Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ቤት ሆይ ወዴት አለህ?

የመኖርያ ቤት ችግር የጥያቄ ምንጭ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከመሠረታዊ የሰው ልጅ ፍላጎቶች የሚመደበው የመጠለያ ችግር በተለይ ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች የዘመናት ፈተና ነው፡፡ የብዙዎች ተስፋ የነበረው የጋራ መኖርያ ቤቶች ፕሮጀክት ስንክሳሩ በዝቶበት ባለበት ሲረግጥ በመቆየቱ፣ በየጊዜው እየተከማቸ ከመጣው የመኖርያ ቤት ፍላጎት ጋር በሚጣጣም አቅርቦት ልክ ግንባታው ባለመካሄዱ ችግሩ እንዲደራረበ አድርጓል ማለት ይቻላል፡፡

ፕሮጀክቱ በአግባቡ ሊመራና ሊተገበር ባለመቻሉ፣ ከተመዘገቡ ከ12 ዓመታት በላይ ሲጠባበቁ ለቆዩ ቤት ፈላጊዎች ማስረከብ አለመቻሉ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ይህ ሳያንስ በሁለት ዓመት ውስጥ ለተመዝጋቢዎች ይተላለፋሉ የተባሉት የ40/60 ቤቶችም   የችግሩ ሰለባ ሆነዋል፡፡ የ40/60 የቤቶች ፕሮጀክት በተለየ የሚታይበት አንዱ ምክንያት ጥቂት የማይባሉ ቤት ፈላጊዎች በወቅቱ የተተመነውን ሙሉ ክፍያ ቀድመው ከከፈሉ ቤቱን ቀድመው የሚያገኙበት ዕድል አለ በመባላቸው ሙሉ ክፍያውን ያጠናቀቁ በርካቶች መኖራቸው ነው፡፡ ይህ ከሆነ ስድስት ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ ዛሬም ግን የ40/60 ቤቶችን ለማግኘት ሙሉ በሙሉ የከፈሉም ሆኑ እስከ 40 በመቶና ከዚያም በላይ የተቻላቸውን ቆጥበው ከሚጠባበቁ ተመዝጋቢዎች አብዛኛዎቹ ቤት አላገኙም፡፡ እንዲህ ያለው የመንግሥት እንዝላልነት ዜጎች በገዛ አገራቸው ያውም የሚጠበቅባቸውን ተወጥው በምላሹ የሚገባቸውን ማግኘት አለመቻላቸው፣ ለበርካቶች ተስፋ መቁረጥና ዕምነት ማጣት ሰበብ ሆኗል፡፡ ብዙ የተባለለትና ተስፋ የተደረገበት የጋራ መኖርያ ቤቶች ፕሮጀክቶች ከእስከዛሬው ባሻገር ነገስ እንዴት ይጓዝ ይሆን የሚለውም ያሳስባል፡፡ ዛሬ በአዲስ አበባም ሆነ በሌሎች ከተሞች አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል፣ በአቅሙና በገቢው መጠን የመኖርያ ቤት ባለቤት የሚያደረገው አማራጭ ማጣቱ ከመሠረታዊ ፍልጎት ውጭ እንደሆንና እንዲራቆት አስገድዶታል ፡፡

አብዛኛው ሕዝብ እንዳሻው ቤት ቀልሶ ለመኖር የሚያስችለው አቅም የለውም፡፡  ቤት ለማግኘት የሚፍጨረጨረውን ዜጋ በጋራ መኖርያ ቤቶች ፕሮጀክት ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ በታሰበውና በተጀመረው መንገድ አለመጓዙ ለብዙዎች እጅግ አሳዛኝ ነው፡፡ ይህንን የሚቀይር የመፍትሔ ዕርምጃ ሊወሰድ ይገባል፡፡

ዜጎች አቅማቸውን ባገናዘበ መልኩ የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ማድረግ ከባድ ነው፡፡ ሆኖም ሊሳካ የሚችልበትን መንገድ ማፈላለግ ተገቢ ነው፡፡ የመንግሥትም መንግሥትነት ለዜጎቹ ፍላጎት መሟላት መውተርተሩ ነውና በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ያለውን የጋራ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ በአግባቡ ማስተዳደር ቢቻል እንኳ ችግሩን በጥቂቱም ቢሆን ማቃለል ይቻላል፡፡ ሪል ስቴቶች ከሚገነቡት ቤት በተወሰነ ደረጃ የጋራ መኖርያ ቤቶች እንደገቡ የሚያስገድደውም መመርያ ቢሆን በትክክል ቢተገበር ለመፍትሔ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡

ለማንኛውም መንግሥት የሚያስገነባው የጋራ ቤቶች ነውና ዋናው ጥያቄ እሱው ላይ እናተኩር፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር ወደ 15 ዓመታት የተጠጋ ዕድሜ ያለው የጋራ መኖርያ ቤት ፕሮጀክት፣ ከመነሻው ጀምሮ በርካታ ችግሮች ነበሩበት፡፡ በጥቂቱ የተገነባውን ቤት በማስተላለፉ ሥራ ላይ የነበሩ ሸፍጦችም ይህ ፕሮጀክት የታሰበለትን ግብ እንዳይመታ አድርገዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ፕሮጀክቶች የዜጎችን መሠረታዊ ፍላጎት ከማሟላት ይልቅ ፖለቲካዊ ገጽታ እንዲላበሱ መደረጋቸውም ችግር ነበር፡፡ ቤቶቹ እንደሚገነቡ የተገለጹት በ1997 ዓ.ም. በምርጫ ወቅት መሆኑም ቀድሞውኑ ለፖለቲካ ፍጆታ እንጂ በሚገባ ታስቦበት ያልተጀመረ ግማሽ ሥራ አድርጎታል፡፡ ጥቂት ቤቶች ተገንብተውም ዕጣ የሚያውጣው ኮምፒውተር ዓባይ ወይም ቀጣፊ እንዲሆን አስቀድሞ በተሞላ ሲስተም ሰዉን ሁሉ እንዳሞኘው የሚደመጡ የመንገድ ዳር ሹክሹክታዎችም የቤት ልማት ሥራውን ትብታቦች አሳብቀዋል፡፡ እንዲህም ሆኖ፣ ከ100 ሺሕ በላይ ዜጎች የቤት ባለቤት ሆነዋል ቢባልም ቅሉ በዕቅዱ መሠረት በአግባቡ ቢሠራ ኖሮ በ15 ዓመታት ውስጥ የተላለፉት ቤቶች ቁጥር በአንድ ወይም በሁለት ዓመት ውስጥ እየተጠናቀቁ የአብዛኛውን ሕዝብ ፍላጎት ለማሟላት ባስቻሉ ነበር፡፡ ስለዚህ እየተንጠባጠበም ቢሆን ሲተላለፍ የቆየው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ጉዳይ ከሚገባው በላይ የተጋነነ ዋጋ ተከፍሎባቸውም፣ በአግባቡ የግንባታ ሒደታቸው ክትትል ይደረግበት ቅሸባ በበዛበት አሠራር፣ በቀሽም የጥራት ደረጃዎች ተገንብተው ቢቀርቡም የዜጎችን  መሠረታዊ ፍላጎት ግን ብሶበት ይታያል፡፡ የአሠራር ዝርክርክነቱ በጊዜ ብቻ መጓተት ሳይወሰን፣ ወጪ በማናርም አስመርሯል፡፡ ስንት ፕሮጀክት የሚያስገነባ ገንዘብ ተበልቶበታል፡፡ የአገርና የሕዝብ ገንዘብ እንዲባክን አድርጓል፡፡ ተገልጋዮችም ያልተገባ ወጪ እንዲያወጡ አስገድዷቸዋል፡፡

ዜጎችን የቤት ባለቤት ለማድረግ እንዲህ ያለው የጋራ መኖርያ ቤቶች ፕሮጀክቶች ይቀጥሉ አይቀጥሉ የሚለው ጉዳይ እንዳለ ሆኖ፣ ካለው ችግር አንፃር ነባሩን ፕሮጀክት ውጤታማ በሚያደርግ አሠራር ቃኝቶ ማስቀጠሉ ግድ ነው፡፡ ቢያንስ የሕንፃዎቹን ወለል ጨምሮ ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ መገንባቱ ላይ ጠንክሮ ካልተሠራና በጥብቅ የግንባታ አስተዳደር ካልተመራ የመኖርያ ቤት ችግር እየባሰበት  ይቀጥላል፡፡

የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክቶቹ ሌላው ችግር ቤቶቹን በተገቢው ጊዜ ማስረከብ ካለመቻል በላይ፣ በሕግ አግባብ ተጠያቂነት የሰፈነበት አሠራር ኖሮት አለመተግበሩ ነው፡ በሁለት ዓመት አልቆ ትረከባላችሁ የተባሉ ዜጎች ከአሥር ዓመታት በላይ እየጠበቁ ነው፡፡ እንዲህ ባለ ዋጋ ትረከባላችሁ ተብለው ሳለ፣ ዕጣው ሲወጣላቸው ግን ክፈሉ የሚባሉት ዋጋ በብዙ እጥፍ ጨምሮ ስለሚመጣ ለብዙዎች ሰቀቀንና ሕመም ነው፡፡

በእጅጉ መታሰብ ያለበት መንግሥት ቤቶቹን ሲገነባና ዋጋ ሲያወጣ የማጠናቀቂያ ጊዜውንም አስልቶ ነው፡፡ ገቢና ወጪውንም አስቦ ነው፡፡ በሌላ በኩል እንዲህ ያሉ የግንባታ ሥራዎች በተራዘሙ ቁጥር ዋጋ ማስጨመራቸው አይቀርም፡፡ ግንባታውን በተገቢው መንገድ ተከታትሎና በተባለው ጊዜ ውስጥ ቢያጠናቅቅ ኖሮ፣ ዛሬ ላይ የግንባታ ዋጋ ጨመረብኝ በማለት የቀደመውን ውል በአዲስ ዋጋ ቀይሮ ከቤት ተዝጋቢዎች ጋር ውዝግብ ውስጥ ባልገባ ነበር፡፡

የፕሮጀክቱ ባለቤት የክትትልና የውል አስተዳደር ደካማ መሆን ለግንባታው ከተቀመጠው ጊዜ በላይ ሲዘገይ ዕርምጃ አለመውሰዱ አንዱ ሰበብ ነውና አሁን የሚተላለፉ ቤቶች ላይ ዋጋ የትየለሌ ጭማሪ እንደሚደረግ መነገሩን አግባብ ነው ብሎ ለመቀበል ይዳግታል፡፡ ቀድሞ ውለታ በተገባበት ዋጋ መሠረት ቤቱን አናስረክብም ማለት አግባብ ሊሆን አይችልም፡፡ ችግሩ የተፈጠረው በማነው? ብሎ ነገሩን መርምሮ አግባብ ያለው ውሳኔ መወሰን ሲገባ፣ ያለጥፋቱ ቤት ተጠባቂው ላይ ዋጋ መቆለል ትክክለኛ ፍርድ አይደለም፡፡ በቅስቀሳ ጭምር የቤቱን ሙሉ ክፍያ ፈጽመናል ያሉ ዜጎች ዛሬ ‹‹ሙሉ ከፍለናል ብላችሁ አታስቡ›› ተብለዋል፡፡ ይህ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ ዜጎች በአምስትና በስድስት ዓመታት ገንዘብ የቆጠቡት በገቡት ውል ታምነው እንደሆነ መዘንጋት የለበትም፡፡ ይሁንና አሁን ከሚገለጸው አንፃር የተደረሰበት ውሳኔ መጤን አለበት ባይ ነኝ፡፡

ነባሮቹ አሠራሮች የፈጠሩት ችግር እንደሆነ ብንስማማም እንኳ፣ በባንክ ተቀምጦ የቆየው የቤት ፈላጊዎች ገንዘብ ቢሠሩበት ኖሮ ሊያስገኝላቸው የሚችለው ጥቅምም ሊታሰብላቸው ይገባል፡፡ ችግሩን ቤት ገዥው ላይ መደርደር ተገቢ አይደለም፡፡ መተሳሰብ ካስፈለገ ዜጎች የቆጠቡት ወይም የፈጸሙት ክፍያ በባንክ ተቀምጦ ሊያስገኝ ይችል የነበረው የወለድ ጥቅምም ሊሰላ ይገባል፡፡ ቤቶቹን የሚገነቡት የግል ድርጅቶች ቢሆኑ ኖሮ የሚደርስባቸው ወከባ፣ መንግሥትን ትዝብት ላይ ይጥለዋል፡፡ መንግሥት አይነኬነቱን ያሳየበት ሆኗልና፡፡

በአጠቃላይ በቤቶች ፕሮጀክቶች ላይ የታዩ ችግች ብዙ ዋጋ  ስላስከፈሉ፤ አሁንም እያስከፈሉ ከመሆናቸው አንፃር መንግሥት ቃሉን እንዲጠብቅ ሕዝብም የሚፈለገውን እንዲያገኝ ወገብን አጥብቆ መሥራቱ ይበጃል፡፡ እየታየ ያለውን ክፍተትም በብልኃት መፍታት አንድ ጉዳይ ሆኖ፣ የወደፊት ፕሮጀክቶች ማሰቡ ይበጃል፡፡ በውል ተቀባይና ውል ሰጪ መካከል ተጠያቂነትን በሚያሰፍን መልኩ የሕግ ማዕቀፍ መኖር አለበት፡፡ ነገም እንዲህ ያሉ ሥራዎች ይኖራሉና የተበላሹ ታሪኮች እንዳይደገሙ መትጋት ያሻል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት