Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  በሕግ አምላክየድሬዳዋ አስተዳደራዊ አቋምና ሁኔታዋ የሕጋዊነት ተግዳሮቶች

  የድሬዳዋ አስተዳደራዊ አቋምና ሁኔታዋ የሕጋዊነት ተግዳሮቶች

  ቀን:

  በውብሸት ሙላት

  በጥር 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ድሬዳዋን ግጭት ሲጎበኛት ከርሟል፡፡ በግጭቱም የንብረትና የሰብዓዊ ጉዳት ደርሷል፡፡ የመከላከያ ሠራዊቱ ወደ አስተዳደሩ ቀጣና በመግባት ግጭቱን ተቆጣጥሮታል፡፡ በመቀጠልም የፌዴራል መንግሥቱም ከአስተዳደሩ ጋር በመሆን ሕዝባዊ ውይይቶችን እያካሄዱ ነው፡፡ ትክክለኛው የግጭቱ መነሻ ምንም ይሁን ምን አብሮ በአጀንዳነት ትኩረት የሳበ ጉዳይም ሲነሳ ነበር፡፡ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ አጀንዳ ከሆነም ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ይኼውም “40-40-20” የሚል ቀመርን ይመለከታል፡፡

  ይህ ቀመር የሚያመለከትው በድሬዳዋ አስተዳደር ያለውን የፖለቲካ ውክልና ነው፡፡ 40 በመቶ ኦሮሞ፣ 40 በመቶ ሶማሌና ቀሪው 20 በመቶ ደግሞ የሌሎች ብሔሮች ድርሻን መለኪያ ነው፡፡ በዚህ መንገድ የሥልጣን ክፍፍልና ውክልና ለማድረግ የሚደነግግ ሕግ ባይኖርም በተግባር እየሆነ ያለው ይህ ነው በሚል ነው ከኦሮሞና ሶማሌ ውጭ የሆኑት የከተማዋ ተወላጆች ቅሬታ፡፡

  ይህ ጽሑፍ የድሬዳዋ አስተዳደርን አቋም ከሕግ አንፃር የተወሰኑ ነጥቦችን በማንሳት ከላይ የተገለጸውን የሥልጣን ክፍፍል ቀመር ከሕገ መንግሥቱ መንፈስና ድንጋጌዎች እንዲሁም ከዴሞክራሲ መርሖች አንፃር ጥያቄዎችን ማቅረብ ነው፡፡

  የድሬዳዋ አመሠራረት

  የድሬዳዋ የከተማነት ታሪክ መቶ አሥራ አምስት ዓመታትን አልፏል፡፡ አመሠራረቷም የባቡር ትራንስፖርት ወደ ኢትዮጵያ መግባት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከጂቡቲ የሚነሳው ባቡር በሐረር በኩል ወደ አዲስ አበባ ማለፍ በወቅቱ አስቸጋሪ ነው በሚል ምክንያት ‘አዲስ ሐረር’ በማለት ድሬዳዋ የባቡር ጣቢያ ተገነባ፡፡ የጉምሩክ ጣቢያውም ከጀልዴሳ ወደ ‘አዲስ ሐረር’ ተዛወረ፡፡ ‘አዲስ ሐረር’ የሚለው ስያሜ ግን ሕዝባዊ ሳይሆን ቀርቶ ድሬዳዋ የሚለው ዘመን ተሻጋሪ በመሆን ቀጠለ፡፡

  ድሬዳዋ በተለያዩ ጊዜያት አስተዳደራዊ አቋሟና ተጠሪነቷ ተቀያይሯል፡፡ የደርግ መንግሥት ሊገባደድ ሲቃረብ እንደ ኦጋዴን፣ አሰብ፣ ትግራይና ኤርትራ ራስ ገዝ ሆና ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ (በተለይም ከ1985 ዓ.ም. ጀምሮ) እንዲሁ ራሷን እንድታስተዳድር ተደርጓል፡፡  

  1983 እስከ 1985 ዓ.ም. ድረስ በሶማሌና በኦሮሞ መካከል አልፎ አልፎ ግጭት ተስተውሏል፡፡ የሶማሌ ክልል መንግሥት ሲመሠረት ዋና ከተማውን ድሬዳዋ ለማድረግ ፍላጎት እንደነበረውም የክልሉም መንግሥት መጀመሪያ አካባቢ ጉባዔዎች ሲደረጉ የነበረው ድሬዳዋ ነበር፡፡ ከዚያ ወደ ጎደ ቀጥሎም ወደ ጅግጅጋ ተመለሰ፡፡ የሶማሌ ክልል መቀመጫውን ድሬዳዋ የማድረጉን ነገር በኦሮሚያ ክልል በኩል ተቃውሞ ገጠመው፡፡ በእርግጥ የኦጋዴን ነፃ አውጭ ግንባርም ድሬዳዋ መሆኑን አልደገፈም ነበር፡፡ ከዚያም የፌዴራሉ መንግሥት በራሱ አስተዳደር ሥር እንድትሆን በ1985 ዓ.ም. ወሰነ፡፡ ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ በአዋጅ ራሷን የምታስተዳድር ሆና ተቋቁማለች፡፡

  ድሬዳዋ ችግር የወለዳት መስተዳድር

  የኢትዮጵያ ውስጥ ግርታን ከሚፈጥሩ ጉዳዮች መካከል አንዱ የክልል አከሏ የድሬዳዋ አፈጣጠር ነው፡፡ ይኸውም በሕገ መንግሥቱ ላይ ሳይጠቀስ፣ የፌዴራሉ መንግሥት ለፌዴራል ተጠሪ የሚሆኑ ክልሎችን ወይም መስተዳድሮችን ስለሚመሠረቱበት ሁኔታ ሳይገለጽ ወይም ሥልጣን ሳይሰጠው የመመሥረቷ ጉዳይ ነው፡፡ ዋናው ነጥብ ድሬዳዋ ለምን ተመሠረተች ሳይሆን ሕገ መንግሥታዊ መሠረቷ/አፈጣጠሯ ምንድን ነው? እንበልና የሆነ ቡድን የድሬዳዋን ቻርተር ሕገ መንግሥታዊ አይደለምና ትርጉም ያስፈልገዋል ቢል ሕገ መንግሥታዊ ለማድረግ ምን መነሻ አለን? ለምን ቀድሞ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል አላስፈለገም ነው?

  ‹‹የጨነቀው እርጉዝ ያገባል›› እንዲሉ ድሬዳዋን ፖለቲካዊ ጭንቀት የወለዳት መስተዳድር ናት ማለት ይቻላል፡፡ የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎች ይገባኛል ጥያቄ፡፡ ሁለቱን ማስማማት ወይም በሌላ መንገድ ውሳኔ መስጠት አስቸጋሪ ሆኖ የቆየ ይመስላል፡፡ መፍትሔ በቀላሉ ማስቀመጥ አዳጋችም ሳይሆን አልቀረም፡፡ ይህንን ለመገመት በአንድ ወቅት ከምርጫ 97 በኋላ በነበረው የሕዝብ ተወካዮች  ምክር ቤት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) ፓርቲ አባል በነበሩት የምክር ቤት አባል ተነስቶ የነበረው ጥያቄ አመላካች ነው፡፡ ጥያቄው በግርድፉ ‹‹ሁለት ከተሞች (ድሬዳዋና አዲስ አበባ) እንዴት ከኦሮሚያ፣ ከአንድ ክልል ብቻ ተቀንሰው ተጠሪነታቸው ለፌዴራል መንግሥት ይሆናሉ››? የሚል ነበር፡፡ መልስ ለመስጠት የሞከሩት የሶማሌ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲው (ሶሕዴፓ) ተወካይ አምባሳደር ሙሐመድ ድሪር በሶማሊኛ ቋንቋ አንድ አባባል ተናገሩ፡፡ ራሳቸው በአማርኛ ተረጎሙት፡፡ ትርጉሙም ‹‹መሬት የፈጣሪ እንጂ የሰው አይደለም›› የሚል፡፡ በመሆኑም የድሬዳዋ መሬት የአላህ እንጂ የሶማሊያ ወይም የኦሮሞ አይደለም እንደማለት ነው፡፡

  ድሬዳዋ በፌዴራል ሥር እንድትተዳደር ለማድረግ አዋጅ የወጣው (አዋጅ ቁጥር 416/1996) የከተማዋ አስተዳደር ላይ በሶማሌዎችና በኦሮዎች መካከል በተነሳው የይገባኛል ጥያቄ መሠረት ነው፡፡ ጭንቀቱ በወቅቱ አዋጁ ከመውጣቱ በፊት ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ይደረግ ቢባል ኖሮ የኦሮሚያ ጨፌ ወይም የሶማሌ ምክር ቤት ከክልሉ ላይ ተቀንሶ ለፌዴራል ይሰጥ ሲባል አዎንታዊ ምላሽ ሊሰጡ  ይችል ነበር ብሎ ማሰብ አንድ ሰው የራሱን ጥቅም አሳልፎ ለመስጠት በፈቃደኝነት ምንም ቅር ሳይለው ይወስናል ብሎ እንደማሰብ ነው፡፡ ይሁን እንጂ አዋጁን ማጽደቅ ከተቻለ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻልም፣ ቅያሜ ሊፈጥር ቢችልም፣ ሁሉን ማድረግ ብዙም አይሳነው ለነበረው ለአውራ ፓርቲው (ኢሕአዴግ)፣ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል አይችልም ነበር ማለት ይከብዳል፡፡

  ደርግ ወደ መጨረሻ ዘመኑ መዳረሻ ላይ ራስ ገዛዊ ክልል ሲያቋቁም አንዷ ድሬዳዋ እንደነበረች እናስታውሳለን፡፡ በዋናነትም የኢሳና ጎርጉራ ጎሳዎች እንዲያስተዳድሯት ነበር፡፡ ይህ የደርግ አወቃቀር ዘላቂ መፍትሔ ባለማምጣቱ ሌላ ችግር ፈጥሯል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብን ፍላጎት በተገቢው ሁኔታ ባለማካተቱ፡፡  አሁንም የድሬዳዋ የፌዴራል ከተማ አስተዳደርነቷ ለተፈጠረው የይገባኛል ጥያቄ ጊዜያዊ መፍትሔ ተደርጎም ሊወሰድ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ በወቅቱ የተደረገው ጊዜያዊ የፖለቲካ መፍትሔ ነው፡፡ ተቀባይነት ያለው ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ማስያዝ ግን ያስፈልጋል፡፡ ከላይ ከኦፌዴን ተወካይ ጥያቄም ይሁን ከአምባሳደር ሙሐመድ ድሪር መልስ ብዙ ነገር መረዳት ይቻላል፡፡ አሁንም ያላለቀ የድንበርና የይገባኛል ስሜት መኖሩንም እንረዳለን፡፡ 

  ሌላው ጥያቄ

  1983 ዓ.ም. ጀምሮ ድሬዳዋ በሶማሌ ወይም በኦሮሚያ ክልል ሥር ትካለል የሚለው መልስ ሳያገኝ ቀጥሏል፡፡ በየትኛው ክልል ትካለል የሚለው መልስ ሳያገኝ ሌላ ጥያቄም ተነሳ፡፡ የድሬዳዋን አስተዳደር ላይ ተግባራዊ የተደረገው ወይም ልማድ የሆነው 80 በመቶ ኦሮሞና ሶማሌ ሥልጣን እንዲጋሩ ቀሪውን ሌሎች ብሔሮች እንዲወከሉበት የሚያደርገው አሠራርን ፍትሐዊነት የጎደለው ነው በሚል ቅሬታ እየተሰማ ነው፡፡

  ሁለትና ከዚያ በላይ ብሔሮች በሚገኝባቸው አገሮች የተለያዩ መሥፈርቶችን በመጠቀም የሥልጣን መጋራት ስልትን ተግባራዊ ማድረግ የተለመደ ነው፡፡ አሠራራቸውንም በሕግ የሚወስኑ እንዳሉት ሁሉ በፖለቲካዊ ድርድር በየጊዜው የሚወስኑ አሉ፡፡ የድሬዳዋ ሁኔታ ሥልጣንና ውክልና ድልድሉ በሕግ ሳይሆን በልማድ ተግባራዊ የሆነ ነው፡፡ እስኪ ይህ የ40-40-20 ድልድል ከብሔሮች ሕዝብ ቁጥር አንፃር ምጥጥኑን እንመለከት፡፡ የድልድሉን ፍትሐዊ መሆን ወይም አለመሆን ለመገንዘብ ይረዳል፡፡

  1987 ዓ.ም. በተካሄደው ሕዝብና ቤት ቆጠራ መሠረት የድሬዳዋ ሕዝብ ብዛት 251,864 ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ የከተማው 173,188 ሲሆን፣ የገጠሩ ደግሞ 86,769 ነው፡፡ 48 በመቶ ኦሮሞ፣ 27 በመቶ አማራ፣ 13.9 በመቶ ሶማሌ፣ 4.5 በመቶ ጉራጌ ነው፡፡

  1999 ዓ.ም. በተካሄደው ሕዝብ ቆጠራ ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳዳር አጠቃላይ ሕዝብ የብሔር ስብጥሩን በስሱ እንቃኘው፡፡ በዚህ ቆጠራ መሠረት የድሬዳዋ አስተዳደር ሕዝብ 342 ሺሕ ገደማ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ 233.2 ሺሕ የከተማ፣ 108.6 ሺሕ ደግሞ የገጠር ነዋሪ ነው፡፡

  ከጠቅላላው የድሬዳዋ ነዋሪ መካከል ኦሮሞ 157 ሺሕ (46 በመቶ)፣ ሶማሌ 83 ሺሕ (24.3 በመቶ)፣ አማራ 69 ሺሕ (20.2 በመቶ)፣ ጉራጌ 15.5 ሺሕ (4.7 በመቶ)  ትግሬ 4.2 ሺሕ (1.2 በመቶ)፣ ሐረሪ 3.7 ሺሕ (1 በመቶ) ይሆናል፡፡ በድሬዳዋ የሚኖሩ በደቡብ ክልል የሚገኙ ብሔሮች በጠቅላላው 7 በመቶ ይይዛሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ ኦሮሞና ሶማሌ በአንድ ላይ 70.4 በመቶ ይሆናል፡፡

  ከድሬዳዋ አስተደዳር ሕዝብ 108.6 ሺሕ በገጠር የሚኖር ሲሆን፣ የጠቅላላውን 31.8 በመቶ ይይዛል፡፡ በቁጥር ካየነው ኦሮሞ 80 ሺሕ ገደማ፣ ሶማሌ 28 ሺሕ በመሆን እንደቅደም ተከተላቸው ከገጠሩ ነዋሪ 73.4 በመቶ ኦሮሞ (ከጠቅላላው ነዋሪ አንፃር 23.4 በመቶ)፣ 26 በመቶ ደግሞ ሶማሌ (ከጠቅላላው ነዋሪ አንፃር 8.3 በመቶ) ነው፡፡  በገጠር የሚኖረው አማራ 234 ነው፡፡

  የከተማውን ነዋሪ ብቻ በመውሰድ የብሔር ስብጥሩን ካየነው ደግሞ ከ233.2 ሺሕ ውስጥ ኦሮሞ 77 ሺሕ (33 በመቶ)፣ አማራ 69 ሺሕ (29.5 በመቶ)፣ ሶማሌ 55 ሺሕ (23.6 በመቶ)፣ ጉራጌ 15.5 ሺሕ (6.7 በመቶ)፣ ትግሬ 4.2 ሺሕ (1.7 በመቶ)፣ ሐረሪ ደግሞ 3.7 ሺሕ (1.6 በመቶ) ይሆናል፡፡

  ከላይ የተገለጸውን መረጃ በመንተራስ ይህንን ‘40-40-20’ በመቶ ክፍፍል በመፈተሽ ቢያንስ የሚከተሉትን ትዝብት ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ የመጀመሪው፣ የኦሮሞና ሶማሌ በጥምር 70.4 በመቶ ስለሚሆን ከሌሎች ብሔሮች 9.6 በመቶ ወስደዋል፡፡ የአማራ ሕዝብ ብዛት 20.2 በመቶ ስለሆነ ቀሪው 9.4 ሌሎች ብሔሮች የሚኖራቸው ውክልና ነው፡፡ ስለሆነም አማራ ብቻውን 20 በመቶ የሚሆን ከአስተዳደሩ ውስጥ ውክልና ሊኖረው ይገባል እንደማለት ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ፍትሐዊነቱ ላይ ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀሬ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡

  ሁለተኛው ትዝብት፣ ድሬዳዋ አስተዳደር ላይ መንግሥት ለመመሥረት ኢሕአዴግ ራሱን ችሎ፣ እንደ አንድ ድርጅት አለመቆሙንም እንረዳለን፡፡ እንደውም ኦሕዴድ (የአሁኑ ኦዴፓ) ከኢሕአዴግ ተነጥሎ ከሶማሌ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሶሕዴፓ) ጋር ጥምር የሚመስል አሠራር ይከተላል ማለት ነው፡፡ ኢሕአዴግ የአዲስ አበባ አሠራሩን ቢከተል ኖሮ ኦሕዴድ፣ ብአዴን፣ ሕወሓትና ደኢሕዴን በአንድነት ከሃምሳ በመቶ በላይ መቀመጫ ስላገኙ መንግሥት መሥርተው ለሶሕዴፓ ግን ፍትሐዊ ነው ያሉትን ያህል ካቢኔ ላይ ማጋራት ነበር ለወትሮው ተገቢ የሚመስለው፡፡ ይሁን እንጂ ድሬዳዋን በሚመለከት ኦሕዴድ አብሮ አባል ከሆነበት ኢሕአዴግ አባላት ውጭ የግንባሩ አጋር ፓርቲን በመምረጥ በጥምረት እያስተዳደሩ ነው ማለት ነው፡፡ ይኼንን አካሄድ ሌሎቹ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ተቃውመዋል ማለት ግን አይደለም፡፡ እንደውም ተስማምተው እንጂ፡፡ ለማንኛውም የተለመደ የፓርቲ አሠራር አይደለም፡፡

  ሦስተኛው ትዝብት ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር የከተማና የገጠር የቀበሌ ምክር ቤቶችና ተሿሚዎችን የሚመለከት ነው፡፡ የገጠር ቀበሌዎቹ ኦሮሞና የሶማሌ ብሔሮች ተዋላጆችን ነው የሚመለከተው፡፡ እንደየቀበሌው ሁለቱም ብሔሮች ከሞላ ጎደል በተለያዩ ቀበሌዎች ስለሚኖሩ ለውክልናም ለሹመትም ብዙም አስቸጋሪ አይደለም፡፡ የከተማ ቀበሌዎችን በሚመለከት ግን ከተወሰኑ ሰፈርና ቀበሌዎች በስተቀር ስብጥሩ ከፍ ያለ ስለሆነ አንድ ብሔር ብቻውን የሚወከልበትም የሚሾምበትም ቀበሌ አይኖርም፡፡ በጥቅሉ የከተማውን በቀበሌ ደረጃ (እንደየቀበሌው ነዋሪ ሊለያይ ቢችልም) ኦሮሞ 33 በመቶ፣ አማራ 29.5 በመቶ፣ ሶማሌ 23.6 በመቶ፣ ጉራጌ 6.7 በመቶ (ደኢሕዴንን በአንድነት 7 በመቶ) ውክልናም ሹመትም ሊኖራቸው ይገባ ነበር፡፡

  ቻርተሩ አንቀጽ አሥራ ዘጠኝ ላይ የከተማውን የሕግ አስፈጻሚ አካል እንዴት መደራጀት እንዳለበት ሲገልጽ፣ ‹‹በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ያለው የፖለቲካ ድርጅት ወይም ከሌላ ጋር በጣምራ በመሆን አስፈጻሚውን አካል ያደራጃል፤›› በማለት  ተደንግጎ እናገኛለን፡፡ ድሬዳዋን በሚመለከት ኦሕዴድ ከሶሕዴፓ ጋር በጥምረት አስተዳደሩን ያደራጃሉ ማለት ነው? ወይም ደግሞ ሶሕዴፓ አብላጫ መቀመጫ አግኝቶ ኦሕዴድን መረጠ ነው የሚባለው? ከግንባሩ (ከኢሕአዴግ) አንዱን አባል ነጥሎ  (በግምባሩ ውስጥ እያለ) ሌላ ጥምረት መፍጠር ይቻላልን? 

  እዚህ ላይ ከግምት መግባት ያለበት ከኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅት ውጭ የቀበሌም ይሁን የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት ላይ መቀመጫ ያለው ሌላ ፓርቲ ስለሌለ ነው፡፡ በተጨማሪም የኢሕአዴግ አባል ሆኑ አጋር ድርጅቶች ከሚወክሉት ብሔር አንፃር የምክር ቤት መቀመጫና የሹመት ቦታ ቢጠይቁና ቢደራደሩ በሚል መነሻነት ነው፡፡ እንደ ቀበሌው የብሔር ስብጥርም የየብሔሮቹ የመቶኛ ድርሻ ሊለዋወጥ እንደሚችልም እንዲሁ የታወቀ ነው፡፡

  አራተኛው ትዝብት የገጠር ቀበሌዎችን ወደ ከተማ አስተዳደሩ ማካለል ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የገጠር ቀበሌዎችን በተለያዩ ገፊ ምክንያቶች ወደ ከተማ አስተዳደር ሊካለሉ ይችላሉ፡፡ ለከተማውም ለገጠሩም ሕዝብ (ብሔር፣ ሃይማኖት ወዘተ ሳይለይ) የሁለቱንም የእርስ በርስ ተጠቃሚነት ለማማሻል፣ የኑሮ ሁኔታን ለማበልጸግ ወዘተ ሲባል ሊካለሉ ይችላሉ፡፡ አስተዳደር ምቹነትም እንዲሁ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ሆኖ የከተማው ነዋሪ የብሔር ስብጥሩ ከላይ የተገለጸው ሆኖ፣  የገጠር ቀበሌዎችን ወደ አስተዳደሩ ሲካተቱ የሚያስከትላቸው ለውጦች አሉ፡፡ ዋናውና ተቀዳሚው ፖለቲከኞች ለምርጫና ለውክልና ሲሉ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ መሠረታቸውን ለማጠናከር የአስተዳደር ወሰኖችን ይለዋውጣሉ፡፡

  ይኼ ዓይነቱ ለፖለቲካዊ ፋይዳ፣ በተለይም ለምርጫና ለውክልና ሲባል፣ የሚደረግ አስተዳደራዊ ድንበርን በመለዋወጥ ግብን ለማሳካት የሚደረግ ሲሆን ‘ጀሪማንደሪንግ’ (gerrymandering) በመባልም ይታወቃል፡፡ ለከተማ ምክር ቤቶች ለመመረጥ ከከተማ ውጭ (በአብዛኛው የከተማ ዙሪያ የሆኑ የገጠር ቀበሌዎች) ያሉ አካባቢዎችን ከሃያ እስከ ሃያ አምስት በመቶ ድርሻ እንዲይዙ የሚያደርጉ አዋጆችን የተወሰኑ ክልሎች (ለምሳሌ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ደቡብና ኦሮሚያ) አሉ፡፡ በከተሞች ዙሪያ የሚኖረውን ብሔር በከተማው መራጭና ተመራጭ ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ አስቀድሞ በማስላት የወጡ ሕግጋትና አሠራር ይመስላሉ፡፡ ስለሆነም የድሬዳዋም ሁኔታ ከዚሁ ጋር አብሮ የሚሄድ ይመስላል፡፡ በ1987ቱ ሕዝብና ቤት ቆጠራ የሶማሌ ሕዝብ 14 በመቶ ገደማ የነበረ ሲሆን፣ በ1999ኙ ወደ 24.3 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡

  የቻርተሩ ድንጋጌዎችና አተገባበሩ አልተገናኝቶነት

  የድሬዳዋ አስተዳደር ቻርተር (አዋጅ ቁጥር 416/1996) በመግቢያውና በዚያም ባለፈ ወደ ውስጥ ዘለቅ በማለት አዋጁን ለተመለከተው ሰው አዋጁ ላይ ከሰፈረው የራቁ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡ በመግቢያው አራተኛው ‘ፓራግራፍ’ ‹‹ለድሬዳዋ ነዋሪ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሥልጣን መስጠት አስፈላጊ ስለሆነ›› ይህንኑ አሠራር ዋስትና መስጠት የአዋጁ አንዱ ግብ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

  ራስን በራስ የማስተዳደር ሥልጣኑን ዕውቅና የተሰጠው ለነዋሪው ነው፡፡ ነዋሪው የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አባላትን በመምረጥ፣ ከዚያም ያለምንም የብሔርና ሌሎች ማኅበራዊ መሠረቶችን መነሻ በማድረግ ልዩነት ሳይደረግ በእኩል የመወከል የመሾም ዕድል እንዲኖር በማድረግ ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ ለማስቻል የሚያግዝ ዋስትና የሚሰጥ ሕግ ማስፈለጉን አዋጁ በመግቢያው ላይ ገልጿል፡፡ በመቀጠልም  ‹‹የከተማ አስተዳደር አደረጃጀቱንም ከዴሞክራሲና ከመልካም አስተዳደር መርሆዎች ጋር የተጣጣመ እንዲሆን በሕግ መወሰን በማስፈለጉ›› ጭምር ነው ቻርተሩ ይወጣ ዘንድ ምክንያት ከሆኑት አንዱ፡፡

  አዋጁ አንቀጽ ስምንት ንዑስ ቁጥር አንድ ላይ የከተማ አስተዳደሩን ዓላማ ሲያስቀምጥ ማኅበራዊ ትስስር (social harmony) የተረጋገጠባት ከተማ ማድረግ ወሳኝ ዓላማ ነው፡፡ በዚሁ አንቀጽ ንዑስ ቁጥር ሁለት ላይ ‹‹ነዋሪዎቹ የከተማዋን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ የሚወስኑባት›› ማድረግ እንዲሁ ተጨማሪ ግብ ነው፡፡ ብሔር ብሔረሰቦች በእኩልነት የሚኖሩባት ከተማ መሆኗን መረጋገጥም የከተማው አስተዳደር ግዴታ እንደሆነ አዋጁ ይገልጻል፡፡ እነዚህ የከተማ አስተዳደሩ ከሚመራባቸው ዓላማዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

  ሌሎች ሕጎችም ይሁኑ አሠራሮችን እነዚህን ዓላማዎች ለማሳካትና ዕውን በማድረግ እገዛ የሚያደርጉ በእነዚህ ዓላማዎች የተቃኙ ሊሆኑ ይገባቸዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ተግባራዊ ያደረገው ከእነዚህ ዓላማዎች በአንፃሩ በማስቀመጥ ቢገመገሙ ለዓላማዎቹ አለመሳካት ደንቀራ እንጂ አሳላጭ ናቸው ለማለት አያስደፍርም፡፡ እነዚህ ዓላማዎች የሕገ መንግሥትም የዴሞክራሲም መርሆዎች  ናቸው፡፡

  ድሬዳዋ የፌዴራሉ መንግሥት ዋና ከተማ አይደለችም፡፡ ራሷንም የቻለች ክልል አይደለችም፡፡ እንደውም የፌዴራሉ መንግሥት አካል እንደሆነች የተቋቋመችበት ቻርተር አንቀጽ ሃምሳ አንድ ላይ ተደንግጓል፡፡ በተወሰነ መልኩ (በቻርተሩ የተፈቀደውን ያህል) ራስ ገዛዊ ሥልጣን ቢኖራትም የፌደራሉ መንግሥት አካል በመሆኗ ተጠሪነትም አለባት፡፡ ስለፌዴራሉ መንግሥት ሆኖ የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርን የሚከታተለው የአቅም ግንባታና ድጋፍ አገልግሎት የሚሰጠው የቀድሞው የፌዴራል ጉዳዮች የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ የሰላም ሚኒስቴር ነው፡፡ እንደውም የከተማ አስተዳደሩን ዕቅዱን፣በጀቱን፣ የከተማውን አጠቃላይ ሁኔታ በሚመለከት ዓመታዊና ወቅታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለዚሁ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ማቅረብ ግዴታ እንዳለበት አንቀጹ ላይ ሰፈሮ እናገኘዋለን፡፡

  ስለሆነም ይህ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ድሬዳዋን በሚመለከት አሠራሮች ሲበላሹም እንዲታረሙ አላደረገም ወይም እንዲበላሹ በዝምታ አልያም በይሁንታ ድጋፍ አድርጓል ማለት ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ከላይ በተደጋጋሚ ያነሳነውን 40-40-20 የሚባለውን አሠራር፡፡ ሌላው ሳይነሳ መታለፍ የሌለበት ጉዳይ የከተማ አስተዳደሩ በፀጥታም ይሁን በሌሎች የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ምክንያት የሕግና ሥርዓት መናጋት ቢፈጠር፣ የሕዝብ ደኅንነት አደጋ ላይ ቢወድቅ የፌዴራል ድርጅቶችን (ፖሊስ፣ መካላከያ ሠራዊት ወዘተ) ወደ ድሬዳዋ በቀላሉ ማስገባት ይችላል፡፡ ለሌሎች ክልሎች የተቀመጡት ቅድመ ሁኔታዎች ተፈጻሚ አይሆኑም ምክንያቱም የፌዴራሉ መንግሥት አካል ስለሆነች፡፡

  ለማጠቃለል ያህል ዴሞክራሲ ነባርና ቀጣይነታቸው የማይቀሩ ጥያቄዎችን ወቅቱን በሚመጥን መልኩ መፍትሔ መሻትን ይጠይቃል፡፡ ለተመሳሳይ ጥያቄ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ መልሶች ሊሰጥም ይችላል፡፡ ትክክለኛነታቸው የሚለካውም በወቅቱ ሚዛን ነው፡፡ ጥያቄው አንድ ሆኖ መልሱ እየተለያየ ሊቀጥል ይችላል፡፡ የማይነካ የሚመለክ መፍትሔ የሆነ ለዴሞክራሲ አይሠራም፡፡

  ስለሆነም ለድሬዳዋ በአንድ ወቅት በቅን ልቦና መፍትሔ ይሆናል ብለው በወቅቱ ያበጁት መፍትሔ አሁን ላይ መፍትሔ አለመሆን ብቻ ሳይሆን ጥያቄም ሊሆን ይችላል፡፡ የቅን ልቦና በማጣት የተተገበረም ከሆነ አሁንም ቢሆን ለማስተካከል መሞከር ነው፡፡ የቀድሞው መፍትሔ አሁንም አዋጭና ተገቢ ከሆነም ሕዝባዊ ይሁንታ ሊያገኝ የሚችልበትንና ሕገ መንግሥታዊ ስለመሆኑም ፍተሻ ማድረግ ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ካልሆነም አይጸናም፡፡ ሕዝቡም ይሁንታ ከነፈገው እንዲሁ፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

   

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...