Sunday, June 16, 2024

በአገር ጉዳይ ዝምታው ይብቃ!

ኢትዮጵያ በታሪክ ከፍ ያለ ሥፍራ የሚሰጠው ወሳኝ ምዕራፍ ውስጥ ብትገኝም፣ አሁንም መፃኢ ዕድሏን የሚያጨልሙና የሕዝቧን ተስፋ የሚያጨፈግጉ ድርጊቶች ቀጥለዋል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ለበርካቶች ሞት፣ ለአካል ጉዳትና ለመፈናቀል ምክንያት የሆኑ ግጭቶች አንዳንዴ ጠንከር፣ ሌላ ጊዜ ረገብ እያሉ በማገርሸት የሕዝብን ተስፋ እያጨለሙ ነው፡፡ ሰሞኑን በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር ዞን ምሥራቅ ደንቢያ ወረዳ ውስጥ በአማራና ቅማንት ተወላጆች መካከል የተከሰተ ግጭት ለበርካቶች ጉዳትና መፈናቀል ምክንያት መሆኑ ተሰምቷል፡፡ በመኖሪያ ቤቶችና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱም እንዲሁ፡፡ ችግሮችን በሰከነ መንገድ የመፍታት አቅምና ችሎታ ሳይጠፋ፣ ፍላጎት ባለመኖሩ ምክንያት ብቻ በሕዝብ ላይ ይህ ሁሉ መከራና ሥቃይ ሲዘንብ ያሳዝናል፡፡ በዚህ መሀል ዓላማቸውን ማስፈጸም የሚፈልጉ ኃይሎች ዕድሉን ተጠቅመው፣ ሰላምና መረጋጋት ሲያደፈርሱ ያበሳጫል፡፡ በግጭቱ ምክንያት ሰለባ የሚሆኑ ወገኖች የፖለቲካ ሒሳብ ማወራረጃ መሆናቸው ያስቆጫል፡፡ የጋራ የሆነ አማካይ በመፍጠር መነጋገር ሲቻል፣ በልዩነት ውስጥ ሆኖ ቅራኔን ማጦዝ ትርፉ ዕልቂትና ውድመት ነው፡፡  አነስተኛ ቅራኔዎችን የማይፈቱ አድርጎ በመተብተብ ሕዝብን እርስ በርሱ ማባላት በሕግም ሆነ በህሊናም የሚያስጠይቅ ወንጀል መሆኑ ተረስቶ፣ የሕዝብና የአገር ተስፋ እንደ ጉም አልጨበጥ ሲል ዝምታ መምረጥ ተገቢ አይደለም፡፡

ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን የምትሆን በነፃነት፣ በፍትሕና በእኩልነት ላይ የተመሠረተች ዴሞክራሲያዊት አገር ለመገንባት ትኩረት ማድረግ ካልተቻለ የወደፊቱ ጊዜ ያስፈራል፡፡ ትልቅና ታሪካዊ አገር ውስጥ እየኖሩ ትንሽ ካልሆንን ብሎ ማነስ የጤና አይደለም፡፡ ለሁሉም የሚበቃ የአገር ፀጋን በስግብግብነት በመናጠቅ፣ አንፃራዊውን ሰላም እያደፈረሱ እርስ በርስ ለመበላላት ማሰብ አደገኛ ደዌ ነው፡፡ ‹‹የእኛ›› ከማለት ይልቅ ‹‹የእኔ›› ብቻ እያሉ ልዩነትን ማራገብ ለዘመኑ አስተሳሰብ የማይመጥን ነው፡፡ የነገውን ብሩህ ተስፋ በማሰብ ከድቅድቅ ጨለማ ውስጥ መውጣት እየተቻለ፣ በስህተት መንገድ ላይ ደጋግሞ መመላለስ ሕዝብና አገርን ለኪሳራ ይዳርጋል፡፡ በርካታ የተጠራቀሙ ችግሮች ባሉበት አገር ውስጥ ለመፍትሔ የሚረዱ ሐሳቦች ከማዋጣት ይልቅ፣ በችግሮች ላይ ተጨማሪ ችግሮች መቀፍቀፍ ለማንም አይጠቅምም፡፡ በአርበኝነት፣ በታጋይነት፣ በነፃ አውጪነት፣ በዴሞክራትነትና በሰብዓዊነት ጭምብል እልህና ቂም ውስጥ የተዘፈቁ ወገኖች፣ አገርን የጦርነት አውድማ እያደረጉ ዝም ማለት የማይወጡበት አረንቋ ውስጥ ይከታል፡፡

ለውይይት፣ ለድርድርና ለስምምነት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ኃላፊነታቸውን መወጣት የሚገባቸው የሃይማኖት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ምሁራንና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች ባሉባት አገር ውስጥ የጥራዝ ነጠቆች ድምፅ በመጉላቱ ምክንያት ብቻ የአገር ተስፋ ዳዋ እየለበሰ ነው፡፡ ትናንት ከመጠን ያለፈ ሰቆቃና መከራ በታየባት አገር ውስጥ ዛሬ ያለፉትን ችግሮች ላለመድገም ጠንክሮ መሥራት ሲገባ አንዴ የማንነት፣ ሌላ ጊዜ የግዛት ይገባኛል፣ ከዚህም ታልፎ የከተማ ባለቤትነት ጥያቄ ትንቅንቅ እያባከነ ያለው ጊዜ፣ ጉልበትና ሐሳብ ያስቆጫል፡፡ እርግጥ ነው ጥያቄዎች መነሳታቸው እንደ ችግር ሊታይ አይገባም፡፡ ነገር ግን ጥያቄዎቹ የሚነሱበትና የሚስተናገዱበት አግባብ ግን የችግሮች ምንጭ እየሆነ ነው፡፡ ጥያቄዎች ሲነሱም ቅደም ተከተል ያስፈልጋቸዋል፡፡ እጅግ በጣም በርካታ አንገብጋቢ ችግሮች ባሉባት አገር ውስጥ ለየትኞቹ ጥያቄዎች ቅድሚያ መስጠት ይገባል? የትኞቹስ በሒደት መቅረብ አለባቸው? የአገሪቱ አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት በሁለት እግሩ መቆም ባልቻለበት በዚህ አሳሳቢ ጊዜ፣ ለብጥብጥና ለግጭት የሚዳርጉ አጀንዳዎችን መቆስቆስ ምን የሚሉት ዕውቀት ነው? ሌላው ቀርቶ አሉ የሚባሉ ልዩነቶች ላይ እኮ ለመነጋገር ጨዋነት ያስፈልጋል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ ሲፈለግ የግድ የሆነው ዲሲፕሊን ለምን ይረሳል? ኧረ ተው የሚል መካሪ እንዴት ይጠፋል? ያስተዛዝባል፡፡

በዚህ ታሪካዊ የሽግግር ወቅት በአንድ በኩል ሆደ ሰፊ በመሆን በሰከነ መንገድ ኃላፊነትን ለመወጣት ፍላጎት ያላቸውን ያህል፣ አንድ ችግር ሲያጋጥም በእሳት ላይ ቤንዚን ለመርጨት የሚሯሯጡ ሞልተዋል፡፡ በተለያዩ መንገዶች ለመታዘብ እንደተቻለው አንድ የጋራ የሆነ ጉዳይ ሲያጋጥም የሚስተናገድበት መንፈስ በፍፁም ዴሞክራሲያዊ አይደለም፡፡ በተለይ ተደማጭነት አለን በሚሉ አክቲቪስቶች መሀል የሚታየው ፉክክር ጤነኛ አይደለም፡፡ የሆነ ወገን አንድ ጉዳይ ሲያነሳ ደርዝ ያለው አቀራረብ ሊኖረው ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ጉዳዩ ያገባኛል በሚለው ወገን ደግሞ በሥርዓት ለመነጋገር ራሱን ማዘጋጀት ይኖርበታል፡፡ ከዚህ ወጪ በተለመደው ‹‹ውረድ እንውረድ…›› ዓይነት ፉከራና ቀረርቶ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት ላለንበት ዘመን አስተሳሰብ አይመጥንም፡፡ የዘመናት ቁርሾ እያስታወሱ በቀጥታና በተዘዋዋሪ መፋጠጥ ከንቱነት ነው፡፡ ለሰጥቶ መቀበል መርህ የማይገዛ አጉል ፉክክር በምንም መመዘኛ ዴሞክራሲያዊ ሊሆን አይችልም፡፡ ለዘመናት ክፉና ደጉን እያሳለፈ አብሮ ለኖረው የተከበረና አስተዋይ ሕዝብ አለማሰብ ከክፋቶች የላቀ ክፋት ነው፡፡ እልህ፣ ቂም፣ ጥላቻና ሴረኝነት ኢትዮጵያንና ሕዝቧን መቀመቅ ከመክተት የዘለለ ምንም ሚና የላቸውም፡፡ የማያዋጣ ነገርን ደጋግሞ መሞከር ደግሞ ፋይዳ ቢስ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ፋይዳ ቢሶች አገር ሲያምሱ እንዴት ዝም ይባላል?

በተለያዩ አካባቢዎች ለግጭት መቀስቀስ ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች በቅርበት ሲታዩ፣ ለሕዝብ ምንም ጥቅም የሌላቸው ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው እብሪት ውጤት ናቸው፡፡ እነሱ ችግሮቻቸውን በሰላማዊና በሠለጠነ መንገድ መፍታት ሲያቅታቸው ወይም ጥቅሞቻቸውን ሲያሳድዱ፣ የቆሰቆሱት እሳት ዳፋው ለንፁኃን ይተርፋል፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ ልዩነትን በማስፋትና ግጭቱን የበለጠ በማራገብ፣ የራሳቸውን ሥልጣንና ጥቅም ለማደላደል የሚሯሯጡ ወገኖች ዓላማቸውን ያሳካሉ፡፡ ከግጭቶች ጀርባ በንፁኃን ደም የሚነግዱ ኃይሎች አጋጣሚዎችን ከመጠቀም ወደኋላ እንደማይሉ ይታወቃል፡፡ ለሕዝብ ነፃነትና እኩልነት ቆመናል የሚሉ ኃይሎች አገር በሴረኞችና በራስ ወዳዶች እብሪት ስትታመስ ለምን ቆመው ያያሉ? ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለማካሄድ ተመሥርተናል የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለምን ዝም ይላሉ? የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ዜጎች ፖለቲከኞችና አጫፋሪዎቻቸው፣ በማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት የግጭቱን አድማስ እያሰፉ ጥፋት ሲደግሱ እስከ መቼ ዝም እያሉ ይጎዳሉ? አገርና ሕዝብ በሥርዓተ አልበኝነት ምክንያት የከፋ አደጋ ውስጥ ከመግባታቸው በፊት በቃ ይባል! በአገር ጉዳይ ዝምታው ይብቃ መባል አለበት!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...

የዘመኑ ትውልድ ለአገሩ ያለውን ፋይዳ ይመርምር!

በዚህ በሠለጠነ ዘመን ኢትዮጵያን የሚያስፈልጓት ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከብዙዎቹ በጣም ጥቂቱን አንስተን ብንነጋገርባቸው ይጠቅሙ ይሆናል እንጂ አይጎዱም፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ብዙኃኑ ሕዝቧ ያስፈልጓቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ...