Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልያልተመለሰው የዴር ሡልጣን የኢትዮጵያ ገዳም የባለቤትነት ጥያቄ

ያልተመለሰው የዴር ሡልጣን የኢትዮጵያ ገዳም የባለቤትነት ጥያቄ

ቀን:

በቅድስት አገር በኢየሩሳሌም ከተማ በሚገኘው የዴር ሡልጣን ገዳም ውስጥ ኢትዮጵያውያን ከአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ይኖሩ እንደነበር ዓለም አቀፍ መረጃዎች ማመልከታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዴሚ የፊኖሎጂ ማዕከል ኃላፊና የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ተመራማሪ አስታወቁ፡፡

በኢየሩሳሌም የዴር ሡልጣን የኢትዮጵያን ገዳም እናድን በሚል ጥር 28 ቀን 2011 ዓ.ም. በተካሄደው የግማሽ ቀን ውይይት ላይ ኃላፊው ሠርገው ገላው (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያውያን በዴር ሡልጣን ገዳም በዘመኑ ስለመኖራቸው ለማረጋገጫነት ከሚጠቀሱት መረጃዎች መካከል አፄ ዘርአያቆብ ከገዳሙ መነኰሳት ጋር የተጻጻፏቸው ጉዳዮች በተዓምረ ማርያም መዘገቡ ነው፡፡

ከዚህም ሌላ በዚሁ መቶ ክፍለ ዘመን ሂሮኒውስ የተባለ የላቲን ቤተ ክርስቲያን አባት ከእህቶቹ ጋር በኢየሩሳሌም አብሮ ይኖር እንደነበር፣ እህቶቹም ወደ ሮም ደብዳቤ ሲጽፉ ከኢትዮጵያውያን ጋር አብረው እንደሚኖሩ መግለጻቸውን ሌላ ተጨባጭ ማስረጃ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረውም የጀርመን ጳጳስ ኢየሩሳሌምን ሲጎበኝ ኢትዮጵያውያንን ማግኘቱን፣ በአፄ ዘርአያቆብ ጊዜ የሮም ፓፓ ፍሎሬንስ ውስጥ ባካሄደው ጉባዔ ኢትዮጵያውያን መልዕክተኞች መሳተፋቸውንና ፓፓውም ከሩቅ አገር ከኢትዮጵያ የመጡ መልዕክተኞች በጉባዔው መገኘታቸውን ካወጀ በኋላ ታዳሚዎቹ ደስታቸውን በጭብጨባ እንዳስታጋቡ ተመራማሪው አስረድተዋል፡፡

መልዕክተኞቹ ከኢየሩላሲም ወደ ፍሎሬንስ ተንቀሳቅሰው ጉባዔውን ሊከታተሉ የቻሉት በአፄ ዘርአያዕቆብ ትዕዛዝ እንደሆነ ከኃላፊው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በኢየሩሳሌም የዴር ሡልጣን የኢትዮጵያን ገዳም እናድን ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ ዘውገ ገድሉ፣ ዴር ሡልጣንን እናድን በሚል ርዕሰ አሜሪካ ውስጥ አንድ ኮሚቴ እንደተቋቋመና ባለፈው ዓመት በዚህ ገዳም ላይ ሊኖር የሚገባውን እውነተኛ ታሪክና ችግር ኮሚቴው ማጥናቱን ገልጸዋል፡፡

ኮሚቴው ሥራውን በሁለት ንዑሳን ኮሚቴዎች አከፋፍሎ ዕቅድ በማውጣት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት በኢየሩሳሌም ከተማ ከተቋቋሙና ‹‹በገዳሙ ጉዳይ ያገባናል›› ብለው ከሚንቀሳቀሱት ጋር ግንኙነት መስመር ዘርግቷል፡፡ ስለ ጉዳዩ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ለኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ የተማጽኖ ደብዳቤዎች መላኩን አቶ ዘውገ ተናግረዋል፡፡

በዓለም ውስጥ ከሚገኙ ጥቂት አብያተክርስቲያናት ውስጥ በዴር ሡልጣን ገዳም ሀብትና ንብረት ያላት ኢትዮጵያ ብቻ እንደሆነች፣ ካላትም ሀብትና ንብረቶች መካከል የመድኃኔዓለም፣ የቅዱስ ሚካኤልና የፊሊጶስ አብያተክርስቲያናት መሆናቸውን፣ ከዴር ሡልጣን ውጭም የኪዳነምሕረት ቤተ ክርስቲያን እንዳላት አስረድተዋል፡፡

የኪዳነምሕረት ቤተ ክርስቲያንን ግንባታ ያስጀመሩት አፄ ዮሐንስ ሲሆኑ፣ ያስጨረሱት ደግሞ ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ናቸው፡፡ ንግሥት ዘውዲቱ ደግሞ ለቤተ ክርስቲያኑ መተዳደርያ እንዲሆን ባለ አራት ፎቅ ሕንፃ አሠርተው እንዳስረከቡ ነው ሊቀመንበሩ የተናገሩት፡፡

እቴጌ መነንም ክርስቶስ በተጠመቀበት ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ የቅድስት ሥላሴ፣ የኢየሩሳሌም መታሰቢያ ድርጅት በቤተልሔም የኢየሱስ፣ አንድ በጎ አድራጊ እናት ደግሞ በኢያሪኮ ገዝተው በሰጡት ቦታ ላይ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የገብርኤል፣ አንድ እናት ሀብትና ንብረታቸውን ለአረጋውያን መተዳደርያ በሰጡት መሠረት የተክለሃይማኖት አብያተክርስቲያናት ተሠርተዋል፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በእስራኤል ምድር ስምንት አብያተክርስቲያናት እንዳላት አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ ዘውገ ገለጻ ከሁሉም አሁን ችግርና ፈተና የደረሰበት ዴር ሡልጣን ውስጥ ያለው ገዳም ሲሆን፣ ከመጀመርያውም ትልቁ ችግር የተነሳው የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ያለይዞታውና ያለሀብቱ የእኔ ነው የሚል እንቅፋት በመፍጠሩ ነው፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እስራኤል በዮርዳኖስ ንጉሥ ሁሴን ቅኝ ግዛት በነበረችበት ጊዜ በገዳሙ ይኖሩ የነበሩ አባቶች በተስቦ በሽታ በማለቃቸውና ይህንንም አጋጣሚ በመጠቀም አንድ ግብጻዊ ቤተ ክርስቲያን እግሩን በስገባቱ ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ንጉሥ ሁሴን የዴር ሡልጣን ገዳም ሀብትና ንብረት የኢትዮጵያ ነው ሲሉ ፍርድ ሰጥተዋል፡፡ የገዳሙ ንብረትና ሀብት የኢትዮጵያ መሆኑን ፍልስጢሞች ሳይቀሩ መስክረዋል፡፡ የፍርዱም አፈጻጸም ሳያልቅ በ1940 ዓ.ም. እስራኤል ነፃነቷን ተቀዳጅታ መንግሥት እንደሆነች፣ ችግሩንም መቀስቀስ ስላልፈለገች ሁሉም ሰው በያዘው ቦታ ይቀመጥ የሚል ትዕዛዝ እንዳሳለፈች ተናግረዋል፡፡

ሁሉም በይዞታው ላይ ከቆየ በኁላ በ1948 ዓ.ም. በጊዜው የነበሩት አቡነ ፊሊጶስ የተሰጠው ፍርድ አፈጻጸሙ እንዲያልቅ አቤቱታ ያቀረቡ ሲሆን፣ አሁንም የእስራኤል መንግሥት ወደ ዝርዝር ጉዳዮች ገብቶ ለማካፈል እንዳልፈለገ፣ አቡነ ፊሊጶስም ፍርዱንና አቤቱታውን በሦስት ቅጽ መጽሐፍ እንደጻፉና ያስቀመጧቸው መረጃዎች ሁሉ ዛሬ ሊነሱ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ከአቡነ ፊሊጶስም በኋላ በርካታ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ አፍቃሪ የሆኑ የውጭ አገር ምሁራን በገዳሙ ዙሪያ ብዙ መጻፋቸውን ገልጸዋል፡፡ ብጹዕ አቡነ ማቲያስ ዳግማዊ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ እጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት በ2005 ዓ.ም. ለእስራኤል መንግሥት ደብዳቤ እንደጻፉ፣ ይህንንም ጉዳይ የሚያዩትና የሚከታተሉ አምስት ሚኒስትሮች እንደተሰየሙ ይህም ቢሆን ግን እስካሁን ድረስ ጉዳዩ እንዳልታየ አቶ ዘውገ አብራርተዋል፡፡

‹‹ያላዩበትም ምክንያት የእስራኤል መንግሥት ግብጽን ማስቀየም ስለማይፈልግ ነው፡፡ ስለዚህ የፖለቲካ እንጂ የሃይማኖትና የንብረት ጉዳይ አልሆነም፡፡ ባለፈው ዓመት መጀመርያ ወር ላይም ከግሪኮች የሕንፃ ጥገና ሥራ ጋር በተያያዘ የወደቀ ትልቅ የግንብ ፍራሽ በቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ጣርያ ላይ ወድቆ ጣርያውን ናደው፡፡ የቤተ ክርስቲያኑም መቅደስ ተገለጠ፡፡ በዚህም ምክንያት የቤተ ክርስቲያኑ አገልግሎት ተቋርጦ ነበር፡፡ ሆኖም በመንግሥትና በሃይማኖት አባቶች በተደረገው ያላሰለሰ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት፣ የእስራኤል መንግሥት ጣርያውን አድሶታል፡፡ ታቦተ ሕጉም ታኅሳስ 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ከብሮ መደበኛ የቅዳሴና ሌሎችንም መንፈሳዊ አገልግሎቶች መስጠቱን ቀጥሏል፤›› ብለዋል፡፡

ይህ ገዳም ኢትዮጵያዊ ቅርስ ብቻ ሳይሆን አፍሪካዊ ከዛም አልፎ ዓለም አቀፋዊ ቅርስ መሆኑን ጠቁመው በዚህም የተነሳ ይህንን የባለቤትነት ጥያቄ ለማስከበር ኢትዮጵያውያን ሁሉ በአንድነት መነሳሳትና ጥያቄውን ማስተጋባት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የኮሚቴው አባል መላከብርሃናት ቀሲስ አስተርዬ ጽጌ ዴር ሡልጣን ገዳም የኢትዮጵያ ሀብትና ንብረት ለመሆኑ መጀመርያ ኢትዮጵያ፣ ቀጥሎ ደግሞ የዓለም ሕዝብ እንዲያውቀው ሁሉን አቀፍ ጥረትና የማያቋርጥ ቅስቀሳና ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ ማካሄድ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...