Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በበጎ ጅምሮቹ ይመስገን በሚነቀፉትም ይወቀስ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ ትይዩ ከሚገኘው መቀመጫው እንግዳ የሚባሉ አንዳንድ ተግባራትና ውሳኔዎችን እየተገበረና እያሳለፈ ይገኛል፡፡

አዲስ አበባን በፊት አውራሪነት የሚመሩት ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) በከተማው ምክር ቤትና ካቢኔ መገኛ ሕንፃ ውስጥ ሆነው በአዲስ አበባችን ያልተሞከሩ  ውሳኔዎችን በየጊዜው እያሳለፉና እያስተገበሩ ነው፡፡ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳች ላይ ያነጣጠሩ ጉዳዮችን በተሻለ መንገድ ለመፍታት የሚደረገው እንቅስቃሴ እሰየው የሚያሰኝ ነው፡፡ ሌላውን ትተን  ከሰሞኑ እንኳ ከሰባት ሺሕ በላይ ግብር ከፋዮች የተደረገላቸውን ምሕረት በአስረጅነት ማቅረብ እንችላለን፡፡ ውሳኔው ለሰባት ዓመታት ሲንከባበለል የቆየውና ከታክስ ዕዳና ጫና ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ሮሮ ከማርገብ አንፃር  ጠቀሜታ ያለው ሲሆን፣ ነገ በመተማመንና በፍትሕ ላይ የተመሠረተ ታክስ ለመሰብሰብ የሚያስችል እንደሚሆን ይታመናል፡፡ ግብር ከፋዮችም የተሻለ መነሳሳት እንዲፈጠርባቸው የሚያደርግ ዕርምጃ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም በከንቲባው ጽሕፈት ቤት የተወዱ አንዳንድ ዕርምጃዎችም ይበል የሚያሰኙ ናቸው፡፡  የከረሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚደረገው እንቅስቃሴም የአንድ ሰሞን ብቻ ከሆኑ ውጤት እንደማያመጡ የታወቀ ነው፡፡ ስለዚህ እየተደረጉ ያሉትን ፈጣንና ለውጥ ተኮር ጥረቶች አለማድነቅ ንፉግነት ይሆናል፡፡ ባይሆን ይህ ይቀራል እንዲህ ይደረግ በማለት መምከሩ የተሻለ ነው፡፡ እንዲህ ቢደረግ ብሎ ማመላከቱ ተገቢ ይሆናል፡፡ የሚበረታቱ መልካም ሥራዎችና ለውጦችን እያየን ነው፡፡ ነገር ግን ከአዲስ አበባ ግዙፍ ችግሮች አንፃር ብዙ ሥራዎችን ከአስተዳደሩ እንደሚጠበቁ በማመን በተቻለ መጠን ተቀራርቦና ተወያይቶ ለመፍታት የሚደረጉ ጥረቶችን ነገ እንዲስፋፉ ማድረጉ መንደጉን መጥረጉ መልካም ነው፡፡ እየተደረገ ያለው ጥረት በከተማው ነዋሪ ከተደረገፈና ከታገዘ፣ የአዲስ አበባን ዘርፈ ብዙ ችግሮች ለማከም የሚፈጀውን ረጅም ጉዞ እንደሚያሳጥረው፣ አስቸጋሪውን እንደሚያቀለው ግልጽ ነው፡፡

ሆኖም የአዲስ አበባ አስተዳደርን የሚመለከቱና ከሰሞኑ ከሰማናቸው ክንውኖችና ዘገባዎች ውስጥ ሁለት የተለያዩ ጉዳዮችን እንደየ ጭብጣቸው አስተያየት ሊሰጥባቸው ይገባል በማለት ለመጻፍ ተነሳሁ፡፡

የአስተዳደሩ የአነስተኛ ግብር ከፋዮችን የቆየ ብሶት በማዳመጥ ምላሽ መስጠቱ እሰየው ነው፡፡ ለግብር ይግባኝ ሰሚ አቤት ያሉ 6000 ግብር ከፋዮች፣ አንዳንዶቹ ግማሹን ከፍለው ፍትሕ ሲጠባበቁ የቆዩ፣ ሌሎችም ግማሽ አስይዘው መከራከር እንደማይችሉ የተረጋገጡ ሱቃቸውን ዘግተው በየቤታቸው ለመቀመጥ የተገደዱና ሌሎችም ችግራቸው ታይቶ መፍትሔ ማግኘታቸው ያስመሰግናል፡፡ ጉዳያቸውን በግብር ይግባኝ ሰሚ ታይቶም ወደ ፍርድ ቤት ሔደው የነበሩ ከ1780 ያላነሱ ግብር ከፋዮችም ፋይላቸው እንዲዘጋ ይደረጋል መባሉም የከተማውን አስተዳደር አበጀህ ያሰኘዋል፡፡ ሌሎችስ የሚለው ግን አሁንም የፍትሕና ለሁሉም በእኩል የማየትና የመወሰን ጉዳይ ላይ ጥያቄዎች ይደመጣሉና ሌሎችንም መመልከቱ እንደሚያስፈልግ እንጠቁማለን፡፡

ከዚህ ባሻገር የስብሰባ ወጪን በተመለከተ ከሰማነው እንጀምር፡፡ አስተዳደሩ የሚያካሒዳቸው ስብሰባዎች መብዛታቸውና የሚያወጣው ወጪም ማየሉንመምጣቱን ሰምተናል፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን፣ በስብሰባ ሰበብ ጊዜ እንዳይጠፋ፣ ገንዘብም እንዳይባክን ይደረጋል በተባለበት አፍታ የአስተዳደሩ ስብሰባዎች መበራከታቸው የአዲስ አበባው  አልበቃ ብሎ ከከተማ ውጭ የሚደረጉትም የትዬ ለሌ ናቸው፡፡ ለወጪ ዕድገቱ ሰበብ መሆኑ መገለጹ ከተጀመረው የለውጥ ዕርምጃ ጋር የሚስማማ አልሆነልኝም፡፡

በእርግጥም ከለውጡ ወዲህ ለስብሰባ እየወጣ ያለው ወጪ ከቀደመው ጊዜ ከባሰ፣ በተለያዩ ተግባራቱ አስተዳደሩን ‹‹በርታ›› የማለታችንን ያህል በዚህ ጉዳይ ላይ ግን ምን ነካህ? ብለን መጠየቃችን ግድ ነው፡፡ የስብሰባ ወጪ መብዛቱ ብቻም ሳይሆን፣ በስብሰባ ሰበብ ተገልጋዮች አሁንም ይጉላላሉ የሚለው ስሞታና ጥያቄ ስለሚነሳበት ጭምር ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋግመው የገለጹት፣ በስብሰባ የሚባክን ጊዜና ወጪ ልጓም እንደሚያስፈልገውና ስብሰባዎች መብዛት እንደሌለባቸው ነበር፡፡ አስተዳደሩ በዚህ ሳቢያ ስሙ መነሳቱ ተገቢ ካለመሆኑም ባሻገር፣ በቶሎ አስተካክሎ የተደረገውን ለውጥ ማስታወቅ እንዳለበት እናምናለን፡፡

በእርግጥም ከስብሰባ ጋጋታ ባሻገር ወረዳዎችን ወይም ስማቸው በመጥፎ አገልግሎታቸው ‹‹ቀበሌ›› ያሰኛቸውን ተቋማትም ማሻሻሉ ላይ ትኩረት መስጠት ይኖርበታል፡፡ ቀበሌ እንኳንና ስብሰባ አግኝተው፣ ቢሯቸውም ቁጭ ብለው የሌሉ በርካቶች የሚሰባሰቡበት ቦታ ከሆነ ስንት ዘመኑ፡፡ አሁን ላይ ለውጥ ካለ ወደ ቀበሌ ጎራ ማለት ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ ለውጡን ከቀበሌ እንዲጀምር ማድረግ እንደውም ብልህነት ነውና አስተዳደሩ ትኩረቱን ታችኛው እርከን ላይ ቢያደርግ እንላለን፡፡

ከዚህ ሌላ የከተማ አስተዳደሩ የከተማዋን ሕመም በመመልከት ለመፍትሔ እየተጋ ስለመሆኑ አመላካች መስሎ የታየኝና እንደ አንድ የከተማ አስተዳደር የተወሰደ ዕርምጃ ስለመሆኑ ወደሚሰማኝ ሁለተኛው ነጥቤ ልግባ፡፡

ይህም የአዲስ አበባን የጎዳና ልጆች ለመታደግ የተወጠነውና እንቅስቃሴው የተጀመረው የትረስት ፈንድ ጉዳይ ትልቅ ጅምር ነው፡፡ በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት፣ ከከንቲባው ሰገነት የተደመጠው የድጋፍ ጥሪና የለወገናችን እንድረስለት ጥሪ መልካም ከሚገልጸው በላይ ነው፡፡ አዲስ መንገድ ያመለክተኛል፡፡

በየጎዳናው የሚታየው አሰቃቂ የጎዳና ሕይወት መቼ ይፈታ ይሆን? ለሚለው የብዙዎች ጥያቄ መልስ ሊሰጥ የሚችል ሥራ ከመሆኑም በላይ፣ ሁሉም ዜጋ እንደ ሰብዓዊነቱና ዜግነቱ የሚያስብለት ተቆርቋሪ መንግሥት ስለመሆኑ ያሳየበት ነውና በርታና ግፋበት እንለዋለን፡፡ አሁን የተጀመረው ለውጥ ለመስጠትና ለመደጋገፍ ቦታ የሚሰጥ፣ ከተመሩ ይልቅ አብረን እንሒድ የሚል ነውና በተግባር የተደገፈ ውጤታማ ለውጥ እንደሚሆን ተስፋ አለኝ፡፡ ለውጥ መጥቷል የሚባለውም እንዲህ ያሉትን ጉዳዩች በመፈተሽ መፍትሔ መስጠትና የተሰነቀውንም ተስፋ ወደ እውነታነት መቀየር ሲቻል ነውና ለዚህ የሚተጋ አስተዳደር እንደሆነ ደጋግሞ መግለጹና ለማሳየትም መንቀሳቀሴ በርታ ያስብለዋል፡፡

መንግሥት መንገዱን ሲያሳይ፣ ማኅበረሰቡም የድርሻቸውን በመወጣት ማገዝና መደገፍ፣ መሳተፍና መሥራት እንዳለበት ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በየጎዳናው የወደቁትን ወገኖቻችንን እንደ ኢትዮጵያዊነታቸውና ሰብዓዊ ፍጡርነታቸው፣ የደረሰባቸውን የቁሳዊ ድህነትና የሞራል ድቀት በማገዝ ልንታደጋቸው መጣጣር፣ ሐሳቡ ያላቸው ሲመጡም፣ በገንዘብ የሚሆነውን በገንዘብ ለመደገፍ አዎንታዊ ምላሽ መስጠት ኃላፊነትን ከመወጣት በላይ ለራስ ማትረፍ ነው፡፡ ለድጋፍ የነሳሱ ወገኖችም በሞቅታ ሳይሆን ከልብ በመነጨ ልግስናና ደግነት ቃላቸውን እንዲጠብቁ፣ ኅብረተሰቡም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ማሳሰብ ግድ ይላል፡፡

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት