ክፍል ፫
በመሐሪ ታደለ ማሩ (ዶ/ር)
በአፍሪካ ቀንድና ከዛም ባለፈ ያሉ አዳዲስ ክስተቶችና የቆዩ ሥጋቶች
በቅርቡ በአገር ውስጥ፣ በአኅጉሩና በዓለም አቀፍ ደረጃ እየታዩ ያሉ ክስተቶች ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ባላት የበላይነት ላይ ትልቅ ፈተና ጋርጧል፡፡ ዋና ዋና ከሚባሉት ቸግሮች ውስጥ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ (በተለይም የመን) ያለው ጦርነትና የፖለቲካ ቀውስ፣ በአውሮፓ ያለው የስደተኝነት ቀውስና በኢትዮጵያ ውስጥ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ዘርን መሠረት ያደረገ ተቃውሞ ያስከተለው ሰፊ ሽፋን ያለው ነውጥ ናቸው፡፡ ከምዕራቡ ዓለም ለየት የሚለው በሶርያ፣ በክሬምያ ያለው፣ የኢትዮጵያ ዕይታም በአኅጉሩና ከዚያም ባለፈ ባለው ዲፕሎማሲያዊ ትብብር ላይ አንድምታ ሊኖረው ይችላል፡፡ ኢትዮጵያ፣ ሌሎች በአፍሪካ ቀንድ ያሉ አገሮችና የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ተመሳሳይ የሚባል የሃይማኖት፣ የሕዝቦች እንቅስቃሴ፣ የንግድና የፀጥታ ሚና የሚጫወቱበት አካባቢ ነው ያላቸው፡፡ ባለፈው የአሥር ዓመት ጊዜ ውስጥ በመካከለኛው ምሥራቅ የተከሰቱት ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ለውጦች በአፍሪካ ቀንድ ያለውን ፖሊተካዊና ዲፕሎማሲያዊ መደላድል ቀይሮታል በቀጣይም ይቀይረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በሳዑዲ ዓረብና በኢራን መካከል ባለው የውክልና ጦርነት ውስጥ በየመን፣ በሶርያና በሊቢያ ካለው በተጨማሪ የአፍሪካ ቀንድም ቢሆን አንዱ ባንዱ ላይ የበላይነቱን የሚያረጋግጥበት የውጊያ ዐውድ ሆኗል፡፡ ከአፍሪካ ቀንድ ዲፕሎማሲያዊና ወታደራዊ ድጋፍ ለማግኘት ካለው ፍላጎት የተነሳ የመን ውስጥ በኢራን የሚደገፈውን የሁቲ አማፅያንን በመዋጋት የሚገኘው በሳዑዲ ዓረብ የሚመራው ወታደራዊ ቅንጅት ከኤርትራ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ግብፅና በቅርቡ ደግሞ ከጂቡቲና ሶማሊላንድ ሲፈልገው የነበረውን ድጋፍ በተለያየ ደረጃ አግኝቷል፡፡ በልዋጩ ለሚያገኙት የገንዘብ ድጋፍ ሲባል ኤርትራ ለቅንጅት ኃይሉ የመሬት፣ የባህርና የአየር አገልግሎትና እንዲሁም የሰው ኃይል ሰጥታለች፣ የሱዳን ወታደራዊ ኃይልም በጦርነቱ ተሳትፏል፡፡ በመነሻው ኤርትራና ሱዳን በኢራን ተፅዕኖ ስር ሆነው የሁቲ አማጽያንን ደግፈዋል፡፡ እ.ኤ.አ ግንቦት 2008 ውስጥ የተደረገው የፕሬዚዳንት ኢሳያስ የኢራን ጉብኝት በውክልና ጦርነቱ ውስጥ ኤርትራ ወዴት እንዳገደለች የሚያመላክት ነበር፡፡
ይሁን እንጂ እ.ኤ.አ. በ2015 ኤርትራና ሱዳን ሁለቱም የኢራኑን ወገን በመተውና በሳዑዲ ዓረብ የሚመራውን ቅንጅት በመቀላቀል አቋማቸውን ቀይረዋል፡፡ ኤርትራ አቋሟን ለመቀየር የተገደደችባቸው ምክንያቶች፣ ያጋጠማት ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት፣ እንዲሁም ሶማሊያ ውስጥ ከተጫወተችው አፍራሽ ሚናና ከኢትዮጵያ ጅቡቲና የመን ጋር ባደረገችው የድንበር ጦርነት የተነሳ ከአሥር ዓመታት በላይ ለሆነ ጊዜ ከጎረቤቶቷና ከዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ የደረሰባትን ዲፕሎማሲያዊ መገለል ናቸው፡፡ በሳዑዲ ዓረብ በሚመራው ቅንጅት ድጋፍ በማድረጓ ኤርትራ ከገልፍ የትብብር ካውንስል (GCC) አገሮች ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማጠናከሯ ብቻ ሳይሆን ከዚህ በላይ ብዙ ትርፍ አግኝታበታለች፣ በዓይነትም ድጋፍ አትርፋበታለች፡፡ የተባበሩት የዓረብ ኤምሬት የአሰብ ወደብን በሊዝ ለ30 ዓመታት እንድትጠቀምበት ዋስትና አግኝታለች፡፡ ኤርትራ በሳዑዲ ዓረብ የሚመራውን ቅንጅት በቀይ ባህር ወስጥ በወታደራዊና በኢኮኖሚው ረገድ በጣም ወሳኝ የሚባል ጂኦፖለቲካዊና ጂኦኢኮኖሚያዊ ይዞታ እንዲኖረው አስችሎታል፡፡
እ.ኤ.አ. በሚያዝያ 2016 ጂቡቲ ሪያድ ላይ ከሳዑዲ ዓረብ ጋር በፀጥታ ጉዳዮች ላይ ትብብሯ የምታሳድግበትን ስምምነት ተፈራርማለች፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ሶማሊያና ሱዳን ከኢራን ጋር የነበራቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማቋረጥ በቅርቡ ከሳዑዲ ዓረብ ጋር ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ ከኢራንና ከሳዑዲ ዓረብ ጋር ያላትን የገለልተኝነት ዲፕሎማሲ ጠብቃ ያለችው ኢትዮጵያ ብቻ ነች፡፡ በታሪክ ኢራንና ሳዑዲ ዓረብ ሁለቱም ኢትዮጵያን በተመለከተ ያላቸው ከተቃርኖ ነፃ የሆነ ፖሊሲ ተመሳሳይነት አለው፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ የአውሮፓ ኅብረት የኤርትራ ስደተኞች ወደ ክልሉ እንዳይገቡ ለማስቆም በሚል የተጣደፈ ሙከራ ከኤርትራ ጋር የገንዘብ ድጋፍን የሚጨምር ስምምነት አድርጓል፡፡ ድርጊቱ የኤርትራን መንግሥት ሞራል ማነቃቂያ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ በላይ ግን በተለይም እንደ አዲስ አበባ ዕይታ በገንዘብ ዕጦት የተዳከመውን የኤርትራ መንግሥት በተለይም የሠራዊቱ ኢኮኖሚ ያነቃቃል፣ በሒደትም ለረዥም ጊዜ የቆየውን ኤርትራ በኢትዮጵያ ላይ ያላትን የጠበኝነት ባህሪይ ያጋግላል፡፡ በጉዳዩ ያላት ሐሳብ ሳትጠየቅ በመቅረቷ ኢትዮጵያ በስምምነቱና ለኤርትራ በተደረገው የገንዘብ ድጋፍ ያላትን ተቃውሞ በሳዑዲ ዓረብ ለሚመራው ቅንጅትና ለአውሮፓ ኅብረት ገልፃለች፡፡
እ.ኤ.አ. በ2000 ከኤርትራ ጋር የነበረውን የድንበር ጦርነት ተከትሎ በነበረው ጦርነት አልባና ሰላም አልባ ሁኔታና ከዚህ ተከትሎም ኢትዮጵያ በአጥጋቢ ደረጃ ወታደራዊ ሁኔታን በድንበር ተወስኖ እንዲቆይ የማድረግና በዲፕሎማሲያዊ መስክም ኤርትራን የመነጠል እንቅስቃሴ የተነሳ የኤርትራ ሠራዊት አገሪቷን መከላከል በማይችልበት ደረጃ ድረስ በከፍተኛ ደረጃ ተዳክሞ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በቅርቡ የተከሰቱ የመካከለኛ ምሥራቅ፣ የአውሮፓ ኅብረትና የአፍሪካ ቀንድ ሁኔታዎች ተዳምረው ኢትዮጵያ ስትከተለው የቆየችውን ፖሊሲ ውጤታማነት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚሸረሽሩትና ዓይነተኛ ክለሳም እንደሚያስፈልገው ይታመናል፡፡
የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ/ኢኮኖሚያዊ አፈጻጸም
ኢሕአዴግ ካለው ወደ ውስጥ የማየት ዝንባሌ በተጣጣመ መልኩ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲው መነሻዎች በውጭ ጉዳይና የደኅንነት ፖሊሲው ውስጥ በግልፅ ሰፍረዋል፣ ኢኮኖሚው ከእነኚህ ዝንባሌዎች በሚገባ ተጠቃሚ ሆኗል፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት የሚከተለው የኢኮኖሚው አስተዳደር በብዙ መልኩ አብነታዊ የሚባልና በጦርነት የተዳከመውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለበርካታ አሠርታት ከቀጠለ የእርስ በርስ ግጭት እንዲያገግም የረዳ ነው፡፡ ዓመታዊ አገራዊ ገቢው (ጂዲፒ) እ.ኤ.አ በ2000 ከነበረበት 8.2 ቢሊዮን ዶላር በ2015 ወደ 61.5 ቢሊዮን ዶላር አድጓል፤ (ከ2008-2015 አማካይ ዓመታዊ ጭማሪው 10.4 በመቶኛ ነበር)፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ትልቅ የኢኮኖሚ አቅም ያላት ዘጠነኛ አገር ስትሆን በዓለም ውስጥ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እያሳየ ካሉት አገሮች ውስጥ አንዷ ናት፡፡ ይህም ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያና ኤርትራ የመሳሰሉት ጎረቤቶቿ ካላቸው አፈጻጸም ጋር በአንፃራዊ ተነፃፃሪነት ያስቀምጣታል፡፡ ለእዚህም ነው የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ኢትዮጵያን እንደ ‘ደማቅ የዕድገት ቦታ’ አድርገው ያስቀመጧት፡፡ በቅርቡ እስከ ተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ ድረስ የኢኮኖሚ ዕድገቱና የነበረው ተነፃፃሪ የፖለቲካ መረጋጋት በዲፕሎማሲው መስክም ከፍተኛ ተቀባይነት አስገኝቶላታል፡፡ መካከለኛ ገቢ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል አድጎ የተጠቃሚ ገቢ እኩል ያድጋል ተብሎ የተጠበቀውን ያህል ንግድና (እ.ኤ.አ በ2011 ከነበረው 11 ቢሊዮን ዶላር በ2016 ወደ 69.2 ቢሊዮን) የመዋለ ንዋይ ዕድሉ በከፍተኛ ደረጃ አድጓል፡፡ እ.ኤ.አ በ2017 የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የኬንያን በመብለጥ በአፍሪካ ቀንድ ትልቁ ሆኗል፡፡ አገሪቷ ከዕርዳታ ይልቅ ንግድና መዋለ ንዋይን በከፍተኛ ደረጃ የምታስገባ ሆናለች፡፡ ይሁን እንጂ በቅርቡ እየታየ ባለው የሰላማዊ ሠልፈኞች ጥቃት የተነሳ ይህ ዕድል ሊቀንስ ይችላል፡፡
የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ማስገባት የውጭ ጉዳይና የደኅንነት ፖሊሲው ምሰሶ ነው፡፡ በውጭ ያሉት የኢትዮጵያ የዲፕሎማቲክ ሚስዮኖች ይህ ሥራ የቅድሚያ ትኩረት ሰጥተው የሚሠሩበት ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአፍሪካ ውስጥ የተመደቡ የዲፕሎማሲ ሚሲዮኖች በምዕራቡ አገሮች ወይም በቻይና ከሚመደቡት ሚሲዮኖች እኩል ትኩረት አይሰጡትም፡፡
ቢሊዮን ዶላር ያስወጣል የተባለለትን የለሙ ወደብ ማበልፀግንና ከለሙ በደቡብ ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚገነባውን የመገናኛ ኮሪደርን ግንባታ የመሳሰሉትን የመሰረተ ልማት ግንባታ ዕቅዶችንና ወደ ጎረቤት አገር የሚላከውን የመብራት ኃይል፣ ወጭ ንግድና የውኃ አቅርቦቶች ሲታይ ኢትዮጵያ በኢጋድ አገሮች ውስጥ ለሚኖረው አካባቢያዊ ውህደት የምትሰጠው ትኩረት አዲስ ጫና ማሳረፍዋን ያመለክታል፡፡ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲዊ ረገድ ለምታደርገው እንቅስቃሴ ትልቁና አስፈላጊው ግብዓት በአገራዊ መሠረተ ልማት ዕድገት ፕሮጀክቶች ላይ የምታውለው መንግሥታዊ መዋለ ንዋይ ነው፡፡ ከ13 በላይ የሆኑ የመገናኛ ኮሪደሮች የኢጋድ አባል አገሮችን ያቆራርጣሉ፡፡ እነኚህ በሙሉ በኢትዮጵያ በኩል አልፈው ወደ ኬንያ፣ ሶማሌላንድ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና ጂቡቲ የሚያልፉ ናቸው፡፡ ይህ በኢትዮጵያ በኩል ያለውን የ1,500 ኪሎ ሜትር ርቀት የተጠናቀቀለት የ4,000 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታን ይጨምራል፡፡ አገሪቷን በአገር ውስጥና ከውጭም በክፍለ አኅጉሩ ደረጃ ለማገናኘት ካለው ዕ
ቅድ ጋር በተያያዘ 4,744 ኪሎ ሜትር የሃዲድ መስመር
የሚሸፍን ስምንት የባቡር መንገድ ኮሪደሮች በሁለት ምዕራፍ ይገነባል፡፡ ለአብነት ያህል እ.ኤ.አ በ2016 በጂቡቲና በኢትዮጵያ መካከል 4744 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባቡር መንገድ ሥራ ላይ ውሏል፡፡ በተመሳሳይ ዓመት በ3.4 ቢሊዮን ዶላር ወጪ አዲስ አበባንና የጂቡቲ ወደብን የሚያገናኝ የ750 ኪሎ ሜትር የባቡር መንገድ ተግባራዊ ሆኗል፡፡ 90 በመቶ የኢትዮጵያ ገቢ ዕቃ በጂቡቲ ወደብ የሚገባ መሆኑ ሲታሰብ የባቡር ግንኙነቱ የዕቃዎች መግቢያ ዋጋን በ600 በመቶኛ እንዲቀንስ ያደርገዋል፡፡ ከአጠቃላይ የጂቡቲ የዕቃ እንቅስቃሴ 80 በመቶ የኢትዮጵያ ገቢ ዕቃዎች ስለሆኑ ኢትዮጵያ ጂቡቲን የ1.2 ቢሊዮን ዶላር የአገልግሎት ግብር ትከፈላታለች፡፡ ሥራው ሲጠናቀቅ የሕዳሴ ግድቡ በአፍሪካ ውስጥ ትልቁ የውኃ ኃይል ማመንጫ ስለሚሆን ኢትዮጵያ በአኅጉሩ ላሉት አገሮች የመብራት ኃይልን አሁን ወደ ማስራጫ ጣቢያው ከተገናኙት (ሱዳን፣ ጂቡቲ፣ ኬንያ) በተጨማሪ ለመሸጥ የሚያስችላት አቅም ታሳድጋለች፡፡ በኢትዮጵያና በአካባቢው ያለው የአየር መንገድ ግንኙነት በአፍሪካ ውስጥ በጣም ከዳበሩት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ውስጥ ቀዳሚው ሆኖ 85 አውሮፕላኖች አሉት (48 ሌሎችም አዟል)፡፡ ቦሌ አየር ማረፍያም በአፍሪካ ውስጥ ሦስተኛው ከፍተኛ የትራፊክ ጫና ያለበት ማዕከል ነው፡፡
እነኚህ ዋነኛ የመሠረተ ልማት ዕድገቶች የኢኮኖሚ ዕድገቱ ፍጥነት በማጠናከር ረገድ አስፈላጊ መሣርያዎች ናቸው፡፡ ምክንቱም የተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎችን በተለያዩ የመገናኛ አውታሮች አማካይነት ያገናኛሉ፡፡ በተጨማሪም ከልማታዊ መንግሥቱ አመራር ሰፊ ትምህርት መውሰድ በሚያስችል መልኩ እንደ አንድ በአኅጉሩ ውስጥ የማዋሃድ ሚና ያላት አገር የኢትዮጵያን ገፅታ አሳድገዋል፡፡ የመሠረተ ልማት ዕድገቱ ኢጋድ ያለውን የመዋሃድ አጀንዳ
በጠንካራ የኢኮኖሚ መሠረት እንዲገነባ ያግዛል፡፡ አንዴ ካለቁ እነኚህ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች የውህደቱ አስተማማኝ መሣርዎች ናቸው፡፡ ምክንያቱም ከላይ ወደታች በሚወርደው መንግሥታዊ ተነሳሽነት ላይ የተመሠረቱ አይደሉም፡፡ የመገናኛ መስመሮቹ በሚያልፉበት አካባቢ በሚገኙት ኅብረተሰቦች ማኅበራዊ ዕድገት ላይ ገንቢ ሚና ይጫወታሉ፡፡ እንዲሁም ሕግና ሥርዓትን የሚያስከብሩ ማኅበራዊ አገልግሎቶችም በተሟላ መልኩ በድንበሮች አካባቢ ተደራሽነት እንዲኖራቸው ያደርጋሉ፡፡ ሰዎች፣ የሥራ ክህሎትና ሀብት ምንጊዜም ቢሆን መዋለ ንዋይን ትራንስፖርትና የመገናኛ መሠረተ ልማትን ተከትለው ነው የሚሄዱት፡፡ የሰዎችን፣ የዕቃዎችንና አገልግሎቶችን ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ በተመሳሳይ መልኩ የማዋሃድ ዕድልን ያዳብራሉ፡፡ እነኚህ ፕሮጀክቶች የአገር ውስጡንና የአካባቢን ፍላጎቶች ያረካሉ፣ ወቅታዊው የአገሪቷ የውጭ ፖሊሲ ግንዛቤ እንዳለ ሆኖም በተራዘመ ሒደት ኢትዮጵያ በአካባቢው ዲፕሎማሲያዊ አተገባበር ላይ ያሉትን ድክመት ለማስተካከል ወሳኝ እንቅስቃሴ ያመላክታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ፀረ ሽብር
በቅርቡ እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 2016 ከደቡብ ሱዳን በሚያዋስነው ድንበር ላይ ታጣቂዎች 140 ኢትዮጵያውያን ሲቪል ዜጎችን የገደሉበትንና በርካታ ሕፃናት አፍነው የወሰዱበትን እንደ አንድ ተጠቃሸ አብነት ሆኖ ኢትዮጵያ ለተከታታይ የውስጥና የውጭ የሽብር ጥቃቶች ተጋልጣ ቆይታለች፡፡ አ
ገራዊ የፖለቲካ ታሪኳ አውዳሚ በሆኑ ግጭቶችና ጦርነቶች ላይ የታገዙ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ኢትዮጵያ ከሶማሊያና ከኤርትራ በኩል ተከታታይ የሽብር ጥቃቶችን፣
እንዲሁም አሁን የጠፋው አል ኢትሃድ አል ኢስላሚያ፣ የተባበሩ እስላማዊ ፍርድ ቤትና አል ሸባብ ከመሳሰሉት ፅንፈኛ ቡድኖችም የሽብር ጥቃቶች አስተናግዳለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኦጋዴን ብሔራዊ የነፃነት ግንባር፣ የኦሮሞ ነፃነት ግንባርና የኦሮሞ ነፃነት እስላማዊ ግንባር የመሳሰሉት ጥቂት የኢትዮጵያ ታጣቂ ተዋጊ ቡድኖች በሶማሊያ በተፈጠረው መንግሥት አልባነት ምክንያት በዚያው እንደ ዋና መናኸርያና በኢትዮጵያ ላይ ለሚሰነዝሩ ጥቃትም መንደርደርያ አድርገው ተጠቅመውበታል፡፡ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር አሁንም ባልታወጀ ጦርነት ውስጥ ነች፣ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ለድንበር ጦርነቱ የምትሰጠውን ትኩረት ለማዛባት ስትል ኤርትራ እነኚህን ታጣቂ ቡድኖችን እንደውክልና ጦርነት አራማጆች ትጠቀምባቸዋለች፡፡ ከዚህ የተነሳ በኢጋድ አገሮች አካባቢ በሚደረገው ፀረ ሽብር ጦርነት ላይ ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊና ጠንካራ ረዳት ለመሆን ችላለች፡፡
ባለብዙ ዘርፍ መድረኮች፣ አኅጉራዊው ድፕሎማሲና አደራዳሪነት
በሉዓላዊነቷ ላይ ላሉት ሥጋቶች መፍትሔ ለመሻት ካላት ፍላጎት የተነሳ ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት መጀመሪያ በመንግሥታቱ ሊግ፣ ቀጥሎም እሱን በተካው የተባበሩት መንግሥታት በሚመሩዋቸው የጋራ የደኅንነት ጥበቃና የባለብዙ ፈርጅ መድረኮችና ተቋማት ላይ ጠንካራ ድጋፍዋን አበርክታለች፡፡
አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ አካባቢያዊ ጥቅሞች የሚጠበቁት በባለብዙ ዘርፍ ተቋማትና በኢጋድ ድጋፍ ሰጪነት ነው፡፡ የውጭ ጉዳይና የደኅንነት ፖሊሲው ዋናው ምሰሶ በዓለም አቀፍ ተቋማት በተለይም በኢጋድና በአፍሪካ ኅብረት ባለው የመሪነት ሚና ነው፡፡ አገሪቷ የኢጋድ፣ ኮሜሳ፣ አፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታትና የምሥራቅ አፍሪካ የተጠንቀቅ
ኃይል (ኢኤኤፍ) መሥራች አባል አገር ነች፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤትና የምሥራቅ አፍሪካ የተጠንቀቅ ኃይል የስንቅና ትጥቅ ማዕከል መቀመጫ ነች፡፡ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ዕድገት አዲስ ትብብር /ኔፓድ/ እ.ኤ.አ ከ2012 ጀምሮ ለስምንት ዓመታት ያህል በሊቀመንበርነት መርታለች፣ ኢጋድንም እ.ኤ.አ ከ2008 ጀምሮ በሊቀመንበርነት አገልግላለች፡፡ እ.ኤ.አ. በ2012 የነበሩት የቡድን 8 ስብሰባዎችን፣ እ.ኤ.አ ከ2009-2012 በነበሩት የቡድን ሃያ ሰብሰባዎች፣ በአየር ለውጥ ላይ ያተኮሩ የተባበሩ መንግሥታትና የአሜሪካ ስብሰባዎችንና የስደተኞችና ድንበር ተሻጋሪዎች ጉባዔዎችን አፍሪካን በመወከል ተሳትፋለች፡፡ በእነኚህ የጋራ መድረኮች የነቃ ተሳትፎ የምታደርግ ቢሆንም በተጨባጭ ግን ሚዛኑን የደፋ ተሳትፎ የምታደርገው ከሌሎቹ ይልቅ በኢጋድ ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም በውስጣዊና አካባቢያዊ ፈተናዎች ላይ ቀጥተኛ አንድምታ ያላቸው የኢጋድን አካባቢ የሚመለከቱት ፈተናዎችና ዕድሎች ናቸው፡፡ በዚህ የተነሳ የመንግሥቱ አስተሳሰብ የሚቃኘው በወሳኝ መልኩ በኢጋድ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የፖሊተካ መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ ኤክስፐርቶችና ወታደራዊ ኃይሎች በአብዛናዎቹ የኢጋድ እንቅስቃሴዎች ላይ ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል፡፡ በተለይም በአልሸባብና በኤርትራ ላይ በተባበሩት መንግሥታት በተጣሉ ማዕቀቦችና በቀጣይነታቸው ላይ በነበሩት ሒደቶች እውነታነቱ የጎላ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ የኢጋድ አባል አገሮችን አሳምና በማሰለፍ፣ የአፍሪካ ኅብረትን በማሳመንና የውሳኔ ሐሳብን ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በማቅረብ ረገድ የአንበሳውን ድርሻ ተጫውታለች፡፡
ኢትዮጵያ በኢጋድ አገሮች ያሏት ስድስት ሚስዮኖችና ሁለት ቆንስላዎች በአጠቃላይ በውጭ አገሮች ካሏት (36) ዲፕሎማቶች ውስጥ 11.5 በመቶ ይሸፍናሉ፡፡ አሥር ዲፕሎማቶች በኬንያ፣ ስምንት በሱዳን፣ ስድስት በጂቡቲ፣ አምስት በደቡብ ሱዳን፣ አራት በሶማሊያ ሲኖራት በኡጋንዳ ግን
ሦስት ብቻ ነው ያላት (በኤርትራ የነበረው ሚሲዮን እ.ኤ.አ በ1998 ከኤርትራ ጋር በነበረው የድንበር ጦርነት ምክንያት ተዘግቷል)፡፡ በአንድ ሚሲዮን ያለው የዲፕሎማት ቁጥር በአማካይ ስድስት መሆኑ ሲታይ በኢጋድ አገሮች ያሉት የኢትዮጵያ ሚሲዮኖች በሌሎች አገሮች ካሉት ሚሲዮኖች አማካይ ቁጥር (6.24) ያነሱ የዲፕሎማት ቁጥር አለው፡፡
ይህ የሚያሳየው ነገር ቢኖር ኢትዮጵያ በአካባቢያዊና ዓለም አቀፋዊ ዲፕሎማሲ ላይ ያላት የበላይነትና ጥቅም ማስጠበቅ የምትችለው በወሳኝ መልኩ ስኬታማ በሆኑና የማዋሃድ ሚና ባላቸው የኢኮኖሚ ፕሮጀክቶችና እንዲሁም ደግሞ በኢጋድ አካባቢ ሰላምና ፀጥታን በማረጋገጥ ጥረት ላይ በምታደርገው ተሳትፎ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ቢታወቅም በቅርብ ጎረቤቶቿ ለእያንዳንዱ ሚሲዮን የምትመድበው የዲፕሎማት ቁጥር በሌላ አካባቢ ከምትመድበው አማካይ ያነሰ መሆኑን ነው የሚያሳየው፡፡ ይህ የሰው ኃይልና የበጀት አመዳደብ የውጭ ጉዳይና የብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲው ለኢጋድ አካባቢ ከሚሰጠው የቅድሚያ ዲፕሎማሲ ትኩረት ጋር የሚጣጣም አይደለም፡፡ ይህ የሚያሳየው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በበጀት አመዳደቡ አፈጻጸም ላይ ወጥነት እንደሚጎድለው ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ከሱዳን ጋር ያለው የንግድ ግንኙነት ከኬንያ ጋር ካለው በአምስት እጥፍ እንደሚልቅ ሲታይ፣ ሱዳን ያላት ስትራቴጂካዊ የኢኮኖሚ ፋይዳ ግምት ውስጥ ሲገባ (80 በመቶ የኢትዮጵያ ነዳጅ የሚገባው ከሱዳን መሆኑ) እንዲሁም ጂቡቲ (94 በመቶ የኢትዮጵያ የባህር ንግድ ከጂቡቲ መሆኑና 980 ሚሊዮን ዶላር ለወደብ አገልግሎት የሚከፈላት መሆኗ) በናይሮቢ የተቀመጡ የዲፕሎማቶች ቁጥርና በጂቡቲና በካርቱም የተቀመጡ የዲፕሎማቶች ቁጥር መዛነፍ ሲታይ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት የሚቃኘው በውጭ ጉዳይና የብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲው እንደተገለጸው በኢኮኖሚያዊ ስልቶች አለመሆኑን ነው፡፡
ኢትዮጵያ በቅርብ ጎረቤቶቿ ካሉት የኢኮኖሚና የንግድ ዕድሎች መጠቀም ትችል ዘንድ በጎረቤቶቿ ላሉት ሚሲዮኖች ከምትመደበው በጀት (ዲፕሎማቶች፣ ገንዘብና ለዲፕሎማቶች የሚሰጥ ማነቃቅያ) በስተጀርባ ያለው መመዘኛ እንደገና መታየት አለበት፡፡ የኢትዮጵያን ፖሊሲ የሚያመነጩ ሰዎች በውጭ ጉዳይና የብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲው በተቀመጠው መሠረት ለኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲው ቅድሚያ መስጠት አለባቸው፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲህ ያለውን አለመመጣጠን በውጭ ጉዳይና የብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲው በተቀመጠው ቅደም ተከተል መሠረት አካባቢውንና የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲውን በሚመጥን መልኩ በተመጣጠነ የበጀት አመዳደብ ሊፈታው ይገባል፡፡
ታማኝ አደራዳሪ
ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ከ1950ዎቹ ጀምሮ በአካባቢው በአደራዳሪነትና በሰላም ሒደት ላይ በመሳተፍ የዳበረ ታሪክ አላት፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1967-1970 የነበረው የናይጄርያው የቢያፈራን ጦርነት መፍትሔ በማፈላለግ ረገድ ረድታለች፣ በቅርብ ጎረቤቷ ደግሞ በሱዳን መንግሥትና በወቅቱ በደቡብ ሱዳን ውስጥ የነበረውን አማጺ ቡድን መካከል እ.ኤ.አ. የ1972ዎቹ የአዲስ አበባ ስምምነት አደራድራለች፡፡ በ1993 ለድርቅና ዕድገት የበይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ መፈጠር በፊት የነበረው) ሲባል በነበረው ስር ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ኬንያና፣ ኡጋንዳ ያሉበት የሰላም ኮሚቴ በማዋቀር ለረዥም ጊዜ የቆየውን የሱዳንን የእርስ በርስ ጦርነት እንዲቆም በማድረግ ኢትዮጵያ ረድታለች፡፡ ይህም ጦርነቱን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስቆም ይቻል ዘንድ ፍትሐዊና ሁሉን አቀፍ መፍትሔ ሊያመጡ የሚችሉ አስፈላጊ ግብዓቶችን መለየት ያለመውን የ1994 የኢጋድ መሠረተ ሐሳቦች ውሳኔ ላይ እንዲደርስ አስችሏል፡፡ እ.ኤ.አ በ2005 የሱዳን መንግሥትና የሱዳን ሕዝቦች የነጻነት ንቅናቄ (ሠራዊት) በኢጋድና በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ሁሉን አቀፍ የሰላም ሰምምነት ተፈራርመዋል፡፡ ስምምነቱን የወጠነውና በቀጣይነትም የአውሮፓ ኅብረት አሜሪካና የተባበሩት መንሥታት ከመሳሰሉት ረዳቶቹ ጋር በመሆን ለስምምነቱ ተፈጻሚነት በቅርበት የሠራው በኢትዮጵያ አነሳሽነት ኢጋድ ነው፡፡
የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ አስፈጻሚ ቡድን /AUHIP/ እንዲቋቋም በዳርፉር በሱዳንና ደቡብ ሱዳን መካከል በሚደርገው የሰላም ድርድርም የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ኢምቤኪ በዋና አደራዳሪነት እንዲመደቡ በማድረግ ላይ ኢትዮጵያ ሚና ነበራት፡፡ ኢትዮጵያ ከሁለቱም ወገኖች ማለትም ከሱዳን መንግሥትና ከሱዳን ሕዝቦች የነጻነት እንቅስቃሴ (ሠራዊት) ተዓማኒነት ማግኘቷን በሚያመላክት መልኩ እ.ኤ.አ የሐምሌ 2008ቱ የአብዬይ ማካለል የድርድር ስምምነት (የፀጥታ ዋስትና ዝግጅቶች እንዲደረጉና ከአወዛጋቢዎቹ ክልሎች የተፈናቀሉትን መልሶ የማስፈር አስፈላጊነትን የሚዘረዝረው ማለት ነው) ፈራሚዎቹ ወገኖች ሁለቱም የአዲስ አበባን የአደራዳሪነትንና ሰላም የማስከበርን ሚና ተቀብለዋል፡፡
በደቡብ ሱዳን የተከሰተውን ቀውስ ምክንያት በማድረግ እ.ኤ.አ በታኅሣሥ 2013 በመንግሥትና በተቃዋሚ ኃይሎች መካከል ጦርነት ከተቀሰቀሰ ከአራት ቀናት በኋላ ማለት ነው ኢጋድ አንድ የሚኒስትሮች ልዑክ ወደ ጁባ ላከ፡፡ በተመሳሳይ ቀን የአፍሪካ ኅብረት በሰላምና ፀጥታው ምክር ቤት አማካይነት ለኢጋድ ያለውን ድጋፍ ገለጸ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በኢጋድ ሰብሳቢነቱ እየወሰደ ያለው ወቅታዊ ተነሳሽነትም አደነቀ፡፡ በቀድሞው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋና አደራዳሪነት የኢጋድ አደራዳሪ ቡድኑ ከኬንያና ሱዳን ጭምር አባላት አካትቶ ነበር፡፡ ይህም ወደ ኢጋድ ፕላስ (የኢጋድ አባል አገሮችና አምስት ተጨማሪ አገሮች፡- አልጄርያ፣ ቻድ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጀርያ ይህም አምስቱ የአፍሪካ ኅብረት አካባቢዎች እንዲወክሉ በማለት ነው፡፡) ምስረታና በሂትም እ.ኤ.አ የነሐሴ 2015 የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ ግጭትን የመፍታት ስምምነት
ወደመፈረም አመራ፡፡ ስምምነቱ እንደ አፍሪካ ኅብረት፣ አውሮፓ ኅብረት፣ አሜሪካና የተባበሩት መንግሥታት የመሳሰሉት ዓለም አቀፍ ተዋንያንን ሰፊ ድጋፍ አግኝቷል፡፡ በቀጣይም በኢትዮጵያ ላይ ያለው እምነት በሚያጠናክር መልኩ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ዕውቅናና ውክልናው ከሰጠና የኃይል መጠኑንም ካሳደገ በኋላ በተባበሩት መንግሥታት የአብዬይ የሽግግር የፀጥታ ኃይል /UNISFA/ አዛዥ የነበረው ኢትዮጵያዊው የሠራዊት መሪ የተባበሩት መንግሥታት የደቡብ ሱዳን ተልዕኮ /UNHISS/ መሪ ሆኖ ተመድቧል፡፡
ወታደራዊ ጥንካሬና የሰላም ማስከበር ግዳጆች
ኢትዮጵያ ያላት ተነጻጻሪ ወታደራዊ አቅምና በአካባቢያዊ ሰላምና ፀጥታ ላይ ያላት ሚና፣ እንዲሁም በሰላም ማስከበር፣ በፀረ ሽብርና በአደራዳሪነት ላይ ያለት ጥሩ ቅድመ ታሪክ ተደምሮ በባለ ብዙ ፈርጅ መድረኮች፣ በረዥም ወዳጅነቶችና ትብብሮች ላይ ተፅዕኖ እንዲኖራት አስችሏታል፡፡ ለዚህ ምስክር በሚሆን መልኩ እ.ኤ.አ. በ2014 ፕሬዚዳንት ኦባማ እንዳሉት፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሠራዊት፣
በዓለም ከምርጦቹ አንዱ ሊሆን ይችላል፡፡ በሰላም ማስከበር ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ ከሚያደርጉት ውስጥ ነው፡፡ ግጭቶችን መፍታት በሚኖርበት ጊዜና በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በሚሆንበት ጊዜም ውጤታማ ተዋጊ ኃይል ከሆኑት ውስጥ አንዱ ነው፡፡››
እ.ኤ.አ በ1998 ከኤርትራ ጋር ከነበረው የደንበር ጦርነት ጀምሮ ኢትዮጵያ ወታደራዊ አቅሟን አሳድጋለች፡፡ ይሁን እንጂ ከሌሎቹ ትልቅ የሚባሉት የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲነጻጸር ወታደራዊ በጀትዋ በተነጻጻሪ መልኩ ዝቅተኛ የሚባል ነው፡፡ በወታደራዊ ወጭ የተደረገው ጭማሪም ቢሆን አነስተኛና ምክንያታዊ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ በ2013/14 የነበረው ወታደራዊ በጀቷ ከአጠቃላይ አገራዊ ገቢዋ (GDP 0.8 በመቶኛ ነው፡፡ ይህም ዝቅተኛ ከሚባሉ ግማሽ የዓለም አገሮች ያስቀምጣታል፡፡ በተነጻጻሪነትም እንደ ኤርትራ (6.3 በመቶ)፣ ጂቡቲ (3.8 በመቶ) ግብፅ (3.4 በመቶ)፣ ሱዳን (ሦስት በመቶ) እና ኬንያ (2.8 በመቶ) ከመሳሰሉት በከፍለ አኅጉሩ ካሉት አገሮች በዝቅተኛ ደረጃ ያስቀምጣታል፡፡ በወታደሩ ጥንካሬና በትጥቅ ረገድ ሲታይ ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉት አገሮች በቀዳሚነት ከአፍሪካ በሦስተኝነት (ከግብፅና አልጀርያ ቀጥሎ)፣ ከዓለም ደግሞ በ40ኛ ደረጃ ትቀመጣለች፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከተመሠረተበት እ.ኤ.አ ከ1945 ጀምሮ ኢትዮጵያ ከአሥር በሚበልጡ የሰላም ማስከበር ግዳጆች ተሳትፋለች፡፡ አሁንም ቢሆን በሰላም ማስከበር ግዳጆች ውስጥ ከፍተኛው የሠራዊት ኃይል የምታዋጣ አገር ነች፡፡ እ.ኤ.አ በ2016 ውስጥ 12,721 ወታደሮች አዋጥታለች፡፡ ከዚህ ውስጥ 4,395ቱ በሶማሊያ የአፍሪካ ተልዕኮ (AMISOM) በመሳተፍ ላይ ያለ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ተልዕኮ በአብዬይ (UNISFA) ከዚህ ሁሉ የተለየ ነው፡፡ ምክንያቱም 4,250 የሠራዊቱ አባላት ኢትዮጵያዊያን ስለሆኑ የሰው ኃይሉ በሙሉ ከአንድ አገር ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ወታደራዊ ጄኔራሎች በአብዬይ እና በሶማሊያው የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች በኃይል አዛዥነት ቦታዎች ተመድበዋል፡፡ በዳርፉር ባለው የተባበሩት መንግሥታትና የአፍሪካ ኅብረት ቅልቅል የሰላም አስከባሪ ኃይል ውስጥም ቢሆን ኢትዮጵያ ሦስተኛ ትልቁን ሠራዊት ያበረከተች አገር ነች፡፡
ማጠቃለያ
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ወሳኝነት ያላት አገር እንድትሆን ባደረጉት የተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ኩነቶች መካከል ያለውን ሚዛናዊነት አስፈላጊነት እንዳለ ሆኖ በአካባቢው ሰላምና ፀጥታ የተወሰዱት በጣም ወሳኝና አስፈላጊ ዕርምጃዎች ግን በኢጋድ አማካይነት የተጀመሩትና የተፈጸሙት መሆናቸው ግልፅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለውስጣዊ ሥጋቷና አካባቢው እያጋጠመው ላለው ፈተና እንዲሁም መወሰድ ስላለባቸው ዕርምጃዎች የምትሰጠው ትንተና ተዓማኒነትና ተቀባይነት እያገኘ ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያትም የምታደርገው ማንኛውም ጥረት አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሚና ካላቸው ኃይላት ጋር ተቀናጅታ ስለምትሠራና የጋራ ውሳኔን መሠረት አድርጋ ስለምትንቀሳቀስ ነው፡፡ በአንዳንዱ አካባቢያዊ የኃይል አሠላለፍና ሁኔታዎች ላይ ኢትዮጵያ ያላት ግንዛቤና አቋም በአካባቢው ዲፕሎማሲና ፖለቲካዊ ዝንባሌ ላይ ገዥ የሚሆንበት ሁኔታ አለ፡፡ የአፍሪካ ኅብረትና ሌሎች ዓለም አቀፍ ኅብረተሰቦች (የተባበሩት መንግሥታት፣ የአውሮፓ ኅብረትና እንደ ቻይና የመሳሰሉ ታዳጊ ኃይላት ማለት ነው) በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በአካባቢው የውጭ ግንኙት ላይ የምታደርገውን ጥረት ይደግፋሉ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ አሜሪካና ቻይና የመሳሰሉት ድርጅቶችና አገሮች ደግሞ በተለይም ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያንና ኤርትራን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ኢትዮጵያን ያማክራሉ፡፡ በኢጋድ የተመራው የደቡብ ሱዳን የሰላም ሒደት በአፍሪካ ኅብረት ክፍተኛ የአስፈጻሚነት ቡድን (AUHIP) ስር በደቡብ ሱዳንና በሱዳን መካከል የተካሄደው የአዳራዳሪነት ሚና፣ በሶማሊያ ሰላምን ለማምጣት የተደረገው ጥረት፣ እንዲሁም እ.ኤ.አ በ1998 ከነበረው የድንበር ጦርነት በኋላ ኤርትራን ከውጭ ግንኙነቷ ለመነጠል የተደረገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በሙሉ የሚያሳዩት ኢትዮጵያ በአካባቢያዊ ዲፕሎማሲ ያስመዘገበችውን ድል ነው፡፡
ኢትዮጵያ የምትከተለው ፖሊሲ በሙሉ ብሔራዊ
ጥቅሟን ከማስጠበቅ አኳያ ቢሆንም በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተው አቀራረቧ አዝጋሚና እንዳንዴም እንቅፋቶች ያሉበት ነው፡፡ በዕድገት ላይ የሚያዘነብለው ውስጣዊ መንግሥታዊ አስተዳደሯ በኢጋድ ዘንድ ተቀባይነት አለው፣ በአፍሪካ ኅብረትም ይደነቃል፣ በዓለም አቀፉ ኅብረተሰብም ይደገፋል፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ውስጣዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ያስገባ የመሆኑ ጉዳይ ከመሠረቱ ትክክል ነው፡፡ ምክንያቱም ውስጣዊ ፈተናዎችን ለመፍታት የቅድሚያ ትኩረት ይሰጣልና፡፡ ለረዥም ጊዜ የቆዩትን የተዛቡ ፖሊሲዎችን በማፅዳት የውጭ ጉዳይና ብሔራዊ የደኅንነት ፖሊሲው በብሔራዊ የደኅንነትና የውጭ ፖሊሲው አገራዊ ምሰሶዎች ላይ ከፍተኛ ሽግግር ፈጥሯል፡፡ ይሁን እንጂ በኤርትራ በኩል የነበረው በጥላቻ ላይ የተመሠረተ የአገር ግንባታና በግብፅ በኩል የነበረውን ለረዥም ጊዜ የቀጠለው በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አማጺ ታጣቂዎችን የመርዳት ሁኔታ በሒደት ሊያመጡት የሚችሉት አደጋ አሳንሶ የማየትን ባህርይ፣ እንዲሁም ለባህርና ለወደብ አገልግሎት ተደራሽ መሆን ያለው ጄኦፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ከፀጥታና ከደኅንነት አኳያም ሁሉን አቀፍ ጥቅም መገመት አለመቻል፡፡ ሁሉም የሚመነጩት የመንግሥትን ወደውስጣዊ ችግር ብቻ ከማየት በህርይ ነው፡፡ አስተማማኝ ወታደራዊ ቁመና ይዞ አለመታየትም ለኤርትራ ጥቃት አጋልጦ እንደሰጠ ሌላው አብነት ነው፡፡ ምክንያቱም ኤርትራ የወቅቱን የኢትዮጵያ ወታደራዊ አቅም አሳንሳ አይታለች፡፡ ይህ ወደ ውስጥ የማየት ፖሊሲ ባህርይ በአኅጉሩ ውስጥ አዲስ የሚፈጠሩ ሥጋቶችን ቀድሞ ከማየትና እንደ አስፈላጊነቱ ይህንኑ ተከትሎ ከሚደረጉ የምላሽ መስተካክሎችም ሊገድብ ይችላል፡፡ በየመን የተከሰተው ቀውስና እሱን ተከትሎ ኤርትራ ያሳካችው ከዲፕሎማሲያዊ መነጠል የመውጣት ሒደት የውጭ ጉዳይና ብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲው ድክመት መገለጫ ይሆናል፡፡
እ.ኤ.አ. ከ1998 የኤርትራ ወረራና እሱን ተከትሎ ከመጣው የድንበርና የዲፕሎማሲ ጦርነት በኋላ ድንገተኛና ከፍተኛ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች ተከስቷል፡፡ እስከዚሁ ወቅት ድረስ በፖሊሲ ደረጃ ኢትዮጵያ በውስጣዊ የዕድገትና የፖለቲካ ሁናቴዎች ውስጥ ተጠምዳ ቆይታለች፡፡ እ.ኤ.አ የ1998ቱ ጦርነት ያመላከተው ቢኖር አገሪቷ ኤርትራን በምታክል በከፍተኛ ደረጃ በምታንስ አገር እንኳን ለወታደራዊ ሥጋት ምን ያህል ተጋላጭ እንደሆነች ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ያመላከተው ቢኖር ወደ ውስጥ ብቻ የሚያይ የውጭ ፖሊሲ በዲፕሎማሲው መስክ ያለበትን ድክመት ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል እስከዚህ ወቅት ድረስ ኢሕአዴግ በኤርትራና ኢትዮጵያ ለወደብ አገልግሎት ባላት ተደራሽነት ደኅንነት ላይ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ እንደ ድንበር አልባ አገር እየደረሰባት ያለው የመከበብን አደጋ ላይ ሲነሱ ለነበሩ ሥጋቶች ግምት አይሰጥም ነበር፡፡ ከኤርትራው ጦርነት በኋላ ባለፉት 15 ዓመታት የውጤት ደረጃቸው ቢለያይም የወደብ አገልግሎት ሲሰጡትና ሰላማዊ የጋራ ተጠቃሚነትን ሊመሠርትባቸው ከሚችሉ እንደ ጅቡቲ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ (ሶማሊላንድ) እና ኬንያ ከመሳሰሉ ጎረቤት አገሮች ጋር ግንኙነቶችን መመሥረት ጀምሯል፡
ካሉት ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ፣ የሕዝብ ብዛትና በቅርቡ እየተመዘገበ ያለው ተስፋ ሰጭ የኢኮኖሚ አፈጻጸም የተነሳ ኢትዮጵያ በኢጋድ ክልል ውስጥ የውህደት ማዕከል ልትሆን ትችላለች፡፡ ይሁን እንጂ ለአካባቢያዊ ውህደት በሚያመቻች መልኩ ኢኮኖሚያዊና የንግድ ዕድሎችን መጠቀም መቻል በአካባቢያዊ ንግድና ኢኮኖሚ ላይ ያተኮረና በራስ ተነሳሽነት ላይ የተመሠረተ የውጭ ፖሊሲ ይሻል፡፡ ኢትዮጵያ በቅርብ ጎረቤቶቿ ዘንድ ትርጉም ያለው የኢኮኖሚና የንግድ ዕድሎች ተጠቃሚ ለመሆን ከፈለገች በጎረቤት አገሮች ባሉት የዲፕሎማሲ ሚስዮኖቿ ላይ የምትከተለው የሰው ኃይል፣ የዲፕሎማትና የገንዘብ አመደደብ ምክንያታዊነት እንደገና ሊታይ ይገባል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለኢጋድ አባል አገሮች ከሚሰጠው የፖሊሲ ትኩረት ጋር ሊመጣጠን በማይችል ደረጃ በሚመድበው በቂ ያልሆነ የሰው ኃይልና በጀት ላይ ያለው አለመጣጣም መፍታት ይኖርበታል፡፡
በመንግሥት ተመሳሳይ ለሆኑ ገንቢ ትችቶች የሚሰጠው የተለመደ መልስ የውጭ ጉዳይና ብሔራዊ ፖሊሲው ዋና ዋና ችግሮች የሚመነጩት በፖሊሲ አቅጣጫው ካሉት ድክመቾቶች ሳይሆን ከአተገባበር ድክመቶች መሆናቸውን ነው፡፡ ይህን ሊሞግት በሚችል መልኩ የአተገባበር ሒደቶችን ቀድሞም ቢሆን እንደ አጠቃላይ የአፈጻጸም ሒደት አካል አድርጎ ያልተገነዘበ ፖሊሲ ከመሠረቱ ጉድለት ያለበት ፖሊሲ ነው ማለት ይቻላል፡፡
በድምሩ ሲታይ ከመጠን በላይ ወደ ውስጣዊ ጉዳዮች በማየት ላይ የተመሠረተ ፖሊሲ የውጭ ሥጋቶችን አሳስቶ ወደ መገመትና አሳንሶ ወደማየት የመሰሉ ስህተቶች አምርቷል፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር ጥላቻ ያላቸው አገሮችና መንግሥታት ሁልጊዜ ሚዛናዊ የሆነ ስሌት ይከተላሉ ወደሚል አደገኛ ግምት ሄዷል፡፡ በእርግጥ ሚዛናዊ የሆነ የሰው ልጅ ድርጊት እንደ ፖሊሲ መነሻነት ሊያገለግል ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ አርቆ የሚያይ ፖሊሲ እ.ኤ.አ. የ1998ቱ የኤርትራ ወረራ ዓይነቱ የተሳሳተ ግምትም ሊሆን እንደሚችል ግምት ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡
ያም ሆነ ይህ ሁኔታዎችን የመገመትና የመተንበይ አቅምንና ወደ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች የማየት ሚዛናዊነት፣ ሚዛናዊ ለሆነ የሀብት አመዳደብ ጠቃሚ ግብዓቶች ናቸው፡፡ ይህ ሲሆንም የሚታዩ ሥጋቶችን መመከትና መከላከልን ያስችላል፡፡ ለውጭ ሥቶችና ዕድሎችም ተመጣጣኝና በቂ በሚባል ትኩረት መስጠትን ያስችላል፡፡ ከዚህም በላይ ፖሊሲው ሁሉም የሚታይና መገመት የሚቻለውን አማራጭ ጥሩውም ይሁን መጥፎው ግምት ውስጥ ማስገባት መቻል አለበት፡፡ በዚህ ረገድ ውስጣዊ አለመረጋጋትና በተለይም በየመን፣ ቀይ ባህርና በአፍሪካ ቀንድ ከኤርትራ ጋር ወደ ቀድሞው ወታደራዊ ፍልሚያ ለመግባት ያለው ዕድል፣ በጅቡቲ ሶማሊያና ሱዳን ውስጥ ወዳጅ ያልሆኑ ኃይሎችን መገኘትና ጣልቃ መግባት ያሉት ውጫዊ ክስተቶች መፍታትና ግምት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በኢኮኖሚው መስክ ያለው ዕድገትና ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባውን የዕቃ መጠን ሲታይ የወደብ አገልግሎት ለኢትዮጵያ ወሳኝ መሆኑና ለዚህ ሲሰጠው የነበረው አነስተኛ ትኩረት መለወጥ እንዳለበት ያመላክታል፡፡ ካልሆነ በአካባቢው እያደገ የመጣው አለመረጋጋት ኢትዮጵያ ለወደብ አገልግሎት ያላትን ተደራሽነት ሊጎዳ ይችላል፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በሶማሊያና በሱዳን መንግሥታት ሊኖር የሚችለው ለውጥ በኢትዮጵያ ላይ አሳሳቢ አንድምታ ሊኖረው ይችላል፡፡
ኔፓድ /NEPAD/፣ አሚሶም /AMISOM/ እና ዩኒስፋ /UNISFA/ በሚወስዷቸው ዕርምጃዎችና በደቡብ ሱዳን የሰላም ውይይቶች እንደነበራት ሁሉ ኢትዮጵያ በብዙ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች የመሪነት ሚና ልትጫወት ትችላለች፡፡ ለምሳሌ ያህል ከትልልቅ የስደተኞች አስተናጋጅ አመንጭና አስተላላፊ አገሮች ውስጥ አንዷ እንደመሆኗና መደበኛ ያልሆነ ስደተኛነትን ከሚያመነጭ ዋና ዋና አገሮች ውስጥ አንዷ እንደመሆኗ ፍልሰትን በማስተዳደሩ ረገድ የመሪነት ሚና መጫወት አኅጉራዊና ዓለማዊ ሚና ባላቸው ተቋማትና አገሮች ዘንድ ጥሩ ተቀባይነት ያስገኛል፡፡
የውጭ ጉዳይና ብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲው ተጋላጭነትን መሠረት ያደረገ የውጭና የደኅንነት ፖሊሲ ነው፡፡ የኤርትራው የድንበር ጦርነት እየተራዘመ የመሄዱና በአካባቢው ያሉ ኢትዮጵያውያን ያላቸው የኢኮኖሚው ተሳትፎ ዝቅተኝነት ሲታይ በወሳኝ መልኩ የኢሕአዴግ ወደ ውስጥ ችግር የማየት ፖሊሲ ወጥነት እንደሌለው ነው የሚያመለክተው፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ውስጣዊ ቀውስና ግጭቶች ኢትዮጵያ
በቀጣይነት እንዳትረጋጋ የዓባይን ውኃ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገቷ ለመጠቀም ያላትን ዕቅድ እንዲሰናከል ለማድረግ ኤርትራና ግብፅ ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡ የእነኚህ ቀውሶች አንድምታዎች ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሞት በኋላ በኢሕአዴግ ውስጥ በተከሰተው የፖለቲካዊ መሪነት መልመስና የአቅም ክፍተት ምክንያት ሊባባስ ይችላል፡፡ በሥጋቶችና ዕድሎች መካከል ያለውን ሚዛን ቢጠበቅና በውስጣዊና ውጫዊ ተጋላጭነት ላይ ትኩረት ቢኖር ኖሮ ኢትዮጵያ ዓይነተኛ ለውጥ ባታደርግም ፈጣን መስተካከል በሚጠይቁት የፖሊሲ አቋሟ ላይ ተፅፅኖ በሚፈጥሩ ጂኦፖለቲካዊ፣ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ላይ ደግማ ማየት ይገባት ነበር፡፡
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ የሚታይ ሥጋት በሚኖርበት ጊዜ የውጭ ጉዳይና ብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲው ሥጋቱን ለመፍታት ያለው ብቃት ጥርጥር ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ፖሊሲው ፈጣን ማሻሻያ ይሻል፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ አሁን ያለው ወደ ውስጣዊ ችግር ብቻ የሚያይ ፖሊሲ በደንብ መፈተሽ ወቅታዊ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ላይ ባላት የበላይነትና በውስጣዊ መረጋጋቷ፣ ዴሞክራሲዋና ኢኮኖሚዋ ላይ አደገኛ የሚባል ፈተና እየደቀኑ ያሉት አንዳንዶቹ አዲስ፤ የቀሩት ደግሞ ለረዥም ጊዜ የቆዩ ውስጣዊ፣ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ችግሮች ናቸው፡፡ ስለዚህ ወደ ውስጥ የመመልከት ፖሊሲው የውስጣዊ አለመረጋጋቱ ምክንያቶች ለይቶ በመፍታት ረገድ ትኩረት ሲያደርግ፣ በሌላ በኩል ግን በቅድመ ተነሳሽነት አገሪቱን በመከላከልና ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች የሰጡትን ሕጋዊ ዕድል በመጠቀም ረገድ ሚዛናዊነትን ይጠይቃል፡፡ ካልሆነ ግን ውስጣዊው የፖለቲካ ቀውስ፣ በየመንና በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉት ግጭቶች፣ በዓባይ ወንዝ ላይ የውኃ ፖለቲካና የተጠቃሚነት ሽሚያና ሽብር፣ እንዲሁም ነውጠኛ ፅንፈኝነት የመሳሰሉ ድንበር ተሻጋሪ ሥጋቶች ኢትዮጵያ እስካሁን ያስመዘገበችውን አስደናቂ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ድል ሊያጨናግፈው ይችላል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የፖለቲካ ተንታኝና የአፍሪካ ቀንድ ኤክስፐርት ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡