Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊድንበር ያላቆመው የመድኃኒቶች ዝውውር

ድንበር ያላቆመው የመድኃኒቶች ዝውውር

ቀን:

የደም ግፊት ሕመም ላለባቸው የሚታዘዝ መድኃኒት ነው፡፡ ሚኖግዚዲል የደም ቧንቧዎች እንዲለጠጡ በማድረግ ደም በሚፈለገው መጠን እንዲንቀሳቀስ የሚያደርግ መድኃኒት ነው፡፡ መድኃኒቱ የደም ቧንቧዎችን ከመለጠጥ ጎን ለጎን ባለው ሌላ ጥቅሙም ይታወቃል፡፡ ሚኖግዚዲል ራሰ በረሃነትን ለማጥፋትና ፀጉርን ለማሳደግ ይረዳል ተብሎ ይታሰባል፡፡ የዘርፉ ተመራማሪዎችም መድኃኒቱ ከፀጉር ዕድገት ጋር ያለውን ሳይንሳዊ ግንኙነት ባይረዱም ለፀጉር ዕድገት እንደሚረዳ አረጋጋጠዋል፡፡

መድኃኒቱ በሐኪም ትዕዛዝ የሚወሰድ ሲሆን፣ ከበድ ያለ የጎንዮሽ ጉዳት እንዳለው ይነገራል፡፡ የማዞር፣ ፈጣን የልብ ምት፣ ራስን መሳት፣ ደረት ላይ የሚሰማ ሕመም፣ የእግርና የእጅ እብጠት፣ ያልተለመደ የክብደት መጨመር፣ የድካም ስሜትና ለመተንፈስ መቸገር የመሳሰሉ የጎንዮሽ ጉዳቶችን በአንዳንዶች ላይ ሊያስከትል ይችላል፡፡

ነገር ግን መድኃኒቱ እንደ ማንኛውም ኮስሞቲክስ ፀጉር ለማሳደግ የሚረዳ መድኃኒት ተብሎ በማኅበራዊ ሚዲያዎች እየተዋወቀ፣ በደላሎች የማግባባት ችሎታ ቤት ለቤት እየተሸጠ ይገኛል፡፡ መድኃኒቱን በተለያዩ መንገዶች ወደ አገር ውስጥ እያስገቡ የሚቸበችቡ ግለሰቦች ተግባር ሕገወጥና የዜጎችን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን የኢትዮጵያ የምግብና የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ሐሙስ ጥር 30 ቀን 2011 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስተውቋል፡፡ መድኃኒቱ በባለሥልጣኑ ያልተመዘገበ፣ አምራች ድርጅቱ የማይታወቅ፣ አግባብነት ባለው የማጓጓዣና የማከማቻ ሥርዓት ያልተያዘና ዜጎችን ለከፍተኛ የጤና ቀውስ ይዳርጋልም ተብሏል፡፡ የሚሸጠውም ቀላል በማይባል ዋጋ በመሆኑ ጉዳቱ ድርብ ነው፡፡

እንዲህ ያሉ ሕገወጥ መድኃኒቶችን ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቡ ሕገወጦች የተለያዩ መውጫና መግቢያ ኬላዎችን ይጠቀማሉ፡፡ በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በኩል የሚገቡት በመንገደኞች ሻንጣ ተደብቀው እንደሆነም ታውቋል፡፡ ባለሥልጣኑ በአዋጅ ቁጥር 661/2002 የተሰጠው ኃላፊነት ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምግብ ነክና የጤና ግብዓቶች ላይ የጥራትና የደኅንነት ቁጥጥር በማድረግ ማኅበረሰቡ ጥራታቸውና ደኅንነታቸው ለተጓደሉ ምግብና የጤና ግብዓቶች እንዳይጋለጥ ቁጥጥር ማድረግ ነው፡፡

ይህንንም ለማድረግ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሰባት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችና መውጫና መግቢያ ኬላዎች ላይ ደግሞ 17 ቢሮዎችን ከፍቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ ከሰባቱ ቅርንጫፎች አንዱ በሆነው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ አምስት ኬላዎች በኢትዮጵያ አየር መንገድ በካርጎ ተርሚናልና በመንገደኞች ማስተናገጃ፣ በቃሊቲ፣ ሞጆና አዳማ ደረቅ ወደቦች ላይ ቢሮዎችን ከፍቶ እየሠራ ይገኛል፡፡

በሕገወጥ መንገዶች ወደ አገሪቱ ሊገቡ ሲሉ የተያዙ ሕገወጥ መድኃኒቶች፣ ኮስሞቲክሶች እንዲሁም ምግብ ነክ ምርቶች በርካታ መሆናቸውን የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሃያልሰው መለሰ ገልጸዋል፡፡ በተለይም በቦሌ ኤርፖርት በኩል በመንገደኞች ሻንጣ የሚገቡት ከጊዜ ወደ ጊዜ መጠናቸው እየጨመረ ይገኛል ብለዋል፡፡ ባለሥልጣኑ ከጉምሩክ ኮሚሽንና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በሠራቸው የቁጥጥር ሥራዎች ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ከ30 ዓይነት በላይ የሚሆኑ መድኃኒቶች በኤርፖርቱ እንዳይገቡ ማስቀረት ተችሏል፡፡

አብዛኞቹ መድኃኒቶች ስንፈተ ወሲብ ላለባቸው የሚታዘዙ፣ የካንሰርና ሚኖግዚዲልን ጨምሮ ለፀጉር ማሳደጊያነት ይውላሉ የሚባሉ መድኃኒቶች ናቸው፡፡ ከሦስቱ በተለየ መጠን በርከት ብሎ በሕገወጥ ሲገባ የሚያዘው የስንፈተ ወሲብ መድኃኒቶች ሲሆኑ፣ ቪማክስ የተባለው ብራንድ በስፋት እየገባ እንደሆነ ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ መድኃኒቱ በባለሥልጣኑ ያልተመዘገበ፣ አምራቹ የማይታወቅና ትክክለኛውን የአከመቻቸት እንዲሁም የአጓጓዝ ሥርዓት ያልተከተለ በመሆኑ በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል፡፡ ማቅለሽለሽ፣ ሆድ ቁርጠት፣ እንቅልፍ መዛባት የመሳሰሉ የጎንዮሽ ጉዳት የሚያስከትል በመሆኑም በሐኪም ትዕዛዝ ብቻ መወሰድ ይኖርበታል፡፡

የተመረቱበት አገር ዕውቅና ያልሰጣቸው፣ አምራቻቸው የማይታወቅ፣ በባለሥልጣኑ ያልተመዘገቡ፣ በዚህ አገርም ወኪል የሌላቸው ምግብና ምግብ ነክ ምርቶችም በኤርፖርቱ ሲገቡ ተይዘዋል፡፡ በአምስቱ መውጫና መግቢያ ኬላዎች ባለፉት ስድስት ወራት 686.8 ቶን የሚመዝኑ የተለያዩ ምግቦችና የምግብ ጥሬ ዕቃዎች ጥራትና ደኅንነታቸው ያልተጠበቀ ሆኖ በመገኘቱ እንዳይገቡ ተደርጓል፡፡ በጉዞ ወቅት ባጋጠመ ጉዳት የተበላሸ 686.15 ሊትር ዘይት ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባም ታግዷል፡፡ 1.18 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ መድኃኒቶች፣ የሕክምና መሣሪያዎችና ኮስሞቲክሶችም ከመስፈርት በታች በመሆናቸው እንዳይገቡ መደረጉን ያብራሩት አቶ ሀያልሰው ናቸው፡፡

ከዚህ አልፈው የሚገቡት ደግሞ እንደማንኛውም ሸቀጥ እየተቸበቸቡ ይገኛሉ፡፡ የማስተዋወቅና የማሻሻጥ ሥራውም እንደ ፌስቡክ፣ ቴሌግራም ባሉ ማኅበራዊ ድረገጾች የሚያልቅ ነው፡፡ እንዲህ ያሉት ሕገወጥ መድኃኒቶችና ምግብ ነክ ምርቶች ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት በእንስሳት እየተጫኑ ጥበቃና ቁጥጥር የማይደርስባቸው ቦታዎችን በማቆራረጥም ጭምር ነው፡፡

እንደ ጥራጥሬ በጭነት መኪኖች እያስገቡ በየከተማው በማዛወር ሲያከፋፍሉ የተገኙ በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ በቦሌ ኤርፖርት በኩል የሚገቡትን ለመያዝ የሚደረገውን ቁጥጥር አጥንተው በአንዱ ሲባሉ በሌላ እያሉ ተደባብቀው የሚያልፉ አሉ፡፡ የቁጥጥር አካላት ጥቆማ ደርሷቸው በተጠንቀቅ ሲጠብቁ በተለያዩ አየር መንገዶች አሳብረው ባልተጠበቀ በር እንደሚገቡ ተነግሯል፡፡

ያገኙትን አጋጣሚ ሳያባክኑ ጥራታቸውና ደኅንነታቸው ያልተረጋገጠ መድኃኒቶችን ከሚያስገቡ ግለሰቦች እየተረከቡ የሚሸጡ መድኃኒት መደብሮች መኖራቸውን የሚናገሩት በባለሥልጣኑ የመድኃኒት ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ እንዳለ፣ በዚህ ተግባር የሚሳተፉ ግለሰቦችና ድርጅቶች አስተዳደራዊ ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸው በሕግም እንደሚጠየቁ ተናግረዋል፡፡ በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በሕግ እየታየላቸው የሚገኙ ጥቂት የማይባሉ ግለሰቦች እንዳሉም ያስረዳሉ፡፡ በቅርቡም 2.33 ሚሊዮን ብር የሚገመት 13 ዓይነት መድኃኒቶችን ይዞ በደቡብ ክልል አለታ ጩኮ አካባቢ ሲዘዋወር የተገኘ፣ በአፋርም ክልል እንዲሁ በሕገወጥ የገቡ መድኃኒቶችን ሲያሰራጩ የተገኙ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በጦርነት የወደመውን የአክሱም አውሮፕላን ማረፊያ ለመጠገን ተቋራጮች ሊመረጡ ነው

ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰበት የባህር ዳር አውሮፕላን ማረፊያ ተርሚናል ምትክ...

ለአደጋ መከላከልና ምላሽ ለመስጠት የሚያግዝ ቴክኖሎጂ በ300 ሚሊዮን ብር ወጪ ተግባራዊ ሊደረግ ነው

በአዲስ አበባ ከተማ የድንገተኛ እሳትና አደጋን ለመከላከልና በፍጥነት ምላሽ...

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ...

ብሔራዊ ባንክ ኅብረተሰቡና ባንኮች በሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶች እንዳይጭበረበሩ አሳሰበ

ሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን በማሳተምና በማሠራጨት ግብይት ላይ ለማዋል ጥረት...