Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበአማራና በደቡብ ክልሎች መስጊድና ቤተ ክርስቲያናት ተቃጠሉ

በአማራና በደቡብ ክልሎች መስጊድና ቤተ ክርስቲያናት ተቃጠሉ

ቀን:

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተከሰቱ ሃይማኖት ተኮር ጥቃቶች አንድ መስጊድና ሰባት ቤተ ክርስቲያናት ቃጠሎ እንደ ደረሰባቸው ታወቀ፡፡ መስጊዱና ቤተ ክርስቲያናቱ ቃጠሎ የደረሰባቸው በአማራና በደቡብ ክልሎች ነው፡፡

እሑድ የካቲት 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ሌሊት በአማራ ክልል በደቡብ ጎንደር ዞን አንዳቤት ወረዳ (ምሥራቅ እስቴ)፣ በግለሰቦች በተፈጸመ ጥቃት አንድ መስጊድ ቃጠሎና ዝርፊያ ተፈጽሞበታል፡፡

‹‹ከዚህ ቀደም ከነበረው ጥቃት በተለየ የአሁኑ ሆን ተብሎ ሕዝብን፣ በተለይም የኦርቶዶክስና የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችን ለማጋጨት የታለመ ሴራ ይመስላል፤›› ሲሉ፣ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ሼክ መሐመድ ሐሰን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በመስጊዱ ላይ ሌሊት ወደ ስምንት ሰዓት አካባቢ ጥቃት እንደተፈጸመ የተገመተ ሲሆን፣ ጥቃት ፈጻሚዎቹ የተለያዩ የእስልምና ሃይማኖት መጻሕፍትና ቅዱስ ቁርዓን  አንድ ላይ ሰብስበው ማቃጠላቸውን ሼክ መሐመድ ገልጸዋል፡፡

የአሁኑ ጥቃት በቅርቡ በእስቴ ወረዳ  በሦስት መስጊዶች ላይ ተፈጽሞ ለነበረ ተመሳሳይ ጥቃት መንግሥት አፋጣኝ ዕርምጃ ባለመውሰዱ፣ ግለሰቦች ተበረታትተው ተመሳሳይ ጥቃት እንዲፈጽሙ የልብ ልብ ሰጥቷቸዋል ሲሉ ሼክ መሐመድ አክለዋል፡፡

ጥር 26 ቀን 2011 ዓ.ም. በእስቴ ወረዳ ቀበሌ 03 (መካነ ኢየሱስ) ሁለት መስጊዶች ሲቃጠሉ፣ በአንድ መስጊድ ላይ ንብረት የማውደም ጥቃት ተፈጽሞ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በወቅቱ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ የሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች የሠርግ ሥነ ሥርዓት ዳስ ለማሳመር ተብሎ ከማተሚያ ቤት ተቆራርጦ ከመጣ የወረቀት ማስጌጫ ጋር አብሮ ተገኘ በተባለ፣ የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች የአማልክት ሥዕል ምክንያት ድርጊቱ መፈጸሙ አይዘነጋም፡፡

‹‹የየካቲት 3 ቀን 2011 ዓ.ም. ጥቃት ሌላ አጀንዳ ያነገበ ሊሆን ይችላል፤›› ሲሉ ሼክ መሐመድ ጠቁመዋል፡፡

የአማራ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መላኩ አላምረው፣ የክልሉ መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ እየሠራ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹በመጀመርያው ጥቃት ምክንያት ስድስት ተጠርጣሪዎች ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው ሲሆን፣ የወደሙትን መስጊዶች ለማሠራት የማቴሪያልና የገንዘብ መዋጮ ከሁሉም የአካባቢው ነዋሪዎች እየተሰባሰበ ነው፤›› ሲሉ አቶ መላኩ አክለዋል፡፡

ሼክ መሐመድ በበኩላቸው ሕዝበ ሙስሊሙ በዚህ ጥቃት በስሜት ተነሳስቶ ያልተገባ ነገር እንዳያደርግ፣ የተፈጸመውም ጥቃት ማንንም እንደማይወክል አሳሳበዋል፡፡››

በደቡብ ክልል በሐላባ ዞን በፕሮቴስታንት ሃይማኖት የአምልኮ ቦታዎች በተፈጸመ ጥቃት፣ ሰባት ቤተ ክርስቲያናት ተቃጥለው ውድመት እንደደረሰባቸው ታውቋል፡፡

የሐላባ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወ/ሮ ሒክማ ሃይረዲን፣ ‹‹ድርጊቱ የትኛውንም ሃይማኖት የማይወክል ነው፤›› ብለዋል፡፡ በተደረገ ማጣራት ጥቃቱን በመፈጸም የተጠረጠሩ ከ50 በላይ የመንግሥት አካላትን ጨምሮ የተለያዩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን፣ ከዞኑ የሕዝብ ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ለመረዳት ተችሏል፡፡

በቁጥጥር ሥር የዋሉት ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ ከተደረገ በኋላ በፍርድ ቤት ክስ እንደሚመሠረት ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...