Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በመድን ዘርፉ የተደራሽነትና የአዳዲስ አገልግሎቶች ጥያቄ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የገንዘብ ተቋማት አጠቃላይ አቅም ከሰሃራ በታች አገሮች አንፃር ሲታይ ብዙ እንደሚቀረው ሲነገር ሲተነተን ቆይቷል፡፡ ዘርፉ ለአገር በቀል ኩባንያዎች ብቻ ክፍት በመደረጉ፣ ከውጭ ለሚመጣበት ውድድር ያልተገባ ከለላ እንደተሰጠው የሚከራከሩ አካላት፣ በተደራሽነቱ ረገድም ዝቅተኛ አፈጻጸም የሚታይበት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

የዘርፉ ባለሙዎችም የተደራሽነቱን ውስንነት ይስማሙበታል፡፡ በባንክም ሆነ በኢንሹራንስ ዘርፉ ያሉት የአገልግሎት ዓይነቶች በጣት የሚቆጠሩ መሆናቸውም ውድድር አልባ መሆኑ የፈጠረው የገበያ መዛባት ተጠቃሚው ማግኘት የሚገባውን አገልግሎት አሳጥቶታል፡፡ በመሆኑም ለዘርፉ መሻሻል ብዙ ለውጥ እንደሚያስፈልግ ይመከራል፡፡ ይዘከራል፡፡

በተለይ ከኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው አንፃር ዘርፉ ብዙ እንደሚቀረው የኢትዮጵያን የኢንሹራንስ ሽፋን የሚያመላክቱ አኃዛዊ መረጃዎች ይናገራሉ፡፡ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ በዓመት የሚሰበሰበው የዓረቦን መጠን 280 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ይህም እ.ኤ.አ. በ2017 የተመዘገበ መጠን ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2018 የተገኘው የዓረቦን ገቢም ይህ ነው የሚባል ጭማሪ አልታየበትም፡፡ በዚሁ ጊዜ ግን ኬንያ ሁለት ቢሊዮን ዶላር መሰብሰቧን የሚያሳዩ መረጃዎች ተመሳክረው፣ የኢትዮጵያን ኋላ መቅረት አሳይተዋል፡፡ ዘርፉ በጥቂት የኢንሹራንስ አገልግሎቶች የተወሰነና በሞተር ኢንሹራንስ ላይ ተንጠልጥሎ የቆየ መሆኑም ትልቅ ችግር ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በየዓመቱ 17ቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በጥቅል የሚሰበሰቡት የዓረቦን መጠን ሲታይም እጅግ አነስተኛ ሆኖ መገኘትም በጥቂት አገልግሎቶች ላይ ብቻ የተወሰነ ስለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡

ኢንዱስትሪው የሚገኝበትን ደረጃ ለማመላከት በዘርፉ ባለሙያዎች ዘንድ በመመዘኛነት ከሚቀርቡት አንዱ የመድን ሽፋን ተደራሽነት ነው፡፡ በዚህ መመዘኛ ኢትዮጵያ በዝቅተኛው ደረጃ ላይ ትመደባለች፡፡ የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ዘርፉ ጠልቆ ተደራሽነት ድርሻው 0.43 በመቶ ነው፡፡ ይህ አኃዝ በአፍሪካ በዝቅተኛ ደረጃ ከሚመደቡ አምስቱ አገሮች ኢትዮጵያን አንዷ ያደርጋታል፡፡

ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚያሰኘው ሌላው ተጨባጭ እውነታ፣ በሕይወት መድን ሽፋን ረገድ የምትገኝበት ደረጃ ነው፡፡ በዚህ መስክ የደቡብ አፍሪካ የሕይወት መድን ድርሻ ሲታይ 16.9 በመቶ ነው፡፡

የኢንሹራንስ ባለሙያው አቶ ፍቅሩ ፀጋዬ እንደሚገልጹት፣ በኢትዮጵያ ከጠቅላላው ኢንሹራንስ ሽፋን አኳያ፣ ኩባንያዎች ከሚሰባሰቡት የዓረቦን ገቢ ውስጥ የሕይወት ዘርፍ የኢንሹራንስ ድርሻ አምስት በመቶ ገደማ መሆኑ፣ የአገሪቱን ዝቅተኛ ደረጃ አመላካች ያደርገዋል፡፡ በሌላ አገላለጽ ኩባንያዎቹ አብዛኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ሊያዳርሱ የሚችሉባቸው የኢንሹራንስ አገልግሎቶች እንደሌሏቸውም የሚጠቁም ነው፡፡ በሌሎች አገሮች የሕይወት ኢንሹራንስ ከሌሎች የመድን መደቦች ይልቅ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡ በኢትዮጵያ ግን የሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፉ ገና ያልተነካና ካለው ተጠቃሚ አቅም አኳያ ብዙ መታየት እንዳለበት ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

ዘርፉን ለማሳደግና ተደራሽነቱን ለማስፋት እንደ ሕዝቡ እምነትና ፍላጎት፣ አመለካከትና አኗኗር ተስማሚ የመድን አገልግሎቶችን ማስጀመርና ማላመድ ያስፈልጋል፡፡ ይህንንም ለማድረግ የሚያስችል ፖሊሲ ማዘጋጀት እንደሚገባም ይገለጻል፡፡ ኢትዮጵያ ካላት የሕዝብ ብዛት፣ የመድን ዋስትና ሽፋን ማግኘትና መጠቀም ከሚችሉ ዜጎች ብዛት አኳያ መንግሥትም በየጊዜው ከሚያጋጥሙ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች አኳያ የተጎጂዎችን ተጋላጭነት ለመቀነስ ከሚያስችል መነሻ የመድን አገልግሎቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲዳረሱ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበትም የሚገልጹ በርካቶች ናቸው፡፡

በመሆኑም እንደ ተጠቃሚው ፍላጎትና አቅም ብሎም እንደ ሥጋት ሁኔታው የመድን ሽፋን ለመስጠት የሚያስችሉ አማራጭ አገልግሎቶችን ማምጣት ግድ እንደሚል የገለጹት አቶ ፍቅሩ፣ ወለድ አልባ የኢንሹራንስ አገልግሎት በሰፊው ሊዳረሱ ከሚገባቸው አገልግሎቶች አንዱ ስለመሆኑም ይጠቅሳሉ፡፡ ሰሞኑንም ወለድ አልባ የፋይናንስ አገልግሎትን በተመለከተ አዲስ አበባ በተካሄደ የውይይት መድረክ፣ አቶ ፍቅሩና የሙያ አጋሮቻቸው ጽሑፎችን አቅርበዋል፡፡ በዓረቡ ዓለም በተለይም በገልፍ ምክር ቤት አባል አገሮች ውስጥ መደበኛው የመድን አገልግሎት ያለው ተደራሽትና ተቀባይነት ወለድ አልባ ከሆነው እንደሚያንስ በጽሑፋቸው ያመላከቱት አቶ ፍቅሩ፣ በኢትዮጵያም እስልምና በርካታ ዓማንያን ያሉት በመሆኑ፣ ለዚህ ቤተ እምነት የሚስማማ የመድን አገልግሎት ማቅረብ እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡

እንደ አቶ ፍቅሩ እንደገለጹት፣ ‹‹ተካፉል ታከማ›› የተባለው የወለድ አልባ የኢንሹራንስ አገልግሎት አንዱ ነው፡፡ ይህ የኢንሹራንስ ዓይነት በአብዛኛው የእስልምና ተከታይ በሆኑ አገሮች ተተግብሮ ውጤታማ የሆነ ነው፡፡

አገልግሎቱ ግን ለእምነቱ ተከታዮች ብቻ የተከለለ ሳይሆን ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች አካቶ የሚሠራ በመሆኑ፣ የእስልምና ተከታይ ባልሆኑ አገሮች ጭምር የሚተገበር ነው፡፡ ኬንያ እ.ኤ.አ. በ2015 ይህንን አገልግሎት መስጠት ጀምራለች፡፡ ሁለት በመቶ ሙስሊም ነዋሪዎች በሚገኙባት ደቡብ አፍሪካም ይህንን አገልግሎት የሚያቀርቡ አሥራ አንድ ኩባንያዎች አሏት፡፡

ተካፉል ኢንሹራንስ በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች አገልግሎቱ እየሰፋ ስለመሆኑም የገለጹት አቶ ፍቅሩ፣ እንደ እ.ኤ.አ. በ2017 የታካፉል ኢንሹራንስ ገበያ 19 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ጠቁመዋል፡፡ ይህ የኢንሹራንስ ዘርፍ አጠቃላይ ሽፋኑ በ2023 ወደ 40 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ተተንብዮአል፡፡ 

በየዓመቱም ከ15 እስከ 20 በመቶ ዕድገት ይታይበታል የተባለው ይህ አገልግሎት፣ በአፍሪካ ጥቂት የማይባሉ አገሮች ሥራ ላይ አውለውታል፡፡ ከኢትዮጵያ አንፃር ሲታይ ግን ይህ አልግሎት ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል በአስረጂ ያመላከተው ጥናታዊ ጽሑፍ፣ በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝበ ሙስሊም ከመኖሩ አኳያ አገልግሎቱን በቀላሉ ለማቅረብ የሚያስችል ዕድል እንዳለ ጠቁመዋል፡፡ አቶ ፍቅሩ እንዳሉት፣ አገልግሎቱን የሚፈልጉ ተጠቃሚዎች በርካታ በመሆናቸው በኢትዮጵያ ቢተገበር ኩባንያዎች ውጤታማ የሚሆኑባቸው ዕድሎችን ምሳሌዎችን በማቅረብ አብራተዋል፡፡ ወለድ አልባ የፋይናንስ አገልግሎቶች በኢትዮጵያ ስላስገኟቸው ውጤቶች ሲያብራሩም፣ ባንኮች የሚሰጡትን የወለድ አልባ አገልግሎት በመጥቀስ ነው፡፡ ባንኮች በመስኮት እየሰጡ ባሉት የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት እነርሱም ሆኑ ተገልጋዮችን እየጠቀመ በመሆኑ በኢንሹራንስ ዘርፉም በተመሳሳይ መተግበር ያለበት ነው ይላሉ፡፡ ይህ ደግሞ የአገሪቱን የኢንሹራንስ ሽፋን ከማስፋት አንፃር ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡

የተካፉል ኢንሹራንስ አገልግሎት እንደ ኢንሹራንስ አገልግሎት ኩባንያዎቹ ፍላጎት መሠራት የሚችል እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡ ከመደበኛው የኢንሹራንስ አገልግሎት በተለየ የሚሠራበት ይህ የኢንሹራንስ ዓይነት፣ ተጠቃሚዎች ኢንሹራንስ ለሚገባለት ንብረት ፈንድ በማድረግ እንደ ኢንሹራንስ የሚገባለት ንብረት ፈንዱ ተሰባስቦ አደጋ ሲደርስ እንደ ንብረቱ ዓይነት አስፈላጊው ካሳ የሚከፈልበት አሠራር ያለው ነው፡፡ ከተሰበሰበው ፈንድ ለጉዳት ካሳ ካልሞላ ደግሞ ፈንዱን ያሰባሰቡት አካላት እንደየድርሻቸው ምንም ዓይነት ወለድ የማይታሰብበት መልሰው መከፋፈል የሚችሉበት ዕድል የሚፈጥርም ነው፡፡ በተካፉል ኢንሹራንስ ሁሉንም ዓይነት የኢንሹራንስ ሽፋን መስጠት የሚቻል ሲሆን፣ ኩባንያዎች ይስማማኛል ያሉትን መርጠው አገልግሎት ሊሰጡበት ይችላሉ፡፡ ታች ድረስ በሚወርድ በመደጋገፍ ላይ የተመሠረተ ነው ያሉት የኢንሹራንስ አገልግሎት በኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመር ምቹ ሁኔታ ቢኖርም አገልግሎቱን ለማስጀመር የሚያስችል ፖሊሲ ግን የለም፡፡ ነገር ግን በተለይ በኢንሹራንስ ዘርፍ እንዲህ ያለውን አሠራር ለመዘርጋት ኩባንያዎች በማኅበራቸው በኩል ጥናት በማድረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መግፋት ይኖርባቸዋል፡፡ ከትርፋማነት በላይ ኢንዱስትሪውን በማስፋት ዓይነተኛ ሚና ያለውን የተካፉል የኢንሹራንስ አገልግሎት መቀጨት ታውቆ ቀድሞ መጀመር ነበረበት የሚልም እምነት አላቸው፡፡ ኢትዮጵያን የአፍሪካ ማዕከል ማድረግ ከተፈለገም እንዲህ ያለውን አማራጭ ማየት ተገቢ ይሆናል፡፡ የኢኮኖሚ ፖሊሲውንም ቢሆን ይኼንኑ ያገናዘበ መሆን እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡

ከሰባትና ስምንት ዓመታት በፊት በተመሳሳይ ወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ከተጀመረ በኋላ በዚህ ዘርፍ የተገኘው ውጤት ጥሩ ቢሆንም፣ ራሱን ችሎ እየተንቀሳቀሰ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት በመስኮት ብቻ እንዲሰጥ በመወሰዱ ነው፡፡

በኢንሹራንስ ዘርፉም በተመሳሳይ መተግበር ቢኖርበትም በሐሳብ ደረጃ እንኳን ንግግር እየተደረገበት አለመሆኑ አንድ ክፍተት ነው ተብሏል፡፡ ለዚህ ደግሞ ለዘርፉ ዕድገት የተለያዩ አማራጮችን ማፈላለግና ተግባራዊ የሚሆኑበትን ፖሊሲ መቅረፅ የነበረበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በጉዳዩ ላይ ያለመሥራት አንዱና ትልቁ ችግር እንደሆነ በውይይት መድረኩ ላይ ከተለያዩ ወገኖች አስተያየት ተሰጥቶበታል፡፡ እንደውም ባንኩ የአገሪቱን የፋይናንስ ስትራቴጂክ ዕቅድ ይፋ ሲያደርግ እንዲህ ያሉትን አማራጭ የፋይናንስ አገልግሎቶችን እንዲካተቱበት ያለማድረጉ ችግሩን ያሳያል ተብሏል፡፡

በባንክ ዘርፉም ቢሆን ከወለድ ነፃ አገልግሎት በመደበኛው ባንክ በአንድ መስኮት እንዲሠራበት መመርያ ወጥቶለት እየተተገበረ ቢሆንም፣ አገልግሎቱን በሰፊው ለማዳረስ የሚያስችል ሁኔታ የለም፡፡ ይህም ሆኖ ቢያንስ በኢንሹራንስ ኩባንያዎች የመስኮት አገልግሎት እንዲጀምሩ ከወዲሁ ዝግጀት መደረግ እንዳለበት አቶ ፍቅሩ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ማዕከላዊ ባንኩ ለዚህ የኢንሹራንስ ዘርፍ ምቹ የሆነ መመርያ እንዲቀረጽ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችና በዘርፉ የሚሠሩ ተቋማት መገፋት ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች