Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየአንጋፋው የኢትዮጵያ ቡና መሥራች ስንብት

የአንጋፋው የኢትዮጵያ ቡና መሥራች ስንብት

ቀን:

የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ መሥራችና የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ፣ ለበርካታ ዓመታት ሲመሩት ከቆዩት ክለባቸው ጋር ለመሰነባበት ተገደዋል፡፡ ከደጋፊዎች የደረሰባቸው ማንጓጠጥና ሥነ ምግባር አልባነት ለዓመታት ከመሩትና ካስተዳደሩት ክለብ እንዲለዩ ምክንያት ሆኗቸዋል፡፡

ክለቡ በሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች መሸነፉን ተከትሎ ቅሬታ ያደረባቸው ደጋፊዎች፣ ከስታዲየም ሲያሰሙት የነበረው ዘለፋና ስድብ በስፖርት ሜዳዎች የማይጠበቅ ብቻም ሳይሆን እንደ እንግሊዝ ባሉ የስፖርት መድኮች በእንዲህ ዓይነቱ ያልተገባ ድርጊት የሚሳተፉ ደጋፊዎች እስከ ዕድሜ ልክ በሚደርስ ቅጣት ወደ ስታድየም እንዳይገቡ የሚታገዱበት፣ ሲብስም በሕግ የሚጠየቁበት አግባብ አለ፡፡

መቶ አለቃ ፈቃደ በቡድናቸው መሸነፍ ሳቢያ በደጋፊዎች ከደረሰባቸው ፈር የሳተ ተቃውሞና ዘለፋ በኋላ ክለቡን መምራት እንደማይፈልጉ በማስታወቅ ረቡዕ፣ ጥር 29 ቀን 2011 ዓ. ም ከኃላፊነታቸው ስለመልቀቃቸው ይፋ አድርገዋል፡፡ ውሳኔያቸው ከተሰማ በኋላም የቡና ደጋፊዎች፣ የመቶ አለቃ ፈቃደ መልቀቅ ተገቢ ነው አይደለም በሚል ጎራ ለይተዋል፡፡ በአንድ በኩል ስህተት እንኳ ቢኖር፣ የክለቡ ኃላፊ መልቀቅ የነበረባቸው ስብዕናቸውን በሚያዋርድ መንገድ መሆን እንዳልነበረበት በቁጭት የሚገልጹ ባይጠፉም፣ ክለቡን ስለመልቀቃቸው ተገቢነት እንጂ ስለደረሰባቸው ዘለፋ ቁብ እንደማይሰጣቸው በአደባባይ የሚናገሩም አልታጡም፡፡

እንደ መቶ አለቃ ፈቃደ ሁሉ፣ በ1980ዎቹ አጋማሽ ክለቡን በፕሬዚዳንትነት፣ ከዚያም በላይ በተለያየ ጊዜ በቦርድ አባልነት በማገልገል የሚታወቁት አቶ ይስማሸዋ ሥዩም መልቀቂያ አስገብተዋል፡፡

ከመቶ አለቃ ፈቃደ በመከተል በኢትዮጵያ ቡና ክለብ ውስጥ በሰፊው የሚታወቁት አቶ ይስማሸዋ፣ ክለቡን ከመሠረቱ ጀምሮ በፕሬዚዳንትነትና በቦርድ አባልነት ከመምራታቸው በተጨማሪ፣ የቡድኑን የፋይናንስ አቅም ለማጎልበት በተደረጉ እንቅስቃሴዎች ማለትም እንደ ሐበሻ ቢራና ሲሚንቶ፣ እንደ ብርሃን ባንክና ሌሎችም ተቋማትን ወደ ክለቡ በማምጣት ለፈጸሙት የስፖንሰር ሺፕ ስምምነት በመሪ ተዋናይነት ይጠቀሳሉ፡፡ እንዲሁም በክለቡ የካምፕ ግንባታ፣ በማሊያ ሽያጭና የተለያዩ የሩጫ ውድድሮችን በማዘጋጀት ለክለቡ ገቢ መጎልበት ዓይነተኛ ሚና መጫወታቸው ይነገራል፡፡

በቅዱስ ዮሴፍ አካባቢ በተለምዶ ስብቴ በሚባለው አካባቢ በ1968 ዓ.ም. የንጋት ኮከብ በሚል መጠሪያ እንደተመሠረተ የሚነገርለት የአሁኑ የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ፣ ለ41 ዓመታት በመቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ሲመራ መቆየቱ ይነገራል፡፡ ክለቡን በቅርበት የሚውቁም ሆኑ ስለክለቡ የሚያወሱ መዛግብት እንደሚስረዱት ከሆነ ግን፣ መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ኢትዮጵያ ቡናን በሙሉ ኃላፊነት ያስተዳደሩት ከተጠቀሰው ጊዜ በእጅጉ ላነሰ ጊዜ ነው፡፡

የክለቡ ታሪክ እንደሚጠቁመው፣ በአሁኑ ወቅት በሕይወት የሌሉትን ጨምሮ በርካታ ግለሰቦች በፕሬዚዳንትነትና በቦርድ አባልነት አስተዳድረውታል፡፡ የመቶ አለቃ ፈቃደ ማሞን ስንብት ተከትሎ ክለቡን ለአራት አሠርታት መርተዋል ተብሎ የሚነገረው ትክክል እንዳልሆነ የሚናገሩ የቅርብ ሰዎች ቢናገሩም፣ ክለቡን በቦርድ አባልነት ለረዥም ዓመታት ካስተዳደሩት መካከል አንዱ ስለመሆናቸው ግን አሌ አይባልም፡፡ ከመቶ አለቃ ፈቃደ ይልቅ አቶ አብዱረዛቅ ሸሪፍ ቡናን ለአሥር ዓመታት በፕሬዚዳትነት ስለማስተዳደራቸው ይነገርላቸዋል፡፡

ከ1970ዎቹ ጀምሮ የንጋት ኮከብ የሚለውን መጠሪያውን የኢትዮጵያ ቡና ገበያ ወደሚለው ስያሜው እንደቀየረ የሚነገርለት ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ፣ በወቅቱ በኢትዮጵያ ቡና ገበያ ኮርፖሬሽን ውስጥ የሚሠሩ 4,000 ሠራተኞች የደመወዛቸውን አንድ በመቶ በማዋጣት በገንዘብ ያግዙት እንደነበር ይወሳል፡፡ የኮርፖሬሽኑ ሥራ አስኪያጅም መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ እንደነበሩ ይነገራል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሕይወት የሌሉትን አቶ አፈወርቅ ሲሳይና ሌሎችም የዛሬውን ቡና በፕሬዚዳንትነት እንደመሩት የክለቡ ቅርብ ሰዎች ይናገራሉ፡፡ አቶ ይስማሸዋ ሥዩምን ጨምሮ አቶ አዲስ ገብረ እግዚአብሔርና ሌሎችም ኢትዮጵያ ቡናን አስተዳድረዋል፡፡ በ1986 ዓ.ም የቡና ዋና የፋይናንስ ምንጮች የሚባሉት የቡና አምራቾች፣ አዘጋጆችና ላኪ ድርጅቶች የመበታተን ዕጣ በጣማቸው ወቅት፣ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ አማካይነት ክለቡ የሚታገዝበት ጥናት ተደርጎ ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ ከአንድ ቶን ቡና አምስት ብር ይታሰብለት ነበር፡፡ ይህ ክፍያ ወደ 30 ብር ከፍ እንዲል ተደርጎ ክለቡም በዓመት እስከ 12 ሚሊዮን ብር በሚደርስ በጀት ሲደገፍ ቆይቷል፡፡

የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ በአሁኑ ወቅት ዓመታዊ በጀቱ 50 ሚሊዮን እንደደረሰ የክለቡ የመረጃ ምንጮች ይናገራሉ፡፡ ወርኃዊ ወጪውም 3.5 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ የክለቡ ተጨማሪ በጀት የሚሸፈነውም በዚሁ ሳምንት የስንብታቸው ዜና ከተሰማው የክለቡ አመራሮች በኩል በስፖንሰሮች ከተገኘ የገቢ ምንጭ ስለመሆኑ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...