አሜሪካዊው ሳሙኤል ሃንቲንግተን (ፕሮፌሰር) የዴሞክራሲ ሥርዓትን መገንባትና ማፅናት እንዴት ይቻላል? ወደዚህ መንገድ የሚወስዱ መሠረታዊያንስ ምንድን ናቸው? በሚሉ ጉዳዮች ላይ በመመራመርና በመተንተን ከመታወቁም በላይ፣ ከዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪ የፖለቲካ ሳይንቲስቶች መካከል ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው፡፡
በተለይ እ.ኤ.አ. በ1991 ያሳተመው “The Third Wave Democratization in The Late 20th Century” የተሰኘው መጽሐፍ ከሚታወቅባቸው የምርምር ሥራዎቹ መካከል አንዱ ነው፡፡ ዝነኛው የፖለቲካ ሳይንቲስት ሳሙኤል ሃንቲንግተን ይኼንን መጽሐፉን ያሳተመበት ዓመት፣ ለ17 ዓመታት እልህ አስጨራሽ የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ የነበረው ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን ሲመራ በነበረው ወታደራዊ መንግሥት ላይ ድል ከተቀዳጀበት 1983 ዓ.ም. ጋር ይገጣጠማል፡፡
ይህ አሜሪካዊ የፖለቲካ ሳይንቲስት የተጠቀሰውን መጽሐፍ ካሳተመ ወይም ኢሕአዴግ የትጥቅ ትግሉን አሸንፎ ሥልጣን ከያዘ ከሁለት ዓመት በኋላ፣ ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማሸጋገር ወጥኖ ደፋ ቀና ሲል የነበረውን የወቅቱን የሽግግር መንግሥት ለማማከር በሕይወቱ ለመጀመርያ ጊዜ በአዲስ አበባ በመገኘት የአንድ ሳምንት ቆይታ አድርጎ የነበረ ሲሆን፣ በወቅቱ ተቋቁሞ የነበረውን የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን አባላት ከሌሎች የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልሂቃንና የሽግግር መንግሥት ፕሬዚዳንት ከነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ ጋር ጥልቅ ውይይት ማድረጉን በመጥቀስ፣ በወቅቱ የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለመገንባት አማራጭ ነው ያለውን ምክረ ሐሳብ አቅርቦ እንደነበር በዚሁ የምክረ ሐሳቡ የማጠቃለያ ሰነድ ላይ ሠፍሮ ይገኛል፡፡
‹‹ከሽግግሩ መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ መለስ ዜናዊ ጋር በተገናኝንበት ወቅት በቅድሚያ ያነሱልኝ ጥያቄ “The Third Wave” የተሰኘውን መጽሐፉህን አንብቤዋለሁ፡፡ በዚህ መጽሐፍ ላይ አገሮች ወይም መንግሥታት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ማስፈን የሚችሉት ወደ ኢኮኖሚ ሀብት ሽግግር ካደረጉ (ሀብታም ከሆኑ) በኋላ ነው የሚል ትንታኔ አስፍረዋል፡፡ ኢትዮጵያ በጣም ደሃ አገር ነች፡፡ ወደ ኢኮኖሚ ልማት ለመሸጋገርም በእጅጉ ሩቅ ነች፡፡ ስለዚህ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በዚህ ሁኔታ በኢትዮጵያ መገንባት አይቻልም? የሚል ነበር፤›› ሲል የነበረውን አጋጣሚ በማስታወስ፣ ለጥያቄው በወቅቱ የሰጠውን ምላሽና ማብራሪያ በሰነዱ ላይ አስፍሯል፡፡ ይኼንን ጥያቄ አቶ መለስ ሊያነሱ እንደሚችሉ ግምት የነበረው መሆኑን፣ ነገር ግን በቀጥታ ይሆናል ብሎ እንዳላሰበ የገለጸው ፕሮፌሰር ሃንቲንግተን በወቅቱ ለጥያቄው በቀጥታ ከመመለስ ይልቅ ዘርዘር ያለ ምላሽ መስጠት መምረጡን ይገልጻል፡፡
በዚህም መሠረት የሰጡት ምላሽ ከ1985 ዓ.ም. በፊት በነበሩት 20 ዓመታት ውስጥ 35 የዓለም አገሮች ከጨቋኝ የፖለቲካ ሥርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሸጋገራቸው፣ አገሮችም ከሞላ ጎደል ባስመዘገቡት የኢኮኖሚ ልማት የዜጎቻቸው ዓመታዊ አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከ1,500 እስከ 2,000 ዶላር ወይም ከዚያ በላይ መሆኑን እንደገለጸላቸው በሰነዱ ላይ አስፍሯል፡፡ ‹‹በኢኮኖሚ ዕድገትና በዴሞክራሲ መካከል ግንኙት ባለመኖሩ ጥሩ ምክንያታዊ መሠረቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ መንግሥታት የተሻለ የኢኮኖሚ ልማት ባስመዘገቡ ቁጥር በሚመሩት አገር ከተሜነት ወይም የከተማ መስፋፋት ይከሰታል፡፡ ከድህነትና ከተፅዕኖዎቹ ለመውጣት መነሳሳት ይፈጠራል፡፡ የተማረና ዕውቀትን መሠረት አድርጎ የሚመዝን ማኅበረሰብ ቁጥር ይጨምራል፡፡ መካከለኛ ገቢ የሚኖራቸው የማኅበረሰብ ቁጥርም እንዲሁ የሚጨምር በመሆኑ የሀብት ክፍፍል ልዩነቶች ይጠባሉ፡፡ የሀት ክፍፍሉ ሚዛን እየጠበቀ ስለሚሄድና ይህም ተጨማሪ ሀብትም የመፈጠሩ ዓይቀሬነትን አመላካች በመሆኑ የፖለቲካ ሥርዓቱ ከመቆራቆዝ ይልቅ መመቻመችንና መቻቻልን እንዲመርጥ ያደርገዋል፤›› ሲሉ ስለሰጡት ማብራርያ ተንትኗል፡፡
በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳም ከሲንጋፖር በስተቀር ሁሉም የነዳጅ ሀብት የሌላቸው ከፍተኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማስፈናቸውን፣ እንዲሁም ከህንድ በስተቀር ሁሉም ደሃ አገሮች ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ማስፈን እንዳልቻሉ ለአቶ መለስ ዜናዊ እንዳብራራላቸው በወቅቱ ያቀረበውን ምክረ ሐሳብ የከተበው ማጠቃለያ ሰነድ ያስረዳል፡፡
በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያውያን ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ 150 ዶላር ብቻ የነበረ በመሆኑ፣ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታው ወደ ዴሞክራሲ ለሚደረግ ሽግግር ምቹ አለመሆኑን ይከራከራል፡፡ ሌሎች በወቅቱ የነበሩ ነባራዊ ሁኔታዎችም የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመትከል ምቹ ሆነው እንዳላገኛቸው የሚገልጸው ፕሮፌሰር ሃንቲንግተን፣ የብሔርን ፅንፍ ይዞ የተከፋፈለ ብዝኃነት ያለው የፖለቲካ ማኅበረሰብ መኖሩ በራሱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማስፈን በኢትዮጵያ ለመመሥረት አያስችልም ባይባልም፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመትከል የሚደረገውን ሒደት ውስብስብ እንደሚያደርገው አስታውቋል፡፡ የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲፈጠር ምቹ መደላድል የሆኑት የሲቪል ማኅበራት፣ የንግድ ማኅበራት፣ የሚዲያ ተቋማት፣ የሠራተኛ ማኅበራትና ሌሎች መሰል ተቋማት አለመኖራቸው ለሒደቱ ምቹ ሁኔታ ስላለመኖሩ በአመላካችነት ጠቁሟል፡፡
ይሁን እንጂ በተቃራኒው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመትከል ውስን ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውንም በወቅቱ አመላክቶ ነበር፡፡ ከእነዚህም መካከል ኢትዮጵያ ታሪካዊና ለረዥም ዓመታት የዘለቀ መንግሥታዊ ሥርዓትና ነፃ አገር መሆኗ፣ የፖለቲካ ማኅበረሰቡ በአመዛኙ ለሕግ፣ ለሃይማኖትና ለባሕላዊ እሴቶች ተገዥ መሆኑ፣ እንዲሁም በወቅቱ የነበሩ ውጫዊ ከባቢያዊ ሁነቶች በኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ለመትከል ምቹ እንደነበሩ ያትታል፡፡
በመሆኑም አቶ መለስ ዜናዊ አቅርበውለት ለነበረው መሠረታዊ ጥያቄ ሰጥቶት የነበረውን ምላሽ ሲያጠቃልልም፣ ‹‹አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ሌሎች መደላድሎች ሚዛናቸውን የሳቱ በመሆናቸው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በዚህ ወቅት ለመትከል ምቹ ሁኔታ አለ ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን ይህ ማለት ማንኛውንም ዓይነት የዴሞክራሲ ሥርዓት በኢትዮጵያ ለመትከል ፈጽሞ አይቻልም ማለት አይደለም፡፡ የምዕራባውያን መሰል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመመሥረት ግን እንደማይቻል እርግጥ ነው፡፡ ነገር ግን የተለየ ዓይነት የዴሞክራሲ ሥርዓት መመሥረት ይቻላል፡፡ ለዚህ የሚያስፈልገው የፖለቲከኞች ቁርጠኛ መሆንና ለዚህ ዓላማ ራሳቸውን የመስጠታቸው ጉዳይ ነው፤›› ብለሏል፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማሸጋገር ምቹ ሁኔታዎች ምንድናቸው የሚለውን መለየት፣ ለዚህ ምቹ አማራጭ የሚሆነውን የፖለቲካ ሥርዓትና የመንግሥት አወቃቀር ማጥናት፣ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ ከተፈጠረ በኋላ ዴሞክራሲውን ለማፅናት መሠረታዊ መርሆዎችን በአቅጣጫነት መለየት እንደሚያስፈልግ በመግለጽ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመጀመር የአውራ ፓርቲ የፖለቲካ ሥርዓት ምቹና አዋጭ እንደሚመስለው አመላክቶ ነበር፡፡ ለዚህ የሚሰጠው ምክንያትም በመጀመርያ ውጤታማ መንግሥትን ማደራጀት ለዴሞክራሲ አስፈላጊ እንደሆነው ሁሉ፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትንም መጀመር በእኩል አስፈላጊ መሆኑን ያስረዳል፡፡
ዝነኛው የፖለቲካ ሳይንቲስት ይኼንን ምክረ ሐሳብ ካቀረበ 26 ዓመታት አልፈዋል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ውስጥም ኢትዮጵያን ሲያስተዳድር የቆየውና አሁንም በሥልጣኑ ላይ የሚገኘው ኢሕአዴግ በመጀመርያ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን፣ በኋላም ወደ አውራ ፓርቲ መድብለ ሥርዓት ራሱን በማሸጋገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመትከል ያደረጋቸው ሙከራዎች አልተሳኩም፡፡ ይሁን እንጂ በእነዚህ ዓመታት የአገሪቱን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ ማሳደጉ በአዎንታዊነት ሲጠቀስ፣ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ለውጥ መፍጠር አለመቻሉ ደግሞ በአሉታዊነት ይታያል፡፡ ሙከራዎቹ ሁሉ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሳያሸጋግሩት መክነው በአገሪቱ ህልውና ላይ ሥጋት ደቅኖ እንደነበር፣ በኢሕአዴግ ውስጥ በድንገት ብቅ ያሉ ተራማጅ ኃይሎች ባደረጉት ውስጣዊ ትግል ሥጋቱን ቀልብሰው አገሪቱን የማዳን ተልዕኮ ውስጥ ገብተዋል፡፡
በዚህም መሠረት ሁሉም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች በአገራቸው ጉዳይ በነፃነት እንዲሳተፉ ማድረግ መጀመራቸው ተጠቃሽ ነው፡፡ በኢሕአዴግ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እየተመራ የሚገኘው ተራማጅ ኃይል፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በኢትዮጵያ ለመትከል ቅድሚያ ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ተግባራዊ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል፡፡
አፋኝ ፖለቲካዊ ሕጎችን ለማንሳትና የሲቪል ማኅበራትን ተሳትፎ ለመፍቀድና ሌሎች ተግባራትን ለማከናወን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡ ወደ አገር ከገቡ ተፅዕኖ ፈጣሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር በመሆንም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓትን ለምን መመሥረት አዳጋች እንደሆነ፣ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚወስድ አማራጭ መንገድን በጋራ ለመለየት ጥናት ላይ የተመሠረቱ ውይይቶች ተጀምረዋል፡፡ ቅዳሜ ጥር 25 ቀን 2011 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሌሎች ሦስት ተፅዕኖ ፈጣሪ ፖለቲከኞች በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመትከል አስቸጋሪ ያደረገው ምን እንደሆነና አማራጮቹን በተመለከተ ጽሑፎች አቅርበዋል፡፡
የሰሞኑ ውይይት
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተደረገው ውይይት ላይ ጽሑፋቸውን ካቀረቡት መካከል የግንቦት ሰባትና አርበኞች ግንባር ሊቀመንበር ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ይገኙበታል፡፡ እሳቸው ያቀረቡት ጥናት በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመትከል የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚናን የተመለከተ ቢሆንም፣ ያቀረቡት የጥናት ወረቀት በስፋት የዳሰሰው ግን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምንነትን በሊበራሊዝም የፖለቲካ ፍልስፍና መነጽር የተመለከተ ነበር፡፡
አንድ የጋራ ፖለቲካ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የጋራ ሕይወታቸውን በሚመለከት የሚወስኗቸው ውሳኔዎች በእኩልነት መሆናቸውን፣ እነዚህ እኩል የሆኑ ማኅበረሰቦች በጋራ በሚወስኗቸው ውሳኔዎች የአገሪቱ ከፍተኛ የሥልጣን አካል ወይም ሉዓላዊ የሥልጣን መገለጫ መሆናቸው የዴሞክራሲ ሥርዓት መሠረታዊ ፍልስፍና መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የዚህ የእኩልነት መርህ መንግሥት በሚባለው ተቋማዊ ሥርዓት ላይም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የመሳተፍ መብትን የሚሰጥና ይህ ውክልናም በምርጫ ሥርዓት የሚፈጸም መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአጠቃላይ የዴሞክራሲ ሥርዓት መገንባት ያለበት የፖለቲካ ማኅበረሰቡ አካል የሆኑ ግለሰቦችን ቃል ያለ ምንም ልዩነት በእኩልነት አሳትፎ፣ የጋራ ውሳኔ የሚሰጡበትንና በዚህም የሥልጣን ባለቤት መሆናቸውን ማረጋገጡ ላይ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
የእነዚህ እኩል የሆኑ የአንድ ፖለቲካ ማኅበረሰብ አባላት ፍላጎታቸውን ተደራጅተው እንደሚገልጹና ይህም የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሚና እንደሚወክል ጠቁመዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና የፖለቲካ ማኅበረሰቡን የማቀናጀት፣ የማሰባሰብ፣ የማኅበረሰቡን ፍላጎት የመወከልና የማስጠበቅ እንደሆነ፣ በዚህ ሒደት ውስጥ ፓርቲዎች የአገርን አንድነትና ቀጣይነት የማስጠበቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡
በአንድ አገር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመትከል ስንት ፓርቲዎች ያስፈልጋሉ ብሎ በቁጥር መወሰን እንደማይቻል፣ ነገር ግን የምርጫ ሥርዓቱ ዓይነት የፓርቲዎችን ቁጥር ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ሊቀንሰውም ሊጨምረውም እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሁኔታ የፓርቲዎች ቁጥር አስቸጋሪ የሆነው ፓርቲዎች የማኅበረሰብን ጥቅምና ፍላጎት ለማስጠበቅ ከመደራጀት ይልቅ፣ ብሔርን ለመወከል መደራጀታቸው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በዚህ መንገድ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመትከል አስቸጋሪ እንደሚሆን አስታውቀዋል፡፡
አሁን በኢትዮጵያ ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎች አመለካከትና ርዕዮተ ዓለም በተመለከተ ብዙ ልዩነት እንደሌለ በመግለጽ፣ በያንዳንዱ ብሔረሰብ ስም በፓርቲ መደራጀት ትርጉም እንደሌለውና የተረጋጋ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለማስፈን ምቹ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመሩትን ፓርቲ ወክለው ሳይሆን በግላቸው፣ ‹‹የዴሞክራሲ ባህል በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ ሥር የዳበሳ ጥናታቸውን አቅርበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያቀረቡት ጥናታዊ ዳሰሳ ትኩረቱን በዋናነት ያደረገው ‹‹የዴሞክራሲ መርህ ላይ የቆመ አገር ነው የሚያስፈልገው? ወይስ ዴሞክራሲን ሊሸከም በሚችል ባህል ላይ የቆመ ማኅበረሰብ ነው የሚያስፈልገው?›› በሚሉ ሁለት ጭብጦች ላይ ነበር፡፡
በዴሞክራሲ ሥርዓት ላይ የቆመ አገር መገንባት በራሱ ዴሞክራሲን የሚከተል አገር ማለት እንዳልሆነ፣ በዴሞክራሲ መርሆች ላይም ዋልታ ረገጥ ክርክር እንጂ ወጥ የሆነ ስምምነት አለመኖሩን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንዳንድ ማሳያዎችንም አመላክተዋል፡፡
ከእነዚህም መካከል የፕሮፌሰር ሃንቲግተን “The Third Wave” የተሰኘ መጽሐፍ በመጥቀስ፣ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የዴሞክራሲ መርህ በመዘርጋት ለመቆም ከሞከሩ 36 አገሮች መካከል ስድስቱ ወደ ነበሩበት መመለሳቸውን፣ በአፍሪካ ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ 42 አገሮች ዴሞክራሲን የመንግሥታቸው መገለጫ ቢያደርጉም አንዳቸውም ዴሞክራሲን ያፀኑ አለመሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም አገሮች ዴሞክራሲን ይሻሉ እንጂ ትግባራ ማድረግ አለመቻላቸውን፣ ኢትዮጵያም በዚህ መሻት ውስጥ የወደቀችና እርስ በእርስ የሚቋሰሉ ፖለቲከኞች ላለፉት 50 ዓመታትና አሁንም የሚፋለሙባት መሆኗን ገልጸዋል፡፡
ይህ የሆነበት ምክንያት ለዴሞክራሲ ከሚኖር የዓተያይ ዝንፈት እንደሚመነጭ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ዴሞክራሲ በሁለት ዋና መንገዶች እንደሚታይ ጠቁመዋል፡፡
አንደኛው መንገድ ዴሞክራሲውን በሒደት የሚያይ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ዴሞክራሲን በውጤት የሚለካ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
የመጀመርያው ዕይታ ዴሞክራሲን በሒደት የሚመለከት በመሆኑ፣ ምርጫ መደረጉ ወይም የዴሞክራሲ መርሆች መሟላታቸው ላይ የሚያተኩር ስለሆነ ዴሞክራሲን የገነባ እንደሚመስለው ገልጸዋል፡፡
እሳቸው የሚመሩት ኢሕአዴግም በሒደቱ ብቻ ሳይሆን በውጤቱም እንደሚተች፣ በማሳያነትም ምርጫ ቢያካሂድም ነገር ግን ሁሌ የሚያሸንፈውና መንግሥት የሚመሠርተው ራሱ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በመሆኑም በኢትዮጵያ ሁኔታ ዴሞክራሲን ከሒደትም ከውጤትም አንፃር አዳብሎ መካከለኛውን መምረጥ እንደሚገባ፣ ለዚህ እንዲረዳም በዋናነት ዴሞክራሲን የሚሸከም ባህልና ማኅበረሰብ መፍጠር ቀዳሚ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በዚህ መንገድ ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ሁኔታ ጊዜ የሚወስድ ሒደት፣ ምናልባትም በሚቀጥሉት 50 ዓመታት ውስጥ ለማፅናት አልሞ መንቀሳቀስ ብቸኛው አማራጭ እንዲሆን የሚያደርገው ዴሞክራሲን መሸከም የሚችል ማኅበረሰብ ገና አለመፈጠሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ሌሎች ጥናታዊ ጽሑፎች ያቀረቡት መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) መድረክ በመባል የሚታወቀው የፓርቲዎች ስብስብ ሊቀመንበር ናቸው፡፡ እሳቸው ያቀረቡት ጥናት ዴሞክራሲን በፌዴራላዊ ሥርዓት ውስጥ የሚመለከት ነው፡፡
ባቀረቡት ጽሑፍም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ብዝኃነት ባለበት በተለይም ቋንቋንና ማንነትን መሠረት ያደረገ ብዝኃነት በሚስተናገድበት አገር ውስጥ ሊገነባና ሊፀና የሚችለው፣ በፌዴራሊዝም የመንግሥት መዋቅር ውስጥ መሆኑን አመላክተዋል፡፡ በዋናነትም በፌዴራሊዝም ሥርዓት ውስጥ የሚገነባ ዴሞክራሲ የሕዝቦችን ብዝኃነት ከእነ መብታቸው ጠብቆ አንድ ሊያደርግ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
ሌላው ጥናት አቅራቢ የቀድሞ የሕወሓት አባል የነበሩት አቶ አረጋዊ በርሔ ሲሆኑ፣ እሳቸውም ዴሞክራሲ ሊመሠረትና ሊፀና የሚችለው የተረጋጋና በሕግ የሚመራ መንግሥታዊ ሥርዓት ሲፈጠር መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ከ26 ዓመታት በኋላ ዳግም ዴሞክራሲ እንዴት መገንባት እንደምትችልና ወደዚያ የሚወስደውን መንገድ በፖለቲካ ልሂቃኖቿ በኩል ለመለየት ጅማሮ ውስጥ መሆኗ ብዙዎችን ያስማማል፡፡