የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን ለሁለት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ሲመራ ቆይቶ ከወራት በፊት ከኃላፊነቱ መልቀቁን ያስታወቀው ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ወደ ኃላፊነቱ እንዲመለስ ክልሎችና የከተማ ስፖርት አመራሮች መጠየቃቸው ታወቀ፡፡
ስፖርት ኮሚሽን ጥር 18 እና 19 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ በአገሪቱ ስፖርታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከክልልና ከከተማ የስፖርት አመራሮች ጋር ባካሔደው ውይይት ወቅት የቀድሞው ባለድል አትሌት ወደ አመራርነት ቦታው ይመለስ ጥያቄ መነሳቱ ታውቋል፡፡
ስፖርት ኮሚሽኑ ያቀረበው የውይይት አጀንዳ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይም በማዘውተሪያዎች አካባቢ የሚስተዋለው የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር፣ በስፖርቱ ሊኖር የሚገባው የመሪነት ሚናና ውጤታማነት ላይ ለመምከር ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን በከፍተኛ ወኔና ብቃት ለመምራት ኃላፊነቱን በመውሰድ ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ ግን ‹‹በቃኝ›› ያለው የኃይሌ ገብረሥላሴ ጉዳይ ተነስቶ ነበር፡፡ ከተወሰኑ ክልሎች ዝምታ በስተቀር፣ ኃይሌ ወደ ቀድሞው ኃላፊነቱ እንዲመለስ የሚጠይቁ አስተያየቶች መስተጋባታቸውን በውይይቱ የታደሙ የክልል አመራሮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ጥያቄውን ካነሱት ክልሎች መካከል ቤንሻንጉል ጉምዝ፣ ደቡብ፣ አማራና ትግራይ ሲጠቀሱ፣ በተለይም ኃይሌ ከፌዴሬሽኑ የለቀቀበት ምክንያት በግልጽ ሊነገር እንደሚገባ ማሳሰባቸው ተነግሯል፡፡ የመድረኩ አዘጋጅ ስፖርት ኮሚሽን፣ ስለጉዳዩ ያለው ነገር ባይኖርም ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የኮሚሽኑ ሙያተኞች በበኩላቸው ኮሚሽኑ ጥያቄው ተገቢ ቢሆንም ዘግይቷል የሚል እምነት እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ የኃይሌ ገብረሥላሴ አስተያየት እንዲሰጥበት የተደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲከስ ፌዴሬሽን አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ በመጥራት የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በስፖርት አመራር ጉዳይ ላይ ለሚያነሱት ጥያቄ ውሳኔ ሊያስተላልፍ እየጠየቁ ነው፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ ስለጉዳዩ እንደገለጹት ከሆነ፣ በፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ፕሬዚዳንቱ በሌሉበት ተቀዳሚው ምክትል ፕሬዚዳንት ተክቶ ይሠራል በሚለው አግባብ ሥራ አስፈጻሚውና የስፖርት ኮሚሽኑ ምክር ቤት በደረሱበት የፌዴሬሽኑ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ በዚህ አኳኋን እየጠመራ ይገኛል፡፡ የዓለም አቀፉን አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤኤፍ) መሠረት በመድረግ የፌዴሬሽኑን ኃላፊነት ተቀብለው እየሠሩ ለሚገኙት ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ የዕውቅና ደብዳቤ መጻፉን ጭምር ተናግረዋል፡፡