Thursday, July 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የንግድ ቤቶችን የኪራይ ውል ቀነ ገደብ አራዘመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በሚያከራያቸው ንግድ ቤቶች ላይ የኪራይ ዋጋ ጭማሪ ካደረገ በኋላ፣ ደንበኞች አዲስ ውል እንዲገቡ ባስቀመጠው ቀነ ገደብ በርካታ ደንበኞች በብዛት በመምጣታቸውና መጨናነቅ በመፈጠሩ ቀነ ገደቡን አራዘመ፡፡

ኮርፖሬሽኑ ደንበኞች አዲስ ውል እንዲገቡ ያስቀመጠው ቀነ ገደብ እስከ ቅዳሜ ጥር 25 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ነበር፡፡ ቀነ ገደቡ ሊጠናቀቅ ሁለት ቀናት ሲቀረው በርካታ ደንበኞች በመጉረፋቸውና ከፍተኛ መጨናነቅ በመፈጠሩ ቀነ ገደቡ እስከ የካቲት 05 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ መራዘሙን አስታውቋል፡፡

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች በአጠቃላይ 6,635 የንግድና የድርጅት ቤቶችን ያስተዳድራል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ 507 የንግድ ቤቶች በድሬዳዋ፣ 6,128 የሚሆኑት ደግሞ በአዲስ አበባ ይገኛሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከሚገኙ 188 ያህል የንግድ ቤቶች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አካል ጉዳተኞችን ለመሳሰሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተከራዩ በመሆናቸው በዋጋ ጭማሪው አልተካተቱም፡፡

በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ከተማ ውል እንዲገቡ የሚጠበቁት 5,947 ደንበኞች ሲሆኑ፣ እስከ ሰኞ ጥር 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ብቻ 3,204 ደንበኞች ውል መግባታቸው ተገልጿል፡፡

ከበርካታ አሠርት ዓመታት በኋላ ኮርፖሬሽኑ አዲስ የዋጋ ጭማሪ ሲያስተዋውቅ ከደንበኞች ቅሬታዎች ተነስተው ነበር፡፡

ቅሬታ አቅራቢዎቹ የኪራይ ዋጋ ጭማሪውን ባይቃወሙም፣ ጭማሪው የተጋነነ ነው የሚል አቋም በመያዝ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ድረስ አቤቱታ አቅርበው ነበር፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ምላሽ ባይታወቅም፣ በኮርፖሬሽኑና ኮርፖሬሽኑን የሚቆጣጠሩ ተቋማት ማለትም የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፣ የኮርፖሬሽኑ ማኔጅመንት ካውንስልና የኮርፖሬሽኑ ሥራ አመራር ቦርድ የኪራይ ጭማሪውን ሲደግፉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ለኪራይ ለጭማሪው ይሁንታውን ሰጥቷል፡፡

ኮርፖሬሽኑ የኪራይ ዋጋ ጭማሪ ያደረገበትን ምክንያት ሲገልጽ፣ ለበርካታ ዓመታት አንድ ቦታ ላይ ቆሞ የቀረው የኪራይ ተመን በየወቅቱ እየጨመረ ከሚገኘው የገበያ ዋጋ ጋር በከፍተኛ ደረጃ መራራቁ ሚዛናዊነቱን አሳጥቶታል ብሏል፡፡

ከግሉ ዘርፍ ንግድ ቤቶችን ተከራይተው በሚሠሩ ነጋዴዎች ላይ የገበያ አመረጋጋት የተፈጠረ ከመሆኑም በላይ፣ የኮርፖሬሽኑ ቤቶች ዝቅተኛ የኪራይ ዋጋ የሚከፈልባቸው በመሆናቸው በዜጎች መካከል ፍትሐዊ ያልሆነ የሀብት ክፍፍል እንዲከሰት አድርጓል ብሏል፡፡

ፍትሐዊ የገበያ ከባቢ ተፈጥሮ የሚገኘው የኪራይ ገቢ ተጨማሪ መኖሪያ ቤቶችን፣ ተጨማሪ የንግድና የድርጅት ቤቶችን ለመገንባት የሚውል ስለሆነ ለማኅበረሰቡ የሚሰጠው ጠቀሜታ የጎላ እንዲሆን ያደርገዋል ሲል ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል፡፡

ማኅበራዊ ኃላፊነት ከመወጣት አንፃር ኮርፖሬሽኑ እሑድ ጥር 26 ቀን 2011 ዓ.ም. ለመቄዶኒያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ድርጅት አምስት ሚሊዮን ብር፣ ፒያሳ አካባቢ ለሚያካሂዳቸው ግንባታዎች 500 ሺሕ ሜትር ኩብ ጠጠርና 200 ሺሕ ብር ግምት ያላቸው አሮጌ የቢሮ ዕቃዎች መለገሱን አስታውቋል፡፡

የፒያሳው የንግድ ድርጅት ለሦስት ዓመታት ከኪራይ ነፃ የተሰጠ መሆኑን፣ አረጋውያኑ የሚያመርቷቸው የዕደ ጥበብ ውጤቶች መሸጫ ይሆናል ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች