Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ወሬና ንፋስ ምንና ምን ይሆኑ?

እነሆ መንገድ! እነሆ ጉዞ! ከመገናኛ ወደ ስድስት ኪሎ። የጎዳናው ጭብጥ ተደጋጋሚ ነው። ሕይወት ቀለም ያለቀባት ትመስላለች። በመንጋ ቅርፅ አሠልፋ የምትነዳው ሕዝብ እልፍ ነው። ሲቃችን ተያያዥ ነው። ውክቢያው ዓይን ያጭበረብራል። ደምቆ ካማረበት ይልቅ ገርጥቶ ያስቀየመው ልቋል። ወጣትና አዛውንቱ፣ ጎበዙና ሰነፉ፣ ሰላማዊውና ፀረ ሰላም ተፋጠዋል። በዚህች ምድር ለሆድ መኖር ዕውቅና ያልተቸረው ከዛሬ ሦስት ሺሕ ዓመት በፊት ይመስላል። አብሲቱን ተሸክሞ፣ ቅሉን አንጠልጥሎ፣ ምጣዱን አሟሽቶ ዓይታይም እንጂ ለወጪ ወራጁ የዕለት እንጀራ ጋጋሪነት የነፍሱ ጥሪ ይመስላል። ሐሳብና ሐሳበኞች ሲቀበሩ ትንሳዔያቸውም አብሮ ሳይቀበር አልቀረም መሰል። እዚያ ድንፋታሙ ለዘብተኛው ላይ ይጮሀል። ዝምታ በአቅም ማጣት የተመሰለበት ደግሞ አንገቱን እንደደፋ መሽቶ ይነጋል። ጊዜ ሄዶ ሄዶ ማለቂው የሌለው ይመስል ነገር ሁሉ ባለበት ይዘልቃል ብሎ የሚያስበው ሞኝ ጥቂት አይደለም።

ፀሐይ ሰማዩ አጉኗት እንደቀረች ኳስ ህዋ ላይ ተደላድላ፣ በሙቀቷ ምድሪቷን ስታሞቅ ይኼን እውነት የምትታዘብ ትመስላለች። ስለሰው ልጆች የታዘበችው ብዙ ያለ ይመስላል። የወደደችውና የጠላችውን መለየቱ ግን ከባድ ነው። የምትለው ብዙ እውነት ኖሯት አፏን እንደለጎሟት ሁሉ አረፋፍዳ የምትለበልበን ለጤና አይደለም። አጠገባችን የቆመ በብዙኃን አጠራር ‹‹ዕብድ›› የሚል ስያሜ የተቸረው (ዘንድሮ ያላበደ ያለ ይመስል) ገርጀፍ ያለ ሰው፣ ‹‹ፀሐይን እዚያ የሰቀላት ማን ነው? እውነትን አብርቶ አልጋ ሥር የደበቃትን ሰው ፈልጉት ብል እምቢ አላችሁ አይደል?›› እያለ ይጮሀል። ታክሲ ጠባቂው ሠልፈኛ እርስ በርሱ ለመተያየት እንኳ አፍሮ ከንፈሩን ይመጣል። በጠዋቱ መርዶ ነጋሪ እንደተላከበት ሁሉ ከንፈሩን ሲመጥ ቁጭት ፊቱ ላይ ይንፀባረቃል። ጉዞው እነሆ እንዲህ ይጀምራል!

ስሜት አልባነት ባጠቃው ታክሲ ተራ ሁለት ወያላዎች በሚደግፏቸው ባላንጣ ቡድኖች ጥላ ሥር ሆነው ይበሻሸቃሉ። ‹‹ዕድሜ ለእኔ በል! ከአገር ቤት ጀምሮ ሙጥኝ ያልከውን ቁንጣ አስወልቄ ጂንስ ሱሪ ማልበሴ ሳያንስ፣ ከጓደኞችህ እንዳታንስ የለንደን ክለብ ደጋፊ አደረግኩህ፤›› ይላል አንደኛው አጠር ደንደን ባለው አካሉ ለመወጣጠር እየተውተረተረ። ‹‹አሁን ባንተ ቤት የገበሬ ልጅ በመሆኔ የማፍር መስሎህ ነው? እስኪ አንድ ኢትዮጵያዊ አምጣልኝ እርፍ መጨበጥ የማያውቅና ዘር አላውቅም የሚል?›› ይለዋል ለትችት የተቀደመው ሳቂታ ወያላ። በማኩረፍና በመደሰት፣ በድል አድራጊነትና በተሸናፊነት ስሜቱ እየዋለለ ‹‹የመሀል ሰፋሪነት›› መንፈስ የተጠናወተው መንገደኛ ጆሮ ሰጥቶ ያዳምጣቸዋል። ሳቅና ኩርፊያቸው እኩል የሆነባቸው ፊቶች እልፍ መሆናቸው እንዳለ ነው። አጭሩ ወያላ እንደ መደንገጥ ብሎ፣ ‹‹ኧረ አንተ እባክህ ሰው አይስማህ? አንተ እንደምትለው ቢሆን በ‹ዲቪ› እና በዱቤ አገር የሚለቀው ሕዝብ እንዲህ ቅጥ ያጣ ነበር?›› ብሎ ይመልስለታል።

ከፊት ከቆሙ ሁለት የባንክ ሠራተኞች አንደኛው፣ ‹‹ትሰማቸዋለህ የሚያወሩትን?›› ሲል ወዳጁን አፈጠጠበት። ‹‹ተዋቸው እነሱን፣ አሁን ይልቅ ስለአዲሱ አለቃችን እናውራ። ደመወዝ ሊጨምሩ ይችላሉ የሚባለውን ወሬ ሰምተካል?›› ብሎ ወያሎቹን በጎን እያየ ጠየቀው። ጓደኛው አምጦ የወለደውን ሳቅ በትንታ እንዳገባደደ፣ ‹‹እኔ እኮ እዚህ አገር በቃ ሰው ከመሬት ተነስቶ ከችግሩ ጋር አያይዞ ሥራ እንደ መፍጠር ወሬ መፍጠር መቼ ነው የሚያቆመው? ኧረ ለመሆኑ የእናታቸው ወይስ የአባታቸው ቤት ሆኖ ነው አዲሱ አለቃችን ደመወዝ ይጨምራሉ የተባለው? እርግጠኛ ነኝ ይኼን ወሬ ያወራው የቤት ኪራይ የተጨመረበት የሥራ ባልደረባችን ይሆናል፤›› ሲል ፈገግታው አሁንም አልጠፋም፡፡ ወዲያው ታክሲያችን ከተፍ ብሎ መሳፈር ጀመርን። መንገዱ በምፀት ተጀምሮ እንዲያልቅ ቃል የተገባለት የሚመስለው እንዲህ የመንገደኛውን ኑሮና ወሬ ሲያጤኑ ነው፡፡

ታክሲው ሞልቶ ጉዞ ጀምሯል። ወያላው የአገር ቤቱን ልጅ በገጠሬነቱ አሳቦ ለማትከን ሲጣጣር የተመላለሳቸው ቃላት አልፎ አልፎ ትዝ ይሉታል መሰል ብቻውን ፈገግ ይላል። ድንገት ኮስተር አለና ደግሞ፣ ‹‹ወይኔ ሳንቲም ሳልዘረዝር. . .›› ሲል ግንባሩን በመዳፉ በጥፊ መታው። ሾፌራችን በዕድሜ የገፉ አዛውንት እንደ መሆናቸው ፍፁም እርጋታ ይታይባቸዋል። ወያላው፣ ‹‹አንዴ አቁሙልኝ እስኪ! ሳንቲም ልዘርዝር. . .›› ሲል ከጣራ በላይ ጮኸ። ‹‹እንዴ ታዲያ ምን ትጮህብናለህ ቀስ ብለህ ብትነግራቸው ይሰሙ የለ?!›› አለች በክርኑ ደገፍ የሚላት መቀመጫ ላይ የተሰየመች እመጫት። ሥጋቷ ልጇ ጭልጥ ካለ እንቅልፉ ነቅቶ እንዳያስቸግራት ነው። ሕፃናት ሳይቀሩ ከእንቅልፋቸው በነቁ ቁጥር ሥራቸው የረብሻ አብዮት መጀመር እንደሆነ የወለደ ያውቀዋል።

‹‹ጆሯቸው እሺ ሲላቸው እኮ ነው! በዚህ ላይ መሪ መጨበጥ ተጨምሮበት አስቢውማ! አምና መንጃ ፈቃድ አውጥቼ ‹እስኪ አሁን እርስዎ ይረፉ ተራውን ለእኔ ይስጡኝ። የቀረችዎትን ዕድሜ አጣጥመው ይኑሯት› ብላቸው የተረፈኝ መደናቆር ሆነ፤›› አለና መልሶ፣ ‹‹ለነገሩ እኔ ነኝ ጥፋተኛው። ልግመኛ ጆሮ ካለው ሽማግሌ ጋር ሙግት መጀመሬ፤›› ብሎ እጁ ላይ ያሉትን ብሮች አመሰቃቅሎ መልሶ በማስተካከል ተጠመደ። ከእመጫቷ ጀርባ ከተቀመጡት የባንክ ሠራተኞች ቀጥሎ አጠገቤ የተቀመጠ ጎልማሳ፣ ‹‹ትሰማዋለህ ይኼንን ወመኔ! ምንም ቢሆን ትልቅ ሰው ናቸው። ያውም በእሱ አፍ እንዲህ ስማቸው መነሳት አለበት? ወይ ዘመን! እኔ አውቃለሁ የሚለውን እንደ ማባዣ ማሽን አባዝቶት ተመሪ መሪውን በአደባባይ የሚያንጓጥጥበት ምዕራፍ ላይ ደረስን። ጉድ እኮ ነው!›› ይላል ወደ እኔ መለስ ቀለስ እያለ። የአስተሳሰቡ ወጥነት አጠራጥሮኝ ለአፍታ ሳዳምጠው በምክንያት ከያዘው አቋም በላይ በእምነት ተዕፅኖ የሚቀበለው እንደሚበዛ አስተዋልኩ። መሬት ከተሸከመችው የተቃርኖ ጎራ ብዛት ልቆ ታክሲያችን ውስጥ የምናየው የአመለካከት ልዩነት የመንገዱ ዕንቅፋት ተለቅሞ የማያልቅ መሆኑን ሲመሰክር ታዘብኩ፡፡

ጉዟችን ቀጥሏል። መጨረሻ ወንበር ላይ ሦስት ሴት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ልክ በሌለው ሳቅ እያሽካኩ ወሬ ያደራሉ። ‹‹ስሚ መኪና አለኝ ሲለኝ በቃ እየመጣህ ‹ፒክ› አድርገኝ ማለት። ‹አይ ብዙ ጊዜ ጋራዥ ነው የምትውለው ስትወጣ ስትወጣ ግን ምንም ችግር የለውም እመጣለሁ› አይለኝ መሰለሽ?›› ስትል ሹራብ ቢጤ ጣል ያደረገች ለግላጋ ሌሎቹ በሳቅ ያጅቧታል። ‹‹የማነው በእናትሽ?›› ይወርዱበት ይጀምራሉ። ‹‹ጋራዥ ብቻ ነው እንዴ የምትነዳት አትይውም ነበር?›› ትላታለች በቀኟ የተቀመጠችው ልጅ። አሁንም ከት ብለው ይስቃሉ። ‹‹አንቺ ብትኖሪልኝ ነበራ! ታውቂኝ አይደል አማርኛው ቶሎ አይመጣልኝም Rather, I Prefer Speak in English!››› አለች፡፡ ተሳፋሪው በተራ በተራ ወደ እነሱ እየዞረ በግልምጫ ያነሳቸዋል፡፡ ቅር ያላቸው አይመስሉም። ‹‹ታዲያ እንዴት ተለያያችሁ?›› ትጠይቃለች ሦስተኛዋ።

‹‹ልነግርሽ እኮ ነው። በሃምሳዎቹ ውስጥ እንደሚተውን የፊልም አክተር ዓይኑን አፍጥጦ ተጠጋኝና ‹የቀሪ ዘመኔ አጋር ብትሆኚኝ እንዴት ደስ ባለኝ› አይለኝም መሰላችሁ? ይኼንን ማሰብ ትችላላችሁ?›› በመገረም ተራ በተራ እያየች ጠየቀቻቸው። ‹‹ቆይ አንቺ ምን አልሽው?›› አንደኛዋ ተቻኩላ ጠየቀቻት። ‹‹ቀላል አለመጥኩበት እንዴ? ‹ይኼውልህ ወንድሜ ዘመኑ የሥልጣኔና የቴክኖሎጂ ነው። ምንም እንኳ የኔትወርክ መቆራረጥ ብሎም የአንዳንድ ጥራዝ ነጠቆች አስተሳሰብ ቢበጠብጠንም. . .› ካልኩት በኋላ፣ ‹ደግሞ እንደ ምታውቀው ዓለም ወደ አንድ ሠፈርነት ተቀይራለች፡፡ ‹ቫኬሽን› ላንጋኖና ሶደሬ ብቻ መውጣት ቀርቶ ፓሪስ፣ ሶሎሞን አይላንድ ምናምን እምር ብለው ተነስተው የሚሄዱበት ጊዜ ነው። ሴት ልጅ ፍላጎቷ ብዙ እንደ መሆኑ መጠን በልቧ ያሰበችውን የሚያደርስላት የራሴ የምትለው ማግኘት አለባት። አንተ ደግሞ እንደነገርከኝ እንኳን ሌላ ፍላጎቴን ልታሟላ መኪናህ ብዙ ጊዜዋን የምታሳልፈው ጋራዥ ነው› አልኩት፤›› ከማለቷ አሁንም ጣራ በሚቀድ ሳቅ አውካክተው እጆቻቸውን አየር ላይ አጋጩ። ቀበናን ከመሻገራችን ክፍል ለመግባት ብዙ ሰዓት እንደሚቀራቸው ተነጋግረው ለመውረድ ጠየቁ። ወዴት ለመሄድ እንደሆነ ማን በምን መብቱ ይጠይቃል? ሁሉ እንደ ፈቀደው የሚፈነጭበት ዘመን!

ወያላችን ሳንቲም ዘርዝሮ መልስ እንደሚመልስ ቃል እየገባ ድፍን ድፍን አሥር ብሮች ተቀብሏል። ዳግማዊ ምንሊክ ሆስፒታልን ከማለፋችን ረዳቱ ሳንቲም የምትዘረዝርለት ዓይቶ ለማስቆም ተስገበገበ። ‹‹ምን ያንቀዠቅዠዋል?›› ሲል አንዱ ከጋቢና፣ ‹‹‘የሰው ገንዘብ በልቶ አያድሩ ተኝቶ’ ሆኖበት ነዋ። ምናለበት ሁሉም ለሰው ገንዘብ እንዲህ ቢሆን ነው ማለት፤›› ይላል ከጎኑ የተቀመጠው። ረዳቱ ሳንቲምና ብሮች ለመዘርዘር ሲወርድ በኪስ ልክ የታተመ መጽሐፍ የያዘ ወጣት ገብቶ ተሳፈረ። ተከትሎት የገባው ጎልማሳ ‹‹እስኪ ልየው?›› ሲል መጽሐፉን ጠየቀው፡፡ ሰጠው። ‹‹ስለላና ሰላዮቹ?›› አለ ጮክ ብሎ። ‹‹ቆየሁ ካነበብኩት። ‹ኢንተርኔት› ባልነበረበት ዘመን አንብቤው ጉድ ብዬ ነበር፡፡ አሁን ያለውን የስለላ ጥበብ አደራጅቶ የሚጽፍልን ሰው ቢገኝ ምን እንደምንል አስበኸዋል?›› ብሎ ጎልማሳው ወጣቱን ለጨዋታ ገፋፋው። ‹‹ምን መጻፍ ያስፈልገዋል ይኼው እንሰማው የለ? ስልካችን፣ ኪሳችን፣ ሕልማችን፣ አቋማችን፣ አቋቋማችን ሳይቀር እየተበረበረ እያየን ምን ማብራሪያ ያስፈልገዋል?›› አለ ወጣቱ ደም ሥሩ ተገታትሮ።

‹‹ኤድያ! ዝም ብላችሁ ነው! ኑሯችን፣ አስተሳሰባችን፣ ተንኮላችን፣ ርህራሔያችን አንድ የሆንን ተሰለልን አልተሰለልን ምን እንዳይቀርብን ነው? ከዚህ በላይ ምን እንዳንሆን ነው?›› ትላለች እመጫቷ ከየት መጣች ሳትባል። ወዲያው ውይይቱ የሁሉም ተሳፋሪዎች ሆነና አረፈው። ታክሲያችን ወደ መዳረሻው ሲጠጋ አጠገቤ የተቀመጠው ጎልማሳ፣ ‹‹ልክ ልካችን ሲነገረን በቅጡ አንሰማ እያልን ካለፈ በኋላ ለምን በከንቱ እንበሳጫለን?›› ሲል ይጠይቃል። ወያላው መልሱን አከፋፍሎ ሲያበቃ ‹‹መጨረሻ›› ብሎ በሩን ከፍቶታል። እመጫቷ እንድትወርድ ቅድሚያ ሲሰጣት፣ ‹እህህ እስከ መቼ?› እያለች ስታንጎራጉር እንሰማት ነበር። ‹እኮ ለምን ይክፋን?› ለማለት እንደሆነ ገብቶናል። ከመገናኛ እስከ ስድስት ኪሎ በተደረገው ጉዞ ድምፃቸው ያልተሰማ አንዲት እናት ግን፣ ‹‹ኤዲያ ምነው ወሬ በዛ? ዓለምን የሚያነጋግር ለውጥ ውስጥ ባለች አገር የምን ወሬ ማብዛት ነው? ወሬ ብቻ. . .›› ሲሉ ሰማናቸው፡፡ አንድ ጎረምሳ ሳቅ እያለ፣ ‹‹እማማ በሥራ መሀል ወሬ ያለ እኮ ነው. . .›› ሲላቸው፣ ‹‹መጀመርያ ስለሥራ አውሩ፡፡ ከዚያ ዘና ስትሉ ጊዜያችሁን ለቁምነገር ተጠቀሙበት፡፡ ከወሬ የተረፈን ረሃብ እንጂ ጥጋብ አይደለም፡፡ በወሬ አርሶ ምርት ያፈሰ ገበሬ ታይቶ አይታወቅም፡፡ ወሬና ንፋስ አይጨበጡም፡፡ የምን እንቶ ፈንቶ ነው?›› ሲሉን በኃፍረት አንገታችንን አቀርቅረን በየአቅጣጫችን ተበተንን፡፡ መልካም ጉዞ!     

            `          

 

 

 

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት