Sunday, April 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በስንቱ እንብሰልሰል?

ሰላም! ሰላም! መቼስ አንዳንዴ ዓለም ምን ፀሐይ ብትመስል ሰው ሐሳብና ቢጤ ሲያጣ ቀን ይጨልምበታል። ይሰውራችሁ ነው። እና አንድ ሰውዬ ነው አሉ። ቀን ጨለመበት። ቀን ሲጨልም እያሰባችሁ ጨለማውን እንድታልሙ ለእናንተ ልተወው። ጊዜው ደግሞ በአይጥ መርዝ ድመትን ማሰናበት የሚሉት ፋሽን ተጣብቶታል። ሰውዬው የአይጥ መርዝ ሊገዛ ሱቅ ደፍ ላይ ደረሰ። ‹‹ባለ ሱቅ የአይጥ መርዝ አለህ?›› ሲለው ባለ ሱቁ ደግሞ፣ ‹‹የአይጥ ወጥመድ ብቻ ነው ያለኝ፤›› በማለት ሲመልስለት በገዛ ፈቃዱና በገዛ ገንዘቡ ሊሰናበት የተሰናዳው ሰውዬ በሳቅ ፈረሰ። እንግዲህ እዚህ ላይ ሰንብች ያላት ነፍስ ለካ በሞላ ገበያ ብቻ ሳይሆን በጎደለም ትሰነብታለች በማለት ያሰበውን ተወው፡፡ ስለጎደሉብን ነገሮች ምሥጋና ማቅረብ የእናንተ ፈንታ ነው እንግዲህ። የገበያ ፃዲቅ የለውም ሲሉ አበው ያላንድ ምክንያት አይደለም ብሎ ማለትም ቢሆን ለእናንተው የተተወ ነው።

ብቻ እኔ ነገሩን ሳነሳው አንዳንዴ ባላሰብነው መንገድ ለበጎ የሚለወጡልንን ሁኔታዎች በማሰብ ተጠምጄ ስለሰነበትኩ ነው። ታዲያ ሲያቀብጠኝ በቀደም ለባሻዬ ልጅ  በጎደሉብን ነገሮች ምትክ የምናገኛቸውን በጎ ነገሮች ላመሳክር ባነሳበት ከአፌ ነጥቆ፣ ‹‹በል እስኪ በያዘ አፍህ የኃይል መቆራረጥን እንደ ምሳሌ አድርገህ ለበጎ የሆነበትን መንገድ አስረዳኝ፤›› ሲለኝ አፌ ተሳሰረ። ወዲያው ግን ከየት እንዳመጣሁት አላውቅም፣ ‹‹ለምሳሌ ከሥራ ወጥተህ ሊፍት ውስጥ ገብተህ፣ ከአሥራኛ ፎቅ ወርደህ፣ ጨርሰህ፣ አስፋልት ለመሻገር በምትደርስባት እንከን አልባ ደቂቃ ውስጥ፣ አንድ ፍሬን የበጠሰ መኪና ሊደፈጥጥህ ታዞልህ ይሆናል። ነገር ግን ስድስተኛ ፎቅ ላይ ስትደርስ መብራት ጠፋ። አሳንሰሩ ለጥቂት ደቂቃ ቆመ። ሰነበትክ ማለት አይደል?›› ስለው በሳቅ ተንፈራፍሮ ሲያበቃ፣ ‹‹ይህች ቃና ላይ ያየሃት ፊልም ናት፤›› ብሎኝ አረፈው። እውነትና ቃናው እየተምታታ ለምሳሌ የማይመች ጊዜ ላይ ደርሰን ቸገረን እኮ እናንተ!

በነገራችን ላይ ባለፈው ሰሞን የባሻዬ የወንድም ልጅ ጥምቀትን ከአጎታቸው ጋር ሊያሳልፉ ባሻዬ ቤት ሰንብተው ነበር። ደላላ መሆኔን ሰምተው ኖሮ፣ ‹‹እንዲያው እባክህ ጉለሌ አካባቢ አንዲት ቦታ አለችኝ። ከዚህ ኋላስ ያን ያህል አልኖርምና እባክህ ሸጠህ ገላግለኝና በልቼ ጠጥቼ ልሙት . . . ›› ብለው ችሮታ የለመኑኝ ይመስል ጉልበቴ ሥር ተደፉ። ባሻዬ ደግሞ ቱግ ብለው፣ ‹‹ምን ትላለች ይህች ልጅ? ምንስ ቢሆን የልጆችሽ ተስፋ አይደለም እንዴ? ተስፋቸውን ልታጨልሚባቸው ነው? በባህረ ጥምቀቱ ይዤሻለሁ አርፈሽ ተቀመጭ . . . ›› ብለው የሚይዙት የሚጨብጡት አጡ። እኔ በመሀል ቤት ሟሟሁ። ‹‹ኤድያ! ደግሞ ለዘንድሮ ልጅ። እነሱ እንደሆኑ ቴሌቪዥን ላይ አፍጠው ከመዋል ሌላ ኑሯቸውን ወዝ የሚያለብስ ነገር አያስቡ። አበላሁ፣ አጠጣሁ፣ አስተማርኳቸው። ለስሙ ባለዲግሪ ናቸው። ፊልም ሲያዩ ውሎ ለማደር ዲግሪ የሚሸልም አገር፡፡ እኔ በፈጣሪ ሥራ ምን ጥልቅ አደረገኝ? በደህና ጊዜ የያዝኩትን ቦታ ሸጬ ኮንዶሚኒየም እገባለሁ። በቃ . . . ›› ብለው ሴትየዋ ሲንገሸገሹ ባሻዬ ተነስተው ወጡ።

እኔም ተነስቼ ልከተላቸው ስል እጄን ለቀም አድርገው ይዘው፣ ‹‹እንዲያው አደራህን ልጄ ጡረኝ፤›› አሉኝ። ምን ልበል? በወጡትና በወረዱት መንግሥታት ፅንፍ የረገጡ ዋይታዎች ስሰማ ኖሬ ምን ልበል? ትናንት እናት ልጇን የምታበላው አጥታና የምታጠጣው አልቆባት ልጇ አንጀቱ ተጣብቆ አንገቱን ማዞር ሲያቅተው፣ በቴሌቪዥን ተቀረፀና ‹ዋይ፣ ዋይ፣ ዋይ! ሲሉ . . . › ተዘፈነ። ደግሞ ዛሬ በሌላ ፅንፍ ተምሮ፣ ተመርቆ ሥራ ፈቶ ተቀምጦ፣ ሳይርበው ሳይጠማው ሲያረጅ ዓይታ ሌላ ‹ዋይ፣ ዋይ፣ . . . › ሰው በሥራ ብቻ አይኖርም በፊልምም ጭምር እንጂ ስትሉ ሰማሁ ልበል!

ታዲያ እንደለመደብኝ እኔም ወሬ አገኘሁ ብዬ ላገኘሁት ሁሉ የባሻዬንና የወንድማቸውን ልጅ ሙግት ነዛሁት። መቼም የእኛ ሰው ሲፈጥረው ፅንፍ አያልቅበትም፡፡ ትንሽ ትልቁ በሴትዮዋ አስተያየት ቁጣ ቀናው። አንዱ ደግሞ፣ ‹‹ምን ማለታቸው ነው? ዘመናችንን ሙሉ በምግብ ዕጥረትና በሆድ ድርቀት ስንሰቃይ ኖረን፣ አሁን ደግሞ በመንፈስ ረሃብና ያለ ክፍያ ቁጠባን በሚፃረር የአኗኗር ዘይቤ መሰቃየታችንን ዓይቶ አምላክ ቃና እንደሰጠን እንዴት አይገባቸውም?›› ሲለኝ ክው ስል በባሻዬ ዕድሜ ያሉ ጎረቤቴ ደግሞ፣ ‹‹እሱ የከፈተውን ጉሮሮ ሳይዘጋው እንደማያድር እየታወቀ፣ በምርጫ ዕጦት የከፈትነውን ቴሌቪዥን አስረስቶ ሌላ ምርጫ ሲከፍትልን ሻማ ይለኮሳል እንጂ ቦታ ያሸጣል?›› ሲሉኝ ሳሰላስል ሰነበትኩ። ዘመኑ የቴክኖሎጂ፣ ከቴክኖሎጂም ምርጫ ያጥለቀለቀው የሃይቴክ ዘመን ሆነና ይኼውላችሁ ኑሮና ፖለቲካው በየት በየት እንደሚነካካ ተመልከቱ። አጃኢብ ነው። በዚህ ዓይነትማ ገና ብዙ እሰማለሁ እያልኩ ሆን ብዬ ባለፍኩ ባገደምኩበት ሳሻሽጥ፣ ሳከራይ ይኼንኑ ጉዳይ ማንሳቴን ቀጠልኩ።

በፌስቡክኛ አማርኛ ከኮሜንት ኮሜንት ይህች ከቁጠባ ተፃራሪ የሆነ አኗኗር የምትባል ነገር ተደጋግማ ጆሮዬ ደረሰች። እንዴት ነው ነገሩ ብዬ የባሻዬን ልጅ ማብራሪያ ስጠይቀው፣ ‹‹እንዴት ብሎ ነገር ምንድነው? ሰው እኮ በእህልና በውኃ ብቻ አይኖርም። መንፈሱን የሚያድስበት፣ የሚናፈስበት፣ የሚዝናናበት ሥፍራና ክንዋኔ በገፍ የሚያስፈልገው ፍጡር ነው። እነ ሮም፣ እነ አቴና፣ እነ ባቢሎን ለልዩ ልዩ ጨዋታዎችና መዝናኛዎች የከለሉዋቸውን ሥፍራዎችና የገነቧቸውን አስደናቂ ስታዲዮሞች አስታውስ። እኛ ግን ሐሳባችን ሁሉ ‹ከእጅ አይሻል ዶማ› ሆኖ ይኼው ስለቁጠባ ጥቅምና ብልኃት የሚተላለፈውን ማስታወቂያ ተከትሎ፣ ቆጥረህ የማትጨርሰው የመጠጥና የዳንኪራ መሰናዶ ማስታወቂያ ያዋክብሃል። እንዴት ማለት ምንድነው?›› ሲለኝ ነቃሁ። ንቃ ያለው አትሉም!   

እንግዲህ ከዚህ በመለስ ያለው የጎጆ ጣጣ ሆኖ ያርፋል። አንዱን በዓል ስንሸኘው ሌላው ከተፍ ሲል ትንፋሽ ሳይሰጥ ሆኗል። ቀን ምን አለበት? አወይ እንዲህ እልም እልም ሲል ቀንም ለአንድ ቀን ሰው ሆኖ ባየው ያስብላል። እውነቴን እኮ ነው። ያስለመድነው ደግሞ አይረሳም። ዜማና ኑሯችን የተቃኘው በትዝታ ቅኝት ነዋ። ታዲያስ! ማንጠግቦሽ በዓል ቢያልፍም ጠቀም ያለ ኮሚሽን ሲገኝ አዲስ ቀሚስ መልበስ ለምዳለች። እኔና ኪሴ ገቢና ወጪ መልመድና መለየት አቅቶናል። ዳሩ ላያስችል አልሰጠኝም፡፡ እኔም ለሚስቴ ሳተና ነኝ። ይብላኝ በወረት ቤቴን ቤቴን ብሎ የሰው ቤት ለምዶ ለቀረው የዘመኑ ሰው እያልኩ እፅናናለሁ። እናላችሁ ተፍ ተፍ ብዬ የሰባሰብኳትን ልበትናት ገበያ ወጣሁ። ገበያው ሲኖር ገበያተኛው፣ ገበያተኛው ሲኖር ደግሞ ገበያው ይጠፋና ደግሞ ግራ ያጋባል። ቀሚሱ ማንገቻ፣ ሱሪው ቀሚስ ሆኖ ስታዩት ደግሞ የድሮ ሰው ሱሪ ባንገት ብሎ ለችኩል መተረቻ ማግኘቱ ምን ዕድለኛ ነው ያስብላችኋል።

ከቡቲክ ቡቲክ ስሽከረከር ግማሽ ቀን ነጎደ። አቤት ሁሉም አለ እባልና ስገባ ቀሚሱ ሁሉ ትልትል፣ ከመጠን ያለፈ አጭር አሊያም ገላጣ ይሆንብኛል። ይኼንንማ ገዝቼ ሳይቸግረኝ በየኤፍኤም ጣቢያው ‹አላምን አለ ልቤን› ስጋብዝ አልውልም ብዬ ቀጥሎ ወደ አለው ቡቲክ ስገባ ከፊቱ ረጅም ቀሚስ ዓይኔ ገባ። ቀለሙ ያምራል። ሳዞረው ከባቱ ጀምሮ እስከ ወገቡ ቅድ ነው። ሻጩ በአራድኛ፣ ‹‹ይኼ ያበደ ፋሽን ነው ማንም አለበሰውም….›› ሲለኝ እየሰማሁ በሆዴ ‹እንዴት ሊለብሰው ኖሯል ወዳጄ? ሰው የብርድንም የኑሮንም ጥፊ ይችለዋል እንዴ?› ብዬ እጠይቃለሁ። ‹ዓይኔማ ወዳጄ ያላንቺ አላይ አለማ…› ዘፈን ሆኖ ቀረ!

እንሰነባበት መሰል። ምናልባት እንዲህ ልብሱም ሰውም መላ የጠፋበት ዘመን ሲሆን እስከ ወዲያኛው መሰነባበትም ያምራል። ሳይቸግረን በገዛ አፋችን ‹ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ› ስንል ኖረን ይኼው ለጥምቀትም ለንጥቀትም እንዳይሆን ሆኖ ቀሚሱ ሁሉ ተበጣጠሰ። በበኩሌ ግን እንዲህ ፋሽንና ዘመን ነገር ዓለሙን ሥጋውንም ቀሚሱንም ዘለዘለው ብዬ ውዷ ማንጠግቦሽ ሲከፋት ማየት አልወደድኩም። ስሮጥ ሽሮ ሜዳ ወጥቼ ዓይኔን ጨፍኜ እንደ ዳያስፖራ መዝርጬ የአገር ጥበብ ቀሚስ ገዛሁላት። ምናባቱንስና አትሉም። ማንጠግቦሽ ቀሚሱን ለክታው ልክክ ሲልባት አንጀቷ ረሰረሰ። የእኔ አንጀት ቅቤ ጠጣ። የሠፈር ሰው ግልብጥ ብሎ ወጥቶ እስኪደነቅ ድረስ ‹ኩሉን ማን ኳለሽ› መባል ብቻ ቀርቶባት ደምቃ ዋለች። ባሻዬ ሳላስበው በጆሮዬ፣ ‹‹አትጣ አያሳጣህ፣ ዘመን ዓለምህን ያሳምረው፤›› ብለው መረቁኝ።

ልጃቸው ጎሸም አድርጎኝ፣ ‹‹ምናለበት እንደ አንተ የአብዛኛው ሰው ትዳር እያበበ፣ እየፈካ፣ እየደመቀ የሚሄድ በሆነ  . . . ›› አለኝ። ይኼኔ ግር አለኝ። ግርታዬን ዓይቶ፣ ‹‹አይ አንበርብር ለከተማው ከአንተ እኔ አልቀርብ። ዘንድሮ የሚያውቀውን፣ የገነባውን፣ ያጨውን፣ ቤቱን ትዳሩን እየበተነ በማያውቁት አገር ቁርበት የሚያስነጥፈው ጅብ በዝቷል። የአገር መሠረቱ ቤተሰብ ሆኖ ሳለ አወቅን ባዩ ሁሉ ነገር ዓለሙን በፖሊሲ ለውጥ፣ በፖለቲካ አቋም ብቻ ካላጠራሁ ሲል ነው እኮ የሚገርምህ። ራሱ ነፃነት ሳይኖረው፣ ለቤተሰቡ፣ ለትዳሩ ነፃነት የሚነፍገው ሁሉ ደርሶ ስለነፃነት ሲቀባጥር አልታዘብኩም ነው የምትለኝ? የቤት ሠራተኛውን በሰብዓዊ ክብር ዓይቶም ይዞም የማያውቅ፣ ደርሶ ስለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሲቀባጥር አልታዘብኩም ነው የምትለኝ?›› ሲለኝ ግሮሰሪያችን ደርሰን ወሬያችን ተቋረጠ።

ስታሳጥሩት ጓዳውን ሳያፀዱ ደጁን መለቅለቅ ሆኗል ሥራችን ነው ነገሩ። ወይም በሌላ አነጋገር እየበተኑ መልቀምም ይሆናል፡፡ ሌላ ምን ይባላል? ቀዝቃዛ ቢራችንን እየተጎነጨን ወሬያችንን ስንቀጥል፣ ከፊት ለፊታችን አንድ ሲጠጣ ወፈፍ የሚያደርገው፣ ‹‹እነሱም ይላሉ ተኩሰን አንስትም፣ እኛም እንላለን ቀታ አናስከፍትም፤›› ሲል፣ ከጥግ በኩል አንዱ ነገረኛ፣ ‹‹ብለነው ብለነው የተውነውን ነገር፣ ዛሬ አዲስ አድርገው ያወሩልን ጀመር፤›› ብሎ ሲመልስለት ግሮሰሪዋ በሳቅ ተናጋች፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ወደ ጆሮዬ ቀረብ ብሎ፣ ‹‹የእኛን ሰው አየኸው በነገር ሲራቀቅ፡፡ ተራው ሰው ፖለቲካውን ሳያጠነዛ በምሳሌ ሲያዋዛው፣ ፖለቲከኛ ተብዬዎች ግን ጅማታቸው እየተገታተረ ግብግብ ይገጥማሉ . . . ›› ሲለኝ፣ በአዛውንቶች የተሞላው የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕጣ ፈንታ ሳይቸግረኝ አሳሰበኝ፡፡ በስንቱ እንጨነቅ? በስንቱ እንጠበብ? በስንቱ እንቸገር? በስንቱ እንፈር? በስንቱ እንብሰልሰል?  መልካም ሰንበት!   

 

 

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት