Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየምርጫ ቦርድን ከመንግሥት ተፅዕኖ የሚያላቅቅና ገለልተኝነቱን ያስጠብቃል የተባለ ረቂቅ ሕግ ቀረበ

የምርጫ ቦርድን ከመንግሥት ተፅዕኖ የሚያላቅቅና ገለልተኝነቱን ያስጠብቃል የተባለ ረቂቅ ሕግ ቀረበ

ቀን:

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለልተኛና ከመንግሥት ተፅዕኖ ተላቆ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ሆኖ በድጋሚ እንዲቋቋም ያስችላል የተባለ ረቂቅ ሕግ፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ።

ምክር ቤቱ ጥር 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው ልዩ ስብሰባ ረቂቅ ሕጉን የተመለከተ ሲሆን፣ በዝርዝር እንዲታይም ለሕግ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል።

ረቂቅ ሕጉ በቀረበበት ወቅት በማብራሪያ አስተያየታቸውን የሰጡት በምክር ቤቱ የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ መስፍን ቸርነት (አምባሳደር) ረቂቁ ምርጫ የሚያስፈጽመው ቦርድ ጠንካራ፣ ገለልተኛና ከአድልኦ ነፃ ሆኖ እንዲሠራና የቦርዱ አባላት ሙሉ ሥራቸውን በንቃትና በተቀናጀ መንገድ እንዲሠሩ የሚያስችላቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ምርጫ ቦርድን በድጋሚ ለማቋቋም የተፈለገበትንና አጠቃላይ የሕጉን መንፈስ የሚያብራራበት የረቂቅ ሕጉ መግቢያም ይኼንኑ ይገልጻል።

 ‹‹ዜጎች በየደረጃው በሚካሄድ ነፃ፣ ፍትሐዊና ሰላማዊ ምርጫ በመረጧቸው ተወካዮች አማካይነት ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ሥልጣናቸውን በተግባር እንዲያውሉ ለማድረግ ነፃ የምርጫ አስፈጻሚ አካል አስፈላጊ በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ለማጠናከር ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ከማንኛውም አካል ነፃ አድርጎ በማደራጀት ፍትሐዊ፣ ተዓማኒና ሰላማዊ ምርጫ ለማስፈጸም የሚያስችለው መዋቅር እንዲኖረው ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ›› ረቂቅ አዋጁ መሰናዳቱን ይገልጻል።

በማከልም የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አባላትን አመላመልና አሿሿም አሳታፊና ግልጽ በማድረግና የቦርዱን የመዋቅር፣ የሠራተኛ ቅጥርና ምደባ፣ እንዲሁም የበጀት ነፃነት በማረጋገጥ በተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶችና በመራጩ ዘንድ ያለውን ተዓማኒነትና ምርጫ የማስፈጸም አቅሙን ማሳደግ ሌላው ረቂቅ ሕጉን አስፈላጊ የሚያደርገው ጉዳይ እንደሆነ በመግቢያው ላይ ተገልጿል።

 በረቂቅ ሕጉ መሠረት ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ከመንግሥትም ሆነ ከማንኛውም ሌላ አካል ተፅዕኖ ነፃ የሆነና ራሱን የቻለ፣ ተጠሪነቱም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሆናል፡፡ በሥራ ላይ ባለው አዋጅ መሠረት ዘጠኝ የነበሩትን የቦርዱ አመራር አባላት ቁጥር ወደ አምስት ዝቅ ያደረገ ሲሆን፣ ከእነዚሁ ውስጥ ሦስቱ የሙሉ ጊዜ ሠራተኛ እንደሚሆኑም በረቂቁ ተመልክቷል።

ላለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት በላይ ቅሬታ ሲቀርብበት የቆየው የቦርድ አባላቱ አመራረጥ ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል። በሥራ ላይ ባለው አዋጅ መሠረት የቦርድ አባላቱ አመላመል ግልጽነት የጎደለውና ዕጩዎቹ በቀጥታ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሾሙ የሚደረግ በመሆኑ፣ ሥልጣን የመሠረተ የፖለቲካ ድርጅት በመንግሥትነት ሥልጣኑ የቦርድ አባላትን እንደ ምርጫው በመመልመል ሥልጣኑን ሲያስቀጥልበት እንደቆየ በተደጋጋሚ ይተቻል።

የቀረበው ረቂቅ ሕግ ይኼንን ቅሬታ ከግምት በማስገባት ለቦርድ አባላት አመላመል ልዩ ትኩረት ያደረገ ይመስላል።

በረቂቅ ሕጉ መሠረት የቦርድ አባላት እንዲሆኑ የሚታጩ ግለሰቦች የሚመለመሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚያቋቁሙት ገለልተኛ ኮሚቴ ይሆናል። የዚህ ኮሚቴ አሰያየም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ እንዳይሆንም፣ የኮሚቴ አባላትን ውክልና የተመለከተ ድንጋጌ አስቀምጧል።

በዚህም መሠረት ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ፣ ከኢትዮጵያ የሳይንስ አካዴሚ፣ ከኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌደሬሽን፣ ከኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከእያንዳንዳቸው አንድ አንድ ሰው እንዲወከል እንዲሁም ከሲቪል ማኅበራትና ከአገር ሽማግሌዎች የሚመረጡ ሦስት ሰዎች እንደሚኖሩት ተገልጿል።

ከተዘረዘሩት ተቋማት የሚወከሉት ወይም የሚመረጡት የኮሚቴ አባላት ገለልተኛነታቸውና ብቃታቸው የተረጋገጠ፣ የማንኛውም ፖለቲካ ድርጅት አባል ያልሆኑ፣ መልካም ሥነ ምግባርና ሰብዕና ያላቸው፣ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለመሸከም የሚያስችል ከፍተኛ የአመራር ብቃት ያላቸው ሊሆኑ እንደሚገባ ይደነግጋል።

ይህ ኮሚቴ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አባላት ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ ያመነባቸውን በውድድር ላይ በመመሥረት እንደሚመለምል ተደንግጓል።

 ከምልመላ መሥፈርቶቹ መካከል ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያላቸው፣ የማንኛውም ፖለቲካ ድርጅት አባል ያልሆኑ፣ ከምርጫ ጉዳዮች ጋር ተያያዥነት ባላቸው በተለይም በሕግ፣ በፖለቲካል ሳይንስ፣ በሕዝብ አስተዳደር፣ በስታትስቲክስ፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና በሌሎች ተዛማጅነት ባላቸው ዘርፎች ከፍተኛ ሙያዊ ብቃት ያላቸው መሆኑን በማረጋገጥ፣ እንዲሁም መልካም ሥነ ምግባርና ሰብዕና ያላቸው፣ ኃላፊነት ለመሸከም የሚያስችል ከፍተኛ የአመራር ብቃት፣ ብሔርና ፆታዊ ተዋጽኦን ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሚመለምል ይደነግጋል።

በዚህ መሠረት ከተመለመሉት ውስጥ በማወዳደር ለሹመት ከሚያስፈልገው ቁጥር እጥፍ የሚሆኑትን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚያቀርብ፣ ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ ግን ኮሚቴው የመለመላቸውን የመጨረሻ ግለሰቦች ፈቃደኝነት ጠይቆ ማረጋገጥ እንዳለበት ረቂቁ ያመለክታል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዕጩ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ስም ዝርዝርን ከኮሚቴው ከተቀበለ በኋላ ዕጩዎች በመሥፈርቱ መሠረት የተመለመሉ መሆናቸውን በተመለከተ፣ እንዲሁም በአጠቃላይ ዕጩዎቹን በተመለከተ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች ጋር ምክክር በማድረግ ተቀባይነት ከሚያገኙት አምስት ሰዎች መካከል፣ እንዳላስፈጊነቱ የቦርዱ ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ የሚሆኑትን፣ እንዲሁም የሥራ አመራር ቦርድ አባል ሊሆኑ የሚችሉትን በመለየት ዕጩዎችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሾሙ እንደሚያቀርብ በረቂቁ ተደንግጓል።

የቦርድ አባል ሆኖ የተሾመ ሰው ቢበዛ ሊያገለግል የሚችለው ለሁለት የምርጫ ዘመን እንደሆነ፣ ከዚህ ኃላፊነት በፈቃዱ ከለቀቀ ወይም ጊዜውን ጨርሶ ከተሰናበተ በኋላ ባሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በማንኛውም ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነት ሊሾም እንደማይችልም ይደነግጋል።

ሌላው ከፍተኛ ማሻሻያ የተደረገበት ጉዳይ የቦርድ አባል የሹመት ጊዜውን ሳይጨርስ ሊነሳ የሚችልበት ሁኔታ፣ በፖለቲካና በመንግሥት ተፅዕኖ ምክንያት እንዳይሆን ከፍተኛ ጥበቃ ያደርጋል።

በመሆኑም አንድ የቦርድ አባል በራሱ ፍላጎት የሹመት ዘመኑን ሳይጨርስ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሊነሳ የሚችለው፣ በሕመም ምክንያት ተግባሩን በተገቢው ሁኔታ ማከናወን ባለመቻል፣ ግልጽ በሆነ የሥራ ችሎታ ወይም ብቃት ማነስና ከባድ የሥነ ምግባር ጉድለት መኖር ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ የቦርድ አባሉ የተሰጠውን ኃላፊነት በገለልተኝነት፣ በነፃነትና በቅን ልቦና እያከናወነ አለመሆኑን፣ በምርጫ የሚሳተፍ የፖለቲካ ድርጅትን ወይም የግል ዕጩን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ደግፏል፣ በሥራ አመራር ቦርድ አባልነቱ ምክንያት ባገኘው ሚስጥራዊ መረጃ ጥቅም አግኝቷል፣ ወይም ለማግኘት ሞክሯል የሚል ክስ ማንኛውም ባለድርሻ አካል በመረጃ ተንተርሶ ለፌዴራል ዳኞች አስተዳደር ማቅረብ እንደሚችል በረቂቁ ተካቷል።

የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ ቅሬታው እንደሚያስቀርብ ካመነበት ጉዳዩን የጠቅላይ ፍርድ ቤት አንድ ዳኛ፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነርና ቅሬታ የቀረበበት የቦርድ አባል በተገኘበት ተመርምሮ ውሳኔ እንደሚሰጥ ተደንግጓል።

ረቂቅ ሕጉ ለዝርዝር ዕይታ ለቋሚ ኮሚቴ የተመራ ሲሆን፣ ፓርላማው ከየካቲት ወር እረፍት ሲመለስ እንደሚያፀድቀው ይጠበቃል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...