Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአነስተኛ ግብር ከፋዮች የታክስ ክርክር መቋረጥ የፈጠረው ግርታ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማ አስዳደር ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ከተማ አቀፍ የታክስ ንቅናቄ መድረክ፣ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) የካቢኔያቸውን ውሳኔ እግረ መንገዳቸውን አስታውቀው ነበር፡፡ ይኸውም የከተማው 6,000 አነስተኛ ግብር ከፋዮች በ2009 ዓ.ም. የተጣለባቸውን ግብር በመቃወም ክርክር ላይ እንደነበሩና አስተዳደሩም ክርክሩ አቅቷቸው ሲታገቱ ለነበሩ እነዚህ ግብር ከፋዮች ክርክሩ እንዲቋረጥላቸው ማድረጉን ይፋ አድርገዋል፡፡

ምክትል ከንቲባው ይፋ ያደረጉት የካቢኔ ውሳኔ በሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር በመገልጽ መግለጫ የሰጡት፣ የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሺሰማ ገብረሥላሴ ናቸው፡፡ በካቢኔው ውሳኔ መሠረት ከቀን ገቢ ግምት ጋር በተያያዘ በግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባዔ አቤቱታ ያቀረቡና ክርክር ላይ የነበሩ ግብር ከፋዮች ለይግባኝ ያስያዙት ‹‹50 በመቶ ፍሬ ግብር በቂ ሆኖ ወለድና ቅጣቱ ቀሪ ተደርጎላቸው ወይም የቀን ገቢ ግምታቸው በ50 በመቶ ተስተካክሎ እንዲሠራና ክርክሩም ተቋርጦ የንግድ ፈቃዳቸው ያላደሱ እንዲያድሱ›› እንዲፈቀድላቸው የሚለው አንደኛው ውሳኔ እንደነበር አቶ ሺሰማ ገልጸዋል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ በዚህ የካቢኔው ‹‹ውሳኔ ያልተስማሙና ክርክራቸውን መቀጠል የሚፈልጉ ካሉ፣ በክርክሩ የመቀጠል መብታቸው ይከበር›› የሚል ሲሆን፣ በሦስተኛ ደረጃ፣ ‹‹የፍሬ ግብሩን 50 በመቶ መክፈል ባለመቻላቸው ወደ ግብር ይግባኝ መሄድ ያልቻሉ ግን በጀመሩት ንግድ ሥራ የመቀጠል ፍላጎት ላላቸው ግብር ከፋዮች፣ የንግድ ፈቃዳቸውን እንዲያድሱና ፈቃዳቸውን መመለስ ለሚፈልጉትም ከገቢያቸው ጋር ተመጣጣኝ ግብር መክፈል የሚያስችላቸው ግምት የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለሥልጣን ኃላፊነት ወስዶ እንዲሠራና እንዲያስፈጽም ካቢኔው በሙሉ ድምፅ ውሳኔ አሳልፏል፤›› ማለቱን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም 4,041 አነስተኛ ወይም የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች በክርክር ሒደት ላይ እንደነበሩና 1,959 ግብር ከፋዮች፣ ለግብር ይግባኝ ሰሚው የ50 በመቶ ቅድመ ክፍያ ማስያዝ እንዳልቻሉ በመረጋገጡ፣ በጠቅላላው 6,000 ግብር ከፋዮች በክርክር ላይ የነበሩበት ሒደት እንዲቋረጥ መወሰኑን አቶ ሺሰማ አስታውቀው፣ በሚዲያ የተላለፉ ዘገባዎች ከዚህ ዓውድ በመውጣት፣ የግብር ምሕረት እንደተደረገ ወይም መንግሥት ለግብር ከፋዮች ይቅርታ እንዳደረገ መገለጹ ግርታ እንደተፈጠረ የተናገሩት አቶ ሺሰማ፣ ሌሎች ግብር ከፋዮች ይህንን ተገን በማድረግ ያልተገባ ጥያቄ ለማቅረብ ሲዳዱ መታየታቸውን ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ግብር ከፋዮች በ2009 ዓ.ም. የተደረገውን የቀን ገቢ ግምት ተከትሎ በተጣለው የግብር ውሳኔ ላይ እንደበዛባቸውና ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ በመግለጽ ለተቋሙ ቅሬታ ሰሚ ያቀረቡ ናቸው፡፡ በተቋሙ ቅሬታ ሰሚ አካል ምላሽም ቅር በመሰኘታቸው፣ ከተጠዩት ግብር 50 በመቶውን ለክርክር በቅድሚያ ክፍለው ውሳኔ ሲጠባበቁ የቆዩ ናቸው፡፡ ከእነዚህም ባሻገር 341 አነስተኛ ግብር ከፋዮች በግብር ይግባኝ ሰሚ ችሎት ፍትሕ ሲጠይቁ መክረማቸውን ያስታወሱት አቶ ሺሕሰማ፣ ከሐምሌ ጀምሮ በነበረው የክርክር ሒደትም በቅርቡ ውሳኔ ካገኙት ከ341 መዝገቦች ውስጥ 337ቱ ባለሥልጣኑ የተረታባቸውና የወሰነው ግብር ተገቢ አይደለም ተብሎ ውሳኔ እንደተላለፈበት ተጠቅሷል፡፡ ይህም ሆኖ በአሁኑ ወቅት ከ900 በላይ ግብር ከፋዮች የግብር ይግባኝ ሰሚ ክርክር ላይ እንደሚገኙም ለማወቅ ተችሏል፡፡ የእነዚህ ግብር ከፋዮች መዝገብም በቅሬታ ሰሚው ችሎት ዳኝነት ይጠባበቃል፡፡

እንዲህ ባለው የተጓተተ ሒደት ለ341 መዝገቦች ውሳኔ ለመስጠት ግማሽ ዓመት የሚጠይቅ ከሆነ፣ ለ6,000 አነስተኛ ግብር ከፋዮች ያውም ምን ያህል ጊዜ እንደሚፈጅ ታስቦ፣ ያውም በከተማው የግብር ገቢ ላይ ይህ ነው የሚባል አስተዋጽኦ የማያደርግ የግብር ገቢን እንዲቋረጥና የተከፈለው ታሳቢ እንዲደረግ በካቢኔ መወሰን ለከተማው አስተዳደርም የተሻለ አማራጭ መፍትሔ ሆኖ ያገኘው ክርክሩን ማቋረጥ እንደሆነ በመግለጽ፣ ሌሎች መዝገብ የሚይዙ፣ ኦዲት የሚደረጉና ተገቢውን ግብር መክፈል የሚጠበቅባቸው ለእኛም ‹‹ምሕረት›› ይደረግልን ማለት እንደማይችሉና ጥያቄያቸውም ተገቢነት እንደማይኖረው ገልጸዋል፡፡

ለ6,000 አነስተኛ ግብር ከፋዮች የተወሰነው ለምን እንደተጋነነ የገረማቸው አቶ ሺሰማ፣ በሐምሌ 2010 ዓ.ም. ከ68 ሺሕ በላይ ነጋዴዎች በ2009 ዓ.ም. ተጥሎባቸው የነበረው ግብር ሲጠና ከአቅማቸው በላይ መሆኑ ተረጋግጦ በግማሽ እንዲቀነስላቸው መደረጉን አስታውሰዋል፡፡ ይህ ግን ብዙም መነጋገሪያ ሳይሆን እንዳለፈም ጠቅሰዋል፡፡ ይህም ሆኖ ባለፈው ዓመት በመዝገብ ከተስተናዱ ትልቅ ግብር ከፋዮች መካከል ከ90 በመቶው በላይ ያቀረቡት መዝገብ ተቀባይነት አግኝቶ ባቀረቡት የግብር መጠን እንዳስተናገዱ አቶ ሺሰማ አስታውሰዋል፡፡

ምንም እንኳ ጉዳዩ በዚህ ቢታይም፣ በአዲስ አበባ እንደተደረገው በክልሎችም የ‹‹ግብር ምሕረት ይደረግልን›› የሚሉ ጥያቄዎች መስተጋባቸው ተሰምቷል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስለ ክልሎቹ ጥያቄዎች ማብራሪያ መስጠት እንደማይችል ገልጸዋል፡፡ መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተው ይህ ውሳኔ፣ በክልሎችም ግብር ከአቅማቸው በላይ ለተገመተባቸውና በዝቅተኛ የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው ኑሮን ለማሸነፍ ለሚጣጣሩት ተጣርቶ የአዲስ አበባ አስተዳደር ዓይነት ውሳኔ መስጠቱ ክፋት እንደሌለው የሚገለጹ አሉ፡፡ ይሁንና ከአብዛኛው ግብር ከፋይ ምን ያህሉ በግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባዔ በኩል መፍትሔ ማግኘት እንዳልቻሉ ማጣራቱ ተገቢ እንደሚሆንም የገለጹ አሉ፡፡

በአዲስ አበባ ከሚገኙ 340 ሺሕ ግብር ከፋዮች ውስጥ 70 በመቶው በቀን ገቢ ግምት ስሌት መሠረት ግብር እንደሚከፍሉ ገቢዎች ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡ የከተማው ግብር ከፋዮች ግለሰብ ነጋዴዎች እንደሆኑና የኩባንያ ግብር ከፋዮች በፌዴራል ደረጃ እንደሚስተናገዱ ተገልጿል፡፡

የገቢዎች ባለሥልጣን በዚህ ዓመት ከታክስ 34.5 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱ ይታወቃል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች