Saturday, April 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የንግድ ባንክ ሰባት ምክትል ፕሬዚዳንቶች ከኃላፊነታቸው ለቀቁ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በከፍተኛው የማኔጅመንት ዕርከን ሲያገለግሉ ከነበሩ ስምንት ምክትል ፕሬዚዳንቶች ሰባቱ ባንኩን ለቀቁ፡፡ ባንኩን ከለቀቁት ኃላፊዎች ውስጥ ሦስቱ የግል ባንኮች ፕሬዚዳንት የመሆን ዕድል አግኝተዋል፡፡

ንግድ ባንክን እንዲመሩ የተሾሙት አዲሱ ፕሬዚዳንት አቶ ባጫ ጊና ኃላፊነታቸውን ከተረከቡ ወዲህ ከበታች የነበሩ ኃላፊዎች በራሳቸው ፈቃድ ባንኩን ስለመልቀቃቸው የሚገልጹ መረጃዎች ሲመጡ ሰንብተዋል፡፡ ለቀዋል በተባሉት ከፍተኛ የማኔጅመንት አባላት ምትክም አዳዲስ አመራሮች ተሹመዋል፡፡

እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት፣ ከአስተዳደር ለውጡ ወዲህ ከዚህ ቀደም ከነበሩበት የአመራር አባላት ውስጥ በቦታቸው እንዳሉ የቆዩት አንድ ግለሰብ ብቻ ናቸው፡፡ በቀድሞው ፕሬዚዳንት በአቶ በቃሉ ዘለቀ ይመራ በነበረው አስተዳደር ወቅት፣ ስምንት ምክትል ፕሬዚዳንቶች የተካተቱበት አስተዳደር የባንኩን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ይመራ ነበር፡፡ አቶ ባጫ ወደ ባንኩ ከመጡ በኋላ የማኔጅመንቱን አባላት ቁጥር ወደ ሰባት ዝቅ አድርገው መጠነኛ የአመራር ሽግሽግ በማድረግ እየመሩት እንደሚገኙ ታውቋል፡፡  

በአቶ በቃሉ ይመራ በነበረው የንግድ ባንክ ኃላፊዎች ቡድን ውስጥ ተካተው ሲያገለግሉ የነበሩት ስምንት ምክትል ፕሬዚዳንቶች አቶ ዓባይ መሃሪ የብድር አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት፣ አቶ ሙሉጌታ ዓለማየሁ የደንበኞች ሒሳብ አካውንትና ትራንዝአክሽን ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ ወ/ሮ ሚልኪያ በድሪ የኢንፎርሜሽን ሲስተም ምክትል ፕሬዚዳነት፣ አቶ ሰይፉ ቦጋለ የሰው ኃይል አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳነት፣ አቶ አትክልት ኪዳነ ማርያም የፋይናንስ ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ ወ/ሮ መሠረት አስፋው የፋሲሊቲዎች አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት፣  አቶ ወንድአለ በላቸው የብድር ግምገማና የፕሮቶኮል ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ከወ/ሮ ሚልኪያ በቀር የተቀሩት ኃላፊዎች በሙሉ በገዛ ፈቃዳቸው ሥራ ስለመልቀቃቸው ተሰምቷል፡፡ በኅዳር ወር ብቻ አቶ ሰይፉ ቦጋለ፣ አቶ ዓባይ መሃሪ፣ አቶ አትክልት ኪዳነ ማርያምና ወ/ሮ መሠረት አስፋው በአንድ ጊዜ ከኃላፊነታቸው እንደለቀቁ የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ባንኩ ባደረገው የማኔጅመንት አባላት ምደባም ሰባት አባላት ባሉት አዲስ አስተዳደር ተዋቅሯል፡፡ ፕሬዚዳንቱን አቶ ባጫ ጊና ጨምሮ፣ አቶ ፍቅረ ሥላሴ ዘውዱ፣ አቶ ዓሊ አህመድ፣ ወ/ሮ ሚልኪያ በድሪ፣ አቶ ሱራ ሳቀታ፣ ወ/ሮ ጥሩ ብርሃን ኃይሉና አቶ ኪዳኔ መንገሻ አዲሶቹ አመራሮች እንደሆኑ ታውቋል፡፡

እነዚህ ከፍተኛ የባንኩ የሥራ አመራር አባላት ውስጥ ወ/ሮ ጥሩ ብርሃን ቀደም ብሎ የሪስክ ማኔጅመንት ኦፊሰር ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩ የነበሩና አሁን በከፍተኛው ማኔጅመንት የተካተቱ ሲሆን፣ ወ/ሮ ሚልኪያ ደግሞ በቀደመው ማኔጅመንት ከሰባቱ የባንኩ የሥራ አመራር አባላት ውስጥ የቀጠሉ ብቸኛው አመራር ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰባት ምክትል ፕሬዚዳንቶች በፈቃዳቸው ለቀዋል የሚለው ጉዳይ አነጋጋሪ ቢሆንም፣ ባንኩን ከለቀቁት ውስጥ አንዳንዶቹ የግል ባንኮችን እየተቀላቀሉ ነው፡፡

በተለይ ባንኩን በምክትል ፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ የቆዩት ሁለቱ ፕሬዚዳንቶችና የባንኩ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ በቃሉ ዘለቀ፣ በሦስት የግል ባንኮች በፕሬዚዳንትነት ተሹመዋል፡፡ አቶ ሙሉጌታ ዓለማየሁ የቡና ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሾመዋቸው የነበሩት አቶ በቃሉ ይህንን ኃላፊነት በመተው፣ የአቢሲኒያ ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡ ሰሞኑን ይፋ እንደተደረገውም የንግድ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት የቆዩት አቶ ዓባይ መሐሪም ባንኩን ከለቀቁ በኋላ የወጋገን ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡

አቶ ዓባይ የወጋገን ባንክ ፕሬዚዳንት የሆኑት ባንኩን የቀድሞውን ፕሬዚዳንት አቶ ገብረ እግዚአብሔር አርዓያን በመተካት ነው፡፡ ይህም በግማሽ ዓመቱ ውስጥ የሦስት የግል ባንኮች ፕሬዚዳንት መሆን መቻላቸውን ያሳየ ሲሆን፣ የቀድሞዎቹ ምክትል ፕሬዚዳንቶች ለቡና ባንክ፣ ለወጋገንና ለአቢሲኒያ ባንክ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ በመታጨታቸውና ሹመታቸውን የሚያፀድቀው ብሔራዊ ባንክም ይሁንታውን ስለሰጣቸው አዲሱን ሥራቸውን ጀምረዋል፡፡

ንግድ ባንክን በምክትል ፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ በቆዩት ተሰናባች ኃለፊዎችና በሌሎች የሥራ መደቦች በነበሩት ምትክ ከግል ባንኮች በመጡ ግለሰቦች እየተካቸው እንደሚገኝ ተገጿል፡፡ እንደ ምንጮች ገለጻ፣ በቅርቡ የአዋሽ ባንክ ስምንት ኃላፊዎች  ባንኩን በመልቀቅ ንግድ ባንክን ተቀላቅለዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች