቸው በሰው ሕይወት ውስጥ ሚና አላቸው፡፡ ይኼንን የምልበት ምክንያት ሁለት ተማሪዎች ሆነን ዝም ብለን በድፍረት ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ ቢሮ ገብተን የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች እንደነበርን፣ እንዴት እንደተባረርንና አጠቃላይ ያለፍንበትን ሁኔታ ገለጽንላቸው፡፡ እና ምንድነው የምትፈልጉት ብለው ጠየቁን፡፡ ትምህርቴን ከመቀጠል ውጪ አማራጭ ስላልነበረኝ መመለስ እንደምፈልግ ገለጽኩላቸው፡፡ ምንም ሳያቅማሙ ራሳቸው ደብዳቤ ጽፈው እንድንመለስ ወሰኑልን፡፡ እውነት ለመናገር በሕይወቴ ውስጥ አንድ ምዕራፍ እንድጀምር ያደረጉት ፕሮፌሰር አንድርያስ ናቸው፡፡ ምናልባት እሳቸው ይኼንን ላያውቁ ይችሉ ይሆናል፡፡

ወደ ዩኒቨርሲቲ ከተመለስኩ በኋላ በአንድ በኩል የኢንጂነሪንግ ትምህርቴን፣ ፖለቲካውን እንዳልተወው ደግሞ የ1997 ዓ.ም. ምርጫ መጣ፣ ሁለቱንም ገፋሁባቸው፡፡ በ1999 ዓ.ም. በኢንጂነሪንግ ተመርቄ በወጣሁበት ወቅት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ አባዱላ ገመዳ ተመራቂ ተማሪዎችን በማነጋገር፣ የክልሉ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ወጣቶችን የማሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ፡፡ በወቅቱ ኦሕዴድ የኦሮሞን ፍላጎት መምራትም ሆነ ማስተዳደር አይችልም የሚል አመለካከት ብዙዎቻችን እናራምድ ነበር፡፡ እሳቸው ታዲያ ግቡና ለውጡት ብለው ቀለል አድርገው በሩን ከፈቱት፡፡ በጣም ብዙ ተማሪዎች ተቀላቀልን፡፡ ምናልባትም በዚህ ውሳኔ ኦሕዴድ ውስጥ የለውጥ እንቅስቃሴ እንዲጀምር ወሳኝ ምዕራፍ የከፈቱ ይመስለኛል፡፡

የሱሉልታ ከተማ አስተዳዳሪ ሆኜ ተመደብኩ፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ ብዙ ለውጥ አመጣን፡፡ ከዚያም በሆለታ ከተማ ከንቲባነት ተመደብኩ፡፡ ሁለት ዓመት በነበረኝ የሆለታ ከተማ ቆይታዬ ብዙ ውጤት አስመዝግቤያለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ ከማኅበረሰቡ ጋርም ጥሩ ቅርበት ነበረኝ፡፡ በኋላ በኦሮሚያ ክልል የፖለቲካ ለውጥ በድንገት ተደረገ፡፡ አቶ አባዱላ ከክልሉ ፕሬዚዳንትነት ተነስተው አቶ ዓለማየሁ አቶምሳ መጡ፡፡ እኔ ከነበርኩበት አመራርነት ተነስቼ ወደ ሰበታ ከተማ እንድሄድ ተወሰነ፡፡ ይኼንን ውሳኔ አልተቀበልኩም፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ ከመጣው የአመራር ለውጥ ጋር ተያይዞ ጥሩ መግባባትም አልነበረኝም፡፡ የእከሌ ቡድን የሚባል የፖለቲካ ወገንተኝነት በክልሉ ስለተፈጠረ፣ ኦሕዴድን የማዳከም እንቅስቃሴ ስለነበረ አልተቀበልኩትም፡፡ አጭር የትምህርት ዕድል አግኝቼ ወደ አሜሪካ ሄድኩ፡፡ ከቆይታ በኋላ ተመልሼ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሬዬን ተማርኩኝ፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ዩኒቨርሲቲ በተመለስኩበት ወቅት እውነተኛ የትምህርት ጣዕምን ያጣጣምኩበት ጊዜ ነበር፡፡ በኋላ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ዓለማየሁ እንዳግዛቸው ጥያቄ አቀረቡልኝ፡፡ ሁለተኛ ዲግሪዬን ከጨረስኩ በኋላ በዩኒቨርሲቲው ለማስተማር ሁሉን ነገር ጨርሼ በነበረበት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ድጋሚ የውጭ የትምህርት ዕድል አሜሪካ አግኝቼ በነበረበት ወቅት ነው አቶ ዓለማየሁ ጥያቄውን ያቀረቡልኝ፡፡ የእኔ የሕይወት ተልዕኮ ሕዝብን ማገልገል ነው፡፡ እርካታም የሚሰጠኝ ይኸው በመሆኑ የእሳቸውን ጥያቄ ተቀብዬ የኦሮሚያ የከተማ መሬት አስተዳደር አንድ ዘርፍ አንድመራ ተሰጠኝ፡፡ በዚህ ኃላፊነት ላይ ማገልገል ጀመርኩ፡፡ ከዚህ በኋላ ቁስ እያለ እውነተኛ የሆነ የፖለቲካ ሪፎርም ውስጥ ለውስጥ ተካሂዶ አሁን የተገኘው ለውጥ መጣ፡፡ እኔም የኦሮሚያ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ሆኜ በፕሬዚዳንቱ አቶ ለማ መገርሳ አስተዳደር ውስጥ ማገልገል ቀጠልኩ፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን የሚገኙበትን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከንቲባነት አገለግላለሁ ብለው አስበው ያውቃሉ? ለዚህ ኃላፊነት ሲታጩ ምን ተሰማዎት?

ምክትል ከንቲባ ታከለ፡በፕሬዚዳንት ለማ አስተዳደር ውስጥ የነበረው ቡድን የአሁኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የነበራቸው ዕቅድ፣ ወጣቶችን ወደ አመራርነት ማምጣት ነበር፡፡ የኦሮሚያ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ሆኜ የአቶ ለማ መገርሳን ቡድን የተቀላቀልነው በሙሉ ማለት እችላለሁ፣ ለምንድነው እዚህ የመጣነው በማለት እየተከራከርን ችግር ለመፍታት እንጥር ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ አንዱ ኢሕአዴግን ወደ ፖለቲካ ሪፎርም ውስጥ ማስገባት ነበር፡፡ በአጠቃላይ በአጭር ዓመታት ውስጥ የነበረኝ ያላቋረጠ የፖለቲካ ተሳትፎ የትም ቦታ ሄጄ መሥራት እንደምችል ጥንካሬውንም እምነቱንም ፈጥሮብኝ ነበር፡፡ ስለዚህ አዲስ አበባ ስመጣ እንቆቅልሽ አልሆነብኝም፣ መገረምም አልፈጠረብኝም፡፡ ስለዚህ አዲስ አበባ እንድመጣ ሲወሰን ብዙም አዲስ አልሆነብኝም፡፡

ሪፖርተር፡- አዲስ አበባ በብዙ ችግሮች የተከበበች ነገር ግን የኢትዮጵያ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማዕከል ነች፡፡ እርስዎ ወደ ኃላፊነት ሲመጡ ስለከተማዋ የነበረዎ ግንዛቤ ምን ይመስል ነበር? ምን ዕቅድ ነበረዎ?

ምክትል ከንቲባ ታከለ፡- ተማሪም ሆኜ፣ ለረዥም ዓመታት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት መቀመጫም አዲስ አበባ ስለሆነች፣ በክልሉ የካቢኔ አባል ሆኜ ባገለገልኩበት ወቅትም እዚሁ ስለነበርኩ አዲስ አበባን እንደ ነዋሪ ነው የማውቃት፡፡ በተጨማሪም ከሙያዬ አንፃር፣ እንዲሁም በኦሮሚያ ውስጥ ከመሬትና ከትራንስፖርት ጋር በተያያዙ ኃላፊነቶች በአመራርነት ያሳለፍኩ በመሆኑ ከነዋሪነት ባለፈ የአዲስ አበባን ችግሮች በተሻለ የመረዳት ዕድል ሊኖረኝ እንደሚችል መገንዘብ አያዳግትም፡፡ ችግሮቹን መረዳትና ከተማዋን ወደ መምራት ኃላፊነት መምጣት ግን የተለያዩ ናቸው፡፡ እውነት ለመናገር አዲስ አበባ ሁለት ከተማ ነች ማለት ይቻላል፡፡ ማኅበረሰቡ ራሱ በሁለት የተራራቁ የሀብት መዋቅሮች ወስጥ የሚገኝ ነው፡፡ አንደኛው ጥሮ ግሮ በጣም ሀብታም የሆነ፣ ቤተሰቡንም ከተማዋንም ያለማ ሀብታም አለ፡፡ ሌላኛው ደግሞ መብላት የተቸገረ አለ፣ በመኖሪያ ቤት ደረጃም እንደዚያው፡፡ በአንድ ከተማ ሁለት ተቃራኒ ገጽታዎችን ነው የምትመለከተው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ብሔር፣ ሃይማኖት፣ ድህነት፣ ባለፀጋነትና ሌሎች ያልገለጽኳቸው ሁሉም የሚኖሩበት ከተማ ነች፡፡ አዲስ አበባ ትንሿ ኢትዮጵያ ናት ቢባል ምንም ማጋገን አይደለም፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ መገለጫ የሆነች ከተማን እንዴት አድርገን ለኢትዮጵያ ሞዴል ልናደርጋት እንችላለን የሚለውን ትኩረት አድርገን መንቀሳቀስ የሚገባን ጉዳይ መሆኑን ዓይቻለሁ፡፡ ፖለቲካውን ትቼ ለማስተዋል የሞከርኩትን የማኅበረሰቡን ስሜት ልናገር፡፡ ሁሉም የመገፋትና የመፈናቀል ስሜት እንዳለው ነው የሚተርክልህ፡፡ አሁን ያለንበት መሀል አራዳም ሆነ የከተማዋ ጥግ ላይ የሚኖረውን ማኅበረሰብን ሄደህ ብትጠይቅ የሚነግርህ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሁሉም ተፈናቀልኩ፣ ተገፋሁ ነው የሚለው፡፡ ከተማዋ የነዋሪው ስትሆን የባለሀብት ወይም የሌላ አካል እንደሆነች ነው ማኅበረሰቡ የሚያሰማው፡፡ ቃለ መሃላ ፈጽሜ ወደ ሥራ ስገባ መጀመርያ ልሠራው ይገባል ብዬ የወጠንኩት ይኼንን ትርክት መቀየር ሲሆን፣ አንድ አጀንዳዬ አድርጌዋለሁ፡፡

ስለዚህ መልሶ ማልማት የሚባለው ፍልስፍና ይፈጸምበት የነበረውን መንገድ መቀየር አለብን ብለን ነው የተነሳነው፡፡ ይኼ ምን ማለት ነው? አንድን አካባቢ ለማልማት ባለሀብት ሲመጣ የአካባቢውን ነዋሪ አፈናቅለህ ወደማይፈልገው ቦታ መስደድ ሳይሆን፣ የልማቱ አካል እንዲሆን የማድረግ ስትራቴጂን ነው የተከተልነው፡፡ ማንንም ሳያፈናቅል ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ የጋራ የማልማት ሥልት ካልተከተልን፣ ከተማዋ የነዋሪዎቿ መሆኗን ማረጋገጥ አይቻልም፡፡ በሌላ አገላለጽ የከተማ ነዋሪ ማለት ያለው ብቻ ከማኅበራዊ መስተጋብሩ ሳይነጠል የሚኖር ሀብታም ብቻ ሳይሆን የጎዳና ተዳዳሪውም፣ ምስኪን እናቶችም፣ የተማረውም ያልተማረውም ነዋሪነቱ መረጋገጥ አለበት፡፡ መካከለኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ወደሚገኘው የከተማዋ ነዋሪ በሒደት እንደርሳለን፡፡ ነገር ግን ታች ያለው የከተማዋ ደሃ ማኅበረሰብ በሥነ ልቦናም ሆነ ኑሮውን በማሻሻል ከፍ እንዲል ቅድሚያ ሰጥተን ነው ወደ ሥራ የገባነው፡፡ ታስታውሱ ከሆነ ክረምት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ይዘን የምስኪን እናቶችን ቤት በመጠገን የነዋሪውን ሥነ ልቦና ከፍ የማድረግ እንቅስቃሴ በማድረግ አዲስ አበባን ማፍረስ ብቻ ሳይሆን፣ ከመሀል ከተማ ማንም ሳይፈናቀል ማልማት እንደሚቻልና ማኅበረሰቡ ከተማዋ የእሱ እንደሆነች እንዲያስብ ለማድረግ ሞክረናል፡፡ በአንድ እናት ቤት የጀመርነው ሙከራ ወጣቱን፣ አርቲስቱን ሁሉንም አንቀሳቅሶ በየወረዳው ተዳርሷል፡፡

ይህ የመገፋት ስሜት በከተማዋ ጥግ ላይ የሚኖር አርሶ አደርም ዘንድ በስፋት አለ፡፡ ይኼንን ያህል ትልቅ መሬት ነጥቀው ይኼ ሁሉ ግንባታ ሲከናወን እኔ ይህችን መሬት ይዤ ቀረሁ፣ ተፈናቀልኩ ሲሉ ትሰማለህ፡፡ ትርክቱ ሁሉም ቦታ አለ፡፡ ስለዚህ ወደ ኃላፊነት ከመጣን በኋላ ይኼንን ስሜት ለማስተካከል ነው የጣርነው፡፡ ሙሉ ለሙሉ ቀርፈነዋል ባልልም በከፍተኛ ደረጃ አስተካክለነዋል፡፡ ከተማዋ የነዋሪዎቿ መሆኗን ማረጋገጥና ይኼንንም ፈጽሜ በዚህ ሥራ መታወስ ነው የምፈልገው፡፡ አንዱ የበላይ አንዱ የበታች የሚሆንበት ሳይሆን፣ ከተማዋ የሁሉም መሆን እንድትችል መሥራትና ማሳካት እፈልጋለሁ፡፡ ሌላው አዲስ አበባን ወደ ስሟ ማምጣት ነው የምፈልገው፡፡ አዲስ አበባ የተጨነቀች ከተማ ነች፣ መተንፈስ ትፈልጋለች፣ ነዋሪዎቿ በነፃነት ከከተማዋ ጋር መተንፈስ እንዲችሉ ማድረግም ያስፈልጋል፡፡ ከመሠረተ ልማት ቀጥሎ ለአረንጓዴ ልማት ትኩረት መስጠት እንዳለብን አቅደናል፡፡ የመሬት ኦዲት አድርገን ታጥረው የከረሙ መሬቶችን መንጠቅ ስንጀምር በርካቶች መሬት አስመልሰን ምን እንደምናደርግበት ወደ ማቀድ የገባን ነው የመሰላቸው፡፡ አይደለም፡፡ አቅደን ነው የገባነው፡፡ ከተማዋ ታንቃለች መተንፈስ አለባት፡፡ ለግንባታ የሚሆነው፣ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መዋል ያለበትም ተለይቶ ለዚህ ተግባር ይውላል፡፡ ለዚህ ሲባል ሕጋዊነትን ማረጋገጥ አለብን ብለን ነው ወደ ሕግ ማስከበር ሥራ የገባነው፡፡    

ሪፖርተር፡- ለዓመታት ታጥረው የነበሩ ይዞታዎች መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ ጉልበት ባላቸው ባለሀብቶች ባለቤትነት ሥር የነበሩ በቀድምቹ የከተማዋ ከንቲባዎች ያልተደፈሩ በመሆናቸው፣ የታጠሩ መሬቶችን ወደ ከተማ አስተዳደሩ በመመለስ ተግባር ደፋር መሪ የሚል ዕውቅና እንዳስገኘልዎት እገነዘባለሁ፡፡ ነገር ግን ይኼንን ተግባር የፈጸሙት በፖለቲካዊ በቀል ተነሳስተው እንደሆነ የሚያምኑም ስላሉ ምን ይላሉ? ከበቀል ንፁህ ነበሩ ወይ?

ምክትል ከንቲባ ታከለ፡- በመሬት ላይ የወሰድነው ዕርምጃ በጣም የተጠና ነው፡፡ ከሰው ቀጥሎ የከተማው ሀብት ምንድነው የሚለውን ጭምር ነው ያጠናነው፡፡ የከተማው ሀብት ከሆኑት መካከል አንዱ መሬት ነው፡፡ ከ1986 ዓ.ም. ጀምሮ እኛ እስክንረከብ ድረስ ይህ የመሬት ሀብት ለአልሚዎች ተላልፎ የልማት ሥራዎች ተከናውነውባቸዋል፡፡ ጥሩ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ነገር ግን ደግሞ ለታለመላቸው አገልግሎት ሳይውሉ ታጥረው በመቀመጣቸው፣ የኢኮኖሚ ሀብት መፍጠር ሳይችሉ ለዓመታት የባከኑ ይዞታዎችም ነበሩ፡፡ ይኼንን በጥናት ላይ ተመሥርተን ለማስተካከል ነው የሞከርነው፡፡ የፖለቲካ በቀል ነው የሚባለው ውሸት ነው፡፡ ቢሆንም ራሱ ስህተት አይደለም፡፡ ምክንያቱም በፖለቲካ ውሳኔ የተሰጠ መሬት የፖለቲካዊ ውሳኔ ይመለሳል፡፡ ነገር ግን እንደዚያ አይደለም ያደረግነው፡፡ አንድም መሬት ከሕግ አግባብ ውጪ የነጠቅነው የለም፡፡ ሁሉንም በሕግ መሠረት ነው የፈጸምነው፡፡ እንደዚያማ ባይሆን ፍርድ ቤት ይከሱን ነበር፡፡ የነጠቅናቸው መሬቶች በአማካይ ከስድስት እስከ አሥር ዓመታት ታጥረው የተቀመጡ ናቸው፡፡ ለሃያ ዓመታትም ታጥረው የተቀመጡ አሉ፡፡ ስለዚህ በስድስት ዓመት ውስጥ ያላለማ ባለሀብት፣ በአሥር ዓመት ያላለማ ባለሀብት ተጨማሪ ጊዜ ብትሰጠውም አያለማም የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰን ነው ዕርምጃውን የወሰድነው፡፡ የነጠቅነው በማንም የተያዘ ሊሆን ይችላል፣ ያለማ መሬትን ነው፡፡  የዲፕሎማቶች፣ በመንግሥት የተያዘ በዋናነትም በመከላከያ ሚኒስቴርና በባለሀብቶች የተያዘ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከተነጠቁት መሬቶች ውስጥ በርካቶቹ ለፓርኪንግ አገልግሎት መዋላቸው አስተዳደሩ ዕቅድ ሳይኖረው ነው መሬቱን የነጠቀው፡፡ ለባለሀብቶቹ ጊዜ ቢሰጥ ወይም ለሌሎች ባለሀብቶች መተላለፍ ወይም የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ለሚያመጡ ልማቶች መዋል ነበረባቸው የሚል ክርክር ይሰማል?

ምክትል ከንቲባ ታከለ፡- ለፓርኪንግ የሰጠነው በጊዜያዊነት ነው፡፡ መሬት ትልቅ ሀብት ሆኖ ገንዘብ ሳያመጣ ጦሙን እንዳያድር ነው፡፡ እነዚህ መሬቶች እኮ ታጥረው ተቀምጠው ነበር፡፡ ለወጣቶች በአጭር ጊዜ ጥሩ ገንዘብ እያስገኙ ነው፡፡ እኛ እስከዚያ ድረስ ልንሠራ ላሰብነው ልማት የዲዛይን ሥራ ለማከናወን ነው፡፡ ለምሳሌ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የሸራተን ማስፋፊያ ላይ የምንጀመረው የልማት ሥራ ይፋ ይደረጋል፡፡ እጅግ የሚገርም ፕሮጀክት ነው አሁን ግን ልነግርህ አልችልም፡፡ ስለዚህ በዕቅድ የተከናወነ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የከተማ አስተዳደሩ የቤቶች ልማት ፕሮጀክት ከጀመረ ቢቆይም ከፍላጎቱ ጋር መጓዝ አልቻለም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከፍተኛ የሆነ የዘረፋና የመጠቃቀሚያ ዘርፍ መሆኑ ይነገራል፡፡

ምክትል ከንቲባ ታከለ፡- የከተማው አስተዳደር የቤቶች ልማት ፕሮጀክት እጅግ በጣም ጥሩ ዕቅዱ የነበረ ቢሆንም፣ ውስብስብ ችግሮች ያሉበት ነው፡፡ አንደኛ ከፋይናንስና ከኮንትራክተሮች አቅም ማነስ ጋር በተገናኝ ችግር፣ በሌላ በኩል ደግም የተገነቡ ቤቶች ከማስተላለፍ ጋር በተያያዙ በርካታ ችግሮች የተወሳሰበ ነው፡፡ አሁን ከ130 ሺሕ በላይ በግንባታ ላይ ያሉ ቤቶች በእጃችን ላይ ይገኛሉ፡፡ ይኼንን በቅርቡ ለማኅበረሰቡ እናስተላልፋለን፡፡ የማስተላለፍ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተወሰኑ ማስተካከያዎችን አድርገናል፡፡ ለምሳሌ 40/60 በሚባለው የቤት ልማት ፕሮጀክት ሥር የቤቱን ዋጋ ሙሉ በሙሉ ለቆጠቡ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ነበር የማስተላለፍ አሠራሩ የሚያስቀምጠው፡፡ ነገር ግን ይህ መሆን የለበትም፡፡ 40 በመቶ የቆጠበ ወደ ዕጣ ሥነ ሥርዓቱ ውስጥ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ቤት ፈላጊውን ያደራጀ ነው 40/60 ብለን ነው፡፡ መንግሥት በቃሉ መታመን አለበት፡፡ መቶ በመቶ ለከፈለ ቅድሚያ የምንሰጥ ከሆነማ ሄዶ ሄዶ ሀብት እጅ ብቻ ነው የሚገባው፡፡ ነገር ግን 40  በመቶ ስንልም ምዝገባው በተካሄደበት ወቅት የነበረውን ግምት ዋጋ ሳይሆን፣ አሁን የምናስተላልፍበትን ዋጋ የቆጠበ ነው የሚሆነው፡፡ በ20/80 የቤቶች ፕሮግራምም ተመሳሳይ ነው የሚሆነው፡፡

በቤቶች ልማት ፕሮጀክት ረገድ ቀጣይ ዕቅዳችን መንግሥት መሬት አቅርቦ ባለሀብቶችና ቤት ፈላጊዎች ተቀናጅተው የሚያለሙበትን፣ መንግሥት መሬት ከማቅረብ ባለፈ የቁጥጥር ሥራ የሚያከናውንበትን ዕቅድ ይዘን ወደ ሥራ እንገባለን፡፡ ለዚህ ተግባር አንድ ሺሕ ሔክታር መሬት አዘጋጅተናል፡፡ አሁን በእጃችን ላይ ያሉትን ቤቶች ባሉበት ደረጃ ለተጠቃሚዎች እናስተላልፋለን፡፡ በእጃችንን ላይ ያሉት 134 ሺሕ ቤቶች በዕጣ ካስተላለፍን በኋላ ባለቤቱ ግንባታውን ይጨርሳል፡፡ አዲስ በምንጀምረው ፕሮግራም ግን በማኅበር እያደራጀን ቤት ፈላጊዎች በራሳቸው መንገድ እንዲያስገነቡ ነው የሚደረገው፡፡ የቤት ችግርን ከመቅረፍ በተጨማሪ መንግሥት ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር የተያያዘ ፍላጎት አለው፡፡ አዲስ በሚጀመረው ፕሮጀክት ውስጥ ስለዚህ ዝም ብሎ አይተወውም፡፡ ሌላው ፕሮጀክት ከባለሀብቶች ጋር በመጣመር በቅርቡ ለገሐር ላይ እንደጀመርነው ዓይነት ፕሮጀክት ተግባራዊ እናደርጋለን፡፡ መንግሥት መሬት በማቅረብ የአክሲዮን ድርሻ አያያዝ የሚከናወን ነው የሚሆነው፡፡ የበለጠ ትኩረት አድርገን እየሠራን ያለነው ችግሮችን መቅረፍ ላይ እንጂ በአስተዳደሩ ውስጥ ከቤቶች ጋር የተያያዘ ብዙ ችግሮች ናቸው ያሉት፡፡ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የተያዙ ከአራት ሺሕ በላይ ኮንዶሚኒየሞችና በርካታ የቀበሌ ቤቶች አስመልሰናል፡፡ ዕጣ ሳይደርሳቸው የያዙ አሉ፡፡ አንዳንዶቹ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ከመከላከያ ሠራዊት ለተሰናበቱ ወታደሮች የተሰጡ ናቸው፡፡ ይህ እጅግ መልካም ተግባር ነው፣ ሊደገፍም ይገባል፡፡ ነገር ግን በዚህ ሰበብ በርካታ ሕገወጥ ተግባራት ተከናውነዋል፣ ሰብረው ገብተው የሚኖሩም ተገኝተዋል፡፡ ሁሉንም እያስተካከልን ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- የአዲስ አበባና በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኘው የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን በኦሮሚያ ተቀስቅሶ ለነበረው ሕዝባዊ ተቃውሞ መነሻ ከነበሩት ምክንያቶች ግንባር ቀደም ነው፡፡ እርስዎ በዚያ ወቅት በይፋ የተናገሩት አቋም በሕዝብ ከሚታወቁባቸው አንዱ ነበር፡፡ ገበሬ እየተፈናቀለ የሚስፋፋ ከተሜነትን እንደማይቀበሉ አምርረው ሲናገሩ በሚዲያ ተላልፏል፡፡ ከጥቂት ዓመት በኋላ ደግሞ የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሆነው ተሹመዋል፡፡ ሹመቱ ከአቋምዎ ጋር አልተጋጨም? ወይስ አሁንም ይኼንኑ አቋምዎን ይዘው የአዲስ አበባን መስፋፋት የመገደብ ተልዕኮ አለዎት?

ምክትል ከንቲባ ታከለ፡- ያኔ የተናገሩክትነ ቃል በቃል ልንገርህ፡፡ አርሶ አደሩንና የአርሶ አደሩን ልጆች ወደ ጎን እየገፋ የሚስፋፋ አዲስ አበባንም ሆነ ኦሮሚያን አልደግፍም ነው ያልኩት፡፡ ይህ አመለካከቴን በቅንነት ማስተዋል ለሚፈልግ ለአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ለመቀሌም፣ ለባህር ዳርም፣ ለሐዋሳም፣ ለሌሎቹም ይሠራል፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ይህ አቋም አሁን በገለጹት መንገድ አሁንም ቀጥሏል?

ምክትል ከንቲባ ታከለ፡- አዎ፡፡ ምን ማለት መሰለህ? ቀደም ብዬ አዲስ አበባ ስመጣ ያስተዋልኩት የመገፋትና የመፈናቀል ስሜት ጋር የተያያዘ ነገር ነው፡፡ ነዋሪዎችን የዚህ ልማት ተጠቃሚ አይደለህም፣ ዞር በል፣ ከዚህ ሂድ ብሎ የሚካሄድ ልማት ሊቆም ይገባል ማለት ነው፡፡ ይህ እኮ በኦሮሚያም የነበረ ችግር ነው፡፡ ለምሳሌ አዳማ በዚህ መንገድ ነው የተስፋፋችው፡፡ እነ ቡራዩም እንደዚያው አርሶ አደሮችን በመግፋት ነው ያደጉት፡፡ የእኔ አቋም አርሶ አደሩ የልማቱ አካል ለምንድነው የማይሆነው የሚል ነው፡፡ አዲስ አበባም አርሶ አደሩን የልማቱ አካል ካደረገ ያድጋል፡፡ ማንም ሊያቆመው አይችልም፡፡ ነገር ግን ሲያድግ አንደኛውን ገፍቶ አንደኛውን የሚያቅፍ መሆን የለበትም፡፡ ሁሉን አቀፍ የከተማ ልማት ነው መሆን ያለበት፡፡ እዚህ አራት ኪሎ ለሸራተን ማስፋፊያ ተብሎ ነዋሪዎቹን አፈናቅሎ ቦሌ አራብሳ መውሰድ ተገቢ አይደለም፡፡ ለምንድነው እዚሁ የልማቱ አካል እንዲሆኑ የማይደረገው ነው የእኔ አቋም፡፡ ወደ አዲስ አበባ ከመጣሁ በኋላ አዲስ አበባ ጠርዝ ላይ የሚኖሩ አርሶ አደሮችን ቀርቤ ሳነጋግር ያስተላለፍኩት መልዕክትም ይኸው ነው፡፡ ይህ ለሁሉም ይሠራል፡፡ እንዲያውም ይህ አቋሜ የበለጠ ጠንካራ ሆኗል፡፡ አቋም ብቻ ሳይሆን በተግባርም እየፈጸምኩት እገኛለሁ፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ ለገሃር አካባቢ ይፋ ያደረግነው ግዙፍ ፕሮጀክት የአካባቢውን ነዋሪዎች ሳይፈናቀል የሚተገበር ነው፡፡ በዚህ አካባቢ የልማት ክልል ውስጥ የሚገኙ 1,600 ነዋሪዎች የተሻለ መኖሪያ ቤት፣ የተሻለ ትምህርት ቤት፣ የውኃ አቅርቦትና ሌሎች አገልግሎቶችን በተሻለ ደረጃ እንዲያገኙ የሚያስችል ነው፡፡ እነዚህን ነዋሪዎች ቦሌ አራብሳ በምን ምክንያት እልካለሁ? እዚሁ የልማቱ አካልና ተጠቃሚ ማድረግ እየተቻለ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ደጋግመው የሚናገሩትን እጋራለሁ፡፡ ልማት ማለት ሰው ነው፡፡ የከተማ ልማት ማለት ሕንፃ ወይም መንገድ ማለት አይደለም፡፡ ከተማ ማለት እኔ ነኝ፣ አንተ ነህ፣ ነዋሪው ነው፡፡ ልማቱም በሰው ወይም በነዋሪው ላይ ነው መሆን ያለበት፡፡ ለምንድነው የጎዳና ተዳዳሪዎች ከከተማ ልማት ተጠቃሚ የማይሆኑት? ስለዚህ አርሶ አደሩንም ሆነ ነዋሪውን የሚገፋ የከተማ ዕድገት አልፈልግም ነው ያልኩት፡፡ ለምንድነው ከዓውዱ ውጪ ፖለቲካዊ ትርጉም የተሰጠው ብለህ ከጠየቅክ ግን ምክንያት አለው፡፡ እዚህ ዝርዝር ውስጥ አልገባም፡፡ ነገር ግን በጥቅሉ አዲስ አበባ የእኔ ናት አዲስ አበባ ያንተ አይደለችም ከሚል ትርክት የሚመነጭ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ካነሱት አይቀር በዚህ ውዝግብ ላይ የእርስዎ አቋም ምንድነው?

ምክትል ከንቲባ ታከለ፡- በአጭሩ ልንገርህ አዲስ አበባ የሁላችንም ናት፡፡ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ናት፡፡ ይህ መርህ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡ ይኼንን የማናደርግ ከሆነ ምንም ጥቅም ማምጣት አንችልም፡፡

ሪፖርተር፡- የከተማዋን መስፋፋት የአዲስ አበባ መስፋፋት ብቻ አድርገው የሚያስቡት አሉ፡፡ ምናልባት የዚህ ምክንያቱ የአዲስ አበባ የአስተዳደር ወሰን ተለይቶ የማይታወቅ በመሆኑ ሊሆን ይችላል፡፡ እርስዎ ይኼንን መጣረስ ለማስተካከልና የአዲስ አበባ የአስተዳደር ወሰንን ለማካለል በዙሪያ ከሚገኘው የኦሮሚያ ክልል ጋር የጀመሩት ጥረት አለ?

ምክትል ከንቲባ ታከለ፡- ሙያዬን መሠረት አድርጌ ላስረዳህ፡፡ የከተማ መስፋፋት በሁለት መንገዶች ሊከናወን ይችላል፡፡ አንደኛው ወደ ጎን መስፋት ሲሆን፣ ሌላኛው ወደ ላይ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ አዲስ አበባ መሀሏን ብቻ ብታለማ ለሚቀጥሉት ሃያ ዓመታት የሚሆን በቂ መሬት አለ፡፡ አዲስ አበባ ወደ ላይ ነው መልማት ያለባት የሚል አቋም አለኝ፡፡ እኔ ወደ አዲስ አበባ ከመጣሁ በኋላ ቀደም ሲል ከኦሮሚያ ክልል ጋር የነበረው መገፋፋት ተቀርፏል፡፡ ምክንያቱም በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ አርሶ አደሮችን አነጋግረን እንዲረዱን ስላደረግን ነው፡፡ ከተማዋ የእነሱም መሆኗን፣ መልሰን እንደምናቋቁማቸውና ከልማት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በማስረዳት፡፡ በተግባርም ተጠቃሚ የሚሆንባቸውን ሥራዎች ማከናወን ጀምረናል፡፡ በመሆኑም የተገፊነት ስሜትን እያጠፋን በመሄዳችን በዚህ መንገድ ችግሮችን ለመቅረፍ እንሠራለን፡፡ ከዚህ መለስ ኦሮሚያ ነው፣ ከዚያ መለስ ደግሞ አዲስ አበባ ነው ተብሎ ድንበር እንዲበጅ መፈለግ የተሳሳተ አመለካከት ነው፡፡ በሕዝብና በሕዝብ መካከል ድንበር የመፍጠር አመለካከት አደገኛ ነው፡፡ ስለአስተዳደራዊ ወሰን ማውራት ግን ይቻላል፡፡ ይኼንንም በተመለከተ ኮሚቴ ተቋቁሞ መሥራት የተጀመረው እኔ ከመምጣቴ በፊት ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥት፣ የኦሮሚያ ክልልና የአዲስ አበባ አስተዳዳር የተወከሉበት ኮሚቴ አለ፣ ሲጨርስ ይገለጻል፡፡ በነገራችን ላይ ውዝግብ ያለበት አካባቢ በጎሮ በኩል የሚገኘው የአስተዳደር ወሰን እንጂ በሌላ በኩል የለም፡፡ እሱም ቢሆን ትንሽ ጉዳይ ነው፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት እንዳቀዱት ዓይነት ግድግዳ በኦሮሚያና በአዲስ አበባ መካከል እንዳይገነባ ነው የሚፈለገው፡፡ 

ሪፖርተር፡- እርስዎ ወደ አዲስ አበባ ከመጡ ጊዜ አንስቶ በድጋፍ አስተያየት ከፍተኛ ተቀባይነትን ቢያተርፉም፣ በተለይ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች በተደጋጋሚ ነቀፌታዎች ይሰነዘርቡዎታል፡፡ ለምሳሌ የኦሮሞ ተወላጆችን ወደ አዲስ አበባ በማስገባት የነዋሪነት መታወቂያ እንደሚያድሉ፣ እንዲሁም በከፍተኛ ወጪ መኖሪያ ቤት ተከራይተዋል የሚሉ ነቀፌታዎች ይደመጣሉ፡፡ እርስዎ ለእነዚህ ነቀፌታዎች ምላሽ ሲሰጡ አይስተዋሉም፡፡ ስለተቀበሏቸው ነው? ነቀፌታዎቹ ለምን ይሰነዘርቡዎታል?

ምክትል ከንቲባ ታከለ፡- አንድ በውቅያኖስ ላይ ጉዞ የጀመረ መርከብ ካፒቴን የት እንደሚደርስ ያውቃል፡፡ ነገር ግን በጉዞው ወቅት ማዕበል እንደሚያስቸግረውም ያውቃል፡፡ ዋናው ነገር ካፒቴኑ ትኩረት አድርጎ መቅዘፉ ላይ ነው፡፡ ይኼንን ካደረገ ማዕበሎቹ ጉዞውን የሚያስናክሉ ሳይሆን፣ በተቃራኒው ተጨማሪ ጉልበትና ፍጥነት ሆነው ሊያግዙት ይችላሉ፡፡ ወደ ኋላ አልመለስም፡፡ የእኔ አመራር መርህ ይህ ነው፡፡ በዚህ መርህ ሠርቼበት ነው እዚህ ደረጃ የደረስኩት፡፡ በቡድንም እንደዚህ ተንቀሳቅሰን ነው በኦሮሚያም ሆነ በፌዴራል ደረጃ ወደዚህ ለውጥ የመጣነው፡፡ አሁን የምትመለታቸው የነቀፌታ ዘመቻዎች በተደራጀ መንገድ የሚሰነዘሩ ናቸው፡፡ መነሻ ምክንያታቸውም ታከለ ለምን ወደ አዲስ አበባ ይመጣል ነው፡፡ በውድ ዋጋ ቤት ተከራይቶ ነው የሚኖረው የሚባለው የዚሁ ዘመቻ አካል ነው፡፡ በምክትል ከንቲባነት ከተመደብኩ በኋላ ወደ ተፈቀደልኝ ቤት የቀደሞው ከንቲባ ቤት ማለት ነው ልገባ ስል፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ከአሜሪካ አቡነ መርቆሪዮስን አግባብተው ተሳክቶ ሲመለሱ ለእሳቸው የሚሆን ቤት በፍጥነት ለማግኘት ተቸግረው ሳለ፣ ለእኔ ተብሎ የታደሰውና እኔም ልገባበት የነበረውን ቤት መልቀቅ እችላለሁ ብዬ ለአቡኑ እንዲሆን አስረከብኩ፡፡ ለእኔ የሚሆን መኖሪያ መንግሥት እስኪያሰናዳ ድረስ ለጥቂት ወራት መንግሥት የኪራይ ቤት አዘጋጅቶልኝ ወደዚያ ገባሁኝ፡፡ ነገር ግን የተቀናጣና ከእኔ ሰብዕና ወይም መርህ ጋር የማይሄድ፣ መንግሥትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለእኔ ቤት እስኪያዘጋጅ ድረስ እንጂ ወጪ ለማውጣት አይደለም፡፡ መንግሥት በተከራየው ቤት በጣም ለአጭር ጊዜ ቆይቼ ለቀቅኩኝ፡፡ አሁን የምኖረው በመንግሥት ቤት ውስጥ ነው፡፡ እውነት ለመናገር አሁን የምኖርበትን ቤት አስመልክቶ የጥበቃ ሠራተኛው ኃላፊነታቸውን ከመወጣት አንፃር እንደተቸገሩ ቅሬታ የሚያቀርቡበት ነው፡፡ እኔ የፕሮቶኮል ሰው አይደለሁም፡፡ በመርህ ያደግኩኝ የአርሶ አደር ልጅ ነኝ፡፡ ዋናው የዘመቻው ምክንያት ታከለ ለምን ወደ አዲስ አበባ ይመጣል ነው፡፡ የዚህን ምክንያትም እረዳዋለሁ፡፡ የብሔሩን ነገር ትቼ ሌላውን ልንገርህ፡፡ እኔ የአቋም ሰው እንደሆንኩ ይታወቃል፡፡ ያመንኩበትን ከመፈጸም ወደ ኋላ እንደማልልና የመርህ ሰው በመሆኔ ነው፡፡ በመሬት ላይ የወሰድኩትን ዕርምጃ ከመውሰድ ወደ ኋላ እንደማልል ይታወቃል፡፡  ልብ ብለህ አጢነህ ከሆነ ዘመቻዎች የሚጀመሩብኝ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን የሚያስደስቱ ትልልቅ ተግባራት በምንፈጽምበት ወቅት ነው፡፡ ኦሮሞን ወደ አዲስ አበባ አስገባ ብሎ ወቀሳ አሁን ምን ይሉታል? ኦሮሞ ወደ አዲስ አበባ መግባት አይችልም? ወደ አዲስ አበባ ለመግባት የሚቻለው በብሔር ማንነት ነው እንዴ? በጣም የሚገርመው አዲስ አበባ በኦሮሚያ የተከበበች ከተማ መሆናን እንኳን አያገናዝቡም፡፡ ኦሮሞን ወደ አዲስ አበባ የሚያስገባው በከተማዋ የሚኖሩ ኦሮሞዎችን ቁጥር ለመጨመር ነው፣ ሌላም ሌላም ይባላል፡፡ ለዚህ ምን ብዬ መልስ መስጠት እችላለሁ? ምክንያቱም ባለጌ አንተን አውርዶ ሊያሸንፍህ ይሞክራል ስለሚባል መውረድና መጫወት የለብንም፡፡ ለምመራው የአዲስ አበባ ነዋሪ በሚመጥን ደረጃ ነው ኮሙዩኒኬት ማድረግ ያለብኝ፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርናና የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ሻሸመኔ ከተማ ማደጋቸውንና መማራቸውን፣ በአግሮ ሜካኒክስ በዲፕሎማ...

የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ወደ ኢትዮጵያ ድንበር እየተጠጋ መሆኑ ተገለጸ

‹‹መንግሥት በሱዳን ያሉ የኢትዮጵያ ስደተኞች እንዲመለሱ አይፈልግም የሚባለው አሉባልታ ነው›› የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሱዳን ከአንድ ዓመት በላይ እየተካሄደ ያለው የእርስ በርስ ጦርነት ወደ ኢትዮጵያ ድንበር...

በህዳሴ ግድብ ላይ የግብፅን ፍላጎት ለማስከበር ጉቦ በመቀበል ወንጀል የተከሰሱት አሜሪካዊው ሴናተር ጥፋተኛ ተባሉ

የዴሞክራት ፓርቲ ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ሴናተር ቦብ ሜኔንዴዝ በህዳሴ ግድብ ላይ የግብፅን ፍላጎት ለማስከበር ጉቦ ተቀብለው በአሜሪካ ሴኔት ውስጥ የግብፅን አጀንዳ በማራመድና በሌሎች ክሶች...