Friday, June 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

 ለአፍሪካ ኅብረት በጀት የአባላቱን መዋጮ በሚጠይቀው ማዕቀፍ ኢትዮጵያ በዓመት እስከ 40 ሚሊዮን ዶላር ልታዋጣ ትችላለች

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የሚተዳደርበትን የገንዘብ አቅምና በጀቱን በአባል አገሮች እንዲሸፈን ለማድረግ እያንዳንዱ አባል አገር በሕጋዊ የገቢ ንግዱ ላይ የ0.2 በመቶ ታክስ በመጣል መዋጮ እንዲያደርግ ስምምነት ከተደረሰ ሦስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

በዚህ ስሌት መሠረት ብንሄድ፣ የኢትዮጵያ ዓመታዊ የገቢ ንግድ መጠን 20 ቢሊዮን ዶላር ገደማ በመሆኑ፣ በየዓመቱ ለኅብረቱ የ40 ሚሊዮን ዶላር ወይም በአሁኑ ምንዛሪ ከ1.1 ቢሊዮን ብር በላይ መዋጮ ማከናወን እንደሚጠበቅባት መረጃው ያመላክታል፡፡ ይሁንና ይህንን ያህል ስለማዋጣቷ የሚያመላክቱ ይፋዊ መረጃዎችን ማግኘት አዳጋች ነው፡፡ ስለጉዳዩ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ሆነ ከገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ማግኘት አልተቻለም፡፡ ይህም ቢባል ግን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩና ዲፕሎማቱ ነቢያት ጌታቸው ግን ዓመታዊው የኢትዮጵያ መዋጮ 40 ሚሊዮን ዶላር እንደማይደርስ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ የ0.2 በመቶው መዋጮው በሁሉም የገቢ ንግድ ሸቀጦች ላይ እንደማይጣልም ይሞግታሉ፡፡

 ይሁንና ዝርዝሩና አጣጣሉን በሚመለከት የተብራራ መረጃ ባይገኝም፣ ታክሱ የሚጣለው ግን የአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮች አባል ካልሆኑት በሚያስገቧቸው ሸቀጦች ላይ ነው፡፡ በአፍሪካ አገሮች መካከል በሚፈጸም የንግድ ልውውጥ ወቅት የ0.2 በመቶ ታክሱ ታሳቢ አይደረግም፡፡ ይህ በመሆኑም የኢትዮጵያ መዋጮ ከ40 ሚሊዮን ዶላር በታች ሊሆን እንደሚችል ያመላክታል፡፡ ይሁንና አብዛኛው የአገሪቱ ገቢ ንግድ ምንጩ አባል ካልሆኑ፣ እንደ ቻይናና አሜሪካ ካሉት በመሆኑ መዋጮው ወደ ተገለጸው አኃዝ እንደሚቃረብ አመላካች ነው፡፡

ሲካሄድ በሰነበተውና ሰኞ ማምሻውን በተጠናቀቀው 32ኛው የአፍሪካ ኅብረት መደበኛ ጉባዔ ወቅት የኅብረቱ ምክትል ኮሚሽነር አምባሳደር ቶማስ ክዌሲ ኳርቲ ስለ ኅብረቱ የፋይናንስ ምንጮች መግለጫ እንደሚሰጡ አስታውቀው ነበር፡፡ ኋላ ላይ በተደጋጋሚ ሰረዙትና መረጃውን ማግኘት ሳይቻል ቀረ እንጂ፡፡

ይሁን እንጂ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ ማህማት፣ በኅብረቱ መክፈቻ ንግግራቸው ወቅት፣ በስምምነቱ መሠረት አባል አገሮች እንዲያዋጡ የሚጠበቀውንና እ.ኤ.አ. በ2016 በኅብረቱ አባል አገሮች የፀደቀውንና በገቢ ንግድ ላይ የሚጣለውን የ0.2 በመቶ ታክስ ለኅብረቱ መዋጮ እንዲውል በተስማሙት መሠረት፣ 26 አገሮች እንደተገበሩት አስታውቀዋል፡፡ የእነዚህ አገሮች መዋጮ በገንዘብ ሲገለጽ ምን ያህል እንደሆነ ግን ሳይገልጹ አልፈውታል፡፡ አንድ ነገር ግን ሳይናገሩ አላለፉም፡፡ ከዝርዝሩ በመቆጠብ ክፍያቸውን በወቅቱ በማይፈጽሙ አባል አገሮች ላይ ማዕቀብ የሚጥል ጠንካራ አሠራር ተዘርግቷል ብለዋል፡፡

የ0.2 በመቶ የመዋጮ ግዴታው ከመጣሉ ቀድሞ በተደረገ ጥናት 30 አገሮች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል የመዋጮ ግዴታቸውን መወጣት ሲያቅታቸው  ታይተዋል፡፡ ከ0.2 በመቶ ግዴታው በፊት አገሮች ከግምጃ ቤታቸው የግዴታ በሚደረግ መዋጮ ለኅብረቱ ዓመታዊ በጀት አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ ይህም ሆኖ ከግማሽ በላይ አገሮች የተጣለባቸውን ግዴታ ለመወጣት ሲፍገመገሙ ቆይተዋል፡፡ በመሆኑም የኅብረቱ 70 በመቶ ሥራ ማስኬጃ በጀት ሲሸፈን የቆየውና አሁንም እየታገገዘ የሚገኘው፣ በውጭ መንግሥታት ድጋፍ እንደሆነ የኅብረቱ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮች ስምምነት መሠረት፣ ለሥራ ማስኬጃ፣ ለፕሮግራም እንዲሁም ለሰላም ፈንድ ተብለው ለተካከፈሉ የበጀት ድልድሎች እየዋለ የሚገኘው የ0.2 በመቶ ታክስ፣ እ.ኤ.አ. ከ2017 ጀምሮ ለሥራ ማስኬጃ መቶ በመቶ፣ ለፕሮግራም በጀት 70 በመቶ እንዲሁም ለሰላም ማስከበር ተግባራት 25 በመቶ እንዲውል ተደልድሏል፡፡

በመሆኑም የኅብረቱን አስተማማኝ የገቢ ምንጭ አገሮችን ጫና ውስጥ በማይጥላቸው መንገድ ለመበጀት፣ የኅብረቱንም ሥራዎች ለማገዝ ይረዳል ተብሎ የታመነበት ይህ የመዋጮ ገንዘብ፣ እ.ኤ.አ. ከ2017 ጀምሮ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ዴሞክራቲክ ኮንጎና ቻድ መዋጮውን ለመተግበር ቀድመው የተስማሙና የጀመሩ አገሮች ስለመሆናቸው የአፍሪካ ኅብረት አመላክቷል፡፡ ስለአፈጻጸሙ ዝርዝር ባይገኙም፣ ኢትዮጵያ በገባችው ቃል መሠረት ለሁለት ዓመታት 80 ሚሊዮን ዶላር ሊደርስ የሚችል ገንዘብ ለአፍሪካ ኅብረት መክፈሏ ይገመታል፡፡ 

የኅብረቱ መደበኛ ጉባዔ በሚካሄድበት ወቅት የተለያዩ ስብሰባዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ እሑድ፣ ከካቲት 3 ቀን 2011 ዓ.ም. በተካሄደው የመሪዎች ጉባዔ ወቅት የተመረቀው የግርማዊ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ መታሰቢያ ሐውልት በአንድ በኩል፣ በቅርቡ የፀደቀው የስደተኞች አዋጅ፣ የኤርትራና የኢትዮጵያ ዕርቀ ሰላም ስምምነት፣ የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ኅብረት ከተቀየረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በኅብረቱ እንደሚገኙ ሲጠበቁት የነበሩት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም የዘንድሮን የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ በኢትዮጵያና በምሥራቅ አፍሪካ ላይ ያተኮረ እንደሚሆን ከጅምሩ ተጠብቆ ነበር፡፡

 ይሁንና ከንጉሠ ነገሥቱ ሐውልት በቀር የስደተኞች ጉዳይ በአጀንዳነት የተቀመጠውን ያህል አንገብጋቢ መነጋገሪያ ነበር ማለት አይቻልም፡፡ እንደውም የምዕራባውያኑ አጀንዳ እንጂ አፍሪካ ከተቀረው ዓለም የበለጠ የስደተኞች ምንጭ ስለመሆኗ አለያም የምዕራብ አገሮች በአፍሪካ ስደተኞች የተወረሩ ይመስል በአፍሪካ ላይ የሚቀርቡት ትችቶች ከእውነታው ያፈነገጡ ናቸው በማለት የሚሞግቱ ድምፆች አልታጡም፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝም አፍሪካውያን ከራሳቸው ጫናና ጎደሎነት ሳይሰስቱ ስደተኞችን የሚቀበሉ፣ ለጋሶች ናቸው ከማለታቸውም በላይ አፍሪካ ለተቀረው ዓለም ምሳሌ ስለመሆኗም በኅብረቱ ጉባዔ ወቅት ተናግረዋል፡፡ ኡጋንዳ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያና ሌሎችም አገሮች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ስደተኞችን በማስጠለል የሚጠቀሱ አገሮች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞችን ስታስጠልል፣ ኡጋንዳ ከ1.4 ሚሊዮን በላይ በማስተናገድ በአፍሪካ ቀዳሚዋ ነች፡፡ ሰሞኑንም ከ75 ሺሕ በላይ የዴሞክራቲክ ኮንጎ ስደተኞችን ለመረከብ ዝግጅት ላይ ትገኛለች፡፡  

የኅብረቱ ጉባዔ የስደተኞች፣ ከስደት ተመላሾችና የተፈናቃዮች ዓመት በሚል ተሰይሟል፡፡ ከስድስት ሚሊዮን በላይ ስደተኞችና ከ14 ሚሊዮን በላይ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች በአፍሪካ እንደሚገኙ የኅብረቱ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ኢትዮጵያም በእርስ በርስ ግጭት ሳቢያ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የአገር ውስጥ ተፈናቃይ ዜጎች እንዳሏት ይታወቃል፡፡

ለስደት መነሻ ከሆኑት አንዱ ምክንያት ግጭትና የሰላም እጦት እንደሆነ የሚገልጸው የአፍሪካ ኅብረት፣ የሰላም ፈንድ የተሰኘ ተቋም በመመሥረት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ለዚህ ተቋም እስካሁን ኢትዮጵያን ጨምሮ 49 አገሮች 89 ሚሊዮን ዶላር እንዳዋጡ፣ የኅብረቱ ተሰናባች ሊቀመንበር የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ አስታውቀዋል፡፡ የሰላም ፈንድ የተሰኘውን ተቋም፣ የቀድሞው የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ካቤሩካ እየመሩት ይገኛሉ፡፡  

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች