Sunday, February 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉበውጭ ኢንቨስትመንት ስም የታዳጊዎች ደኅንነትና የማኅበረሰቡ ጤና ለሽያጭ እንዳይቀርብ ፓርላማው ጥበቃ ያድርግ

በውጭ ኢንቨስትመንት ስም የታዳጊዎች ደኅንነትና የማኅበረሰቡ ጤና ለሽያጭ እንዳይቀርብ ፓርላማው ጥበቃ ያድርግ

ቀን:

በደረጀ ሽመልስ

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ታኅሳስ 2 ቀን 2011 ዓ.ም. የምግብና መድኃኒት አስተዳደር ረቂቅ አዋጅን መርምሮ ለቋሚ ኮሚቴ መመራቱ የሚታወስ ሲሆን፣ የሚመለከታቸው ኮሚቴዎችም ረቂቁን የሚደግፉና የሚቃወሙ ባለድርሻ አካላትን ጨምሮ ብዛት ካላቸው ድርጅቶች ጋር ሰፊ የሆነ ውይይት አድርገዋል፡፡ ረቂቁ በተለይ ከአልኮል መጠጥ ማስታወቂያና ከትምባሆ ምርት ቁጥጥር ጋር በሚያያዝ ከአምራቾች፣ ከተወሰኑ ነጋዴዎች፣ እንዲሁም ጥቅማችን ይጎዳል ከሚሉ ሌሎች አካላት በኩል ጠንከር ያለ ተቃውሞ እያስተናገደ ይገኛል፡፡

ትምባሆ፣ ከትምባሆ ተያያዥ የሆኑ ምርቶችና የአልኮል መጠጦች ለጤና ምን ያህል ጠንቅ እንደሆኑ፣ በዓለም በየዓመቱም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት እየቀጠፉ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን፣ በአገራችን የሚታየው ከልክ ያለፈ የአልኮል መጠጥ ማስታወቂያ እንዲሁም ደካማ የሆነ የትምባሆ ቁጥጥር አሠራር ጠንካራ በሆነ የቁጥጥር ሕግ እንዲደገፍ የቀረበ ረቂቅ ነው፡፡ ረቂቁ በዋናነት ከከለከላቸው ጉዳዮች መካከል ማንኛውም የአልኮል መጠጥ በቴሌቪዥንና ሬድዮ ማስተዋወቅን፣ የአልኮል መጠጥን ከሎተሪ ዕጣ ጋር በማንኛውም መንገድ በማያያዝ የሚደረግ የማስተዋወቅ ተግባርን፣ የአልኮል መጠጥ ከ21 ዓመት በታች ለሆኑ ሰዎች መሸጥን፣ እንዲሁም የአልኮል ይዘቱ ከአሥር በመቶ በላይ የሆነ መጠጥ ነጋዴ የሕዝብና የመንግሥት በዓላትና ስብሳባ፣ የንግድ ትርዒት፣ የስፖርት ውድድር፣ የትምህርት ቤት ዝግጅትና ሌሎች ወጣት የሚሳተፉበትን ኩነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋወሪ ስፖንሰር ማድረግ ይጨምራል፡፡

ትምባሆን በሚመለከት ረቂቁ በዋናነት ታዳጊዎችን ከትምባሆ ሱሰኝነት ለመከላከል ከከለከላቸው ጉዳዮች መካከል የሺሻ ምርቶች፣ የኤሌክትሮኒክ ኒኮቲን መስጫ መሣርያ ወይም ሌላ ከሲጋራ ጋር ተመሳሳይ የሆነ የቴክኖሎጂ ምርትና ልዩ ማጣፈጫ የያዘ የትምባሆ ምርት ይገኙበታል፡፡ በተጨማሪም የትምባሆ ምርት የውጭ ማሸጊያ የጤና ማስጠንቀቂያ በትምባሆ ምርት የውጭ ማሸጊያ በእያንዳንዱ የፊትና የኋላ ገጽ ከ70 በመቶ ያላነሰ ቦታ የሸፈነ መሆን እንዳለበት፣ በችርቻሮ ሱቆች ውስጥ ትምባሆ መቀመጥ ወይም መደርደር ያለበት ሸማቹ በቀጥታ በእጁ ሊያነሳው ወይም በዓይኑ ሊመለከተው በማይችልበት ሁኔታ መሆን እንዳበት ይደነግጋል፡፡

ረቂቅ ሕጉ በተለይ ከትምባሆና ከአልኮል ኢንዱስትሪ ጣልቃ ገብነት ተጠብቆ በዋናነት ወደ 50 ሚሊዮን የሚጠጉ ዕድሜያቸው 15 እና ከዚያ በታች የሆኑ ኢትዮጵያዊ ሕፃናትንና ታዳጊዎችን የሚጠብቅ ጠንካራ ሕግ ሆኖ እንዲፀድቅ ያገባናል የሚሉ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የሚድያ ባለሙያዎችና በዘርፉ የተሰማሩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ጠንካራ የሆነ ድጋፋቸውን ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡ መንግሥትም ዜጎቻችን ከትምባሆና ከአልኮል መጠጥ ለመጠበቅ ጠንካራ ዕርምጃዎችን የመውሰድ የሞራልና የሕግ ኃላፊነት እንዳለበት ምክር ቤቱ ባዘጋጀው ሁለት የሕዝብ አስተያየት መድረክ ላይ አንስተዋል፡፡  

በሌላ በኩል ረቂቅ ሕጉን ለማዳከም፣ እንዲሁም ሕጉን ለማዘግየት የአልኮል መጠጥና የትምባሆ ኢንዱስትሪዎች የተለያዩ ስልቶችን በመንደፍና እንቅፋቶችን ለመፍጠር እየሞከሩ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የትምባሆና የአልኮል አምራች ኩባንያዎች ጠንካራ የቁጥጥር ሕግ ተግባራዊ ካደረጉ ያደጉ አገሮች ዓይናቸውን ዝቅተኛ ቁጥጥር በሚደረግባቸው የአፍሪካ አገሮችና ሌሎች ታዳጊ አገሮች ላይ አድርገዋል፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች ቀጣይ መዳረሻቸው የሚሆን የአፍሪካ አገር ለመምረጥ እንደ መመዘኛ የሚጠቀሙት ዝቅተኛ የአጫሽ ወይም የአልኮል ተጠቃሚ ቁጥር ያለባቸውንና ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ያለበትን አገር ነው፡፡ ኢትዮጵያም ለእነዚህ ኩባንያዎች ምርጥና አዋጭ መዳረሻ ነች፡፡ ለዚሁም ማሳያ በመንግሥት ባለቤትነት ሥር የነበሩ የቢራና የትምባሆ ድርጅቶች ለመግዛት ያወጡት የገንዘብ መጠን ትልቅ ነው፡፡

ከዚህ ጋር በሚገናኝ በዋናነት እየቀረቡ ካሉ መከራከሪያዎች ውስጥ ረቂቅ ሕጉ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን የሚያሰናክል ነው የሚል ሲሆን፣ የመንግሥት ተቀዳሚ ዓላማ የማኅበረሰብን ጤናና ደኅንነት ከመጠበቅ ያለፈ እንዳልሆነና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን የመሳብ ጉዳይ ከሕዝብ ጤናና ከታዳጊዎች ደኅንነት ጋር ሳይጣረስ አጣጥሞ መሄድ እንዳለበት ሊሰመርበት ይገባል፡፡ የጤና ሚኒስቴሩ ክቡር ዶ/ር አሚር አማንም ፓርላማው ባዘጋጀው የሕዝብ አስተያየት መድረክ ላይ ተያያዥ የሆነ ጥያቄ የመለሱት፣ የኢኮኖሚ ጥቅም የኅብረተሰብን ጤናና የታዳጊዎችን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል ከሆነ ቀይ መስመር ነው የሚል ነበር፡፡ በመሠረቱ የኅብረተሰብ ጤና ቁጥጥር የሚሠራ የመንግሥት አካል የትምባሆን ምርትን ከሚያመርትና ከሚሸጥ አካል፣ እንዲሁም ጠንካራ ገደብ እንዳይጣል ከሚከራከሩ ከተወሰኑ የአልኮል አምራቾች ጋር ያለው ፍላጎት የማይታረቅ (irreconcilable interest) መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡

በተለይ የትምባሆ ኢንዱስትሪው አገሮች የሚያወጡት የቁጥጥር ሕጎችን ለማዘግየት ካልሆነም ድንጋጌዎችን ደካማ ለማድረግ በዓለም ዙሪያ የሚጠቀሙበትን መከራከሪያዎች አሳሳች፣ በእጅጉ የተጋነኑና ትክክል እንዳልሆኑ የሚያስረዱ ማስረጃዎች በብዛት ይገኛል፡፡ መንግሥት በብሔራዊ ትምባሆ ውስጥ ያለውን ቀሪ የባለቤትነት ድርሻ ከዓመት በፊት መሸጡ የትምባሆ ቁጥጥር ሕግን ሙሉ ለመሉ ለመተግበር የሚያግዝ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት መንግሥት ከድርጅቱ መውጣቱ ሥነ ምግባርንና ሕግን የጠበቀ የትምባሆ ምርት ግብይት እንዳይኖርም ከፍተኛ ዕድል ይፈጥራል፡፡ አገራችን ለረጅም ጊዜ በአንፃራዊ ሁኔታ አነስተኛ የትምባሆ ተጠቃሚ ምጣኔ እንዲኖራት ካደረጉ ዋና ዋና ምክንያቶች ድርጅቱ በመንግሥት ባለቤትነት ስለነበር፣ ዜጎች ላይ በማነጣጠር ለትርፍ ብቻ የማይሠራ መሆኑን መገንዘብ የሚያዳግት አይደለም፡፡ አሁን ያለንበት ጊዜ በእጅጉ የተለየ ነው፡፡ መንግሥት የሕዝብን በተለይም የታዳጊዎችንና ወጣቶችን ጥቅም ማስጠበቅ የሚችለው ጠንካራ በሆነ የቁጥጥር ሕግ ብቻ ነው፡፡

ሁለተኛው መከራከሪያ ረቂቁ ሕግ ሆኖ የሚወጣ ከሆነ የመንግሥት ገቢ ይቀንሳል፣ በአልኮል አምራቾችም የሚደገፈው ስፖርት ይዳከማል የሚል ነው፡፡

የኅብረተሰብ ጤና መጠበቅና ታዳጊዎችን ከትምባሆና ከአልኮል መጠበቅ ከኢንዱስትሪው ገቢ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑ በማንኛውም መመዘኛ ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡ በተያያዥ በትምባሆና በአልኮል መጠቀም ምክንያት በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚደርሰው ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ጉዳትና ጫና፣ በብዙ እጅ ከንግድ ጋር በሚያያዝ መንግሥት በተለያዩ መንገዶች የሚገኘው ግብርና ገቢ ሊበልጥ ይችላል የሚል መከራከሪያም ባለሙያዎች ያቀርባሉ፡፡ በተለይ በትምባሆ ምክንያት ለሚደርስ የጤና ችግርና ያለጊዜ ከሚደርስ ሕልፈት ጋር የሚወጣው ወጪ እጅግ ከፍተኛ መሆኑ አከራካሪ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ያህል በዓለም ላይ በትምባሆ ምክንያት የሚደርስ የኢኮኖሚ ጫና ከአንድ ትሪሊዮን ዶላር በላይ ሲሆን፣ ለጤና አገልግሎት የሚወጣው ወጪ ደግሞ ከአጠቃላይ የጤና ወጪ 5.7 በመቶ ነው፡፡

ረቂቁና ስፖርትን በሚመለከት አሳሳች ሊሆን የሚችል መከራከሪያም እየቀረበ ይገኛል፡፡ በመሠረቱ ረቂቁ የቢራ ፋብሪካዎችና የአልኮል ይዘቱ ከአሥር በመቶ በታች የሆነ አልኮል አምራች፣ አስመጪ ወይም አከፋፋይ የስፖርት ውድድርን ወይም ስፖርትን ስፖንሰር ማድረግ አይከለክልም፡፡ ረቂቁ የሚከለክለው ከአሥር በመቶ በላይ በሆነ አልኮል መጠጥ አምራቾች እንዳይደገፍ ነው፡፡ በውስኪና በቮድካ አምራቾች ስፖርቱ ይደገፍ የሚል ተከራካሪ ያለ ስለማይመስለኝ ይህ ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡   

ሌላው ዋነኛ መከራከሪያ በአሁኑ ጊዜ ከ44 በመቶ በላይ ሕገወጥ የትምባሆ ንግድ እንዳለና ረቂቁ የሚጠቅመው የሕገወጥ ነጋዴዎችን እንደሆነ የትምባሆ አምራቹ ይገልጻል፡፡ ሆኖም ግን ገለልተኛ በሆነ ተቋም በተሠራ ጥናትና በዚህ ወር ይፋ በተደረገ ጥናት መሠረት፣ የአገሪቱ የሕገወጥ የትምባሆ ንግድ ከ19 በመቶ በላይ እንደሆነና እጅግ በብዛት የሚገኘው በሶማሌ ክልልና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እንደሆነ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው የትምባሆ ኢንዱስትሪው ሆን ብሎ ሕግ አውጪዎችን ለማስፈራራት ወይም ለማስደንገጥ ብዛት ባላቸው አገሮች እንደታየው ሁሉ፣ የሐሰት መረጃና ጥናት እንደሚያቀርብ ነው፡፡

ከመረጃው አሳሳችነት በተጨማሪ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከፍተኛ የሕገወጥ ንግድ የሚኖረው ደካማ የሕግ ማስፈጸም፣ ዝቅተኛ የወንጀል መተላለፍ ክስ በሚመሠረትባቸው፣ የወንጀል ድንጋጌዎች ቀጪና አስተማሪ ባልሆነባቸውና ሙስና በተንሰራፋባቸው ሁኔታዎች ነው እንጂ ረቂቁ ባስቀመጣቸው የትምባሆ ቁጥጥር መሥፈርቶች አይደለም፡፡ የትምባሆ ቁጥጥር በሕገወጥ መንገድ የሚገኝን ትምባሆ ፍላጎት አይጨምርም፡፡ አገሮች የታክስ አስተዳደራቸውንና የሕግ አፈጻጸም በማጠናከር ችግሩን መፍታት ይችላሉ፡፡ በችርቻሮ ሱቆች ውስጥም ትምባሆ መደርደር ያለበት በማይታይ ቦታ መሆኑ፣ ሕግ አስፈጻሚዎችን ሕጋዊውን ሕጋዊ ካልሆነው ምርት ለመለየት የሚቸገሩበት አይደለም፡፡  

በአሁኑ ጊዜ የገቢዎች ሚኒስቴርና የጉምሩክ ኮሚሽን በሕገወጥ ንግድ ላይ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እያሳዩ በመሆናቸው የሕግ ማስፈጸም አቅማቸውን እያሳደጉ እንደሆነ ከተለያዩ ሚዲያዎች፣ የወንጀል መተላለፍ ዕርምጃና የአስተዳደር ዕርምጃዎች በየቀኑ እየተመለከትን ነው፡፡

የሕዝብ ጥቅምን የሚያስጠብቅ ፐቢሊክ ፖሊሲና የሕግ ጉዳይ በገንዘብ የሚሸጥ ተራ ጉዳይ ሳይሆን፣ የምክር ቤቱ ጥበቃ የሚደረግለት እንደሆነ ከዚህ በኋላ ለሚመጡ የውጭ ኢንቨስተሮችም ማሳያ እንዲሆን ረቂቁን አዋጅ አድርጎ በማፅደቅ፣ የሕዝብ ውክልናውንና የሕግ አውጭነት ኃላፊነቱን እንደሚወጣ እተማመናለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የጤና ሕግ ባለሙያና አማካሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው malito:[email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በጦርነቱ የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ የመገንባቱ ውጥን

በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል በሦስት ዙር ተካሄዶ በነበረው ጦርነት ምክንያት...

በርካታ ሰዎችን እያጠቁ የሚገኙት የሐሩራማ አካባቢ በሽታዎች

ትኩረት የሚሹ የትሮፒካል /ሐሩራማ በሽታዎች በአብዛኛው ተላላፊ ሲሆኑ፣ በዓይን...

ስለአገር ኢኮኖሚ ማሰብ የነበረባቸው ጭንቅላቶች በማያባሩ ግጭቶች ተነጥቀዋል!

አገራችን ኢትዮጵያ ውጪያዊና ውስጣዊ ፈተናዎቿ መብዛት ብዙ ዋጋ እያስከፈላት...