መንግሥት ከውጭ የልማት አጋሮች ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ በዘንድሮ የበጀት ዓመት ካገኘው ስድስት ቢሊዮን ብር ውስጥ 5.3 ቢሊዮን ብር የሚከፋፈሉት አራት ክልሎች፣ ሙሉ በጀቱን ለተቀናጀ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እንዲጠቀሙበት ወሰነ። ክልሎቹ አማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ናቸው፡፡
የአገሪቱን የኢኮኖሚ መዋቅር ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር በሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከተያዙ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ፣ የተቀናጀ አግሮ ፕሮሰሲንግ (የግብርና ልማት) ኢንዱስትሪዎችን በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች በመገንባትና ከሌሎቹ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ጋር ለማስተሳሰር ታስቦ ነበር።
ይኼንን ውጥን ለማሳካት ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ሪፖርተር ያገኘው ጥናት ያመለክታል። ይሁን እንጂ አጠቃላይ በጀቱንም ሆነ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ፓርኮችን በተለያዩ ክልሎች ለማስጀመር ያስፈልጋል የተባለውን ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ለማግኘት እጅ ያጠረው መንግሥት፣ የገጠመውን የፋይናንስ ችግር በመግለጽ ከውጭ የልማት አጋሮች ጋር በመወያየት ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ለኢትዮጵያ በየዓመቱ ፈሰስ የሚያደርጉትን ገንዘብ የኢንዱስትሪ ፓርኮቹን ግንባታ ለማስጀመር እንዲጠቀምበት ጠይቋል፡፡
ይኼንንም ገንዘብ የልማት አጋሮቹ ባስቀመጡት አሠራር መሠረት ክልሎች ለተባለው ዓላማ እንዲያውሉት በመደራደር ይሁንታ ማግኘቱን ለማወቅ ተችሏል።
መንግሥት ይኼንን ድርድር ያደረገው የልማት አጋሮቹ የፋይናንስ ድጋፉን የሚያደርጉት ከምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች ፕሮጀክት በኋላ ለተቀረፀው የዘላቂ ልማት ግቦች ፕሮግራም በመሆኑ፣ ይኼንንም ፕሮግራም ለማስፈጸም በፌዴራል መንግሥት በኩል የሚልኩት የገንዘብ ድጋፍ በቀጥታ ለክልሎች ስለሚከፋፈል ነው።
በተጨማሪም በዘላቂ ልማት ግብ ፕሮጀክት ሥር የሚጠቃለሉ የልማት ፕሮጀክቶች ለመሠረታዊ አገልግሎቶች ማለትም ለጤና፣ ለትምህርት፣ ለመጠጥ ውኃና ለመሰል የልማት ፕሮጀክቶች ብቻ የሚውል በመሆኑ ነው ድርድሩ የተደረገው፡፡
በመንግሥት የቀረበውን ጥያቄ የልማት አጋሮች መቀበላቸውን፣ በዚህም ምክንያት የገንዘብ ሚኒስቴር ከአማራ፣ ከትግራይ፣ ከኦሮሚያና ከደቡብ ክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች ጋር በመመካከር ለዘጠኝ ክልሎችና ለሁለት የከተማ አስተዳደሮች ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ከተፈቀደው ስድስት ቢሊዮን ብር ውስጥ 5.3 ቢሊዮን ብር ስለሚደርሳቸው፣ ክልሎቹ በጀቱን ለአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እንዲያውሉ ከስምምነት መደረሱን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በዚህም መሠረት ለአማራ ክልል 1.296 ቢሊዮን ብር፣ ለትግራይ ክልል 361 ሚሊዮን ብር፣ ለኦሮሚያ ክልል 2.067 ቢሊዮን ብር፣ ለደቡብ ክልል 1.206 ቢሊዮን ብር ለተባለው ፕሮጀክት እንዲውል መወሰኑን ለማወቅ ተችሏል።