Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየካንሰር ሕሙማንን ለመታደግ

የካንሰር ሕሙማንን ለመታደግ

ቀን:

በኢትዮጵያ የካንሰር ሕሙማን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመምጣቱን ያህል ቀድሞ የመከላከሉም ሆነ የታመሙትን በሕክምና የመድረሱ ጉዳይ አሁንም ፈተና ነው፡፡ ከ21 ዓመት በፊት ለካንሰር ሕሙማን የጨረር ሕክምና የጀመረው የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልም አሁንም ድረስ ሕክምናውን በብቸኝነት ይሰጣል፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ ለሆስፒታሉም ብቻ ሳይሆን ለሕሙማኑም እንግልትና ስቃይ ነው፡፡

ሕፃናት አይሉ አዋቂ፣ ከተሜ አይሉ ከክልል የሚመጡት የካንሰር ሕሙማን ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሕክምናን ሽተው ሲንከራተቱ ማየቱም ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ ከሕክምናው ውስብስብነት በበለጠም ሕክምናው በተለያዩ ሆስፒታሎች አለመሰጠቱ ታማሚውን ለተደራራቢ ችግር አጋልጧል፡፡ ጥቂት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከየክልሉ መጥተው መግቢያ ያጡ፣ ሕክምና የሚጠባበቁ የካንሰር ሕሙማንን የማስጠለልና የመርዳት ሥራ ቢያከናውኑም ችግሩ እንዲህ በቀላል የሚፈታ አልሆነም፡፡

አቅሙ ያላቸው ከኢትዮጵያ ውጪ የጨረሩንም ሆነ የኬሞቴራፒውን ሕክምና ሲከታተሉ፣ አቅሙ የሌላቸው ሕክምና ለማግኘት የተሰጣቸውን የወራት ቀጠሮ እንኳን ሳይደርሱበት ይሞታሉ፡፡ ካንሰር ከታማሚው ባለፈም ለቤተሰብም ከባድ ዋጋ የሚያስከፍል ነው፡፡

በዓለም አስቸጋሪና ቀዳሚ ሕይወት ቀጣፊ የሆነውን የካንሰር ሕመም ለማከምና ለመከላከል አገሮች የተለያዩ ጥረቶችን ቢያደርጉም፣ ሕመሙን አክሞ ማዳኑ አሁንም ለብዙዎች ፈተና ነው፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ የሕክምና ተደራሽነቱ ዝቅተኛ በሆነባቸው አገሮች ሕመምተኛውን አክሞ ማዳን ብቻ ሳይሆን ለሕመሙ ማስታገሻ እንኳን አግኝቶ መሞትን ማግኘት የሰማይን ያህል የራቀ ነው፡፡

በአንጀት፣ በጡት፣ በማሕፀንና በሌሎችም የካንሰር ዓይነቶች ታመው ሕክምና ከጀመሩ በኋላ በሕመሙ ከሚሰቃዩት ባለፈም በኬሞቴራፒ ጊዜ የሚገጥማቸውን ሕመም ሊያስታግሱ የሚችሉ መድኃኒቶችን በቀላሉ ማግኘትም በኢትዮጵያ ፈተና ነው፡፡

ከፀጉር መነቀልና መርገፍ ጀምሮ በጥፍርና በቆዳ ላይ ለሚገጥመው ለውጥ ሁሉ አስቀድሞ ምክር ማግኘትና የሚመጣውን ለመቀበል ሕሙማንን ማዘጋጀቱ ደግሞ ምናልባትም ሕክምናውን አጥተው ለሚንከራተቱትና አግኝተውም ሞታቸውን ለሚጠብቁት ሕሙማን ቅንጦት ሊመስል ይችላል፡፡

የካንሰር ሕመምን ቀድሞ ለመከላከልም ሆነ ከታመሙ በኋላ አክሞ ለማዳን፣ ግንዛቤ ለማስጨበጥ፣ ሕመሙ ከተከሰተ በኋላም የምክር አገልግሎትን ጨምሮ የጨረርና የኬሞቴራፒ ሕክምና ድረስ ያለውንና ከዚህ ተያይዘው የሚከሰቱ ሕመሞችን ያማከለ አጠቃላይ ሕክምናው አንድ ላይ ተጣምሮ መሰጠቱ በተለይ የሕሙማኑን እንግልትና ስቃይ የሚቀንስ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ግን ይህንን አገልግሎት አንድ ላይ አሟልቶ መስጠቱ ብቻ ሳይሆን ሕክምናውንም በቅጡ የሚሰጡ ተቋማት ማግኘቱ ፈተና ነው፡፡ የጥቁር አንበሳው የካንሰር ሕክምና ማዕከልም ቢሆን የቁሳቁስ ብቻ ሳይሆን በሕክምና ባለሙያዎችም እጥረት ጭምር የሚፈተን ነው፡፡ ከአቅሙ በላይ ሕሙማንን እያስተናገደም ይገኛል፡፡

የዓለም ካንሰር ቀንን አስመልክቶ ጥር 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ‹‹ራሴንም ሆነ ቤተሰቤንና ወገኔን ከካንሰር ሕመም ለመከላከል ቆርጬ ተነስቻለሁ›› በሚል መሪ ቃል ሲከበር የተገኙት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ዳዊት ወንድማገኝ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የካንሰር ሕክምና ክፍል ከበፊቱ የተሻለ አገልግሎት እየሰጠ ቢገኝም፣ በተሻለ መንገድ ማዋቀርና ማደራጀት ያስፈልጋል፡፡

የካንሰር ሕሙማንን ለማከም የሚሰጡ አገልግሎቶች የተለያየ ቦታ መሆናቸው ሀብት እንዲበታተን፣ ሕሙማን እንዲንገላቱ፣ ሕክምናዎች በፍጥነት እንዳይከናውኑ የሚያደርግ በመሆኑ አንድ የካንሰር ሕመምተኛ የሚያስፈልጉትን ሙሉ ሕክምናዎች በአንድ ማዕከል የሚያገኝበትን አሠራር ለመዘርጋትና ወጥ ለማድረግ ዋና መቀመጫውን አሜሪካ ካደረገው ፒፕል ቱ ፒፕል ጋር አብረው እየሠሩ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የፒፕል ቱ ፒፕል መሥራችና ዋና ዳይሬክተር እናውጋው መሐሪ (ዶ/ር)፣ ሕክምናውን በአንድ ማዕከል ማለትም የአንድ መስኮት አገልግሎት እንደሚባለው ሕሙማን ከምርመራ እስከ ሕክምና በአንድ ሕክምና ማዕከል የሚያገኙበትን ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ፣ ለዚህም ፒፕል ቱ ፒፕል ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኤችአይቪ ኤድስ፣ የሳንባ ነቀርሳና የወባ ሕመሞች በጋራ ከሚቀጥፉት የሰው ሕይወት በበለጠ የካንሰር ሕመም የሚገድለው ይበልጣል፡፡ ችግሩን መቆጣጠር ካልተቻለም በቀጣዩ 20 ዓመት በየዓመቱ 24 ሚሊዮኖችን ይገድላል፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ በየዓመቱ ከ67,000 ሰዎች በላይ በካንሰር የሚያዙ ሲሆን፣ ሕክምናው ተደራሽ ባለመሆኑም 44,000 ያህሉ ሕክምና ሳያገኙ ይሞታሉ፡፡ የሕፃናት ካንሰር ደግሞ ትኩረት ያልሰተሰጠውና ከጨቅላ ሕፃናት እስከ 19 የዕድሜ ክልል ያሉትን እየቀጠፈ የሚገኝ ነው፡፡

ካንሰር በኢትዮጵያ እየፈጠረ ያለውን ከፍተኛ ጫና ለማቃለልም ብሔራዊ የካንሰር መከላከል ዕቅድ በጤና ሚኒስቴር ተዘጋጅቶና ፀድቆ እየተገበረ ነው፡፡ በጅማ፣ በሀሮማያ፣ በጎንደር፣ በመቐለና በሐዋሳ የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች የካንሰር ሕክምና ማዕከሎች ግንባታ እየተካሄደ ሲሆን፣ እነዚህ ማዕከሎች ግንባታ የተጓተተ ቢሆንም በቅርቡ ተጠናቀው ሥራ ላይ ይውላሉ ተብሎ ይጠበቃለ፡፡ ከ22 ሚሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ስድስት ዘመናዊ የጨረር ወይም የራዲዮቴራፒ መሣሪያዎች ግዢ ተካሂዷል፡፡

ይህም በቅርቡ የካንሰር ሕክምና አገልግሎትን ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በአምስት የክልል ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ውስጥ ለመስጠት እንደሚያስችልና የተጠቃሚዎችን መንገላታትና ረዥም የሕክምና ቀጠሮን የሚያስቀር መሆኑን በጤና ሚኒስቴር የካንሰር መከላከልና መቆጣጠር አማካሪ ኩኑዝ አብደላ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

እጅግ የተራቀቁና ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሹ እንደ መቅኒ የመለወጥ (Bone Marrow Transplant) ሕክምናዎች ጭምር የሚሰጡበት የካንሰር ልቀት ማዕከል ግንባታ በአዲስ አበባ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ውስጥ እየተካሄደ ሲሆን፣ የማዕከሉ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር፣ ኢትዮጵያ ይህን መሰል አገልግሎት ከሚሰጡ ጥቂት የአፍሪካ አገሮች አንዷ እንድትሆን ያደርጋታል፡፡ ሕክምናውን ለማግኘት ወደ ውጪ አገር የሚደረገውንም ጉዞ ይቀንሳል፡፡

የካንሰር ሕክምናን ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግ በመወሰድ ላይ ከሚገኙት ዕርምጃዎች መካከል የማሕፀን ጫፍ ካንሰር መከላከያና መቆጣጠሪያ ደንብ መፅደቁ፣ በ200 የመንግሥት ሆስፒታሎችና መንግሥታዊ ያልሆኑ የሕክምና ተቋሞች አማካይነት የማሕፀን ጫፍ ካንሰር መመርመሪያና ማከሚያ መሣሪያ ሥራ ላይ መዋሉ፣ የተጠቃሚዎች ቁጥር እንዲጨምር የግንዘቤ ማስጨበጥና የቅስቀሳ ሥራ መሠራቱ፣ አገልግሎቱን በመላው አገሪቱ ተደራሽ ለማድረግ የ1,500 የመመርመርያና ማከሚያ መሣሪያዎች ግዢ እየተካሄደ መሆኑ፣ በእያንዳንዱ ወረዳ አንድ ማዕከል አገልግሎቱን እንዲሰጥ ለማድረግ መታቀዱ፣ የካንሰር ሕክምና ባለሙያዎች (ኦንኮሎጂ) ትምህርት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መሰጠቱና የባለሙያዎቹ ቁጥር አሁን ካለበት 13 ወደ 30 ከፍ እንዲል እየተሠራ መሆኑ ይገኙበታል፡፡

ከአንድ ሦስተኛ በላይ ወይም እስከ 40 በመቶ የሚሆኑትን የካንሰር ሕመም አምጪ ምክንያቶች አስቀድሞ መከላከል ይቻላል፡፡ ከእነዚህም የመከላከያ መንገዶች መካከል ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓት መከተል፣ ጤናማ የአካል ክብደት መያዝ፣ በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ትምባሆ አለመጠቀምና ከጭሱ መራቅ፣ ከተቻለ ሙሉ በሙሉ አልኮል ከመጠቀም መቆጠብ ወይም የሚጠቀሙትን የአልኮል መጠጥ በእጅጉ መቀነስ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ከአልኮልና ከትምባሆ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ያለውን ልቅ አካሄድ ይታደጋል የተባለውን አዋጅም የተወካዮች ምክር ቤት ጥር 28 ቀን 2011 ዓ.ም. አፅድቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...