የንግድ ማኅበረሰቡ ነባር ጥያቄዎችና ሥጋቶች ተንጸባርቀዋል
ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን (አይኤፍሲ)፣ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል ፖሊሲ ነክ፣ የማክሮ ኢኮኖሚና ሌሎችም በንግዱ ማኅበረሰብ ዘንድ ማነቆ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሁሉ መነጋገሪያና መፍትሔ ማመላከቻ የሚሆን የጋራ የውይይት መድረክ ዳግም እንዲጀመር እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡
ከዚህ ቀደም በዓመት ሁለት ጊዜ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሚገኙበት ከነጋዴው ለሚነሱ ጥያቄዎች መንግሥት ምላሽ የሚሰጥበት የፖሊሲ ምክክር የሚካሄድበት መድረክ እንደሚሆን ቢታመንም፣ በቋሚነት መካሄድ ሳይችል ቆይቷል፡፡ ያዝ ለቀቅ ሲል የቆየው የሁለቱ አካላት ግንኙነትና ምክክር የተጠነሰሰው በ2000 ዓ.ም. ነበር፡፡ በመንግሥትና በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ስምምነት መሠረት፡፡ ይህም ይባል እንጂ ከ1997 ዓ.ም. በፊት የዓለም ባንክ ይህ ዓይነቱ ግንኙነት እንዲፈጠር ሲሞክር፣ የግሉ ዘርፍም ሲጠይቅ ቆይቷል፡፡ ይሁንና ስምምነቱ ሳይተገበር እየተጓተተ በያዝ ለቀቅ ቆይቶ በ2001 ዓ.ም. አጥቢያ ግን ጽሕፈት ቤት ተቋቁሞለት ወደ ሥራ ገብቶም ነበር፡፡
ጥቂት ፈቅ ቢልም የመንግሥት ባለሥልጣናት በተለይም በወቅቱ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና በንግድ ምክር ቤቱ የመግባቢያ ስምምነትና ተጠሪነት የተጀመረው መድረክ እንደ አጀማመሩ ሊቀጥል አልቻለም፡፡ ለብዙ ጊዜም ተቋርጦ ቆየ፡፡ በወቅቱ የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ በመስጠት ጭምር መድረኩን ያግዝ የነበረው አይኤፍሲ ነበር፡፡ በአዲሱ አስተዳደር ወቅት ግን ሄድ መለስ የነበረው የምክክር መድረክ በቋሚነት መቀጠል እንዳለበት ተወስቷል፡፡
ሐሙስ፣ ጥር 23 ቀን 2011 ዓ.ም. በተካሄደው ስብሰባም ከለውጥ እንቅስቃሴው አኳያ የግሉ ዘርፍ ተሳታፊነትና የወደፊት መፍትሔዎችን መነሻ ያደረገ ውይይት ተካሒዷል፡፡ በዚህ ወቅት ከካፒታልና ከሪፖርተር ጋዜጣ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት አቶ አበበ፣ ከዚህ ቀደም የነበረው የምክክር መድረክ ውጤታማ እንዳይሆን ያደረጉ ሁኔታዎች እንደነበሩ አስታውሰዋል፡፡ መንግሥት የግሉን ዘርፍ በጥርጣሬ የሚያይበት፣ እንደሚፈለገውም ያልቀረበበት እንደነበር ያወሱት አቶ አበበ፣ ይህም ቢባል ግን ከመንግሥት ጋር የተሳኩ የምክክር መድረኮች ስመካሄዳቸውም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡
አዲሱ አስተዳደር ከማኅበሰረቡ ልዩ ልዩ ክፍሎች ጋር በፖለቲካ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይቶች እየተካሄዱ በመሆናቸው፣ ከግሉ ዘርፍ ጋርም የሚካሄዱት ምክክሮች የዴሞክራሲው ግንባታ አካላት በመሆናቸው፣ በጋራ ጉዳዮች ላይ የጋራ መፍትሔዎችን በውይይት የማፈላለፈግ ዝንባሌ መታየቱ ከቀደሙት መድረኮች የተለየ የሚያደረገው ጅምር መምጣቱን አቶ አበበ አብራርተዋል፡፡
ነባሮቹ ችግሮችና አዲሱ አስተዳደር
እንደ አዲስ ሊጀመር ለታሰበው የምምክር መድረክ፣ መክፈቻ በተደረገው ስብሰባ ወቅት ነባር ቅሬታዎችና ችግሮች ተስተጋብተዋል፡፡ ሥጋቶች ተደምጠዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ማኅበር የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የዋልያ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ኩባንያ ባለቤት አቶ ያሬድ ዓለማየሁ ጎላ ባለ ድምጸት የቆዳ ኢንዱስትሪውን ብሶት ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ ያሬድ በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ 20 የቆዳ ፋብሪካዎች ሊዘጉ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል፡፡ ይኸውም በባንክ ብድር ጫና ሳቢያ ነው፡፡
አቶ ያሬድ ዘርፉ ያሉበትን ችግሮች ከሁለት ዓመታት በፊት፣ ፕሪሳይስ ኮንሰልት ኢንተርናሽናል በተሰኘው ተቋም አዘጋጅነት በተሰናዳው የሥራ አስፈጻሚዎች መድረክም ይህንኑ አስተጋብተው ነበር፡፡ በወቅቱ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ለነበሩት አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) ይህ ጥያቄ ቀርቦ ነበር፡፡ የቆዳ ኢንዱስትሪዎች በሥራ ማስኬጃ እጥረት፣ በብድር ዕዳና በወለድ ጫና መላወሻ ማጣታቸውን አስታውቀው ነበር፡፡ ዘንድሮ ምናልባትም በመጪዎቹ አራት ወራት ውስጥ ይዘጋሉ ያሏቸው ፋብሪካዎች መነሻቸው በባንክ ዕዳ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ያሬድ፣ ከዚህ ቀደም ባቀረቡት የመፍትሔ ሐሳብ መሠረት መንግሥት ‹‹የተመላሽ ገንዘብ›› አሠራርን በመከተል ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀው ነበር፡፡
ይኸውም ለውጭ ገበያ ከቀረበው ምርት ከሚገኘው የውጭ ምንዛሪ፣ በብር ተመንዝሮ ምናልባት እስከ 30 በመቶ ለፋብሪካዎች በማበረታቻ መልክ እንዲሰጣቸውም በመፍትሔ ሐሳብነት አቅረበው ነበር፡፡ የተጠየቀው መፍትሔ እንደ ቱርክ ባሉ አገሮች ውስጥ ለወጪ ንግድ መስፋፋት እንደ ማበረታቻ ሲወሰድ የነበረ ነው፡፡ ይህም ይባል እንጂ ዘርፉ ካገኘውም ድጋፍና ማበረታቻ አኳያ እንኳ ይህ ነው የሚባል ውጤት አለማሳየቱ ይብሱንም በአካባቢ ብክለት ከፍተኛ ወቀሳ የሚደርስበትና ለበካይ ፍሳሽ ማጣሪያ የወጡ የአሠራር ግዴታዎችን ማክበር የተሳነው ሆኖ መቆየቱ ከሚያስወቅሱት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
ይህም ሆኖ የሶል ሬብልስ ጫማ አምራች ኩባንያ፣ ጋርደን ኦፍ ኮፊ የተሰኘና የቡና መሸጫ መደብሮችን ከኢትዮጵያ አልፎ በቻይና እያስፋፋ የሚገኝ ኩባንያ ብሎም ‹‹ሜድ ባይ ኢትዮጵያ›› የተሰኘ የጫማ ግብይትን የሚመራ ተቋም ከሌሎች 12 ጫማ አምራች ፋብሪካዎች ጋር የመሠረተችው ታዋቂዋ ወ/ሮ ቤተልሔም ጥላሁንም የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ማነቆነቱን አውስታለች፡፡ እንደ ወ/ሮ ቤተልሔም ከሆነ፣ አነስተኛ ማምረቻ ያላቸው ኩባንያዎች ለሚፈልጉት አነስተኛ የካፒታል አቅርቦት የሚሰጥ ተቋም ማግኘት ከባድ ፈተና ነው፡፡ ከዚህ ሲያልፍም ባንኮች ያለ ማስያዣ ብድር ለማበደር ፈቃደኛ አለመሆናቸው ለሥራቸው አዳጋች እንደሆነባቸው ወ/ሮ ቤተልሔም አውስታለች፡፡ በጋራ መንቀሳቀስ የጀመሩት አምራቾች ሁለት ሚሊዮን ጥንድ ጫማዎች ከውጭ ገዥዎች ቀርቦላቸው፣ ‹‹ዝግጁ ስላልነበርን፣ አቅሙም ስላልነበረን ማቅረብ አልቻልንም፤›› ያለችው ወ/ሮ ቤተልሔም፣ ለአምራች ኢንዱስትሪው በተለይም በአነስተኛና መካከለኛ መደብ ለሚገኙት የተሰጠው ትኩረት፣ የፋይናንስ አቅርቦቱ በተለይ መስተካከል እንደሚገባው ጠይቃለች፡፡ ባንኮች ለፕሮጀክት ሐሳብ ማዳበር እንዲጀምሩም አሳስባለች፡፡ ሌላው በዚህ መስክ ብዙ ስለመሄዱ አጣቅሳም በኢትዮጵያ ያለው ማነቆ እንዲፈታ ጥሪ አቅርባለች፡፡
ሌሎችም በአምራች ኢንዱስትሪው መስክ የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎች ከውጭ ኩባንያዎች አኳያ የሚደርስባቸውን ጫና በተመለከተም ሥጋትና ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ የውጭ ኩባንያዎች በተለይም በወጪ ንግድ ላይ የተሠማሩቱ፣ በአብዛኛው ከውጭ በሚያስመጡት ጥሬ ዕቃ ላይ የተመረኮዘ የምርት ሒደት ይከተላሉ፡፡ ይህ ምንም እንኳ በአገሪቱ ካለው የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር አኳያ እንደሆነ ቢታመንም፣ በውይይቱ ወቅት እንደተነሳው ከሚሰጣቸው ድጋፍና ማበረታቻ አኳያ ከአገር ውስጥ አምራቾች ምንም የተለየ ነገር ሳያበረክቱና የዕውቀትም ሆነ የቴክኖሎጂ ሽግግር ሳያሳዩ ይልቁንም ያስገኙትን የውጭ ምንዛሪ በሙሉ መልሰው እያስወጡ ነው ያሉት አምራቾች ከእኛ በምን ተሻሉ? ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ እንደውም እኛ እየተገፋን ከገበያ እየወጣን እኛው የምንሠራው ሥራ በውጭዎቹ እየተያዘ ነው ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
እንዲህ ያሉ ቅሬታዎችና ሥጋቶች የተስተጋቡበት መድረክ ላይ የተገኙት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ አማካሪውና የቀድሞው የአይኤፍሲ ባልደረባ አቶ ማሞ ምሕረቱ ሐሳባቸውን አካፍለዋል፡፡ በዕለቱ የተገኙት ለሚነሱ ጥያቄዎች ሁሉ ምላሽ ወይም መፍትሔ ለመስጠት እንዳልሆነ አስታውቀው፣ ነገር ግን የተነሱትን ጥያቄዎች በሙሉ ለመሚመለከታቸው እንደሚያቀርቡ፣ መድረኩ ግን ከነጋዴው ለመማርና ጥያቄዎቹንም ለማድመጥ ያገዛቸው ስለመሆኑ ጠቅሰዋል፡፡ መንግሥት ከሌላው ጊዜ ይልቅ ለመፍትሔና ለተግባር ቁርጠኛ ስለመሆኑ የገለጹት አቶ ማሞ፣ የግሉ ዘርፍም በተጠያቂነት ዙሪያ የሚጋራቸው ኃላፊነቶች እንዳሉበት፣ በአብሮ በመነጋገር መፍትሔ ማስቀመጡ ላይም ሚናውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት እንዲህ ያለውን መድረክ ዳግም ለማስጀመር አይኤፍሲ ከሌሎች ጊዜያት ይልቅ ጉልህ እንቅስቃሴ ማድረግ ጀምሯል፡፡ የተቋሙ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ የጂቡቲ፣ የዴሞክራቲክ ኮንጎ፣ የሶማሊያና የሱዳን ተጠሪ የሆኑት አዳሙ ላባራ ስለ መድረኩ አስፈላጊነት ለሪፖርተር ሲገልጹ፣ በግሉና በመንግሥት መካከል መግባባትና መመካከር እንዲስፋፋ፣ በመንግሥት የበላይነት ይመራ የነበረው ኢኮኖሚም በግሉ ዘርፍም ተሳትፎ እንዲመራ የሚያስችሉ የለውጥ ዕርምጃዎች በመታየታቸው ተቋማቸው ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአይኤፍሲ መሥራች አባል ስትሆን፣ የኮርፖሬሽኑ ባለድርሻም ነች፡፡ እ.ኤ.አ. በ1956 በአሜሪካ የተመሠረተው ይህ ተቋም፣ ዋና ተልዕኮው ለግሉ ዘርፍ የልማት ፋይናንስ ማቅረብና ድህነትን ለሚቀንሱ ፕሮጀክት ድጋፍ መስጠት ነው፡፡ በአሁኑ በኢትዮጵያ ለግሉ ዘርፍ ቦታ የሚሰጥ ኢኮኖሚያዊ ጅምር ለውጥ ስለመጣ፣ ኮርፖሬሽኑም ለዚህ ድጋፍ የሚሰጥባቸውን እንቅስቃሴዎች ጀምሯል፡፡ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በቅርቡ በአዲስ አበባ ተገኝተው በገቢ ንግድ ላይ ለባንኮች ዋስትና የሚሰጥ እንዲሁም በውጭ ምንዛሪ ተበድረው ለአገር ውስጥ ምርቶቻቸውን የሚያቀርቡ የተመረጡ ኩባንያዎች ብድራቸውን በብር መክፈል የሚችሉባቸው ስምምነቶችን መፈራረማቸው የሚታወስ ነው፡፡