Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበ40/60 የቤቶች ፕሮግራም መቶ በመቶ የቆጠቡ ነዋሪዎች የከተማ አስተዳደሩን አዲስ አቋም ተቃወሙ

በ40/60 የቤቶች ፕሮግራም መቶ በመቶ የቆጠቡ ነዋሪዎች የከተማ አስተዳደሩን አዲስ አቋም ተቃወሙ

ቀን:

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር መቶ በመቶ የሚቆጥብ ካለ ቅድሚያ እንደሚያገኝ ገልጿል

በ40/60 የቤቶች ፕሮግራም በአዲስ አበባ ከተማ የሚገነቡ ቤቶችን በቅድሚያ ለማግኘት ፕሮግራሙ ይፋ በተደረገበት ወቅት በተቀመጠው መሥፈርት መሠረት መቶ በመቶ ቁጠባ ፈጽመናል ያሉ ነዋሪዎች፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር ቤቶቹን መቶ በመቶ የቆጠቡ ቅድሚያ የማግኘት መብት ሊኖራቸው አይገባም በማለት በያዘው አቋም ላይ ተቃውሞ አቀረቡ።

 በ40/60 ፕሮግራም ተጠናቀው የሚተላለፉ ቤቶችን በቅድሚያ ለማግኘት ተመዝግበው፣ ውል ፈጽመውና ቅድሚያ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያበቃውን ውል በፈጸሙበት ወቅት የተገለጸ የቤቱን ዋጋ መቶ በመቶ መቆጠባቸውን የገለጹ ነዋሪዎች፣ ባቋቋሙት የጋራ ኮሚቴ አማካይነት ተቃውሞአቸውን ለሪፖርተር አሰምተዋል።

 ለቅሬታቸው መነሻ የሆነው ጉዳይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)፣ ባለፈው ሳምንት በታተመው ሪፖርተር፣ በ40/60 የቤቶች ፕሮግራም የተገነቡ ቤቶች ለተመዝጋቢዎች የሚተላለፉት መቶ በመቶ ለቆጠቡ ቅድሚያ በመስጠት እንደሆነ የሚገልጸው መርህ ትክክለኛ አሠራር አለመሆኑን በመግለጻቸው ነው።

‹‹ቤት ፈላጊውን ያደራጀነው 40/60 ብለን ነው፡፡ ይህም ማለት 40 በመቶ የቆጠበ 60 በመቶውን በረጅም ጊዜ እንዲከፍል የመንግሥትን ድጋፍ ያገኛል በሚል ነው። በሌሎቹም የ20/80 እና 10/90 የቤቶች ልማት ፕሮግራሞችም እንደዚሁ ነው። መንግሥት በቃሉ መታመን አለበት፡፡ መቶ በመቶ ለከፈለ ቅድሚያ የምንሰጥ ከሆነማ ሄዶ ሄዶ ሀብታሞች እጅ ብቻ ነው የሚገባው፤›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡

 በዚህ የምክትል ከንቲባው አቋም ላይ ቅሬታቸውን ያቀረቡት መቶ በመቶ የቆጠቡ ነዋሪዎች በበኩላቸው፣ ‹‹በሕይወታችን ቅድሚያ ለምንሰጠው ቅድሚያ በመስጠት ቁርጠኛ ስለሆንን እንጂ እኛ ሀብታም አይደለንም፡፡ ቀርበው ሊያነጋግሩን ቢሞክሩ ይረዱን ነበር፤›› ሲሉ አንድ ነዋሪ ምክትል ከንቲባው ያራመዱትን አቋም ተቃውመዋል።

መንግሥት መቶ በመቶ የቆጠቡ ቤት ፈላጊዎችን ገንዘብ ተጠቅሞ የገነባውን ቤት ከዚያ በታች የቆጠቡትም እኩል የተጠቃሚነት መብት እንዲኖራቸው ካደረገ፣ እምነት ያጎደለው መንግሥት ነው ሲሉም ቅሬታቸውን በክርክር አቅርበዋል።

የቤቶቹን ግንባታና ማስተላለፍ ኃላፊነት ከወሰደው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የፈጸሙት ውል መቶ በመቶ የቆጠበ ቅድሚያ ተጠቃሚ እንደሚሆን መግለጹን፣ ይህንንም በመጥቀስ አስተዳደሩ ባራመደው አቋም ከቀጠለ ሕግን ከማስከበር ግዴታው ወጥቶ ሕግ ወደ መጣስ መሸጋገሩን እንደሚያመለክት ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

ይህንን የአስተዳደሩን አቋም በጭምጭምታ ከሰሙበት ጊዜ አንስቶ ቅሬታቸውን ለማቅረብ ወደ ምክትል ከንቲባው ጽሕፈት ቤት እንደሄዱና ማግኘት እንዳልቻሉ፣ በተመሳሳይም የከተማ አስተዳደሩ የቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊዎችን ማግኘት አለመቻላቸውን ገልጸዋል። ይህ በመሆኑም ቅሬታቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በጽሑፍ ማስገባታቸውን አስረድተዋል።

ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ባደረገው ተጨማሪ ማጣራት የከተማ አስተዳደሩ ቤቶቹ በእኩል ተጠቃሚነት መርህ ሊተላለፉ ይገባል የሚል አቋም ቢይዝም አቋሙን ወደ ውሳኔ አለመቀየሩን፣ ይህንን አቋሙን በተናጠል ተግባራዊ ለማድረግ እንደማይችል፣ አቋሙን ተግባራዊ ለማድረግ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ማለትም ንግድ ባንክና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር መስማማት አለባቸው።

 ረቡዕ ጥር 29 ቀን 2011 ዓ.ም. የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሩ አቶ ዣንጥራር ዓባይ፣ በ40/60 የቤቶች ፕሮግራም ቅድሚያ ተጠቃሚ ለመሆን የተመዘገቡ ነዋሪዎች ቅሬታን በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠይቀዋል።

 በሰጡት አስተያየትም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤቶቹ መተላለፍ ያለባቸው 40 በመቶና ከዚያ በላይ ለቆጠቡ በሙሉ እኩል በሚሳተፉበት የዕጣ ሥነ ሥርዓት ሊሆን እንደሚገባ አቋም ቢያራምድም፣ በዚህ ፕሮግራም የተገነቡ ቤቶች የሚተላለፋበትን መመርያ የማሻሻል ኃላፊነት የሚኒስቴሩ እንደሆነና መመርያውን ለማሻሻል በቂ ምክንያት አለመኖሩን አስረድተዋል።

 በመሆኑም በዚህ ፕሮግራም በቅርብ ወራት የሚተላለፉ 17 ሺሕ ቤቶች በተገባው ውል መሠረት እንደሚተላለፉ ገልጸዋል። ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ መቶ በመቶ የቤቱን ዋጋ የቆጠበ ተመዝጋቢ አለ ማለት እንደማይቻል፣ የዚህ ምክንያቱም የቤቶቹ ዋጋ በግሽበትና ግንባታው በመጓተቱ ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ እንደሆነ ተናግረዋል።

 በዚህ ፕሮግራም ተመዝግበው ከንግድ ባንክ ጋር ውል የፈጸሙ ነዋሪዎች የገቡትን ውል መመልከት ከቻሉ፣ የቤቶቹ ዋጋ ማለት በሚተላለፉበት ወቅት የሚወጣው የመጨረሻ ዋጋ መሆኑን ተቀብለው ውል መፈጸማቸውን መረዳት እንደሚችሉ ገልጸዋል።

 በምዝገባ ወቅት የነበረው ባለ ሦስት መኝታ ቤት ዋጋ ተብሎ የተገለጸው 386 ሺሕ እንደነበር፣ ነገር ግን ከዓመታት በፊት ተጠናቀው ከተላለፉ ቤቶች መካከል ባለ ሦስት መኝታ ቤት የተላለፈው በ491 ሺሕ ብር መሆኑን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡ መቶ በመቶ መቆጠባቸውን ከሚገልጹ ተመዝጋቢዎች መካከል በዚህ መጠን የቆጠበ አለመኖሩን፣ ቢቆጥቡ እንኳን በቀጣይ የሚተላለፉት ቤቶች ዋጋ የሚከለስ በመሆኑ መቶ በመቶ ቆጥበዋል ማለት እንደማይቻል አስታውቀዋል፡፡

 ቅሬታ አቅራቢዎቹ ግን ቤቶቹ የተላለፉበት ዋጋ ቢከለስም ቅድሚያ ተጠቃሚ ለመሆን የተቀመጠው የመቶ በመቶ ቁጠባ መጠን በምዝገባ ወቅት ይፋ የተደረገው ዋጋ በመሆኑ፣ አሁንም በዚህ መሠረት መከናወን እንዳለበት ይከራከራሉ።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...