Wednesday, June 19, 2024

ታላቅ መሆን የሚቻለው ያለፈውን በማንኳሰስ መጪውን በማጨለም አይደለም!

ከአፍሪካ አንድነት መሥራች አባቶች መካከል ግንባር ቀደም የሆኑት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በወታደራዊው መንግሥት ከሥልጣን ከተወገዱ ከ44 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ፣ ሰሞኑን በተካሄደው በ32ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ሐውልታቸው በከፍተኛ ሥነ ሥርዓት ይፋ ተደርጓል፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በሥልጣን ዘመናቸው ባከናወኑዋቸው በርካታ ድርጊቶች ይታወሳሉ፡፡ በደግም በክፉም ማለት ነው፡፡ ነገር ግን አፍሪካውያን ለነፃነታቸው ባደረጉት ተጋድሎ ወቅትም ሆነ ከነፃነት በኋላ፣ በአንድ ድምፅ የሚወከሉበት ተቋም እንዲኖራቸው ላደረጉት አስተዋጽኦ ይህ ታሪካዊ ሐውልት ተቀርፆላቸዋል፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ታላላቅ ተግባራት የሚያወድሱም ሆነ በእሳቸው ደስተኛ ያልሆኑ አንድ መገንዘብ ያለባቸው ሀቅ አለ፡፡ ይኸውም ንጉሠ ነገሥቱ በዘመናቸው ጥለዋቸው ያለፉ አሻራዎች ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ የሚያስተጋቡ መሆናቸውን ነው፡፡ በአፍሪካም ሆነ በተቀረው ዓለም በተለያዩ አጋጣሚዎች ስማቸው የሚነሳው፣ በነበሩበት ዘመን ተፅዕኖ ፈጣሪ በመሆናቸው ጭምር መሆኑን መተማመን ይገባል፡፡ እሳቸው ያስተዳደሯት አገር ምንም ባታደርግላቸውም፣ አፍሪካውያን ውለታ አለብን ብለው ሲያስታውሷቸው በፀጋ መቀበል ተገቢ ነው፡፡ ይህ ትውልድ ካለፈው ዘመን የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት መትጋት ሲኖርበት፣ በጭፍን ድጋፍና ጥላቻ ውስጥ ሆኖ ወደ ተግባር በማይመነዘር ጭቅጭቅ ጊዜውን ማባከን የለበትም፡፡ ታላቅነትን ማግኘት የሚቻለው ታላቆችን ከሚገባቸው በላይ በማግዘፍ ወይም በማዋረድ ሳይሆን፣ አርዓያ የሚሆን የተሻለ ሥራ ሠርቶ በተጨባጭ በማሳየት ብቻ ነው፡፡

በዚህ ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ እጅግ ከሚያሰለቹና ከሚያታክቱ ነገሮች አንደኛው፣ ስላለፈው ዘመን ያለው ጽንፍ የረገጠ አተያይ ነው፡፡ ይህ የተዛባና ኢምክንያታዊ አተያይ በዚህ ዘመን ክንውኖች ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር ድጋፍና ታቃውሞ እየተሳከሩ ነጩን ጥቁር፣ ጥቁሩን ደግሞ ነጭ በማለት ውዝግብ መፈልፈል ልማድ ሆኗል፡፡ በዚህ ታሪካዊ ወቅት እንኳን ነገሮችን ከማንነትና ከቡድን ጥቅም ጋር ብቻ በማቆራኘት፣ ተስፋ የተጣለባቸው በርካታ ጉዳዮች ሲደበዝዙ ይስተዋላል፡፡ ያለፉ ዘመናትን ቁርሾዎችና መቋሰሎች ለታሪክ ዶሴዎች ትቶ እንደ አዲስ የጋራ አማካይ ከመፈለግ ይልቅ፣ አሰልቺ ትርክቶች ውስጥ ተዘፍቆ መጠዛጠዝ ተለምዷል፡፡ እያንዳንዱ ትውልድ የራሱን ታሪክ የመጻፍ ብቻ ሳይሆን የመሥራት ግዴታ አለበት፡፡ ይህ ግዴታ የሚመነጨው ደግሞ በመጪው ትውልድ ተጠያቂ ላለመሆን ነው፡፡ በመጪው ትውልድ መጠየቅ ካልተፈለገ ደግሞ ከበፊቱ የተሻለ ሆኖ መገኘት የግድ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ትውልዱ ታሪኩን ለመሥራት ሲነሳ ያለፈውን ዘመን ዞር ብሎ መቃኘት የግድ ይለዋል፡፡ በዚያን ዘመን የነበሩ ድርጊቶችን ሲመረምር አንደኛ ስህተት ላለመድገም ትምህርት ያገኛል፡፡ ሁለተኛ የተሻለ ለመሥራት የሚያግዙ ድክመቶችንና ጥንካሬዎችን ይገነዘባል፡፡ ሦስተኛ ለመጪው ትውልድ ልምድ ያጋራል፡፡ ታላቅ መሆን የሚቻለው እንዲህ የማድረግ ብቃትና ድፍረት ሲኖር ብቻ ነው፡፡

እያንዳንዱ ትውልድ የራሱ ጀግኖች አሉት፡፡ እነዚህ ጀግኖች በአገር አስተዳደር፣ በትምህርት፣ በምጣኔ ሀብት፣ በሕክምና፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በጦር ሜዳ ጀብድና በመሳሰሉት መስኮች ሊገኙ ይችላሉ፡፡ አገሪቱ እንደምትገኝበት ሥርዓትና መንግሥታዊ አስተዳደር ዜጎች በየተሰማሩባቸው የሥራ መስኮች ኃላፊነታቸውን ሲወጡ፣ አንዳቸው ከሌላው በተሻለ በሚኖራቸው ትጋትና ውጤት ይከበራሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ስማቸው ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል፡፡ በታሪክም ሁነኛ ሥፍራ ያገኛሉ፡፡ ይኼንን ዓይነቱን የተከበረና ስም ያለው ተግባር ተቋማዊ በማድረግ፣ ለአገር አስተዋጽኦ ያበረከቱ ወገኖችን በሕይወት ሳሉ ጭምር ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ በፖለቲካ አቋም፣ በማንነት፣ በእምነት፣ በፆታ፣ ወይም በተለያዩ ምክንያቶች ጎራ እየፈጠሩ የራስን መካብ፣ የሌሎችን የማዋረድ አዘቅት ውስጥ ሲገባ ሰው የመሆን ትርጉሙ ፋይዳ ቢስ ይሆናል፡፡ በሁሉም ነገር መስማማት የግድ ባይሆንም፣ የጋራ የሆነ አማካይ እየፈጠሩ ባለ ውለታዎችን ማሰብ የታላቅነት መገለጫ ነው፡፡ ‹‹ባለቤቱ የናቀውን አሞሌ ማንም አይፈልገውም›› እንደሚባለው፣ እርስ በርሱ የማይከባበር ትውልድም ሆነ ማኅበረሰብ ተንቆ ይቀራል፡፡ ታላቅነትን ማሰብም አይቻልም፡፡

ለምሳሌ የወቅቱ ጉዳይ ሆኖ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን አነሳን እንጂ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ ተግባሮቻቸው የሚታወቁ የተከበረ ስም ያላቸው ነበሩ፣ ዛሬም አሉ፡፡ እነዚህን ክብር የሚገባቸው ታላላቅ ሰዎች እንደምንከተለው የፖለቲካ አስተሳሰብና ወገንተኝነት እየፈረጅን የምንደግፍና የምንቃወም ከሆንን፣ ከስህተት ተምረን ነገውን ለማቃናት ያለን ዕድል ከዜሮ በታች ይሆናል፡፡ ሁሉንም ነገር በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አቋምና በመሳሰሉት መሥፈርቶች በመከለል የቅራኔና የውዝግብ ምንጭ ማድረግ ተገቢ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የዴሞክራሲ አገር መሆን ይገባታል ሲባል ነፃነት፣ ፍትሕና እኩልነት ስለሚያስፈልጉ ነው፡፡ በዚህ መሠረት መስማማት ሲቻል ልዩነቶችን በማጥበብ የጋራ የሆነ አማካይ መፍጠር ቀላል ነው፡፡ ወደኋላ እየሄዱ የተለያዩ ድርሳናትን በማገላበጥ ልዩነቶችን እያራገቡ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን መፈታተን፣ ለአሁኑም ሆነ ለመጪው ትውልድ ፋይዳ የለውም፡፡ ታላቅ ሆኖ ታላቅ አገር መገንባት የሚቻለው የጋራ ራዕይ ይዞ መነሳት ሲቻል ነው፡፡ አሜሪካም ሆነ አውሮፓ፣ እንዲሁም የእስያዎቹ ጃፓን፣ ኮሪያና ቻይና በዕድገት የገሠገሡት የጋራ ራዕይ ስለነበራቸው ነው፡፡ ያለፈውን ዘመን ከእዚህኛውና ከመጪው ጋር ማቆራኘት ጥቅሙ ክፉና ደጉን ለመለየት ከማስቻል በላይ፣ የታላቅነትን ፀጋ ለማግኘት ስለሚያግዝ ጭምር ነው፡፡

ሌላው መጠቀስ ያለበት ቁምነገር የአሁኑ ትውልድ ዕድለኛ መሆን መቻሉ ነው፡፡ የዘመኑ የአስተሳሰብ ልቀት ከመቼውም ጊዜ በላይ የተለያዩ ምልከታዎችን መፍጠር ስለሚያስችልና ቴክኖሎጂውም የረቀቀ በመሆኑ፣ ከብርሃን ፍጥነት በማይተናነስ ደረጃ ከፍተኛ የሆነ የመረጃ ፍሰት አለ፡፡ በዚህም ምክንያት ሰዎች ዕውቀት የሚገበዩባቸው መደበኛና መደበኛ ያልሆኑ ምንጮች በመብዛታቸው፣ የአስተሳሰብ ዕድገት ከሚታሰበው በላይ ለብዙዎች ተደራሽ እየሆነ ነው፡፡ በመሆኑም ሰዎች ለመወያየት፣ ለመከራከር፣ ለመደራደርና ለመስማማት የሚያስችሏቸው ዓውዶች እየበዙ ነው፡፡ ተቀምጦ ለመነጋገር ፍላጎት ሲኖር ደግሞ መስማማት እንኳን ባይቻል፣ ነገርን አውሎና አሳድሮ እንደገና በተሻለ መንፈስ ለመነጋገር ዕድሉ እየተገኘ ነው፡፡ መቀራረብና መነጋገር ባህል በሆነ ቁጥር የጋራ አማካይ ለመፍጠር የሚያስችሉ በርካታ ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡ ከዚህ ቀደም በኩርፊያ፣ በጥላቻ፣ በቂም በቀልና በመሳሰሉት ክፉ ደዌዎች የተመረዙ ሳይቀሩ መታከም የሚችሉበት ዕድል እየተፈጠረ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ መልካም አጋጣሚ ደግሞ ማኅበረሰቡ ውስጥ በስፋትና በጥልቀት እየዘለቀ ሲሄድ፣ ከአውዳሚ ድርጊቶች በመታቀብ ወደ ሥልጣኔ መሸጋገር ይቻላል፡፡ ታላቅነትም ቅርብ ይሆናል፡፡ ያለፉትን ዘመናት ድርጊቶች ከመጠን በላይ በመኮነን ወይም በተጋነነ ሙገሳ ሰማይ ጥግ በማድረስ ሳይሆን፣ ለመጪው ትውልድ በሚጠቅም መንገድ ታላቅነትን ማሳየት የግድ ይላል፡፡ ታላቅ መሆን የሚቻለው ያለፈውን በማንኳሰስ መጪውን በማጨለም አይደለምና!

 

 

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...

ብሔራዊ ባንክ ጥርስ እያወጣ ይሆን እንዴ?

በአመሐ ኃይለ ማርያም ‹‹Better late than never›› (ከቀረ የዘገየ ይሻላል) የኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው...

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...