ኢትዮ ቴሌኮም በ2011 ዓ.ም. አጋማሽ ከ16 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ እንዳስመዘገበ ያስታወቀው የልማት ድርጅቱ፣ የትርፍ መጠንና ሌሎች ክንውኖቹን የሚያሳይ ሪፖርትም ይፋ አድርጓል፡፡
ሰኞ፣ ጥር 27 ቀን 2011 ዓ.ም. መግለጫ የሰጠው ኩባንያው፣ በግማሽ ዓመቱ 20.86 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት አቅዶ ነበር፡፡ ይሁንና 16.71 ቢሊዮን ብር አግኝቷል፡፡ አፈጻጸሙ ከዕቅዱ አንፃር 80 በመቶውን እንዳሳካ ያሳያል፡፡ አጠቃላይ ትርፉም 11.8 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ከዕቅዱ አንፃር 91 በመቶ ማሳካቱን አስታውቋል፡፡
በግማሽ ዓመቱ ከተገኘው ገቢ ውስጥ ከሞባይል ተጠቃሚዎች 63.2 በመቶ፣ ከዳታና ኢንተርኔት 28.7 በመቶ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ጥሪዎች 5.5 በመቶ ድርሻ መገኘቱ ጠቅሷል፡፡ ከዚህ ክንውኑ በተጓዳኝ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ አራት ቢሊዮን ብር ለታክስ፣ ሦስት ቢሊዮን ብር የትርፍ ድርሻም ለመንግሥት ገቢ እንዳደረገ ይፋ አድርጓል፡፡
ከተቋሙ መረጃዎች እንደሚታየው፣ በግማሽ ዓመቱ ያገኘው ገቢና ትርፍ በዕቅድ ካስቀመጠው ብቻም ሳይሆን፣ ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅትም ቅናሽ የታየበት ነው፡፡ በስድስቱ ወራት ያገኘው ገቢና ትርፍ ከዓምናው አኳያ በንጽጽር ባይቀርብም ከኩባንያው የዓምና ግማሽ ዓመት መረጃዎች አኳያ፣ የዘንድሮው ገቢ ከ1.7 ቢሊዮን ብር በላይ፣ ትርፉም ከ1.4 ቢሊዮን ብር ቅናሽ ታይቶበታል፡፡
በመግለጫው የዘንድሮው ገቢና ትርፉ የቀነሰባቸው ምክንያቶች በቀጥታ ባይገለጹም፣ የኩባንያውን ገቢ ከማሳደግና የተገልጋዩን ዕርካታ ከመጨመር አኳያ ከ40 እስከ 50 በመቶ የአገልግሎት ታሪፍ ቅናሽ ማድረጉ በገቢ ላይ ጫና ሊፈጥር እንደሚችል ታሳቢ መደረጉን ጠቁሟል፡፡ ይሁንና ተጨማሪ የአገልግሎቱ ደንበኞችን ማፍራት፣ አገልግሎቱንም በብዛት እንዲጠቀሙ የሚያበረታቱ ዕርምጃዎች ስለመወሰዳቸው ተገልጿል፡፡ የአገልግሎት ጥራትና ቅልጥፍናን ማሻሻል፣ አዳዲስ አገልግሎቶችን ለገበያ ማቅረብ፣ ወጭ ቆጣቢና የውጭ ምንዛሪ አመንጪ ሥራዎች ላይ ማተኮር፣ የሠራተኛን ምርታማነት ማሳደግ እንዲሁም የአመራሩን አቅምና የውሳኔ ሰጪነት ሚና የሚያጎለብቱ ዕርምጃዎች ላይ ትኩረት መደረጉን ኩባንያው ይገልጻል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ከወራት በፊት በአገልግሎቶቹ ላይ የዋጋ ቅናሽ ሲያደርግ ገቢው ላይ ተፅዕኖ እንደማያደርግበት መግለጹ አይዘነጋም፡፡ ይሁን እንጂ የስድስት ወራት አፈጻጸሙ ገቢው መቀነሱን ያሳያል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ፣ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ወቅት፣ የታሪፍ ቅናሹ የተቋሙ ገቢ ላይ ተፅዕኖ አያደርግም ወይ ተብለው ተጠይቀው ነበር፡፡ ገቢው እንደማይቀንስ አስታውቀውም ነበር፡፡
በወቅቱ እንደገለጹት ‹‹ተቋሙ በ2011 በጀት ዓመት ያቀደው ገቢ 47 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ የታሪፍ ቅናሽ አድርገንም የምናገኘው ከ47 ቢሊዮን ብር በላይ መሆን እንደሚችል አረጋግጠን ነው ቅናሹን ያደረግነው፤›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡
የገቢ ቅናሽ የታየበት አፈጻጸሙ ቢጠቀስም፣ የዕለት ሥራዎቹን ግን ውጤታማ በሆነ መንገድ መምራት እንደቻለ አስታውቋል፡፡ የለውጥ ሥራዎችና ለረዥም ጊዜ መፍትሔ ሳይሳጣቸው የቆዩ በተለይም በውጭ ምንዛሪ እጥረትና ወቅታዊ ውሳኔ ሳይሰጣቸው በቆዩ ጉዳዮች ላይ ፈጣን ውሳኔዎችን በማሳለፍ አመርቂ ውጤቶች እንዳስመዘገበ ይጠቅሳል፡፡ የበጀት ዓመቱ ሲጀምር ኩባንያው ከፍተኛ ሥጋት ውስጥ መውደቁን በሥራ አመራር ቦርዱ አቋም ተይዞበት እንደነበር መገለጹ ይታወሳል፡፡ በስድስት ወራት የአፈጻጸም ግምገማው ግን ተቋሙ ከሥጋት ወጥቶ ወደ ተረጋጋና ጤናማ አቋሙ መመለሱን ማረጋገጥ እንደቻለም አስታውቋል፡፡
ከለውጥ ጋር በተያያዘ በትኩረት ከተሠራባቸው ነጥቦች መካከል የአደረጃጀት ለውጥ፣ የአመራርና የሠራተኛ አቅም ግንባታ፣ የአመራሩ የውሳኔ ሰጪነት ሚና ማሳደግ የሚለው ይገኝበታል፡፡ የሥራ ከባቢንና የሥራ ባህልን ማሻሻል፣ የአገልግሎት አሰጣጥና ጥራት ማሻሻል፣ የታሪፍ ክለሳና ከአጋር ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት ማሻሻል፣ የንብረት አስተዳደርና የሀብት አጠቃቀም ላይ ትኩረት በማድረግ ሰፊ ሥራዎች ስለመሥራታቸው በመግለጫው አስታውቋል፡፡
የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ከመቅረፍ አንፃር፣ የውጭ ምንዛሪ ለአገልግሎት ክፍያዎች ማነቆ የማይሆንበት ደረጃ የደረሰ ሲሆን፣ ለተለያዩ አቅራቢዎች መከፈል ያለባቸውን ዕዳዎች በመክፈል ያለውን የቢዝነስ አጋርነት እያጠናከረ እንደሚገኝም ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል፡፡ በስድስት ወራት ውስጥ በውጭ ምንዛሪ ከተከፈለው ዕዳ ውስጥ 51 በመቶው ተቋሙ ባመነጨው የውጭ ምንዛሪ አማካይነት መሆኑ በጥንካሬ ተመልክቶታል፡፡
በአጋማሽ ዓመቱ በተከናወኑ እንቅስቃሴዎች የቴሌኮም ተጠቃሚዎችን ብዛት 44.91 ሚሊዮን ለማድረስ ታቅዶ ክንውኑ 41.11 ሚሊዮን ሲሆን፣ ከዕቅድ አንፃር የ91.5 በመቶ ውጤት እንደተገኘበት ተጠቅሷል፡፡ የሞባይል ተጠቃሚዎች (የድምፅ) 39.54 ሚሊዮን፣ 426 ሺሕ ተጨማሪ የዳታና ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች፣ የመደበኛ ስልክ 1.14 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች ሲመዘገቡ፣ የዳታና የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች 19.49 ሚሊዮን ናቸው፡፡ አጠቃላይ የቴሌኮም ሥርጭቱ 43 በመቶ ስለመድረሱ የሚገልጸው የኩንባንው መግለጫ፣ በስድስት ወራት ውስጥ የመጀመርያቸውን ጥሪዎች ያከናወኑ ደንበኞች ብዛትም 4.17 ሚሊዮን እንደነበሩም ተገልጿል፡፡
በሞባይል መስክ የአገር አቀፍ አማካይ ተደራሽነቱ 91.33 በመቶ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ 98.49 በመቶ፣ የክልሎች 88.47 በመቶ እንደደረሰም ተመልክቷል፡፡ የጥሪ መውደቅ መጠን 0.57 በመቶ እንዲሁም የኢንተርኔት ኔትወርክ የመገኘት መጠን 97.12 በመቶ አፈጻጸም እንዳላቸው የጠቀሰው ኩባንያው፣ የአገልግሎት አሰጣጡን ከማሻሻል አኳያ በሦስት ቀናት ውስጥ 48 በመቶ የድምፅና የዳታ አዲስ መስመሮችን ማስገባት እንዲሁም 86.5 በመቶ የአገልግሎት ጥገና ማከናወን እንደቻለ የሚገልጸው ኢትዮ ቴሌኮም፣ በተጨማሪም የአቅራቢዎችና የአማካሪ ጥገኝነት የሚታይባቸው የሥራ ዘርፎች ላይ ትኩረት በማድረግ የራሱን ባለሙያዎች የማብቃት ሥራዎች እንደጀመረ አስታውቋል፡፡
በስድስት ወራት ውስጥ አጋጥሞት የነበሩ ችግሮችንም በመግለጫው ያመለከተ ሲሆን፣ ከነባሮቹ ችግሮች መካከል የፋይበር መስመሮች መቆራረጥ፣ የቴሌኮም ማጭበርበር፣ የኃይል አቅርቦት መቆራረጥ እንዲሁም የሰው ኃይል አቅም ውስንነቶች ተጠቅሰዋል፡፡
በአጠቃላይ ከአመራር አቅም ማሳደግና የውሳኔ ሰጪነት ሚና ማሳደግ በተጓዳኝ፣ ከተቋማዊ የለውጥ ሥራዎች መሻሻል፣ ከገቢ መጨመርና ወጪ መቀነስ፣ የተቋሙን ስም ከማደስና ከሀብት አጠቃቀምና ንብረት አስተዳደር ጋር በተገናኘ እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ጠንካራ አፈጻጸምና አበረታች ውጤት መታየቱንም አስታውቋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም የቀደሙ ዓመታት የሥራ አፈጻጸሙን የሚያመለክቱት መረጃዎች እንደሚጠቀሙት፣ በ2008 ዓ.ም. አጠቃላይ ገቢው 28.37 ቢሊዮን ብር እንደነበር ነው፡፡ በ2009 ዓ.ም. አጠቃላይ ገቢውን ወደ 33.34 ቢሊዮን ብር ማሳደግ እንደቻለም መረጃዎቹ ያሳያሉ፡፡ ዓምና 37.7 ቢሊዮን ብር ገቢ በማስመዝገብ ዓመቱን እንዳጠናቀቀ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዓመታዊ ሪፖርት ያሳያል፡፡ በዚሁ መረጃ መሠረት፣ ኢትዮ ቴሌኮም በ2008 ዓ.ም. ከታክስ በፊት 12.9 ቢሊዮን ብር፣ በ2009 24.8 ቢሊዮን ብርና በ2010 ዓ.ም. 27.02 ቢሊዮን ብር እንዳተረፈ አስፍሯል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በአሁኑ ወቅት ያሉት ቋሚ ሠራተኞች ብዛት ከ15 ሺሕ በላይ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 72 በመቶ ወንዶችና 28 በመቶ ሴቶች እንደሆኑም ታውቋል፡፡