ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የሚያተርፉ ባንኮች እንደሚበራከቱ ይጠበቃል
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨምሮ የሁሉም ንግድ ባንኮች የ2011 ዓ.ም. ግማሽ ዓመት አፈጻጸም ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ወቅት ካስመዘገቡት ውጤት ይልቅ የበለጠ መሆኑ ተመለከተ፡፡ 17ቱ ባንኮች በስድስት ወራት ብቻ ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ከ16.4 ቢሊዮን ብር አስመዝግበዋል፡፡
ባንኮቹ በግማሽ ዓመቱ ያስመዘገቡት ውጤት የሚያሳየው የሒሳብ ሪፖርት፣ ሁሉም የትርፍ ምጣኔያቸውን ማሳደጋቸውን አስፍሯል፡፡ ንግድ ባንክና 16ቱ የግል ባንኮች ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት በጥቅል ካስመዘገቡት 16.4 ቢሊዮን ብር ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው ንግድ ባንክ ሲሆን፣ ከታክስ በፊት 9.4 ቢሊዮን ብር እንዳተረፈ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ ንግድ ባንክ በ2011 የመጀመርያዎቹ ስድስት ወራት ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ማስመዝገብ የቻለው ትርፍ 9.4 ቢሊዮን ብር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አንፃር ሲታይ፣ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው ሆኗል፡፡
የግል ባንኮች በበኩላቸው ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ማስመዝገብ የቻሉት ትርፍ ሰባት ቢሊዮን ብር እንደሆነ ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡ ንግድ ባንኮቹ ከታክስ በፊት ያገኙት የትርፍ መጠን ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው አኳያ የ5.5 ቢሊዮን ብር ጭማሪ የታየበት ሆኗል፡፡
ንግድ ባንክ በግማሽ ዓመቱ ይፋ ያደረገው የትርፍ መጠን ለየት የሚልበት ሌላው ገጽታው ባለፈው ዓመት በሙሉ ሒሳብ ወቅት ካስመዘገበው 10.4 ቢሊዮን ብር አንፃር ሲታይ፣ የዚህ ግማሽ ዓመት ትርፉ ከፍተኛ በመሆኑ ነው፡፡ ከዓምናው የሙሉ ዓመት ትርፉ የዘንድሮው ግማሽ ዓመት ትርፉ የሚያንሰው በአንድ ቢሊዮን ብር ብቻ በመሆኑም፣ በዚህ ዓመት መጨረሻ ሊያስመዘግብ የሚችለው ትርፍ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ አመላክቷል፡፡ ባንኩ በ2010 ዓ.ም. ያስመዘገበው ትርፍ ከ2009 ዓ.ም. አንፃር ሲታይ በ4.3 ቢሊዮን ብር ያነሰም ነበር፡፡
16ቱ የግል ባንኮች በግማሽ ዓመቱ በጠቅላላው ያስመዘገቡት የትርፍ መጠን ሰባት ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ባንኮቹ በስድስት ወራት ውስጥ የደረሱበት የትርፍ መጠን ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ2.6 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው፡፡ ባንኮቹ በተናጠል ያገኙት ትርፍም ከዓምናው አኳያ ብልጫ ያለው ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ባንኮች ትርፋቸውን በእጥፍ ያሳደጉበትም ነበር፡፡
ከግል ባንኮች በግማሽ ዓመቱ ከፍተኛውን ትርፍ ያስመዘገበው አዋሽ ባንክ ነው፡፡ አዋሽ በግማሽ ዓመት ውስጥ ብቻ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ አትርፏል፡፡ ከ2009 ዓ.ም. ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም በእጥፍ ብልጫ ያሳየበት ሆኗል፡፡
አዋሽ ባንክ ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት 1.37 ቢሊዮን ብር አትርፏል፡፡ ከባንኩ የተገኘው መረጃም ሆነ ስለኢንዱስትሪው የቀረበው ሪፖርት እንደሚጠቁሙት፣ ዘንድሮ የተገኘው ትርፍ ካለፈው ዓመት የመጀመርያው ግማሽ ዓመት አኳያ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው፡፡
ባንኩ በቀደመው ዓመት አጋማሽ ዓመት ያስመዘገበው ትርፍ፣ 660 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ በመሆኑም ባንኩ በግማሽ ዓመቱ ያስመዘገበው ትርፍ ከፍተኛ እንደሆነ ያሳያል፡፡ ከባንኮቹ ምሥረታ ጀምሮ በግማሽ ዓመት ውስጥ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገብ የተቻለበት ጊዜ ሆኗል፡፡ አዋሽ ባንክ ባለፈው ዓመት ከታክስና ከሌሎች ተቀናሽ ወጪዎች በፊት የሁለት ቢሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገቡ ይታወሳል፡፡
የተቀሩት ባንኮችም የትርፍ ምጣያቸው ዕድገት ካለፈው ዓመት አኳያ ቀላል የማይባል ጭማሪ እያሳየ መምጣቱ ታይቷል፡፡ ይህም ከአዋሽ፣ ከዳሸንና ከወጋገን ባንክ ባሻገር ሌሎች ባንኮችም ዓመታዊ ትርፋቸውን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ሊያሸጋግሩ የሚችሉበት ሰፊ ዕድል እንዳለ በግማሽ ዓመቱ የደረሱበት የትርፍ መጠን ይጠቁማል፡፡
ከዓምናው የባንኮች አፈጻጸም አኳያ፣ ከአዋሽ ባንክ በተጨማሪ ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ያስመዘገቡት ዳሸንና ወጋገን ባንኮች ብቻ ነበሩ፡፡ በዚህ ዓመት ግን እነዚህ ባንኮች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም ባንኮች ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያተርፉ አመላካች ውጤት መታየቱን የባንክ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ በግማሽ ዓመቱ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ማትረፍ የቻሉ ባንኮች በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ የትርፍ ምጣኔያቸው ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ይደርሳል የሚል ግምትም እየተሰነዘረ ነው፡፡
በግማሽ ዓመቱ ዳሸን ባንክ 753 ሚሊዮን ብር ያተረፈ ሲሆን፣ ይህ የትርፍ ምጣኔ ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት አኳያ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ የታየበት ነው፡፡ በ2011 ዓ.ም. መጨረሻም የባንኩ የትርፍ መጠን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያሻቅብ ከወዲሁ ተገምቷል፡፡
ከዳሸን በተጨማሪ በግማሽ ዓመቱ ከፍተኛ ትርፍ በማስመዝገብ የዓመቱን የትርፍ መጠን አንድ ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያሻግር የሚጠበቀው አቢሲኒያ ባንክ ነው፡፡ ባንኩ በስድስቱ ወራት ከታክስና ከሌሎች ተቀናሽ ሒሳቦች በፊት 628 ሚሊዮን ብር አትርፏል፡፡
በ2010 ዓ.ም. ከ910 ሚሊዮን ብር በላይ በማትረፍ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበው ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክም፣ በግማሽ ዓመቱ ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት 590 ሚሊዮን ብር በማትረፉ በ2011 ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስመዘግብ ከሚጠበቁት መካከል ተካቷል፡፡
ከእነዚህ ባንኮች በተጨማሪ ወጋገን ባንክ ከ481 ሚሊዮን ብር በላይ፣ ንብ ባንክ ከ436 ሚሊዮን ብር በላይ፣ አንበሳ ባንክ 444 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገባቸውን ከግርድፍ የሒሳብ ሪፖርታቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡ ሌሎች ባንኮችም ከ97 እስከ 374 ሚሊዮን ብር ባለው ዕርከን አትርፈዋል፡፡ ከ16ቱ የግል ባንኮች እናት ባንክ 123 ሚሊዮን ብር፣ አዲስ ኢንተርናሽናል ባንክ 95 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ደቡብ ግሎባል 97 ሚሊዮን ብር በማትረፍ የመጨረሻዎቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡
አቢሲኒያ ባንክ በግማሽ ዓመቱ ያገኘው ትርፍ ባለፈው ሙሉ ዓመት ካገኘው ትርፍ ጋር ተቀራራቢ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ባንኩ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ በ2010 ዓ.ም. መጨረሻ ከታክስ በፊት 771 ሚሊዮን ብር፣ ከታክስ በኋላም 680 ሚሊዮን ብር አግኝቷል፡፡
በዚህ ግማሽ ዓመት ከታክስና ከተቀናሽ ወጪዎች በፊት ያገኘው ትርፍ 628 ሚሊዮን ብር በመሆኑ፣ በአጋማሽ ዓመቱ ያገኘው ትርፍ ዓምና በሙሉ ዓመቱ ያገኘውን ያህል ትርፍ ወይም የተቀራረበውን መጠን እንዳስመዘገበ ያመላክታል፡፡
አብዛኛዎቹ የግል ባንኮች በዓምናው እንቅስቃሴያቸው ያሰባሰቡት የተቀማጭ ገንዘብና የሰጡት ብድርም ከቀዳሚዎቹ ዓመታት ብልጫ አሳይተዋል፡፡ ባለፈው ዓርብ በፓርላማ ተገኝተው ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ፣ ዓርብ ጥር 24 ቀን 2011 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ላቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት፣ የኢኮኖሚው ዕድገት ተቀዛቅዟል የሚለው የበርካቶች ምልከታ ከባንኮች የገንዘብ እንቅስቃሴ አኳያ ሲታይ ኢኮኖሚው እንደሚባለው እንዳልተቀዛቀዘ አመላካች ነው፡፡ ባንኮች የሚያንቀሳቅሱት ገንዘብ፣ ያሰባሰቡት ገንዘብ ብዛትና ያተረፉት መጠን ሲታይ፣ ኢኮኖሚው ተቀዛቅዟል ለሚለው ስሞታ ምላሽ የሚሰጥ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የባንኮቹ የትርፍ ዕድገት ምንን ያመለክታል የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው የባንክና የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ግን ምልከታቸው ይለያል፡፡ አንዳንዶች የገንዘብ ኢንዱስትሪው ከሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ይልቅ አሁንም በከፍተኛ መጠን ትርፋማ እንደሆነ ያሳያል ይላሉ፡፡ አንድ የባንክ ባለሙያ ግን የታየው የትርፍ ብዛት ዕድገትን እንደማያሳይ ይገምታሉ፡፡ ምክንያታቸውም ከብር የመግዛት አቅም አንፃር፣ ባንኮቹ ያገኙት ትርፍ ሲመዘን በዕድገት ደረጃ ሊወሰድ መቻሉ ይከብዳል ይላሉ፡፡
በአንፃሩ እነዚህ ተቋማትም ሆኑ ሌሎች የንግድ ዘርፎች ውጤታማ እንዲሆኑ ከተፈለገ የግሉ ዘርፍ በከፍተኛ ሁኔታ ሊንቀሳቀስ የሚችልበት ዕድል ማግኘት ይገባዋል የሚሉም አሉ፡፡ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ አነስተኛ ነው፡፡ መንግሥት ይህንን ለማስተካከልና የግሉ ዘርፍ ዋናው የኢኮኖሚ ዘዋሪ እንዲሆን ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል፡፡ ከዚህም በላይ ትልልቅ የልማት ድርጅቶቹን በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ወደ ግል እንደሚያዞር ማስታወቁ በተስፋ የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ይህ እስኪመጣ ግን ለግሉ ዘርፍ እንቅስቃሴ አመቺ ከባቢ ሁኔታን መፍጠር ካልተቻለ በቀር ባንኮች የሚያገኙት ትርፍ ብቻውን የኢኮኖሚውን ዕድገት አይገልጸውም የሚሉም አልታጡም፡፡
ሁሉም ባንኮች በቀደመው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ብልጫ ያለው ውጤት እንዲያገኙ ካስቻላቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ኢኮኖሚው እንቅስቃሴው ከቀደመው ዓመት በተሻለ ሁኔታ መራመድ በመቻሉ እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡
ባለፈው ሳምንት የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸሙን የገመገመው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ባጫ ጊና እንደገለጹት፣ የኢኮኖሚው መነቃቃትና ባንኩ ሀብት በማሰባሰብ ያደረገው እንቅስቃሴ የተሻለ በመሆኑ ነው፡፡
ከአንዳንድ የግል ባንክ የሥራ ኃላፊዎች የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው፣ ባንኮች የተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰቡ ረገድ ከቀደመው ጊዜ የተሻለ በመሆኑ ነው፡፡
ባንኮቹ አሁንም ከእያንዳንዱ ብድር 27 በመቶ እየተሰላ የሚያውሉት የቦንዱ ግዥ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ ቢኖረውም ትርፋቸው አድርጓል፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት ካለው የውጭ ምንዛሪ እጥረትና ከሚገኘውም የውጭ ምንዛሪ 30 በመቶውን በቀጥታ በገዙበት መጠን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገቢ እንዲያደርጉ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ ተቋቁሞ እንደቀደሙት ወቅቶች አሁንም አትራፊ ሆነው መቀጠል መቻላቸው ኢንዱስትሪው ከሌሎች በተለየ እንዲታይ አድርጎታል፡፡