Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየኢትዮጵያ ቡና ነባር አመራሮች ወደ ኃላፊነታቸው ተመለሱ

የኢትዮጵያ ቡና ነባር አመራሮች ወደ ኃላፊነታቸው ተመለሱ

ቀን:

ከኃላፊነታቸው ለመልቀቅ ደብዳቤ ያስገቡት የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ሊቀመንበር መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞና አቶ ይስማሸዋ ሥዩም በኃላፊነታቸው እንዲቆዩ ተደረገ፡፡

ሁለቱ የክለቡ የበላይ ኃላፊዎች ቡድኑ ያስተናገዳቸውን ተከታታይ ሽንፈቶች ተከትሎ ባለፈው ሳምንት በደጋፊዎች በደረሰባቸው ሥነ ምግባር የጎደለው ማንጓጠጥና ስድብ የተነሳ መልቀቂያ ማስገባታቸው አይዘነጋም፡፡

የቦርድ አመራሮቹ ውሳኔ ከተሰማበት ዕለት ጀምሮ ወደ ኃላፊነታቸው እንዲመለሱ ስምምነት እስከወረደበት ጊዜ ድረስ፣ የክለቡ ደጋፊዎች በሁለት ጎራ ተከፍለው ሲሟገቱ ሰንብተዋል፡፡ ከፊሎቹ ለክለቡ ውጤት መበላሸት አመራሩን ተጠያቂ ሲያደርጉ፣ ገሚሶቹ ደግሞ ለክለቡ ውጤት ማጣት ቦርዱ የመጀመርያው ተጠያቂ ቢሆንም፣ በቴክኒክ ረገድ የቡድኑን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴና የብቃት ደረጃ የማወቅና የመገምገም ኃላፊነት የተጣለባቸው አሠልጣኞችና ተጫዋቾች፣ እንዲሁም እንደ 12ኛ ተጫዋች የሚታየው ደጋፊ ለተፈጠረው ችግር ድርሻውን ይወስዳል ይላሉ፡፡

የክለቡን አመራሮች መቃወም ቢያስፈልግ እንኳ በሠለጠነ አግባብና በጨዋ ደንብ ሐሳብን መግለጽ እየተቻለ፣ የግለሰቦቹን ሰብዕናና ክብር መንካት ተገቢ እንዳልነበር የሚያምኑ ደጋፊዎች፣ ያልተገባ ስድብና ዘለፋ በሰነዘሩት ደጋፊዎች ላይ ትችታቸውን አሰምተዋል፡፡

በዚህ አኳኋን ሲወዛገብ የሰነበተው የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ አመራርና ደጋፊ፣ ሰኞ የካቲት 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ክለቡን በገንዘብ የሚደግፈው የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎችና አቅራቢዎች ማኅበር ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አሸብር ወልደጊዮርጊስ (ዶ/ር)፣ የክለቡ የደጋፊዎች አመራሮችና የክለቡ ነባር አመራሮችና የሚመለከታቸው በተገኙበት በራስ ሆቴል በተደረገ ውይይት፣ የቦርድ ሰብሳቢው መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞና አቶ ይስማሸዋ ሥዩም በኃላፊነታቸው እንዲቀጥሉ መስማማታቸው ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኝ ከሚያምኑ የስፖርቱ ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑትና ባለፈው ሳምንት ከቡና መሸነፍ ጋር ተያይዞ በደጋፊዎች ስድብና ወቀሳ የደረሰባቸው የኢትዮጵያ ቡና የቦርድ አባል አቶ ይስማሸዋ ሥዩም እንደ መቶ አለቃ ፈቃደ ሁሉ የመልቀቅ ሐሳባቸውን በማንሳት በኃላፊታቸው ለመቀጠል ተስማምተዋል፡፡

‹‹አሁን ያለው የኢትዮጵያ ቡና ወቅታዊ ብቃት ከመቼውም ጊዜ ጋር ሲነፃፀር ክለቡንና ደጋፊውን የሚመጥን አይደለም፡፡ ለዚህ ደግሞ ክለቡ በመፍትሔነት ያስቀመጠውና እየሠራበት የሚገኘው በታዳጊ ወጣቶች ላይ ማተኮር ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ተሠላፊዎች ዘጠና በመቶ ወጣቶች እንዲሆኑ የተደረገው ለዚህ ነው፤›› የሚሉት አቶ ይስማሸዋ፣ ሌሎችም ክለቦች በዚህ አግባብ ካልተጓዙ፣ የአገሪቱ እግር ኳስ አሁን ከሚገኝበት የባሰ አዘቅጥ ውስጥ የሚገባበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን አሳስበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ቡናን ጨምሮ አብዛኞቹ ክለቦች፣ የገንዘብ ቀውስ ውስጥ መግባታቸው መነገር ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ለተጫዋጮች የግዥና የዝውውር ዋጋ መናር በመንስዔነት የሚጠቀሰው የደደቢት እግር ኳስ ክለብ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ይሁንና ደደቢት በአሁኑ ወቅት በነበረበት ተስኖት የክለቡ ህልውና አደጋ ላይ መውደቁ ልብ ሊባል እንደሚገባ የሚገልጹ አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ቡናም ቢሆን አካሄዱን መፈተሽና ማስተካከል ካልቻለ ዕጣ ፈንታው ከደደቢት እንደማይለይ አቶ ይስማሸዋ ገልጸዋል፡፡ ሌሎችም ክለቦች በተጫዋቾች ዝውውር ላይ የሚያራምዱትን አሠራርና የገንዘብ አወጣጥ በማስተካከል ለኢትዮጵያ ወጣቶች ትኩረት እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 

  

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

    

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...