በልዑልሰገድ ግርማ
በአብዛኛው በፖሊሲ ምርምርና ትንተና ላይ በማተኮር ለችግሮች መፍትሔ በመሻትና ምክር በመለገስ ሥራ ላይ የተሠማሩ ተቋማት አሰላሳይ ተቋማት (Think Tanks) ይባላሉ፡፡ እነዚህ ተቋማት የፖሊሲ ቀረፃ ጥራት ባለው መንገድ እንዲከናወን ለፖሊሲ አውጪዎች አዳዲስ አስተሳሰቦችንና አመለካከቶችን በማቅረብ ዴሞክራሲ፣ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ መስተጋብሮች ተስማሚ ወደ ሆነ ደረጃ እንዲያመሩና እንዲደርሱ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡ አሰላሳይ ተቋማት መንግሥታትን በውስጥና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች በዕውቀት ላይ የተመሠረተ የፖሊሲ ቀረፃና ውሳኔ አሰጣጥ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መርዳት አንዱና ዋነኛው ተግባራቸው ነው፡፡
በፖሊሲ ቀረፃ ሒደት የፖሊሲ ቀራጮችንና ባለድርሻ አካላትን በማገናኘት አዳዲስ ሐሳቦችንና መረጃዎችን እንዲለዋወጡ ሊያግዙ ይችላሉ፡፡ በሕዝቡ መካከል የሚገኙ መስተጋብሮችን በማጥናትና በመተንተን ለአጠቃላይ መንግሥታዊ አመራር ወይም ለተወሰኑ ሕዝባዊ ተቋማት የሚያገለግሉ የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦችን በመቀመር፣ ለሚመለከታቸው ማድረስ ዋነኛ ተግባራቸው ነው፡፡ በተመራማሪዎቻቸውና በመልዕክት አስተላላፊዎቻቸው አማካይነት የግንዛቤ ሥራንም ይከውናሉ፡፡ የተለያዩ ጉዳዮችን ከመተንተን ባሻገርም አገር የምትመራበትን የፖለቲካ ፍልስፍናና አካሄድም በመመርመር ጭምር፣ ሕጋዊነትንና ለውጥን ለማጠናከርም ይሠራሉ፡፡
ለአሰላሳይ ተቋማት ለሥራ አመቺ የሆነ የፖለቲካ ምኅዳር አስፈላጊ ነው፡፡ የፖሊሲ ውይይቶችና ክርክሮችን ለማካሄድም የማሰብንና የመግለጽን ነፃነት የሚያግዝ ምኅዳር ዋነኛ የሥራ ግብዓታቸው ይሆናል፡፡ የፖለቲካ ምኅዳር በጠበበ ሁኔታ የሚሠሩ አሰላሳዮች የማሰላሰያቸው ወርዱና ቁመቱ አምባገነናዊ ሥርዓቱን ለማገልገል ብቻ ስለሚውል፣ ሕዝብንና የፖሊሲ አውጭዎችን ለማገናኘት የሚያስችለውን የድልድይነት ተግባር ሊወጡት ቀርቶ ሊያሰላስሉትም አይችሉም፡፡ እንደነዚህ ዓይነት አሰላሳይ ተብዬዎች አዳዲስ ሐሳቦችን አያነሱም፣ አማራጭ አስተሳሰቦችን እንዲንሸራሸሩ አያደርጉም፣ የፖሊሲ አማራጮችንም አያቀርቡም፡፡ ከስም በቀር አሰላሳዮች ናቸው ማለትም አይቻልም፡፡ ለአሰላሳዮች መፈጠርና መኖር ምክንያት ዋነኛው መገለጫቸው የሆኑትን በመረጃና በማስረጃ ላይ የተመሠረተ ምርምርና ጥናት በግልጽ ካልተስተዋለ አሰላሳይነት ቦታ ሊሰጠው አይችልም፡፡
መንግሥት በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የማሻሻያና የለውጥ መስኮች እየተጋ ባለበት ወቅት የጎለመሱ አሰላሳይ ተቋማት ቢኖሩ በወደደ ነበር፡፡ ይኼንን የአሰላሳይ ተቋማትን እጥረት ለመሸፈን በጊዜያዊ አሰላሳይነት ሊጠቅሙ የሚችሉ አማካሪ ኮሚሽኖችን አቋቁሟል፡፡ ዘላቂና ውጤታማ የማሰላሰል ሥራ እንዲሠራ ግን ተቋማዊ ነፃነትን የተጎናፀፉና አገራቸውን በዕድገት ማማ ላይ ለማየት ራዕይ ያላቸው አሰላሳይ ተቋማት ያስፈልጉናል፡፡ ያኔ ኢትዮጵያ አንፃራዊ በሆነ የሥልጣኔ ማማ ደርሳ በነበረበት ወቅት የነበረና ዝናብና በሬን ሙጥኝ ያለ የአስተራረስ ዘዴን ተንተርሰን፣ ዓለም አራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ላይ በደረሰበት በአሁኑ ወቅት በዘር የፖለቲካ ጎዳና እንድንተራመስ ስንሆን አለማሰላሰላችንን ያሳብቅብናል፡፡ ሌላው ቀርቶ በዓድዋ ድል የተፈጠረውን አገራዊ መግባባትና መተማመን ማስቀጠል ሳንችል ቀርተን ማሰላሰልን ሳይሆን መናከስን ተቋማዊ ቅርፅ ሰጥተን ስንባላ መክረማችን፣ አሰላሳዮችን ጨምሮ የተቋማት ግንባታችን መስመር እንዳልያዘ ማሳያ ነው፡፡ በመሆኑም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የፖለቲካ የፓርቲ ዲሲፕሊን ባልዳበረበትና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት የማይችሉ የሕዝብ ተቋማት ባሉበት፣ ነገር ግን ለመለወጥ አዲስና እውነተኛ ተነሳሽነት ባለባቸው አገሮች ውስጥ የፖሊሲ አሰላሳዮች መኖር የግዴታ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርምርና የትንተና ዲፓርትመንት ሊኖራቸው ቀርቶ፣ ራሳቸው ለምርምና ለትንተና የተመቻቹ አይደሉም፡፡ የግሉ ሴክተርም ለዚህ እገዛ ሲያደርግ አይስተዋልም፡፡
አሰላሳይ ተቋማት የለውጥ ግፊት ሚናቸውን በሁለት ዋና ዋና መንገዶች ይወጣሉ፡፡ የመጀመርያና ዋነኛው በመረጃና በማስረጃ ላይ የተመሠረቱ የምርምር ሥራዎችን በመሥራት ግኝቶቹን በኅትመት ውጤቶች፣ በኮንፍረንሶችና የፖሊሲ ውይይት በማድረግ ለተጠቃሚዎች ማድረስ ሲሆን፣ ሌላኛውና ሁለተኛው ደግሞ በአንድ ጉዳይ ላይ ክርክር ማድረግ፣ የአቅም ግንባታና የሥልጠና ሥራ በመሥራት የፖሊሲ ለውጥ ግንዛቤን ለመፍጠርና ለማራመድ ይችላሉ፡፡
ምርምር የአሰላሳይ ተቋማት የጀርባ አጥንታቸው ከመሆኑ ባሻገር፣ የዕውቀታቸውና የሐሳብ አመንጪነታቸው መሠረት ነው፡፡ በዕውቀት፣ በመረጃና በማስረጃ ላይ የተመሠረተ የፖሊሲ ምክረ ሐሳብ የሚያቀርቡትም ከዚሁ ከምርምር ሥራቸው በመነሳት ብቻ ነው፡፡ የምርምር ግኝቶችን ለክርክርና ውይይት በማቅረብም አማራጭ የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦችን ያቀርባሉ፡፡ ክርክርና ለውይይት ፅንፍ የያዙ ወይም ተቃርኖ ያላቸውን አካላት በመረጃ፣ በማስረጃና በትንተና ወይም ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በማሳመንና ወደ አንድ አቅጣጫ በማምጣት ለአገራዊ ለውጥ አስተዋጽኦ የሚያደርጉበትን መንገድ ይፈልጋሉ ወይም ያመቻቻሉ፡፡ ተቃርኗዊ አካሄድ ያላቸውን አካላትም ገንቢ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ያግዛሉ፡፡
አሰላሳይ ድርጅቶች የምርምሮቻቸውንና የጥናቶቻቸውን ግኝቶች የፖሊሲ ተጠቃሚ ለሆነው የኅብረተሰብ ክፍል ማድረስ ለተፈጻሚነታቸው ወሳኝ ግብዓት ሊሆን ይችላል፡፡ አዳዲስ ሐሳቦችን በቀላሉ ለማስረፅ አዳጋች በሚሆንበት ጊዜም በውይይትና በማስረፅ ዘዴ ተቀባይነት እንዲኖር ማድረግም አለባቸው፡፡ የፖሊሲ ለውጦቹ የመንግሥትና የኅብረተሰብ ሆነው እንዲወጡም ማድረግ አለባቸው፡፡ ለዚህም ለምርምርና ትንተና ሥራ የተሰጡና በፖሊሲ የተቃኘ አስተዋጽኦ ለማበርከት የሚችሉ ባለሙያዎችን ማቀፍ ይኖርባቸዋል፡፡ አሰላሳይ ድርጅቶች ብቃት ያላቸውን የምርምርና የትንተና ባለሙያዎች ካልያዙ አንድ ጎምቱ የዲፕሎማሲ ባለሙያ እንዳሉት “የመኪና ማቆሚያ” ብቻ ነው የሚሆኑት፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ በሆኑ ችግሮች ታጥራና ተተብትባ ባለችበት ሁኔታ፣ የአሰላሳይ ተቋማት አለመኖር ወይም ያሉትም ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ሥራ አለመሥራታቸው እየጎዳት ይገኛል፡፡ ምክንያታዊና አመክኗዊ በሆነ ሁኔታ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ ከሊበራል ዴሞክራሲና ከሶሻል ዴሞክራሲ የትኛው ለኢትዮጵያችን እንደሚበጅ የተሰላሰለ ጉዳይ አይደለም፡፡ የመንግሥትን ሚና አጉልቶ በሚያሳየው የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብና የግል ሴክተሩን የጎላ ሚና በሚጠይቀው የሊበራል የኢኮኖሚ መርህ መካከል ያለው አካሄድ፣ በአሰላሳዮች ተመርምሮና ተተንትኖ አልቀረበልንም፡፡ በሃምሳዎቹና በስልሳዎቹ ተፀንሶ አሁን ጎልምሶ ያለው የብሔር ፖለቲካ እግሮቹ ሲሰነካከሉ ማስተካከያውን አሰላስለው አልነገሩንም፡፡ ማኅበራዊ ካፒታላችን ይኼንን መከላከል አቅቶት ለመንጋ ፖለቲካ እጁን ሲሰጥ ዝም ብለዋል፡፡ ግዙፍ ፕሮጀክቶቻችን ብሔራዊ መግባባት መፍጠር ተስኗቸው የሌቦች መናኸሪያ ሆነው ስናያቸው አሰላሳዮችም እንዲሁ ዳር ቆመው ያያሉ፡፡
አካባቢያችን (የአፍሪካ ቀንድ) በዓለም አቀፍ ኃያላንም ሆነ ወደ ኃያልነት እያኮበኮቡ ባሉ አገሮች መነጽር ውስጥ በመግባት፣ የአካባቢውን ጂኦ–ፖለቲካዊ ሁኔታ በማያቋርጥ ሁኔታ ሲለውጡትና የወደፊቱ ጉዳያችንን በሥጋት ስናይ ሥጋት ከመሆኑ ውጪ እንዴት እንደሚፈታ ሲያሰላስሉት አናስተውልም፡፡ በውጭ አገር ይገኙ የነበሩና ትጥቃቸውን ፈተውም ይሁን ሳይፈቱ አገር ውስጥ በመግባት ምርጫው ይካሄድ አይካሄድ በሚል አዙሪት ውስጥ ገብተው ኢትዮጵያን ግራ ሲገባት፣ አሰላሳዮቹ ወደሚሻለው ጎዳና በዚህ በኩል ሂዱ ሲሉ አናያቸውም፡፡ በአጠቃላይ አገርን ወደተሻለ አቅጣጫ የሚወስዱ የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦችን ያሰላስላሉ ተብለው የሚጠበቁ አካላት እያሰላሰሉ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያችን በዚህ ረገድ አልታደለችም፡፡
አስተሳሰባቸውና ተግባራቸው መካከለኛው ምሥራቅንና ቀይ ባህርን ተሻግሮ የመጣው የአሸባሪ ቡድኖች እንደምን ሊጎዱን እንደሚችሉና እነሱን የማጥፊያ ወጥመድ አሰላሳዮቹ በእጅ አላሉንም፡፡ የቀንዱ አገሮች ትንሳዔም ሆነ ውድቀት የጋራ መሆኑን ይነግሩንና እንዴት ሥራ መሥራት እንደምንችል ወይም እንዴት እንዳልቻልን ፍንትው አድርገው አያሳዩንም፡፡ አካባቢያዊ ተቋማችን የሆነው ኢጋድ ድርሻውን እየተወጣ እንደሆነና እንዳልሆነ በተግባር የምናውቀው ቢሆንም፣ የአካባቢው አገሮች እርስ በርስ ሲተራመሱ እልባት የመስጠት አቅሙ ምን ያህል እንደሆነ ግን አላሰላሰሉትም፡፡ ኢጋድም ስለራሱ እንዲያሰላስል አልረዱትም፡፡ አፍሪካችንን በ2020 የጥይት ድምፅ የማይሰማበት አኅጉር እናደርጋለን እያልን ስንደሰኩር፣ በኢትዮጵያችን የጦር መሣሪያ ዝውውሩ እንዴት እያየለ እንዳለ ሲያሰላስሉ አይታዩም፡፡ በአውሮፓ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የማርሻል ዕቅድ መልክ እንዲይዝና አውሮፓ እንድታገግም አሰላሳይ ተቋማትና አሰላሳዮቻቸው ከፍተኛውን ሚና ተጫውተዋል፡፡
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በመነሳት ዳግም ዕልቂት እንዳይከሰት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እ.ኤ.አ. በ1948 ፀረ ጅምላ ጭፍጨፋ ዓለም አቀፍ ስምምነትን ያፀደቀው በአሰላሳዮች ግፊት መሆኑ ይታወቃል፡፡ በአጠቃላይም ዓለም አቀፍ ችግሮችን ለመፍታት የሚወሰዱ ዓለም አቀፍ መፍትሔዎችን እየጠቆሙና የፖሊሲ ትኩረት እንዲያገኙ በማድረግ አሰላሳዮች ሚና አላቸው፡፡ ዓለም ከአንድና ከሁለት ገዥ አስተሳሰቦች በመውጣት በርካታተፅዕኖ አሳዳሪዎች ፍላጎታቸውን ለመጫን በሚያደርጉት ጥረት፣ የአገራችን ብሔራዊ ማንነትና ኩራት ለማስጠበቅ የሚያስችል ስትራቴጂ እንዴት ይሰፋል ተብሎ ቢጠየቅ አሰላሳዮቻችን ምን ይሉ ይሆን? አሰላሳዮች ሁል ጊዜ አዎንታዊ ሚና ይጫወታሉ ብሎ መበየን አለማሰላሰል ሊሆን ይችላል፡፡ አሳማኝ መረጃን ወይም ማስረጃን ያልተንተራሰው የአሜሪካ በኢራቅ ጣልቃ ገብነት በወቅቱ በኢራቅ የመንግሥት ለውጥ እንዲኖር በሚሹ አሰላሳዮች ግፊት የተወሰደ ዕርምጃ መሆኑን ምሁራን ይነግሩናል፡፡
እኝህ ጦርነት ያቀነቅኑ የነበሩት አሰላሳዮች ኢራቅንም ሆነ መካከለኛው ምሥራቅን ውድ የሆነ ዋጋ እንዲከፍሉ አድርገዋቸዋል፡፡ አንድ የፖሊሲ ሐሳብ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት በክርክርና በውይይት ሊንገዋለል ይገባዋል፡፡ ማሰላሰልም ይኼንን ሒደት መጨመር አለበት፡፡ በአገራችን ኢትዮጵያ ጥፋትን ያስከተሉ የማሰላሰልም ሆነ ያለማሰላሰል ውጤቶችን አይተናል፡፡ የኢፌዴሪ መንግሥት ምን ያህል አሰላሳይ ተቋማት እንዳሉት ግልጽ ዓይደለም፡፡ ወይም ውሳኔዎቹና ተግባሮቹ በአጠቃላይ በአማካሪዎች ብቻ የተመሩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ያለ ማሰላሰል በድምፅ ብልጫ ብቻ ተግባራዊ የሆኑም ይገኙበታል፡፡ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት የእውነተኛ አሰላሳዮች እጅ ቢኖርበት ኖሮ ወንድም ከወንድሙ ጋር ባልተጋጨ ነበር፡፡ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አሉት እንደተባለው፣ በፓርቲ የድምፅ ብልጫ የተጎሰመው ጦርነት ጠባሳውን ዓይተናል፡፡ ምርጫ ዘጠና ሰባትን ተከትሎ ፖለቲከኞቻችን ፀረ ሽብርንና የበጎ አድራጎት ማኅበራት ሕጎችን ያለማሰላሰል በማውጣታቸው፣ ወይም አሰላሳዮቻቸው በግራ በኩል እንዲጓዙ በማድረጋቸው ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዳፋውን አስታቅፈውናል፡፡
ኢትዮጵያ አሰላሳይ ተቋማት አይብቀልብሽ ተብላ የተረገመች አገር አይደለችም፡፡ ተቋማቱ እንዲያብቡና ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ ማድረግ እንዲችሉ የሕግ፣ የተቋማዊና የትብብር ማዕቀፎችን ማመቻቸት የመንግሥት ግዴታ ነው፡፡ አሁን በተፈጠረው ለውጥ ሁኔታዎችን መገመት አይከብድም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በዳቮስ የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ላይ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በመደመር ፍልስፍናና አሠራር ትጓዛለች፡፡ የመደመር ፍልስፍናም ዴሞክራሲን፣ ኢኮኖሚንና ቀጣናዊ ውህደትን አቅፎ እንደያዘ አስረግጠው ነግረውናል፡፡ እነዚህ የሰላም ግንባታ አካል የሆኑት የመደመር ፍልስፍናዎች ያለ ማሰላሰል የትም አናደርሳቸውም፡፡ በመመራመር፣ በመተንተን፣ በመወያየትና በመከራከር ፖሊሲዎቻችንን ሥርዓት ባለው መንገድ ለአገራዊ ልማት ፋይዳ እንዲኖራቸው ማሰላሰልን መጀመርና የዕለት ተዕለት ሕይወታችን ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ የወደፊቱን ትውልድ ሕይወት የተሻለ ለማድረግ አሰላሳይ ተቋማት ያስፈልጉናል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የጂኦ ፖለቲካ ተንታኝና ተመራማሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡