Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በኢትዮጵያ 70 በመቶ እናቶች ሳያስቡት ቢያረግዙም እርግዝናውን ይቀበሉታል›› አቶ ዘነበ አካለ፣ የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማኅበር ፕሬዚዳንት

አቶ ዘነበ አካለ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ በሚድዋይፍ በመጀመርያ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡ በሶማሌ ክልል ጎዴ ጤና ኮሌጅ ለአራት ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን፣ በደብረ ብርሃን ሪፈራል ሆስፒታል በሕፃናትና እናቶች ክፍል ደግሞ ለሁለት ዓመት ሠርተዋል፡፡ ከ2008 ዓ.ም. ወዲህ በጤና ሚኒስቴር በመጀመርያ የእናቶች ጤና ኦፊሰር፣ አሁን ደግሞ የእናቶች ጤና ቡድን አስተባባሪ ሆነው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ከ5,000 በላይ አባላት ያሉትን የኢትዮጵያ ሚድዋይፍ ማኅበርን በፕሬዚዳንትነትም ይመራሉ፡፡ ከተቋቋመ ከ25 ዓመታት በላይ ባስቆጠረው የማኅበሩ እንቅስቃሴ ዙሪያ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ ከተቋቋመ ከሁለት አሠርት ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ስላከናወናቸው ሥራዎች ቢገልጹልን?

አቶ ዘነበ፡- ሚድዋይፍ ከሆንኩ አሥር ዓመታት ሆኖኛል፡፡ ማኅበሩ ደግሞ 27 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በዋናነት ሲሠራ የቆየውም እናቶችና ሕፃናት ደረጃውን የጠበቀ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ነው፡፡ ዓላማ አድርጎ የተነሳውም የእናቶችን ጤና ችግር መቅረፍ ነው፡፡ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት በመስጠት የእናቶችን ሞት መቀነስ ሥራችን ነው፡፡ ትልቁ ግቡም የእናቶችንና የሕፃናትን ሞትና ሕመም ዜሮ ማድረግ ባይቻልም መቀነስ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በዓመት 3.2 ሚሊዮን እናቶች ያረግዛሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ በመቶኛ ሲሰላ የሚሞቱ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ያህል?

አቶ ዘነበ፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ መከላከል በማንችላቸው ችግሮች ሦስት በመቶ እናቶች ይሞታሉ ተብሎ ይገመታል፡፡ በምጥ ጊዜ በሚከሰት ድንገተኛ ችግር የጤና ባለሙያው በማይገምተው አጋጣሚ በየትኛውም ዓለም እናት ልትሞት ትችላለች፡፡ ማኅበራችን የሞት ቁጥሩን ለመቀነስ ይሠራል፡፡ በአውሮፓ 16 ከ100 ሺሕ ወላድ እናቶች፣ በአሜሪካ 52 ከ100 ሺሕ እናቶች ይሞታሉ፡፡ በኢትዮጵያ በአጠቃላይም በአፍሪካ ያለው ከዚህ የተለየ ነው፡፡ በአፍሪካ ከ34 እናት አንድ ትሞታለች፡፡ በአደጉት አገሮች ከ3,400 እናቶች አንድ ሞት ይመዘገባል፡፡ የዚህ ምጣኔ ሲታይ ያለው ልዩነት የእናቶች ሞት ለኢትዮጵያ የተሰጠ ይመስላል፡፡ ስለሆነም ቁጥሩን መቀነስ ትልቁ ጥያቄና የቤት ሥራ ነው፡፡ እርግዝና ሁሌም ያለ በመሆኑ እርግዝናውን እንዴት ጤናማ እናድርገው? የሚለውም ዋና ጉዳይ ነው፡፡ ጤናማ ያልሆነ እርግዝና አለ ማለት እናትን እያጣን ነው ማለት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ከወሊድ ጋር በተያያዘ ችግር በዓመት 40 ሺሕ እናቶች ይሞቱ ነበር፡፡ ይህ አሁን ላይ በዓመት 11 ሺሕ ሆኗል፡፡ በተለይ ስለእናቶች ሞትና ምክንያት በቂ መረጃ መገኘት ከጀመረ ወዲህ የእናቶችን ሞት መቀነስ ችለናል፡፡ 

ሪፖርተር፡- የማኅበሩ አስተዋጽኦ እዚህ ላይ ምን ነበር? የሚድዋይፎችን ቁጥር በመጨመር በኩልስ ምን ሠርታችኋል?

አቶ ዘነበ፡- የእናቶችን ሞት ለመቀነስ የሚድዋይፍን ቁጥር መጨመር ወሳኝ ነው፡፡ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት መስጠትም እንዲሁ፡፡ ማኅበሩም ላለፉት አሥር ዓመታት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን ሲሠራ ቆይቷል፡፡ የባለሙያዎች ቁጥርም ጨምሯል፡፡

እንደ አገር ለመጣው ለውጥ የሚድዋይፎች አስተዋጽኦ አለ፡፡ ኢትዮጵያ የእናቶችን ሞት በ75 በመቶ ለመቀነስ ከአሥር ዓመታት በፊት በመጀመሪያው የምዕተ ዓመቱ ግብ ላይ ፈርማለች፡፡ እ.ኤ.አ. 2015 ላይ ከታቀደው 75 በመቶ 72 በመቶ አሳክተናል፡፡ የዓለም አቀፍ መንግሥታትም ኢትዮጵያ ይህንን በማሳካቷ አድንቀዋታል፡፡ በዚህ መጠን የእናቶችን ሞት የቀነሰ የአፍሪካ አገርም የለም፡፡ ይህ ከኢትዮጵያ ጋር በስፋትም ሆነ በሕዝብ ቁጥር በምትቀራረበው ናይጄሪያ በዓመት ከ100 ሺሕ እናቶች 800 ይሞታሉ፡፡ በኢትዮጵያ ከ100 ሺሕ 412 እናቶች ናቸው የሚሞቱት፡፡ ከአፍሪካ አገሮች ሲነፃፀር ኢትዮጵያ መሄድ ባለባት ልክ ሄዳለች፡፡ ይህ ኢትዮጵያ ለሚድዋይፎች ትኩረት ሰጥታ በመሥራቷ የመጣ ነው፡፡ ባለፉት አሥር ዓመታት ዩኒቨርሲቲዎችም ሰፍተዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- የጤና ባለሙያዎችን በማፍራት ረገድ ጤና ኮሌጆች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ የእናንተ ሚና ምን ይመስላል? ምን ያህል ሚድዋይፎች አሉ?

አቶ ዘነበ፡- የመጀመርያው ሥጋት የነበረው የሚድዋይፎች ቁጥር አናሳ በመሆኑ የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ከባድ ይሆናል የሚል ነበር፡፡ ሚድዋይፎችን ማብዛት የእኛ ብቻ ሳይሆን የመንግሥትም ዕቅድ ነበር፡፡ መንግሥት ሚድዋይፎችን ሲያስተምርና ዩኒቨርሲቲዎችን ሲያበዛ እኛ ደግሞ ሚድዋይፎች ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጡ ከኢንተርናሽናል ኮንፌዴሬሽን ኦፍ ሚድዋይፍ ጋር በመሆን እንደግፋለን፡፡ 30 ያህል ዩኒቨርሲቲዎች ሚድዋይፍ በዲግሪ ደረጃ ይሰጣሉ፡፡ ሁሉም ጤና ሳይንስ ኮሌጆችና የግል ጤና ኮሌጆች ይሰጣሉ፡፡ በሚቀጥሉት ዓመታት በሚፈለገው ደረጃ ልክ ይኖረናል፡፡ አሁን ላይ 12,500 ሚድዋይፎች አሉን፡፡

ሪፖርተር፡- የሚፈለገው ደረጃ ምን ያህል ነው?

አቶ ዘነበ፡- እ.ኤ.አ. በ2025 በኢትዮጵያ 25 ሺሕ ሚድዋይፍ ቢኖረን መልካም ነው፡፡ በዓለም ጤና ድርጅት በተሠራው ጥናት መሠረት ኢትዮጵያ ካላት 100 ሚሊዮን ሕዝብ ሲሰላ 50 ሺሕ ሚድዋይፍ ያስፈልጋታል፡፡ ኢትዮጵያ ይህን አሁን ላይ ለማግኘት አቅሟ አይፈቅድም፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ አሁን ላይ 12,500 ሚድዋይፍ ቢኖሩም፣ በብዛት የሚገኙት የክልል ከተማ ላይ ነው፡፡ ሚድዋይፎችም መመደብ በሚገባቸው ቦታ ሁሉ አይመደቡም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ እናቶች ሳያስቡት ያረግዛሉ፡፡ እርግዝናው ከተከሰተ በኋላ ያለው ጥሩ ዜና ግን እርግዝናውን ይቀበሉታል፡፡ ይህ የሚያሳየው ሚድዋይፎቻችን እናቶች ጋር እየደረሱ አለመሆኑን ነው፡፡ እናት ፈልጋ ላረግዝ ነው ብላ መዘጋጀት አለባት፡፡ ለዚህም የቤተሰብ ዕቅድ መጠቀምም ወሳኝ ነው፡፡ እናቶች እርግዝናውን ፈልገው ካረገዙ የጤና ክትትል ስለሚያደርጉ 30 በመቶ ያህል የእናቶችን ሞት መቀነስ እንችላለን፡፡ ሆኖም የሰው ኃይል ስለሌለ ከማርገዟ በፊት እንኳን በቂ ክትትል ለማድረግ ባለሙያ እጥረት አለ፡፡ እርግዝናው አምስት ወራት ካለፈው በኋላ ለክትትል የሚመጡ አሉ፡፡ በመንግሥት መሠራት ያለበት አንዲት እናት ከማርገዟ በፊት፣ በእርግዝና ጊዜ፣ በወሊድና ከወሊድ በኋላ ጤና ድርጅት ሄዳ ክትትል ሳታቋርጥ ማድረግ በምትችልበት ሁኔታ ላይ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- በዚህ ረገድ ለእናቶች ግንዛቤ ማስጨበጡ ፈተና አይሆንም?

አቶ ዘነበ፡- ትልቅ ፈተና ያለው እናቶች ወደ ጤና ተቋም ሄደው ማርገዝ የማርገዝ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው፣ ምክር መውሰድ ላይ ነው፡፡ ስለሆነም እየሠራን ያለነው ማንኛዋም ሴት ከ18 ዓመት በፊት እንዳታገባና እንዳታረግዝ ነው፡፡ ምክንያቱም ከ18 ዓመት በፊት የሚከሰት እርግዝና ለሞትና ለፌስቱላ የማጋለጥ ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም ትምህርት የመማር ዕድሏ ይዘጋል፡፡ ማንኛዋም እናት ከ18 ዓመት በላይ ሆና ካረገዘች ለቀጣይ እርግዝናዋ ቢያንስ ሁለት ዓመት መቆየት አለባት፡፡ ምክንያቱም ማኅፀኗ ወደ ነበረበት ለመመለስ ይህን ያህል ጊዜ ይፈልጋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን አንድ ሴት 35 ዓመት ሳይሞላት ቢያንስ አንድ መውለድ አለባት፡፡ ምክንያቱም ከ35 ዓመት በኋላ የማርገዝ ዕድል እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ በአቅም ልክ መውለድም ያስፈልጋል፡፡ መጠቀም የምትፈልገውም የቤተሰብ ምጣኔም በራሷ ምርጫ መሆን አለበት፡፡ ለእናቶች ተገቢውን ምክር መስጠትም ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ሚድዋይፎችን ጨምሮ የጤና ባለሙያዎች ሥነ ምግባር ለጤናው ዘርፍ ቁልፍ ነው፡፡ ሚድዋይፎች ከእርግዝና ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ የባህሪ ለውጦችንም ሆነ አጠቃላይ ሥነ ምግባር የተሞላበት አገልግሎት እንዲሰጡ ማኅበሩ ምን እየሠራ ነው?

አቶ ዘነበ፡- የማኅበሩ ዋና ዓላማ ከጤና ጥበቃም በላይ ኃላፊነት የሚወስድበት የሚድዋይፎች ሥነ ምግባር ነው፡፡ ሥነ ምግባር የሌለው አገልግሎት ዋጋ የለውም፡፡ በመሆኑም ሥነ ምግባር የተሞላበት የጤና አገልግሎት ለመስጠት ከሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ጋር አብረን እንሠራልን፡፡ አንዲት እናት ምጥ ከጀመራት አንስቶ እስክትወልድ ያለው ጊዜ እንደየምጡ ቢለያይም፣ በምጥ ጊዜና ከወሊድ በኋላም ሚድዋይፍ ከእናት ጋር አብራ መሆን አለባት፡፡ ለሚድዋይፍ ይህ ትልቅ ኃላፊነት ነው፡፡ ሚድዋይፎችም ከሌላው በተለየ መልኩ ለረዥም ጊዜ ያለ ዕረፍት የሚሠሩበት ሁኔታ ያጋጥማል፡፡ ይህ ጫና የሥነ ምግባር ችግር እንይዳፈጥር እኛም ጤና ሚኒስቴርም የምንሠራው ሥራ አለ፡፡ ከጤና ሚኒስቴር ጋር ሩኅሩኅና አክብሮት የተሞላበት አገልግሎት ለእናቶች ለመስጠት ፕሮጀክት ተነድፏል፡፡ እኛም ሥልጠና ሰጥተናል፣ እንሰጣለንም፡፡ ከዚህ በፊት እናት ለምጥ ስትገባ ሌላ ሰው አይገባም ነበር፡፡ አሁን ከሚድዋይፍ በተጨማሪ አንድ ቤተሰብ እንዲገባ የተጀመረባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ በምጥ፣ በወሊድ ጊዜ ስለሚደረገው ተግባቦት/ንግግር ሁሉ እናት እንድትረዳ ማድረግ የተግባባንበት ሥራ ነው፡፡ ታች ማውረድ ግን ይቀራል፡፡ ሩኅሩኅና አክብሮት የተሞላበት የጤና አገልግሎት መስጠት የሚድዋይፎች የመጀመርያ ተግባራቸው ነው፡፡ ይህ እንዲሆንም በሥልጠና ሚድዋይፎችን እየደረስን ነው፡፡      

ሪፖርተር፡- አንዲት በምጥ ትወልዳለች ተብላ የምትጠበቅ እናት ምጧ ጀምሮ ድንገት ቀዶ ሕክምና ቢያስፈልጋት ሚድዋይፎች ይህንን ወስነው ቀዶ ሕክምና መስጠት ይችላሉ?  

አቶ ዘነበ፡- የሠለጠኑ ሚድዋይፎች በጤና ተቋም መኖራቸው 87 በመቶውን የእናቶች ሞት ይቀንሳል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሠለጠኑ ሚድዋይፎች ካሉን 87 በመቶውን የእናቶች ሞት እንቀንሳለን፡፡ በኢትዮጵያ 50 በመቶ እናቶች የሚሞቱት በደም መፍሰስ ነው፡፡ በኢትዮጵያ በዓመት 11 ሺሕ እናቶች ከወሊድ ጋር ተያይዞ ከሞቱ፣ ከአምስት ሺሕ በላዩ የሚሞቱት በደም መፍሰስ ነው፡፡ ደም መፍሰስን ሚድዋይፎች መከላከል ይችላሉ፡፡ እናት ደም ሊፈሳት ከሚችሉባቸው ምክንያቶች አብዛኛዎቹን ጤና ጣቢያ ላይ መከላከል ይቻላል፡፡ አንዳንዴ ከጤና ጣቢያ በላይ ሊሆን ይችላል፡፡ ሚድዋይፍ ብትኖርም ከአቅም በላይ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ሲሆን ሚድዋይፍ ባለበት በአምቡላንስ ከጤና ጣቢያ ወደ ሆስፒታል ትወሰዳለች፡፡ የማኅፀን ሐኪምም ይቀበላታል፡፡ አሁን ላይ በቀዶ ሕክምና የሚያዋልዱ ሚድዋይፎች ጥቂት ናቸው፡፡ ጎንደርና መቀሌ ዩኒቨርሲቲዎች በቀዶ ሕክምና የሚያዋልዱ ሚድዋይፎችን በሁለተኛ ዲግሪ ማሠልጠን ጀምረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ሚድዋይፎቻችን ግን አንዲት እናት ቀዶ ሕክምና እስክትደርስ ያሉትን ክትትሎች ሁሉ መጨረስ አለባቸው፡፡ ሚድዋይፎች ከወሊድ ጋር የተያያዙ ሁሉንም የሕክምና ዕርዳታ እንዲሰጡ ለሁለት ዓመት የሚቆይ ፕሮጀክትም ይዘናል፡፡  

ሪፖርተር፡- ቀዶ ሕክምና መሥራት እንዲችሉ ከማብቃት ባለፈ ሚድዋይፎች ፅንስን አልትራሳውንድ ማየትና ውሳኔ ለማሳለፍ የሚያደርስ ሥልጠናን ፕሮጀክቱ ይጨምራል?

አቶ ዘነበ፡- በኢትዮጵያ ባሉ አራት ሺሕ ጤና ጣቢያዎች ሁሉ አልትራሳውንድ የማቅረብ ችግር አለ፡፡ ሚድዋይፎች ክህሎታቸውን ተጠቅመው ነው የልጅ አቀማመጥ የሚለዩት፡፡ አብዛኛዎቹን ችግሮች ሚድዋይፎች የሚለዩ ቢሆንም፣ የእንግዴ ልጅ አቀማመጥ የአዕምሮ ዕድገቱ፣ የአካል ጉዳትና ሌሎች ችግሮች ቢኖሩ ማወቅ አይችሉም፡፡ አልትራሳውንድ በየጤና ጣቢያው ማስገባት የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ 100 ጤና ጣቢያዎች ላይም ገብቷል፡፡ በ100 ጤና ጣቢያዎች አልትራሳውንዱን የሚያሳዩት፣ የሚያነቡትና የሚወስኑት ሚድዋይፎች ናቸው፡፡ ማኅበራችን ክፍተቶችን እያየ ሥልጠና ይሰጣል፡፡ መንግሥት አልትራሳውንድ ሲገዛ ሚድዋይፎችን እኛ እናሠለጥናለን፡፡

ሪፖርተር፡- 70 በመቶ ኢትጵያውያን እናቶች ቤት ውስጥ ይወልዳሉ፡፡ እናትን ለሞት ከሚያጋልጡ ምክንያቶች አንዱ ደግሞ ያለ ሕክምና ባለሙያ ዕርዳታ በቤት ውስጥ መውለድ ነው፡፡ ማኅበሩ ግንዛቤ መፍጠር ላይ ምን ይሠራል?

አቶ ዘነበ፡- የማኅበራችን ዓላማ የእናቶችና ሕፃናት ሞትን መቀነስ ነው ካልን እናቶችን መድረስ ግድ ነው፡፡ እናቶችን የማግኘት የመጀመርያው ኃላፊነት የመንግሥት ነው፡፡ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት መስጠት የሚድዋይፎች ኃላፊነት ነው፡፡ እናቶች አንዴ ጤና ተቋም ከመጡ በኋላ እንዳይጠፉ የምንከታተልበትና በስልክ የምናገኝበት ፕሮጀክት አለን፡፡ ይህ እናቶች ቀጠሮ ረስተው እንዳይቀሩም ያግዘናል፡፡ ወደፊት በጀት ከተገኘ እናቶች መልዕክት በስልክ የሚያገኙበት ሁኔታ ላይ እንሠራልን፡፡ ከመንግሥት ጋርም በጋራ የምንሠራው ይሆናል፡፡ ሚድዋይፎች ከጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች ጋር ግንኙነት እንዲኖራቸው እያደረግን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከጤና ሚኒስቴር ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?

አቶ ዘነበ፡- ጤና ሚኒስቴር በሚፈልገው ፕሮጀክትና ቅድሚያ በሚሰጠው ችግር ላይ አብረን እንሠራለን፡፡ ሚኒስቴሩ በጀት ይዞ እኛ የምናሠለጥንበት አካሄድም አለ፡፡ ከጤና ሚኒስቴር በተጨማሪ ከዩኒሴፍ፣ ከዩኤንኤፍፒኤ፣ ዩኤስኤአይዲ፣ አምሬፍና በሌሎች አጋር ድርጅቶችም ጋር እንሠራለን፡፡ በኢትዮጵያ መቀመጫ የሌላቸውም አጋሮችም ከእኛ ጋር ይሠራሉ፡፡ ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በደም መፍሰስ የሚሞቱ እናቶችንና በመታፈን የሚሞቱት ጨቅላዎች ለማዳን ለሚተገበር ፕሮጀክት፣ ኢንተርናሽናል ኮንፌዴሬሽን ኦፍ ሚድዋይፍ (የካናደ መንግሥት) 450 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ሰጥቶናል፡፡ የካናዳ መንግሥት ይህን ብር የሰጠን 50 በመቶ እናቶች በደም መፍሰስ ይሞቱብናል፣ ሕፃናት ታፍነው ይሞታሉ ማኅበሩ ምን ይረዳኛል ብሎ ጤና ሚኒስቴር ስለጠየቀንና ፕሮፖዛሉን ጽፈን ስላስገባን ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት በ30 ዩኒቨርሲቲዎች፣ በ100 ጤና ጣቢያዎችና በ52 ሆስፒታሎች ላይ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡  

ሪፖርተር፡- የጤናማ እናትነት ወር እየተገባደደ ነው፡፡ ምን ሠራችሁ?

አቶ ዘነበ፡- የጤናማ እናትነት ወርን አባላትን አሰባስበን፣ በራስ አቅም ግንዛቤ ለመፍጠር፣ ከሁሉም ዞንና ከጤና ተቋማት በተውጣጡ ሚድዋይፎች በአዳማ የእግር ጉዞ በማድረግ አክብረዋል፡፡ በክልል ቋንቋ የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን እንዲኖር አድርገናል፡፡ የደም ልገሳም ተከናውኗል፡፡    

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ያለው ሦስተኛው ከግል ባንክ ሆነ

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ከ100 ቢሊዮን...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...