Sunday, April 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበደቡብ ጎንደር መስጊዶችን ባቃጠሉ ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ ተጠየቀ

በደቡብ ጎንደር መስጊዶችን ባቃጠሉ ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ ተጠየቀ

ቀን:

በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ እሑድ ጥር 26 ቀን 2011 ዓ.ም. በሦስት መስጊዶች ላይ ቃጠሎና ንብረት የማውደም ድርጊት ከተፈጸመ በኋላ፣ በአካባቢው ለሚገኙ ወጣቶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ምክክሮች ሊደረጉ መሆኑን ተገለጸ፡፡ በአጥፊዎች ላይ ደግሞ ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወሰድ ተጠይቋል፡፡

በእስቴ ወረዳ ቀበሌ 03 ውስጥ የሚገኙ ሁለት መስጊዶች ላይ ሙሉ በሙሉ ማቃጠል፣ እንዲሁም በግንባታ ላይ የነበረ ሦስተኛ መስጊድ ላይ የማፈራረስ ድርጊት በአካባቢው ወጣቶች መፈጸሙን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ጥር 26 ቀን 2011 ዓ.ም. ከቀኑ 10 ሰዓት አካባቢ የተፈጸመው ይህ ድርጊት፣ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ በሆኑ የአካባቢ ነዋሪዎች የሠርግ ሥነ ሥርዓት ወቅት ነው፡፡ ዳስ ለማሳመር ከማተሚያ ቤት ተቆራርጦ በመጣ የወረቀት ማስጌጫ ውስጥ አብሮ ተገኘ በተባለ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ሥዕል ጋር በተያያዘ ድርጊቱ መፈጸሙ ተገልጿል፡፡

የቤተ እምነቶቹን መቃጠል እንደተሰማ ወደ ቦታው ጉዳዩን የሚያጣራ ቡድን መላኩንና ግርግሩም ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይሠራጭ የማረጋጋት ሥራ መከናወኑን፣ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ሼክ ሙሐመድ ሐሰን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹ቡድኑ ባቀረበለን ሪፖርት መሠረት ድርጊቱ በስሜት በተነሳሱ የአካባቢው ወጣቶች መፈጸሙን ለማወቅ ችለናል፤›› ሲሉ ሼክ ሙሐመድ አክለዋል፡፡

ከቤተ እምነቶቹ ማቃጠልና ማፈራረስ ባለፈም በአካባቢው የሚኖሩ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች የንግድ ተቋማት መዘረፋቸው ተገልጿል፡፡

‹‹ይህ የሚያሳየን ጉዳዩ ሃይማኖታዊ አለመሆኑን ነው፡፡ የትኛውንም አማኝ አይወክልም፤›› ሲሉ ሼክ ሙሐመድ አስረድተዋል፡፡

በወቅቱ ሱቅና ንግድ ተቋማት ዘረፋ ሲካሄድ በአካባቢው የነበሩ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ድርጊቱን በመቃወም ዘረፋውን ማስቆማቸውን ዋና ጸሐፊው ተናግረዋል፡፡ ድርጊቱን በፈጸሙት ላይ መንግሥት ተገቢውን ሕጋዊ ዕርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡

እስካሁን ድርጊቱን መፈጸማቸው የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ለመያዝ ማጣራት እየተደረገ መሆኑን፣ በዋናነት ግን ለሁለቱም ሃይማኖቶች ምዕመናን የጋራ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እንደሚከናወን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ድርጊቱን በተመለከተ መግለጫ የወጣው የአማራ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔም ጉዳት ያደረሱትን አካላት አውግዟል፡፡ የጉባዔው ተወካይና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ዋና ጸሐፊ መላከ ብርሃን ፍሰሐ ጥላሁን በበኩላቸው፣ ድርጊቱን ቤተ ክርስቲያኑ አጥብቃ እንደምታወግዝ ገልጸዋል፡፡

‹‹የፈረሰውን መስጊድ ከእስልምና እምነት ተከታዮች ጋር በመሆን አብረን እንሠራዋለን፡፡ ድርጊቱን የፈጸሙ አካላትም ተጣርተው ወደ ሕግ መቅረብ አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡

በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የከተማ ልማትና የኮንስትራክሽን አማካሪ አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) ወደ አካባቢው በመሄድ የሙስሊሙን ማኅበረሰብና ሌሎች ነዋሪዎችን አነጋግረዋል፡፡ ጉዳት የደረሰባቸውን ጭምር በማፅናናት፣ አጥፊዎች ለሕግ መቅረብ እንዳለባቸውና መስጊዶችም በትብብር በተቻለ ፍጥነት እንዲገነቡ መመቻቸት እንዳለበት መናገራቸው ታውቋል፡፡

የአማራ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ የሱፍ ማሩ፣ በመስጊዶቹ ላይ የተፈጸመው ድርጊት ሰላም የማይፈልጉ ኃይሎች መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መልካም እሴቶች በነበሩበት እንዲቀጥሉ የእምነት ተቋማትና መሪዎች ምዕመኖቻቸው ከእንዲህ ዓይነት ድርጊት እንዲቆጠቡ ማስተማር እንዳለባቸው፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ ሰላም የማይፈልጉ ኃይሎች የፈጠሩት ሴራ ስለሆነ መንግሥት አስፈላጊውን የሕግ ዕርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኦቲዝምን ለመቋቋም በጥምረት የቆሙት ማዕከላት

ከኦቲዝም ጋር የሚወለዱ ልጆች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ...

አወዛጋቢው የወልቃይት ጉዳይ

የአማራና ትግራይ ክልሎችን እያወዛገበ ያለው የወልቃይት ጉዳይ ዳግም እየተነሳ...

ተጠባቂው የቴሌኮም ኦፕሬተሮች የውድድር መለኪያ የሆነው የሞባይል ገንዘብ ዝውውር በኢትዮጵያ

የሞባይል ገንዘብ ዝውውር የሞባይል ስልክን በመጠቀም ሊገኙ የሚችሉ የፋይናንስ...

የአማራና ደቡብ ክልሎች ለሠራተኛ ደመወዝ መክፈል መቸገራቸውን የፓርላማ አባላት ተናገሩ

በአማራና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት...